በሰለጠነው ዓለም የቢዝነስና ንግድ ሀሳብ ከማንኛውም ሸቀጥ በላይ ውድ ነው። ምን ያህል ገንዘብ ሊያስገኝ እንደሚችል በመገንዘብም ለቢዝነስ ወይም ንግድ ሀሳቡ ከፍተኛ ግምት ይሰጣል። እንደውም የቢዝነስና ንግድ ሃሳቦችን በመሸጥ የሚተዳደሩና ህይወታቸውን የለወጡ ጥቂት አይደሉም። አዎ! በሰለጠነው ዓለም አዳዲስ የቢዝነስና ንግድ ሀሳቦች እለት በእለት ይመነጫሉ፤ ልክ እንደሸቀጥ ለገበያ ይቀርባሉ።
የአዳዲስ የቢዝነስ ሃሳቦችን ጠቀሜታ አስቀድመው የተረዱ ሀገራትም ሰዎች አዳዲስ የንግድና የቢዝነስ ሃሳቦችን እንዲያመነጩና ሃሳባቸው ተወዳድሮ ገበያ እንዲያገኝ የሚያስችል አሠራር እስከመዘርጋት ደርሰዋል።ይህንኑ አሠራር የሚከውኑ ተቋማትም በህግ ተቋቁመው የንግድ ሃሳብ ውድድር በማካሄድ የምጡቅ ንግድ ሃሳብ አመንጪ ባለቤቶችን አወዳድረው ይሸልማሉ። ከሽልማት በዘለለም ሀሳባቸው መሬት ወርዶ ወደተግባር እንዲቀየር አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋሉ። ወይም ደግሞ ሌሎች እንዲደግፏቸው ሁኔታዎችን ያመቻቻሉ።
በኢትዮጵያም በአንድ ወቅት የንግድ ፈጠራ ሃሳብ ውድድር በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ተጀምሮ የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ግዜ ግን ውድድሩ ተቃርጧል ። ጅምሩ ጥሩ ቢሆንም ሊዘልቅ ግን አልቻለም ። በቅርቡ ግን በፌዴራል ሥራ እድል ፈጠራ ኮሚሽን አዘጋጅነትና በማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ድጋፍ ‹‹ብሩህ›› የተሰኘ የንግድ ፈጠራ ሃሳብ ውድድር በተለያዩ ዘርፎች ተካሂዷል። የውድድሩ ዋነኛ አላማም በሀገሪቱ የተለያዩ ዘርፎች ቁልፍ ችግሮችን ለመፍታትና የሥራ አድሎችን ለመፍጠር የሚችሉ አዳዲስ ሀሳቦች ያሏቸው ወጣቶችን ለማበረታታት መሆኑ ታውቋል። የሦስት ዓመት መርሐግብር መሆኑም ተነግሯል።
በተለያዩ ዘርፎች ለውድድሩ ከቀረቡ 356 ተወዳዳሪዎች ውስጥ ሰባዎቹ ለመጨረሻው የማጣሪያ ዙር አልፈው ከሰባዎቹ ሃያዎቹ በማሸነፋቸው እያንዳንዳቸው 200 ሺ ብር ተሸልመዋል። ከውድድሩ አሸናፊዎች ውስጥም ከወላይታ ሶዶ አንድ፣ ከአዲስ አበባ አስራ ስድስት፣ ከዱራሜ አንድ እንዲሁም ከደብረ ማርቆስ ሁለት ይገኙበታል። ከነዚሁ አሸናፊዎች መካከል ደግሞ አምስቱ ሙሉ በሙሉ በሴቶች የሚመሩ የንግድ ፈጠራ ሀሳብ ውድድሮች እንደሆኑና አስራ አራቱ ሴቶች በከፊል የሚገኙበት መሆኑም ተረጋግጧል።
የንግድ ፈጠራ ሃሳቦቹ በዘርፍ ደረጃ ሲታዩም በማኑፋክቸሪንግ ሦስት፣ በኮንስትራክሽን አንድ፣ በፈጠራ ጥበብ ሁለት፣ በአገልግሎት አንድ፣ በጤና ሁለት፣ በአይ ሲ ቲ አራት፣ በአግሮ ፕሮሰሲንግ አራት እንዲሁም በታዳሽ ሃይል ሁለት መሆናቸውም ከፌዴራል የሥራ እድል ፈጠራ ኮሚሽን የተገኙ መረጃዎች ጠቁመዋል። የውድድር መርሐ ግብሩ ተወዳዳሪዎችን ከመሸለም ባሻገር ሌሎች ወጣቶችም ተሸላሚዎችን አርአያ አድርገው አዳዲስ የንግድ ፈጠራ ሀሳቦችን እንዲያመነጩ የሚያነሳሳቸው መሆኑም ተገልጿል።
