የሀገር ባህል ልብስ በኢትዮጵያ በጣም እየተወደደ እና እየተለመደ የመጣ ነው፡፡አሁን ላይ በተለይ በወጣቱ ዘንድ ልዩ ልዩ ዝግጅቶችና ስብሰባዎች እንዲሁም ክብረ ዓላት ሲኖሩ የባህል አልባሳቱ እንደ ፋሽን የሚዘወተሩ የሚለበሱ ሆነዋል፡፡ለዚህ ደግሞ ዲዛይን የሚያወጡ ሰዎች ሚና አላቸው፤ በብዛት በቀሚስ ብቻ ይታይ የነበረው የጥበብ አልባሳት እንደ ኮት፣ ቲሸርት በመሳሰለ መልኩ እየመጣ ነው፡፡
የቅድስት ዲዛይን ተወካይ አቶ ጳውሎስ ተሰማ እንደሚሉት ድርጅቱ የጥበብ አልባሳትን ይሸጣል፤ የአልባሳቱን ዲዛይን በማወጣት ልብሶቹን ያዘጋጃል።ጥበብ በሁሉም መለበሱን ተከትሎ በሀገራችን በተለይ በአዲስ አበባ የተለያዩ ዲዛይነሮች ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል ይላሉ አቶ ጳውሎስ።
እርሳቸው እንደሚሉት፤ ዲዛይነሮች የሀገር ባህል ልብስ ላይ የተለያዩ ጥበባትን በመጥለፍ የተለያዩ ስልቶችን በመከተል ዲዛይን በማውጣት የበለጠ ተወዳጅ እንዲሆን አድርገውታል።ይሄም የሚያሳየውም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚደረጉ ማናቸውም የበዓል ፕሮግራሞች ልዩ ስብሰባዎች በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ ሚዲያዎች እንደሚታየው ታዳሚዎች በሙሉ የሀገር ባህል ልብስ በመልበስ ተወዳጅነቱንም ፋሽኑንም ከፍ እያደረገ ነው፡፡
ከዚህ ቀደም ሲደረግ ከነበረው በበለጠ የሠርግ የምርቃት እና የተለያዩ ዝግጅቶች የጥበብ ልብሶች መድመቂያ ሆነዋል።የራት ተብሎ የሚዘጋጁ ዝግጅቶች የተለየ ልብስ ነበሩ የሚለበሱት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በራት ዝግጅቶች ሙሉ ለሙሉ በሚባል መልኩ የሀገር ባህል ልብስ እየተለወጠ ነው።የቅድስት ዲዛይን የሀገር ባህል ልብስ ወደ ሥራ ከገባ አራተኛ ዓመቱን እንደያዘና በዚህ ጊዜ ውስጥ በሀገር ወስጥም ከሀገር ውጪም
በርካታ ደንበኞችን ማፍራቱን ኃላፊዋ ይናገራሉ። የጥልፍ፣ የስፌት ሥራና የማርኬቲንግ ሠራተኞች አሉት።፡ሥራውን ለማስፋት የማርኬቲንግ ሠራተኞች፤ ኢንስታግራም፣ ቴሌግራም፣ ፌስቡክ የመሳሰሉ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ተጠቅመው ድርጅቱንና ሥራዎቻቸውን ያስተዋውቃሉ።የፈለገም ሰው ከተለጠፉት ሥራዎች አይቶ ያዛል፡፡በማኅበራዊ ሚዲያው አይተው ድርጅቱ ድረስ መጥተው የሚገበያዩም አሉ።የፈለገውን ልብስ የሚሠራበት አጋጣሚ ሰፊ ነው፡፡የጥበብ ልብስ ሥራው ጥሩ ደረጃ ላይ ነው ያለው፡፡
