ወይዘሮ ሣራ ዘመኑ ሠናይ በጋዜጣችን ለወላጆች ምክር የሚያካፈሉ እናት ናቸው። የህክምና ባለሙያ ሲሆኑ፤ ልጆቻቸውን አሳድገው ለቁም ነገር አብቅተዋል። ነዋሪነታቸው በአሜሪካን ሀገር ሲሆን፤ ለወገኖቼ የተወሰነ ነገር ከልምዴ ባካፍል ብለው በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን መልዕክቶችን ያስተላልፋሉ። ለዛሬም ካካፈሉን ውስጥ እነሆ።
ዕድሜያቸው ከ1 እስከ 3 ያሉ ሕፃናት የሚፈልጉትን ነገር ካላገኙ በጣም የማልቀስ ፀባይ ይታይባቸዋል።ታዲያ ወላጆች ይህንን ፀባይ በዘዴ ካልያዙት ልጆቻችን በዚያ ዕድሜ ላይ ሲሆኑ አልቃሻ እና አስቸጋሪ ይሆናሉ።ነገር ግን አንዳንድ ቀላል የሆኑ ዘዴዎችን በመጠቀም ይህንን ፀባይ መግታት ይቻላል።ከዚህ በታች ለዚህ የሚጠቅሙ ሦስት ዘዴዎች እነሆ፡፡
የመጀመሪያው ዘዴ ለልጆቻችን ምርጫ መስጠት ነው።ለምሣሌ ጠዋት ተነስተን ወደ ሆነ ቦታ ለመሄድ ልጃችንን በማዘጋጀት ላይ እያለን እኔ ይኼንን ልብስ መልበስ አልፈልግም፤ ብላ ልጃችን በጣም ማልቀስ ትጀምራለች።በዚህን ጊዜ የግድ እኛ የመረጥነው ልብስ መልበስ አለብሽ ብሎ ከማስገድደ ፋንታ ይኼ ወይስ ይኼንን ወይም ደግሞ ይኼንን የቱን ትመርጫለሽ? ብሎ ሁለት ምርጫ መስጠት።ይህ ውሣኔያቸውን ቀላል ያደርግላቸዋል ማለት ነው።በተጨማሪም እኔ የምፈልገውን መምረጥ እችላለሁ የሚለው ሥሜት ይሰማታ (ዋ)ል።በዚህ መንገድ ስሜቷ ሳይጎዳ እርሷም እኛም የምንፈልገውን ልብስ በማልበስ ያስለቀሳትን ጉዳይ መፍታት ይቻላል፡፡
ሁለተኛው ዘዴ ደግሞ ማዘናጋት ነው።ከ1 እስከ 3 ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆች የማስታዎስ ወይም ትኩረት የመስጠት አቅማቸው ውስን ነው።በዚህም ምክንያት አንዳንድ ነገሮችን በቀላሉ ማዘናጋት ይቻላል።ለምሳሌ አንድ ልጃችን ከወንድሙ ወይም ከእህቱ ጋር በመጫወት ላይ እያለ የሆነ መጫወቻ ካልተሰጠኝ ብሎ ለመቀማት በሀይል ማልቀስ ይጀምራል።በዚህን ጊዜ እስቲ በር እየተንኳኳ ነው ማን ነው የመጣው፤ ሄደን እንይ በማለት ሃሳቡን መከጫወቻው ላይ አንስቶ ወደ ሌላ መውሰድ ይቻላል።ወይም ደግሞ ያልጠበቀውን ሌላ መጫወቻ አሳይቶ በማዳነቅ ሃሳቡን ወደ ሌላ መጫወቻ መውሰድ ይቻላል።በዚህ መንገድ ማልቀስ ጀምሮ የነበረው ሕፃን ሃሳቡ በሌላ ተይዞ ማልቀሱንም ያለቀሰበትንም ጉዳይ ይረሳዋል፡፡
በትንሽነት ዕድሜ (ከ1 – 3) ያሉ ልጆቻችን አልቃሻ እንዳይሆኑ ልንጠቀመው የምንችለው ሦስተኛው ዘዴ ደግሞ ከቦታው ዞር ማድረግ ነው።በዚህ ዕድሜ ላይ ያሉ ልጆች ከመጠን ያለፈ ደስታም ወይም በጣም ማዘን አይችሉም።ብዙውን ጊዜ ሁለቱም ወደ ማልቀስ ያመራል።ለምሣሌ ከጓደኞቻቸው ጋር በመጫወቻ ቦታ በመጫወት ላይ እያሉ በድንገት ተጣልተው በጣም ማልቀስ ይጀምራሉ።በዚህን ጊዜ እኛ ለማማበል እንሞክራለን።ከሁኔታቸው የማቆም አዝማሚያ ካላየን ወደ ቤት መግባት አለብን፤ ወይም ወደ ሌላ ቦታ መሄድ አለብን ብሎ ካሉበት ቦታ ዞር በማድረግ ማልቀሳቸውን እንዲያቆሙ ማድረግ እንችላለን፡፡
ከ1 እስከ 3 ዓመት ያሉ ሕፃናት እኔ ያልኩት ካልሆነ ብሎ ማልቀስ የተለመደ ነው።በዚህን ጊዜ የጠየቁትን ሁሉ ለመፈፀም ከሞመከር፤ ወይም ደግሞ ዝም ብሎ እንዲያለቅሱ ከመተው ፋንታ ከላይ የተጠቀሱትን ሦስት ዘዴዎች በመጠቀም ሥሜታቸውን በጠበቀ መንገድ አልቃሻ እንዳይሆኑ ማድረግ ይቻላል፡፡
ሳትወልድ ብላ እንዲሉ አባቶች ከወለዱ በኋላ የወላጅ ተኩረት የህፃናቱ እድገት ላይ ነውና የልጅ አስተዳደጋችንን በድካም ሳይሆን በጥበብ እንዲሆን ለወላጆች እንመክራለን።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ግንቦት 29/2013