በውድድሩ ቀርበው ሽልማት ካገኙት መካከልም የከንባታ ጠምባሮ ዞን ዱራሜ ከተማው የራንታ ቲማቲም ማቀነባበሪያ የንግድ ፈጠራ ሃሳብ አንዱ ነው። ወጣት ጌታቸው ድንቅነህና ጓደኞቹ ደግሞ የንግድ ፈጠራ ሃሳቡ አመንጪና ባለቤት ናቸው። ወጣት ጌታቸው በአፕላይድ ኬምስትሪ የመጀመሪያ ዲግሪ ያለው ሲሆን በተለያዩ ፋብሪካዎች ውስጥ በተማረበት የትምህርት ዘርፍ በማገልገል ሰፊ ልምድ አካብቷል። በፋብሪካ ውስጥ ያሉ እያንዳንዳቸውን ምርት ሚስጥርም ጠንቅቆው አውቋል። በተማረበት የትምህርት መስከ አንድ ቀን አዲስ የንግድ ፈጠራ ሃሳብ ይዞ እንደሚመጣም የዘወትር ሀሳቡ ነበር።
በመጀመሪያ እርሱና ጓደኞቹ በሚኖሩበት አካባቢ ያለውን ነገር በጥሞና ማየት ጀመሩ። በተለይ በዱራሜ ከተማና አካባቢው ለመስኖ እርሻ የሚመች ሰፊ መሬት እንዳለና ከዓመት እስከ ዓመት የሚፈሱ ወንዞች መኖራቸውን አረጋገጡ። አካባቢው በስፋት ቲማቲም አብቃይ መሆኑንም ተረዱ። በአካባቢው ቲማቲም በስፋት ቢበቅልም ታዲያ ወዲያውኑ ጥቅም ላይ ካልዋለ አልያም ለሚፈልገው አካል በቶሎ ካልደረሰ የመበላሸት እድሉ ከፍተኛ መሆኑንም ተረዳ። ቲማቲም ተቀነባብሮ ሳይበላሽ ረጅም ግዜ እንዲቆይ የሚያስችል አሰራር ባለመኖሩም ሀገሪቱ ከውጪ ሀገራት በከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ የተቀነባበሩ የቲማቲም ምርቶችን ወደ ሀገር ውስጥ እንደምታስገባም ተገነዘቡ።
ከዚህ በመነሳትም ወጣት ጌታቸው የሲቪል ኢንጂነሪንግ ባለሞያ ከሆነው አቤል አድማሱና የማርኬቲንግ ባለሞያ ከሆነችው እየሩሳሌም ሃይሉ ከተባሉ ጓደኞቹ ጋር በመሆን ቲማቲምን በሀገር ውስጥ በማቀነባበር ለሀገር ውስጥ ገበያ የማቅረብ ሀሳብ መጣላቸው። ሃሳቡ ድንቅ ቢሆንም ቲማቲምን ሳይበላሽ ለረጅም ግዜ የሚያቆዩ ሚቲየል ፓራብን እና ሶዲየም ቤንዞይት የተባሉ ኬሚካሎችን ከውጪ ሀገር ማስገባት ግድ ሆነባቸው። የንግድ ሃሳቡን ለመጀመር ለእነርሱም ሆነ ለሀገሪቱ ከባድ ፈተና መሆኑን ተረዱ። በይበልጥ ደግሞ ኬሚካሎቹ ለካንሰር፣ ስኳርና የደም ግፊት በሽታዎች የሚያጋልጡ በመሆናቸው ኬሚካሎቹን በተፈጥሯዊ መንገድ ማግኘት እንዳለባቸው ከድምዳሜ ላይ ደረሱ።
በመቀጠል የሁለቱንም ኬሚካሎች ባህሪይና ስሪት ካጠኑ በኋላ ኬሚካሎቹን በተቀራራቢነት የሚተኩት አራት የተፈጥሮ ቅመማት /ቀረፋ፣ነጭ ሽንኩርት፣ ቁሩንፉድና ዝንጅብል/ ስብጥተሮቹን በማቀያየር ተደጋጋሚ ሙከራ አደረጉ። ከአስራ አንደኛ ሙከራቸው በኋላም የቲማቲም ማቆያ መድሃኒቱን መስራት ቻሉ። በሂደትም የንግድ ፈጠራ ሃሳቡ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል የንብረት ባለቤትነት መብት እንዲኖረው ተደረገ። በኢትዮጵያ ጥራትና ደረጃዎች ባለስልጣን መፈተሽ ስለነበረበትም በአርተፊል ሲሙሌሽን ፍተሻ ተደርጎለት የባክቴሪያ መፈጠርን ሙሉ በሙሉ እንዳቆመ ተረጋገጠ። በይበልጥ ደግሞ በዚህ አይነቱ የማቆያ መንገድ የተቀነባበረው የቲማቲም ምርት ከስኳርና ኬሚካል የፀዳ በመሆኑ ከስኳርና ከካንሰር ጋር በተያያዘ የሚከሰተውን ሞት የሚቀንስ መሆኑም ታወቀ። ምርቱ ምንም ሳይበላሽ እየተከፈተና እየተዘጋ ለስድስት ወራት እንደሚቆይም በሚመለከተው አካል ተረጋገጠ።
የኢፌዴሪ የሥራ እድል ፈጠራ ኮሚሽን ‹‹ብሩህ›› የንግድ ፈጠራ ሃሳብ ውድድርን ሲያመቻች የእነርሱም የንግድ ሃሳብ ለውድድር ቀረበ። የንግድ ፈጠራ ሃሳቡ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባውን የተቀነባበረ የቲማቲም ምርት የሚያስቀር ፣ ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል የሚፈጠርና የሚታይ በመሆኑ ከቀረቡት የንግድ ፈጠራ ሃሳቦች ውስጥ አሸናፊ ለመሆን በቃ። ተስፋ ከተጣለባቸው የንግድ ስራ ፈጠራ ሃሳቦች ውስጥም አንዱ ለመሆን ችሏል።
በአሁኑ ጊዜም የንግድ ፈጠራ ሃሳቡ ከሃሳብነት በዘለለ ወደ ተግባር ተቀይሮ ጥቅም ላይ መዋል የሚችል መሆኑ በኢፌዴሪ የሥራ አድል ፈጠራ ኮሚሽን ተረጋግጧል። በከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ ከውጪ ሀገር የሚገባውን የተቀነባበረ የቲማቲም ምርትም በ2 ከመቶ እንደሚተካም የንግድ ፈጠራው ሃሳብ አመንጪዎቹ አረጋግጠዋል። ለኢንቨስትመነቱ መነሻም 259 ሺ ብር ካፒታል እንደሚያስፈልግ አውቀዋል።
የንግድ ፈጠራ ሃሳቡ ሙሉ በሙሉ ወደ ተግባር ሲሸጋገር እ.ኤ.አ በ2022 በአንድ ዓመት ውስጥ 8 ሚሊዮን 500 ሺ ሁለት መቶ ብር ገቢ እንደሚያመጣና 5 ሚሊዮን 769 ሺ 300 ብር ትርፍ እንደሚያስገኝ ይጠበቃል። በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ውስጥ በግብርናው ዘርፍና በማርኬቲግ ውስጥ ለሚገኙ እንዲሁም በየደረጃው እስከጫኝና አውራጅ ድረስ ላሉ 600 ለሚሆኑ ሰዎችም የሥራ እድል እንደሚፈጠር ተገምቷል። ምርቱ ምንም አይነት ሰው ሰራሽ ቀለምና ኬሚካል ያልያዘና በአንቲ ኦክሲደንትና ማግኒዢየም የበለፀገ መሆኑም ከልብ ጋር በተያያዙ የሚከሰቱ በሽታዎችን እንደሚቀንስም ተነግሮለታል። ምርቱ ወደ ገበያ ሲቀርብም መንግሥት፣ ሆቴሎች፣ ልዩ ልዩ ተቋማትና በተለይ ደግሞ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ይጠበቃል።