ድርጅቱን አልባሳት ከማህበራዊ ሚዲያው ላይ አይተን ነው ከሚሉ ዲያስፖራና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የስልክ ጥሪዎች በብዛት እንደሚደርሷቸው ተወካዩ ተናግረው፣ የሀገር ውስጥ ዜጎችም እንዲሁ አይተው በቀላሉ መምረጥ ማወዳደርና ማዘዝ ስለሚቻል ደንበኞች አፍርተንበታል ይላሉ።የውጭ ሀገር ኢትዮጵያውያን አንዱ ያላቸው ምርጫ ማኅበራዊ ሚዲያው ስለሆነ፤ ሲመርጡ ሲያዙ እዚህ ላይ ዓይተን ነበር ፤ እናንተ በዚህ መልኩ ትሠራላችሁ ወይ? ብለው ያዛሉ፡፡ስለዚህ ማኅበራዊ ሚዲያው ገበያውን ለመሳብም ሆነ የጥበብ ልብስ ሥራ ባለሙያዎችንና ነጋዴዎች ለማቆም አንዱ አማራጭ ሆኖ እያገለገለን ነው ይላሉ፡፡
ትንሽ ከኮረና ጋር ተያይዞ ሥራም የመቀዛቀዝ ነገሮች ነበሩ የሚሉት አቶ ጳውሎስ፣ ችግሩ የተለያዩ ሁነቶች፣ የሠርግ ፣የምርቃት ዝግጅቶች የመሳሰሉት ለተወሰነ ጊዜ አስተጓጉሎ እንደነበር ይጠቅሳሉ።በአስቸኳይ አዋጅ ሥር ስለነበር ላለፈው አንድ ዓመት ሥራው ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል ይላሉ።ሥራው በኅብረተሰቡ ዘንድ በሠፊው ተቀባይነት አግኝቷል፡፡በርካታ ዲዛይነሮች በሙያው የተሠማሩ መጥተዋል፡፡በውጭ ሀገርም ያሉ ትውልደ ኢትዮጵያውኖች፤ለተለያዩ ፕሮግራሞች የጥበብ አልባሳት እያዘዙ እያሠሩ አስልከው መጠቀም ጀምረዋል ሲሉ ያብራራሉ፡፡
እንደ ተወካዩ ገለጻ፤ የጥበብ ልብስ ሥራ የበለጠ የሥራ ፈጠራ ያለበት ነው፡፡እንደ ችግር የሚታየው፤የሽመና ሥራው አለመዘመኑ ነው፡፡የሽመና ሥራው ቀድሞ እንደነበረ ነው።ትዕዛዞች ሲመጡ ልብስ ከገበያ ላይ ለማግኘት ዲዛይነሮች ይቸገራሉ ።ልብስ አዞ ለማሠራትም ሸማኔዎቹ ጋር የተቀላጠፈ አሠራር የለም፡፡ሸማኔዎች በራሳቸው የግብአት፣ የሰው ኃይል እጥረት እንዲሁም የቦታ ችግር አለባቸው። ትንሽ የሽመና ሥራው ጎተት ይላል።ዲዛይን የማድረግ የመሥራት ገበያውን የማግኘት ችግር የለም።የፈትል ሥራ አለ፤ ትልቁ ችግር የክር እጥረት ነው ፤ክር ከውጭ ሀገር ነው የሚመጣው፡፡አንዳንዴ ደንበኞች የራሳቸውን ክርና ዲዛይን መርጠው ያዛሉ፡፡ሥራውን ሸማኔ ጋር ስናዝ ክሩ የለም የሚሉበት ጊዜ አለ፡፡ያ ክር ገበያ ላይ ከሌለ፤ ሸማኔው በታዘዘው መሠረት ሊሠራ አይችልም፡፡ሥራው ላይ ከፍተኛ የግብአት ችግር አለ፡፡
ከመንግሥት ብዙ ነገር ይጠበቃል፡፡እዚህ ሥራ ላይ ለተሠማሩ ሰዎች ማበረታታት አለባቸው፡፡በውጭ ሀገር የተለያዩ የንግድ ትርዒት (Trade Fair) ይኖራሉ፤ ቡናን ጨምሮ የባህል ቅርፃ ቅርፅ የባህል አልባሳት በቀላሉ እዛ ላይ እንዲሳተፉ ቢያንስ ቪዛ የማግኘትና የድጋፍ ደብዳቤ የመሳሰሉት ትብብር ቢያደርግ የበለጠ ሥራውን ያሳድገዋል፤የሀገሪቱን ውጭ ምንዛሪ የማግኘት አማራጭ ያሰፋዋል።የተለያየ የውጭ ሀገር ትሬድ ፌየሮችን ለመካፈል፤ አማራጩን ዕድሉን እናገኝና የቪዛ ችግሮች ይኖራሉ። የድጋፍ ደብዳቤ የሚጽፍ አካል እንኳ አናገኝም።የትጋም እንዳለ አናውቅም ሲሉ ይናገራሉ፡፡ራሳችን ፈልገን ወጪውን ሸፍነን ለምንካፈልበት የንግድ ኤግዚቢሽን የአፍሪካ ሀገሮች በተለያየ አቅጣጫ ሲካፈሉ፤ ለእኛ ቪዛ ስንጠይቅ የሚያየን የለም፤ሲሉ ተወካዩ ቅሬታቸውን ጠቁመዋል፡፡
በተለያዩ ሀገሮች የንግድ ኤግዚቢሽን ሲዘጋጁ መንግሥት ለሀገር ባህል ልብስ ዕውቅና ሰጥቶ የሀገር ውስጥ ዲዛይነሮች በሙያው ለተሰማሩ ሰዎች በኮታም ሆነ በዕጣ ዕድል እየሰጠ እንዲካፈሉ ቢያደርግ፤ መንግሥት በተወሰነ መልኩ ዶላር ያገኛል ያሉት አቶ ጳውሎስ፣ የላካቸው ድርጅቶች በራሳቸው በሚያገኙዋቸው የንግድ ኤግዚቢሽን ኤምባሲዎች ቪዛ አይሰጡም፡፡ስለዚህ ድርጅቶቹ የድጋፍ ደብዳቤ እንኳን ለማጻፍ ይሄንን የሚመለከት ክፍል የለም ነው የሚሉት። ሁሉም ጋር ብትሄድ እኛ አይመለከተንም ይላሉ፡፡ እንደዚሁ ሲባል ጊዜው ያልፋል፡፡ ባህላዊ ልብሶች የውጭ ግብይት የተመለከተ አንድ ክፍል ቢኖር በቀላሉ በሙያው የተሰማሩ ሰዎች በንግድ ኤግዚቢሽን ይሳተፋሉ የውጭ ምንዛሪ ያመጣሉ፡፡ የንግድ ምክር ቤት ድጋፍም ውስንነት ያለው ነው ሲሉም ያመለክታሉ።
የትራንስፖርትም ሆነ ሌሎች ወጪዎችን ልንጠይቅ አንችልም፤ የንግድ ኤግዚቢሽን እንሳተፍ ነው የምንለው ይህም የሀገራችንን ገጽታ የሚገነባ የውጭ ምንዛሪም የሚያመጣ ነው፡፡ ለዚህ የመንግሥት ድጋፍ እጅግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ማስፋፊያ ባለሥልጣን የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አሸናፊ መለሰ ባለሥልጣኑ ከሥልጠና ጀምሮ በፋይናንስ ሥራ ቦታና መሣሪያ በማመቻቸት በርካታ ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።ለቀረበው ቅሬታ በሰጡት ምላሽ የድጋፍ ባለሥልጣን የድጋፍ ደብዳቤ ለመጻፍ ችግር የለብንም፤ የዕዝ ሰንሰለቱን ሳይጠብቁ የሚመጡ ካሉ ችግር ነው፡፡ከንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ የድጋፍ ደብዳቤ ይዘው መምጣት አለባቸው።መጀመሪያ የተመዘገበ ኢንዱስትሪ ነው ወይ የሚለውም ይታያል፡፡ሂደቱን ተከትሎ ለመጣ ሰው በደስታ ነው የምንጽፈው ብለዋል፡፡ግባችንም ይህ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡በባለሥልጣኑ ድጋፍ ተደርጎላቸው የውጪ ንግድ ኤግዚቢሽን የተካፈሉ በጣም ብዙ ናቸው ሲሉም ጠቁመዋል።
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ግንቦት 30/2013