ወጣትነት ብዙ ውጣ ውረዶች የሚያልፉበት የዕድሜ ክልል እንደመሆኑ የተለያዩ ሰዎች ይህንን ዕድሜያቸውን በማይረሱ ትዝታዎች ያሳልፋሉ:: ለምሳሌ በትምህርት ቤት፣ በሚኖሩበት አካባቢና በመሳሰሉት። ከእነዚህ «ከመሳሰሉት» መካከል አንዱ የፍቅር ሕይወት ሲሆን፤ ሰዎች በዚህ ሕይወታቸውም አይረሴ፤ አይጠገቤ የሆኑ ክስተቶችን ያስተናግዳሉ:: ነገር ግን አንዳንድ ሰዎች ወጣትነታቸውን በውጣ ውረድ፣ በብቸኝነትና በችግር ውስጥ ሆነው ለማሳለፍ ይገደዳሉ:: ለዚህ ደግሞ አቅም ከሌላቸው ቤተሰብ መፈጠር እንደ ምክንያትነት ሊጠቀስ ይችላል:: ለዛሬ ይዘንላችሁ የቀረብነው የወጣት ካሊድ ድጉማ የሕይወት ውጣ ውረድን የተመለከተ ነው::
ከድር ከልጅነቱ ጀምሮ በሥራ ያሳለፈና ትምህርት ለመማር ዕድል ያላገኘ ወጣት ነው:: ወደ አዲስ አበባ ከመጣ በኋላ ግን ትምህርት በመጀመሩ በአሁኑ ወቅት አራተኛ ክፍል መድረስ ችሏል:: የሚወደውንም የኪነጥበብ ሥራ በተቻለው አቅም እየሰራም ይገኛል:: ከወጣት ካሊድ ጋር ባደረግነው ቆይታ ወቅት ስለ ሕይወት ተሞክሮውና ስላሳለፋቸው ውጣ ውረዶች አውግቶናል፤ እንደሚከተለውም አርበነዋል:: መልካም ንባብ::
ልጅነትና እድገቱ
ወጣት ካሊድ ተወልዶ ያደገው በጅማ ዞን፣ ቢኖራ የሚባል አካባቢ ነው:: የመጀመሪያ ስሙም ከድር ይባል ነበር:: ሁለት ዓመት ሲሞላው ወላጅ አባቱ በሞት ስለተለየው የልጅነት ጊዜውን ከእናቱ ጋር ነበር ያሳለፈው:: እናቱ እሱን ለማሳደግ ማታ ማታ ሰፌድ በመስፋት ይሸጡ የነበረ ሲሆን ቀን ቀን ደግሞ እህል የመፍጨት ሥራ ያከናውኑ ነበር:: ካሊድ ሰባት ዓመት ሲሞላው እናቱ ሌላ ባል በማግባታቸው ወደ አጎቱ ዘንድ ሄደ:: አጎቱ ጋር በሚኖርበት ወቅት ከፍተኛ ስቃይ የደረሰበት ሲሆን ያለ ዕድሜው ሥራዎችን ያከናውን ነበር:: እንጀራ አባቱ ካሊድን ለማሳደግ በመፈለጉ አጎቱ ጋር ሁለት ዓመት እንደተቀመጠ ወደ ትውልድ መንደሩ ተመለሰ::
ካሊድ ወደ እናቱ ቤት ከተመለሰ በኋላ በእንጀራ አባቱ ከፍተኛ ስቃይ የደረሰበት ሲሆን በተለያዩ ጊዜያትም በግርፋት ምክንያት ለአካል ጉዳተኝነት ተዳርጓል:: ከዚህም ባለፈ በአግባቡ ምግብ ስለማያገኝ ሰውነቱ ተጎድቶም ነበር:: እንጀራ አባቱ አስሮና ሰቅሎ ግርፋት ስለሚያደርስበት ካሊድ ከሚኖርበት አካባቢ ለመጥፋት አሰበ:: አስቦም አልቀረም፣ 1993 ዓ.ም አካባቢ ከቤቱ ወጥቶ ኮማ ወደምትባል ገጠር ሄደ:: ጠፍቶ በሄደበት ቦታም በአንድ አርሶ አደር ቤት በእረኝነት ተቀጠረ:: በዛም ቡና ለቀማና ሌሎች ሥራዎችን ቢሰራም ምንም ዓይነት ክፍያ አያገኝም ነበር::