በአሁኑ ወቅት ተፈጥሯዊ የቲማቲም ማቆያ መድሃኒቱ የሙከራ ደረጃውን አልፎ ወደትግበራ በመግባት ሂደት ላይ ይገኛል። ከፌዴራል የሥራ እድል ፈጠራ ኮሚሽን ጋር በመነጋገርም ምርቱ ከጀመረ በኋላ የጥሬ እቃ እጥረት መፈጠር ስለሌለበት እዛው ዱራሜና በአካባቢው መስኖ ያለባቸው በርካታ ክፍት መሬቶች ላይ በውሃ መሳቢያ ሞተር በመታገዝና በትራክተር በማረስ ቲማቲምን ዓመቱን ሙሉ ለማምረት ቅድመ ዝግጅቶች እየተደረጉ ይገኛሉ። ቲማቲሙን በማቀነባበርና የማቆያ መድሃኒቱን በመጠቀም ለገበያ የሚቀርብበትን ሁኔታ ለማመቻቸትም ስራዎች እየተሰሩ ነው። ለዚህም የማምረቻ ቦታ እንዲሰጥ ከዞኑ አስተዳደር ቃል ተገብቷል። ሆኖም በተገባው ቃል መሰረት ጉዳዩ እንዲፈፀም አሁንም የፌዴራል ሥራ እድል ፈጠራ ኮሚሽንን ግፊትና ድጋፍ ይፈልጋል።
የቲማቲም ማቀነባበሪያው የተለያዩ ማሽኖችንና የፋይናንስ ካፒታል የሚጠይቅ ከመሆኑ አኳያ ወደ ትግበራ ለመግባት የተገኘው የ200 ሺ ብር ሽልማት እንዳለ ሆኖ ማሽን ከሚሰሩ ሰዎች ጋር በመነገጋገር እስከ 250 ሺ ብር በሚሆን ዋጋ በማይዝግ ብረት በ250 የኤሌክትሪክ ቮልት የሚሰራ ማሽን ለማሰራት ስምምነት ተደርጓል። ገንዘቡ ማሽኑን ለማሰራት በቂ ካለሆነም ባለው ገንዘብ ምርቱን ማምረት ይጀመራል።
ጌታቸውና ጓደኞቹ ያለቀለት የቲማቲም ምርት መርካቶ ድረስ ለማቅረብ ውጥን ይዘው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ። በቀጣይም የቲማቲም ማቀነባበሪያ ስራው እንዳለ ሆኖ ከቲማቲም ምርት ወደሚሰሩ የኮስሞቲክስ ምርቶች የመሸጋገር እቅዶችም አሏቸው። ይህም በተለይ በውድ ዋጋ ከውጪ ሀገር የሚገቡ የኮስሞቲክስ ምርቶችን ያስቀራል ተብሎ ይታሰባል።
በቀጣይ ከሃያዎቹ አሥሩ አሸናፊዎች ለስድስት ወራት ያህል ወደ ንግድ ማበልፀጊያ እንደሚገቡና የእነጌታቸውን የንግድ ሃሳብን ጨምሮ ቀሪዎቹ አሥሮቹ ደግሞ ቀድመው ወደ ንግድ ሥራ የመግባት ሂደት ውስጥ በመሆናቸው የፋይናንስ ድጋፍ በኮሚሽኑ በኩል እንደሚደረግላቸው ይጠበቃል።
የፌደራል ሥራ እድል ፈጠራ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ንጉሱ ጥለሁን በተለያዩ ዘርፎች አሸናፊ የሆኑ የንግድ ሥራ ፈጠራ ሀሳቦችን በቀጣይ ዘርፉ ከሚመለከታቸው የተለያዩ የመንግሥት አመራሮች፣ የሥራ እድል ፈጠራ ኮሚሽን፣ የግሉ ዘርፍና የፋይናንስ ተቋማት ጋር በመሆን መሬት በማውረድ ሃሳቡ የሚሊዮኖችን ህይወት እንዲቀይር የማድረግ ሥራ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።
በተጨማሪም የንግድ ሥራ ፈጠራ ሃሳቡ ኢትዮጵያን የሚቀይርና የህብረተሰቡን ችግር የሚፈታ እንዲሆን ለማድረግ ብሎም በጅምር እንዳይቀጭ ሀሳብ አመንጪዎች ረዘም ያለ ሃሳብ እንዲጨምሩበት ኮሚሽነሩ ጠይቀዋል።
በዚህ ረገድ ኮሚሽኑም ሆነ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል። ሌሎች ሃሳቦችም እንዲበረታቱ ኮሚሽኑ የበኩሉን ሚና እንደሚጫወትና ስርዓቱን የመገንባት ሃላፊነቱን በአግባቡ እንደሚወጣ ነው የገለጹት።
ወጣት ጌታቸው ድንቅነህ፤
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ግንቦት 28/2013