ልጆች እንዴት ናችሁ ሠላም ነው? አሁን የሁለተኛ ወሰነ ትምህርት ተጠናቆ ወደ ፈተና እየተቃረባችሁ እንደሆነ ሰምቻለሁ? ከፈተና በኋላ ለሚመጡት የእረፍት ቀናት ምን አስባችኋል? እኔ በልጅነቴ ብዙ መፅሃፍትን አነብ ነበር፤ እናንተስ? በያላችሁበት ተነጋገሩ እሺ፤ ልጆች ማንበብ የማታውቁትን ነገር በማወቅ ሙሉ ሰው አንደሚያደርጋችሁ አምናችሁ ማንበብን በደንብ ተለማመዱ እሺ። ለዛሬም የሀገራችን ትልልቅ ሰዎች የኢትዮዽያ ተረቶችን በአንድ ሰብስበው ካስቀመጡልን ላይ ከወደ ትግራይ አካባቢ የተገኘውን በዚህ መልኩ አቅርቤላችኋለሁ።
በአንዲት መንደር የሚኖሩና አንዲት ሴት ልጅ ያላቸው ባልና ሚስት ልጃቸው ከብቶቹን ከመንደሩ አጠገብ ካለው ውሃ አጠጥታ እንድትመጣ ነገሯት።ልጅቷም ከብቶቹን ወደ ምንጩ ውሃ ነድታቸው ስትሄድ ውሃው ተበጥብጦና ደፍርሶ አገኘችው።በሁኔታው ስለተቸገረች ምን ማድረግ እንዳለባት ግራ ገባት።አባቷም በመጣ ጊዜ ውሃውን የበጠበጠው ክፉ ሰው ከውሃው ውስጥ ወጥቶ “ከብቶችህ ጥሩ ውሃ እንዲጠጡ ከፈለክ ልጅህን ስጠኝ፡፡” አለው፡፡
ሰውየውም ልጅቷን በኋላ እንደሚሰጠው ተስማምቶ ወደ ቤት ሲመለሱ አባትየው “አይይ! አንደኛውን ጫማዬን ወንዙ ጋ ጥዬዋለሁና ሄደሽ ከውሃው ዳርቻ አምጪልኝ፡፡” አላት፡፡
በዚህ ጊዜ ክፉ ሰው ከተደበቀበት ወጥቶ በግጥም እንዲህ አለ፤
“አንቺ ቆንጆ ልጅ ረጅም ፀጉርና ትልልቅ አይኖች ያሉሽ መጥቼ ልወስድሽ ነው፡፡” አላት
ልጅቷም ወደ ቤቷ እየሮጠች ስትመለስ የቤቱ በር ተዘግቷል።እርሷም “አባቴ ሆይ! ‘ረጅም ፀጉርና ትልልቅ አይኖች’ እያለ እየተከተለኝ ነውና እባክህ በሩን ክፈትልኝ፡፡” አለችው፡፡
ነገር ግን አባትየው በሩን ከፍቶ አላስገባም ሲላት ወደ አክስቷ ቤት እየሮጠች ሄዳ ግጥሙን ደግማ ብትናገርም አክስቷ ስለፈራች በሩን አልከፍትም አለች፡፡
ከዚያም ልጅቷ ወደ ጓደኛዋ ቤት ሄዳ ለቅርብ ጓደኛዋ ግጥሙን ስትነግራት ጓደኛዋ ከፈተችላት፡፡
ጓደኛዋም የሚበላ አበባ ሰጥታት “ወደ ቤትሽ ስትሄጂ የአበባውን ቀንበጦች አንድ በአንድ እየቀነጠስሽ አንዱን ስትበዪ አንዱን ጣዪ።አንዱን እየበላሽ፣ አንዱን እየጣልሽ ሂጂ፡፡” አለቻት፡፡
ክፉ ሰውም በአበባው ቀንበጦች ግራ ተጋባ፡፡
ልጅቷም ወደ አያቶቿ ቤት ሄዳ ከእነርሱ ጋር መኖር ጀመረች።በመጨረሻም አርባ ውሾች ኖሯት።ወላጆቿም ሊጠይቋት ሲመጡ የልጅቷ ስም አልማዝ ነበርና አያቷ “አልማዝ፣ ወላጆችሽ ሊጠይቁሽ መጥተዋል፡፡” አሏት፡፡
አልማዝም መጥታ በግጥም እንዲህ አለች፤
“እናቴ ሆይ፣ አባቴ ሆይ
ለክፉ ሰው ሰጥታችሁኛል
አርባዎቹ ውሾቼ ጩኹ!”
በዚህ ጊዜ ውሾቹ የአልማዝ ወላጆች ላይ ጮኸው
አባረሯቸው።በሌላም ጊዜ አክስቷ ስትመጣ ያንኑ ግጥም ደግማ እንዲህ አለች፤
“አክስቴ ሆይ፣
ለክፉ ሰው ሰጥተሽኛል
አርባዎቹ ውሾቼ ጩኹ!”
አክስቷንም አባረሯት፡፡
በመጨረሻም ጓደኛዋ መጣች።አልማዝም የጓደኛዋን መምጣት ስትሰማ በደስታ ተቀብላት እንዲህ አለች፤
“ጓደኛዬ ሆይ፣ ጓደኛዬ ሆይ
የነፍሴ አዳኝ
አርባዎቹ ውሾቼ አትጩኹ!”
በማለት በደስታ ተቀበለቻት። ልጆች ደግ ነገር መሥራት ሰዎችን መርዳት መጨረሻው ከሰዎች ጋር በፍቅር አንድንኖር ያደርገናል። ስለዚህ ሁልጊዜም የተቸገሩ ሰዎችን በጥበብ ማገዝ እንዳትተዉ፤ እሺ። መልካም ጊዜ ይሁንላችሁ።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ግንቦት 29/2013