በተጨማሪም በአካባቢው የሾርባ ምግብ በማዘጋጀት እንዲሁም ሳምቡሳና ብስኩት በመጥበስ ያከፋፍል ነበር:: በትርፍ ሰዓቱ ደግሞ ከብት በመጠበቅ ቢሰራም ለውጥ ባለማምጣቱ ወደ ሊሙ ገነት አቀና:: ሊሙ ገነት እንደደረሰም ወባና ሌሎች ህመሞች ከረሀብ ጋር ተደማምረው በድንገት ጣሉት፤ በአካባቢው የነበሩ ሰዎችም አንስተው ሆስፒታል አስገቡት:: በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ ከወጣ በኋላ ምንም ዓይነት ረዳትና መጠጊያ ማግኘት ባለመቻሉ በረንዳ ላይ ማደር ጀመረ::
በልጅነት ወደ ሥራ ዓለም መግባት
ሊሙ ገነት ከተማ እንደገባ ቀድሞ በሚያውቀው ጓደኛው አማካኝነት ጓደኛው እናት ቤት በሠራተኝነት ተቀጠረ:: የተቀጠረባቸው ሰዎች መምህራን በመሆናቸው ልጃቸውን እየጠበቀ፣ የቤት ሥራውንም እያከናወነ መኖር ጀመረ:: እዚያው ቤት አራት ዓመት የኖረ ቢሆንም ትምህርት የመማር ዕድል ግን አላገኘም ነበር:: በዚህም ከነበረበት ቤት ለመውጣት አሰሪውን ወይ ትምህርት እንዲያስተምሩት ወይም ገንዘብ እንዲከፍሉት ጠየቀ:: አሰሪውም የተሻለ የሚያገኝ ከሆነ ለቆ መሄድ እንደሚችል ስለነገሩት ካሊድ ከነበረበት ቤት በመውጣት ጎዳና ላይ መኖር ጀመረ::
ሊሙ ገነት ከተማ በበረንዳ አዳሪነት ሕይወቱ ለሰዎች ውሃ በመቅዳት ገንዘብ ማግኘት ጀመረ:: አብረውት የነበሩት ልጆች በአህያ ሲመላልሱ እሱ ግን በጭንቅላቱ ያመላልስ ነበር:: በዚህም ሥራ ለአንድ ዓመት የቆየ ሲሆን ማደሪያው ግን እዛው ጎዳና ላይ ነበር:: እሰው ቤት ገብቶ ከመስራት በጎዳና ላይ ሆኖ የተለያዩ ሥራዎችን ማከናወን ተመራጭ በመሆኑ ቡናና ጫት በማምጣት ለሱቆች ማድረስ ጀመረ::
በጎዳና ላይ እያለ ባሳየው ቅልጥፍና ካፌ ውስጥ የመቀጠር ዕድል አገኘ:: ነገር ግን ተቀጥሮ ይሰራበት የነበረው ካፌ ባለቤት ለካሊድ ማደሪያ ቢሰጠውም የጉልበቱን ዋጋ ግን መንፈግ ጀመረ:: ካሊድ ከሳምቡሳ መጥበስ ጀምሮ እስከ ማስተናገድ የደረሰ ሥራ ቢሰራም ገንዘብ ግን ማግኘት አልቻለም ነበር:: በዚህም በሌሊት ተነስቶ ለመጥፋት ተገደደ:: ከዚያም ወደ ጎዳና ሕይወት ተመልሶ ገባ:: ከዚያም ሱቅ በደረቴ መስራት የጀመረ ሲሆን በፈረቃ ትምህርት መማር ጀመረ:: ትምህርቱን እየተማረ ጠዋት ጠዋት ለሻይ ቤት ብስኩት በማመላለስ በወር 90 ብር ደመወዝ ማግኘት ጀመረ::
ካሊድ ከልጅነቱ ጀምሮ እናቱን ለመርዳትና አርቲስት ለመሆን ያስብ ነበር:: ከእናቱም ጋር በኖረበት ጊዜ ከፍተኛ ስቃይ ማሳለፉን አይረሳም:: እናቱ ምንም አቅም ስላልነበራቸው የሚኖሩበት ቤት በክረምት ጎርፍ እንዳይወስዳቸው በመሳቀቅ በማሳለፋቸው ካሊድ ሁሌም ትልቅ ነገር ይመኝ ነበር:: ነገር ግን ሁኔታዎች ሳይመቻቹለት ያሰበው ደረጃ መድረስ አልቻለም:: በአሁኑ ወቅት እናቱን በስልክ እንጂ በአካል ካገኘ ቆይቷል::
