ጎንደር (ኢዜአ)፡- በማዕከላዊና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች በጸረ-ሰላም ኃይሎች የደረሰውን የዜጎች ሞትና መፈናቀል በማያዳግም ሁኔታ ለማስቆም እየሰሩ መሆናቸውን የመከላከያ ሰራዊት 33ኛ ክፍለ ጦርና የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቁ። የክፍለ ጦሩ ዋና አዛዥና የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር በጋራ በጎንደርና አካባቢው ወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታ ላይ ከትናንት በስቲያ በጎንደር ከተማ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። በመግለጫውም የአካባቢው ሰላም ወደ ነበረበት እስኪመለስ ድረስም ከጎንደር መተማ እና ከጎንደር ሁመራ በሚወስደው መንገድ በ5 ኪሎ ሜትር ርቀት በቡድንም ሆነ በተናጠል ትጥቅ ይዞ የመንቀሳቀስ ክልከላ ተደርጓል ፡፡
ኮሚሽነር ዘላለም ልጃለም በሰጡት መግለጫ፤ በህዝቦች መስዋእትነት የመጣውን ለውጥ ለመቀልበስና አካባቢውን የትርምስ ቀጣና ለማድረግ የታጠቁ ሃይሎች ሰላምን ለማደፍረስ ብርቱ መፍጨርጨር ማድረጋቸውን ገልጸዋል። በዚህም የዜጎች ሞት መፈናቀልና ከፍተኛ የንብረት ውድመት መከሰቱን ኮሚሽነሩ ገልጸው፤ ህይወታቸውን ላጡ ዜጎች ቤተሰቦች መጽናናትን በክልሉ መንግስት ስም ተመኝተዋል። የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር በዘላቂነት ከመፍታት አኳያም የፌዴራልና የክልሉ የጸጥታ ሃይል አካባቢውን ወደ ነበረበት ሁኔታ ለመመለስ በፌዴራልና በክልሉ መንግሥት ትእዛዝ መሰጠቱን በመግለጫቸው አመልክተዋል። ‹‹የጸጥታ ሃይሎቹ በጋራ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በማያዳግም ሁኔታ የአካባቢውን ሰላም ለማረጋገጥ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ርብርርብ ያደርጋሉ›› ብለዋል።
አካባቢውን ሲያተራምሱ የነበሩ ሁከትና ብጥብጥ በመፍጠር ለዜጎች ሞት መፈናቀልና ለንብረት ውድመት ምክንያት የሆኑ ሃይሎች በቁጥጥር ስር የሚውሉበት ሁኔታ እንደሚፈጠርም ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል። በአካባቢው አስተማማኝ የሆነ የህግ ማስከበር ሥራ እንደሚሰራ የጠቆሙት ኮሚሽነሩ፣ ህብረተሰቡ ይህን ተገንዝቦ የጸጥታ ሃይሉ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ተሳታፊና ተባባሪ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ይህን ህግ የማስከበር ተልእኮ ለማስፈጸምና በአካባቢው አስተማማኝ ሰላም እስኪረጋገጥና በቀጣናው ሰዎች ህይወታቸውን የሚያጡበት ሁኔታ እስኪቆም ድረስ በጎንደርና አካባቢው ጊዚያዊ ክልከላዎች ተላልፈዋል።
በጎንደር ከተማም ሰላማዊ የፖለቲካ የኢኮኖሚና የቱሪዝም እንቅስቃሴውን የሚገድቡ ሁኔታዎች እንዳይፈጠሩም ከተፈቀደለት የጸጥታ ሃይል ውጪ ማንኛውም ሃይል ትጥቅ ይዞ እንዳይንቀሳቀስ ተከልክሏል። ክልከላ በተደረገባቸው አካባቢዎች ትጥቅ ይዞ ሲንቀሳቀስ የተገኘ ሃይል መንግስትና ተልእኮ በተሰጠው የመከላከያ ሰራዊትና የክልሉ የጸጥታ ሃይል ህጋዊ እርምጃ የሚወስዱ መሆናቸውን ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል። ሌሎች ለጸጥታ ሥራ አጋዥ እንሆናለን ብለው የሚያስቡ ሃይሎች በመንግሥት በኩል ፈቃድና ስምሪት እስኪሰጣቸው ድረስ በየትኛውም የጸጥታ ማስከበር ተልእኮ መሰማራት የተከለከለ መሆኑን ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።
የ33ኛ ክፍለ ጦር ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጄነራል አለሙ አየነ በበኩላቸው፤ ‹‹የዜጎች ህይወት ከዚህ በኋላ በከንቱ ማለፍ የለበትም ፤ ተመጣጣኝ እርምጃ በመውሰድ የአካባቢው ሰላም ወደ ነበረበት እንዲመለስ ይደረጋል›› ብለዋል። የክልሉ መንግሥት ባቀረበው ጥያቄ መሰረት የፌዴራል መከላከያ ሰራዊት ወደ ክልሉ ገብቶ የፀጥታ ሥራ እንዲሰራ ትእዛዝ መሰጠቱን ጠቅሰው ህዝቡ ከጸጥታ ሃይሉ ጎን በመሆን የተለመደ ትብብሩን እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል። በአካባቢው ላይ የተላለፉትን ክልከላዎች ህዝቡና በሰላማዊ መንገድ የታጠቁ ሃይሎች በማክበር ለተግባራዊነቱ እንዲረባረቡም አሳስበዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 12/2011