አዲስ አበባ፡- በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአራዳ ክፍለ ከተማ በ591 ሚሊዮን 500 ሺህ ብር የተሠሩት 81 ፕሮጀክቶች በመጪው እሁድ እንደሚመረቁ ተገለፀ። ፕሮጀክቶቹ ከዚህ ቀደም ህብረተሰቡ ሲያነሳቸው የነበሩ በርካታ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ትርጉም ባለው ደረጃ እንደሚያቃልሉም ይጠበቃል። የክፍለ ከተማው ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወይዘሮ አበባ እሸቴ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ የካቲት 17 በይፋ የሚመረቁት ፕሮጀክቶች በሥራ ዕድል ፈጠራ የወጣት መዝናኛ ሥፍራዎችና ማዕከላት ግንባታን ያካተቱ ናቸው። ሥራ ዕድል ፈጠራ መንግሥትም በልዩ ትኩረት የሚመራው ቁልፍ ዘርፍ ነው የሚሉት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ በክፍለ ከተማው ችግሩን ለማቃለል የሚረዱ በጥቃቅንና አነስተኛ ለተደራጁ ዜጎች የመሥሪያና መሸጫ ሼዶች ግንባታ ማካተቱንም ገልፀዋል። በተለይም በክፍለ ከተማው ወረዳ አንድ ላይ በርካታ ጥያቄዎች ይቀርቡበት የነበረው የወጣት ማዕከል ግንባታ መከናወኑን ተናግረዋል።
በትምህርት ዘርፉ የመማር ማስተማሩን የሚደግፉና የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ የሚስችሉ ተግባራትም በፕሮጀክቶቹ ውስጥ የሚካተቱ ናቸው ያሉት ወይዘሮ አበባ በዚህም የቤተመፃህፍት ግንባታዎችና ማስፋፊያዎች ይገኙበታል ብለዋል። በጤናው ዘርፍም በተመሳሳይ የማዋለጃና ሌሎች ያልተሟሉ ግብዓቶችን በመለየት እንዲሟሉ መደረጉ በሕብረተሰቡ በሰፊው ጥያቄ ሆኖ የቆየውን የአገልግሎት አሰጣጥ ክፍተት ለማቃለል ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ጠቁመዋል።
እንደ ወይዘሮ አበባ ገለፃ የወረዳ አስተዳደር ግንባታዎች ቀድሞ ሲሠሩ በአሁኑ ወቅት የደረሰበትን ደረጃ ታሳቢ ያደረገ አይደለም። ወረዳዎች እየሰፉ በመሆናቸውም የሚሰጡት አገልግሎትና ተገልጋዩ ባለመመጣጠን ሲቸገሩ ይስተዋላል። በመሆኑም በቀጣይ ቦታ ሲገኝ ደረጃውን የጠበቀ ግንባታ የሚደረግ ቢሆንም እስከዛው ግን ለማስተንፈሻ የሚሆንና አገልግሎት አሰጣጡ ላይ ይነሱ የነበሩ ቅሬታዎች ማቃለል በሚችል መልኩ የአንድ ማእከል አገልግሎት ግንባታና ማስፋፊያ ተሠርቷል። ከዚሁ ጎን ለጎንም የክፍለ ከተማው አስተዳደር አዲስ ህንፃ ግንባታ ሥራ ተጠናቋል።
የኮብልስቶን ንጣፍ መንገድ ሌላው የሚመረቅ የፕሮጀክቱ አካል ነው ያሉት ኃላፊዋ በዚህም ቀድሞ ተጀምረው የተቋረጡ ከ 11 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር በላይ የመንገድ ግንባታ ማጠናቀቅ ተችሏል ይላሉ። ምንም እንኳ ፕሮጀክቶቹ 81 ይባሉ እንጂ በውስጣቸው ያካተቷቸው በርካታ ሥራዎች መኖራቸውንና ለአብነት በቦሌ ቡልቡላ በማሰራት ላይ የሚገኘው ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች አጠቃላይ ወጪው 64 ሚሊዮን ብር የፈጀ ደረጃውን የጠበቀ ቤት መኖሩንም ጠቅሰዋል።
ፕሮጀክቶቹ ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ምክንያቶች ሲጓተቱ የቆዩ መሆናቸውንና የተጀመረው ሳይጠናቀቅ ሌላ አዲስ ፕሮጀክት ሲጨመርባቸው መቆየቱም ለመጓተታቸው ዋነኛ ምክንያት እንደሆነም ኃላፊዋ አብራርተዋል። በመሆኑም የከተማ አስተዳደሩ በአሁኑ ወቅት ነባር ፕሮጀክቶች ሳይጠናቀቁ ወደ አዳዲስ ሥራዎች መገባት እንደሌለበት አቋም መያዙንና በ2011 ዓ.ም የካ ጉራራ ላይ የተገነቡት 25 የሼድ ግንባታ ፕሮጀክቶች የተሠሩትም ሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ያለውን ችግር ለማቃለል ታስቦ እንደሆነ ተናግረዋል።
በቀጣይም ፕሮጀክቶቹ አገልግሎት መስጠት ሲጀምሩ ቀድሞ ይነሱ የነበሩ ችግሮችን ከማቃለላቸውም በተጨማሪ ለበርካታ ነዋሪዎች የገቢ ምንጭ እንደሚ ፈጥሩም አመላክተዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 11/2011
ፍዮሪ ተወልደ