ጉዞ ከሊሙ ገነት ወደ ጅማ
ሊሙ ገነት ከተማ ለካሊድ ብዙ የሕይወት መንገዶችን ብታስተምረውም ወደ ለውጥ ልትመራው ባለመቻሏ ወደ ጅማ መጓዝን ምርጫው አደረገ:: ከሊሙ ገነት ወደ ጅማ ሲመጣ ሁለት ቀን በእግሩ ተጉዞ ስለነበር መስኪድ አካባቢ ለማረፍ ተገደደ:: በአካባቢውም በወቅቱ ልብሶቹን በመዘረፉ የተወሰኑ ቀናትን በጎዳና ላይ ያድርም ነበር::
ወደ ጅማ ሲገባ ሕይወት ያስተማረችው ሙያዎች ስለነበሩት ምንም ዓይነት ፍራቻ አላደረበትም ነበር::
በጅማ በከሰል ሥራ የተወሰኑ ቀናትም እያሳለፈ በጎዳና ላይ ኑሮውን ጀመረ:: በአንድ አጋጣሚም አንድ ሥራ ከሚያስቀጥረው ደላላ ጋር ተገናኘ:: ደላላውም በከተማው ወደሚገኝ ጭፈራ ቤት ወስዶ አስቀጠረው:: በጭፈራ ቤት ውስጥ የቢራ ሳጥን፣ እንጀራና ሌሎች ሥራዎችን ማከናወን ጀመረ:: በተጨማሪም በወጥ ቤት ውስጥ የምግብ ማብሰል ሥራን መስራትም ቻለ:: በጭፈራ ቤት ውስጥ የሥራ ጫናዎች ስለሚደራረቡበት በቂ እረፍት አያገኝም ነበር:: የሚከፈለውም ደመወዝ በቂ ባለመሆኑ የሚፈልጋቸውን ነገሮች ማሟላት አልቻለም:: በዚህም ይሰራበት ከነበረው ጭፈራ ቤት ለቆ ወጣ::
ከነበረበት ጭራ ቤት እንደወጣ ሌላ ሆቴል ቢገባም የሥራ ጫናው ግን አለቀቀውም:: ሆቴሉ ጭፈራ ቤት ያለው ሲሆን ሙሉ ቀንና ሌሊት ሥራ ስለሚያከናውን ለህመም ተዳርጓል:: በዚህም ሰው ቤት ላለመስራት በመወሰን ቤት ተከራይቶ ቀን ቀን ብቻ ለመስራት እንቅስቃሴ ቢጀምርም ድንገት ሥራ በመፍታቱ የቤት ኪራይ የሚከፍለው አጣ:: በዚያ ወቅት ከፍተኛ ችግሮችን አስተናግዷል:: በቀን አንድ ጊዜ እየበላ የችግር ቀናትን አሳልፏል:: ከነበረበት ችግር እንዲወጣ ያስቻለው በጅማ ዩኒቨርሲቲ በሚገኝ ካፍቴሪያ ውስጥ የወጣ ማስታወቂያ ነበር:: እዚያ ተቀጠረ። በካፍቴሪያው ውስጥ ከሻይ ቡና ማሽን ሥራ ጀምሮ እስከ ማስተናገድ ጀመረ:: በጅማ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በኮንስትራክሽን ሥራ ላይም ሰርቷል::
ከጅማ ወደ አዲስ አበባ መምጣት
ከጅማ ወደ አዲስ አበባ ሲመጣ ዘመድም ሆነ ምንም የሚያውቀው ሰው ስላልነበር አውቶቡስ ተራ አካባቢ በእጁ ያለው ገንዘብ እስኪያልቅ ድረስ ተቀመጠ:: ገንዘቡ እንዳለቀ ያሉትን ልብሶች በመሸጥ የዕለት ጉርሱን ለማሟላት መጣር ጀመረ:: ነገር ግን ወደ አዲስ አበባ በመጣበት ወቅት የኪነጥበብ ፍላጎቱን መስመር ለማስያዝ ቅድሚያ ለመስጠት ነበር:: ነገር ግን አዲስ አበባ እንደፈለገው አላስኬደውም:: ለቀን ምግብ የሚሆነውን ጎዳና ላይ ከተዋወቃቸው ልጆች ጋር ከየሆቴሉ የሚወጡ ምግቦች ይመገብ ነበር::
በአውቶቡስ ተራ አካባቢ ለሚገኙ ሰዎች ውሃ በመቅዳትና በመላላክ ገንዘብ ማግኘት ጀመረ:: ባገኘውም ገንዘብ የሊስትሮ ዕቃዎችን ገዝቶ እየተንቀሳቀሰ መስራት ጀመረ:: በሚንቀሳቀስባቸው ቦታዎች በአግባቡ ሥራውን እያከናወነ አዲስ አበባ መኖርን ለመደ:: ቤትም ተከራይቶ መኖር፤ እየኖረም የኪነጥበብ ፍቅሩን የሚወጣበትን መንገድ ማውጠንጠን ጀመረ:: ነገር ግን የነበረው ሁኔታ ለፊልም ሥራና ለኪነጥበብ ምቹ ባለመሆኑ እንዳሰበው አልሄደለትም ነበር::
እየተዘዋወረ የሚሰራውን የሊስትሮ ሥራ በአንድ ቦታ ላይ ተቀምጦ እንዲሰራ በአንድ በሚያውቀው ሰው አማካኝነት አሁን ያለበትን ቦታ አገኘ:: በቦታውም ላይ ካልሲ፣ የጫማ ገበር እና ሌሎች ነገሮችን በመሸጥ ደንበኛ ማፍራት ቻለ:: የሊስትሮ ሥራውን በተረጋጋ መንፈስ ማከናወን እንደጀመረ ሙሉ ቀልቡን ወደ ኪነጥበብ አዞረ:: ወደ ኪነጥበቡ ሙያ መግቢያ በሩን የከፈተለት «ብሉ ስካይ የፊልም ፕሮዳክሽን» ያወጣውን ማስታውቂያ የማየቱ አጋጣሚ ነበር:: ነገር ግን ድርጅቱ አላማው ሌላ ስለነበር መታውቂያ ተሰጥቶት ተቀመጠ:: በሚያውቃቸው ሰዎች አማካኝነትም ፊልም ሥራ ለመስራት ጥረት ማድረግ ጀመረ::
ካሊድ የኪነጥበብ ፍላጎቱን ለማርካት የተለያዩ ቦታዎች የተዘዋወረ ቢሆንም ሊያሰራ የሚችል ምንም ዓይነት ሁኔታ ሊገጥመው አልቻለም:: በወቅቱ የኮሮና ወረርሽኝ ተስፋፍቶ ስለነበር ለካሊድ ፍላጎት የሚሆኑ መንገዶች ሁሉ ዝግ ነበሩ:: በዚህም ተስፋ ወደ መቁረጡ እንደደረሰ የክቡር ዶክተር ተስፋዬ አበበ (ፋዘር) ጋር ሄዶ በመመዝገብ መማር እንደሚችል ሰው ጠቆመው፤ የተባለውንም አደረገ:: የኪነጥበብ ፍላጎቱን በሳይንሳዊ እውቀት ለመደገፍ በክቡር ዶክተር ተስፋዬ አበበ (ፋዘር) በተመሰረተው ትምህርት ቤትም ገባ::
የኪነጥበብ ትምህርት ከመጀመሩ በፊት በሬድዮ ፕሮግራሞች ላይ በግጥም፣ በቀልድና በመነባንብ ተሳትፎ ያደርግ ነበር:: ትምህርቱን መከታተል ከጀመረ በኋላ ድፍረት ያገኘ ሲሆን አጫጭር ጭውውቶችን፣ የመድረክ ድራማና ሌሎች ሥራዎችን መስራት ቻለ:: በሚማርበት የኪነጥበብ ትምህርት ቤት ስም በተከፈተ የዩ ቲዩብ ቻናል ላይ በሚሰሩ አጫጭር ጭውውቶች ላይ ይሳተፋል:: ኑሮ ተወዷል፣ መንገድ ጠራጊዎቹ፣ እናትና ልጅ፣ ሁለቱ ዘበኞች፣ ጠርጣራው ጎጃሜው እንዲሁም ሁለገብ የሚሉ ሥራዎች ላይ ተሳትፏል::
በቀጣይ ካሊድ በፊልም ሥራው በርትቶ ሰርቶ ቀድሞ ከነበረበት ሕይወቱ በተሻለ መንገድ ለመኖር ያስባል:: የተሻለ ሁኔታ ላይ ሲደርስ አቅም የሌላቸውን በመደገፍና መስኪድ ለማስገንባት ሀሳብ አለው:: በተጨማሪም በጎ አድራጎት ማህበር በመመስረት ችግረኞችን ለመርዳትም ርእይ ሰንቋል::
መርድ ክፍሉ
አዲስ ዘመን ሰኔ 4/2013