ከትናንት በስቲያ ማልዶ በጅግጅጋ ስታዲዬም የነበረው የስምንተኛው የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም የመክፈቻ መርሐ ግብር መቋጫ ማግኘቱን ተከትሎ፤ ዘጠኝ ኪሎ ሜትሮችን የፈጀ ጉዞ ተደርጎ ሌላ ትዕይንት የሚታይበት ስፍራ ተደርሷል፡ ፡ ያማሩ ቤቶችን በውስጡ በያዘው ቅጥር ግቢ አቅራቢያ በረድፍ ተተክለው በርቀት ይታዩ የነበሩ ነጫጭ ድንኳኖች ሲቀርቧቸው የተረበሸ ከተማ መስለዋል፡፡ የሞንታርቦዎች ጩኸት፣ የሰው ትርምስና ጫጫታ ስፍራውን የደራ ገበያ አስመስሎታል፡፡ በርግጥ ገበያው ደርቷል፤ 169 የኢትዮጵያ ከተሞች፣ ሦስት የጎረቤት አጋር ከተሞችና ሌሎች መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሥራ ውጤቶቻቸውን ይዘው የእኔን ጎብኙልኝ ጥድፊያው በቃል ከሚነገረው በላይ ነው፡፡ የፎረሙን መጀመር በንግግር ያበሰሩት የዕለቱ የክብር እንግዳ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ፤ በዚህ ስፍራ በመገኘት የፎረሙ ተሳታፊዎች ሥራዎቻቸውን ለዕይታ ያቀረቡበትን ኤግዚቢሽን ከሌሎች የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች ጋር በመሆን መርቀው ከፍተዋል፡፡
ሥራዎቻቸውን ጎብኝተውም ከተሞች ፎረሙን በአግባቡ እንዲጠቀሙበት በመምከር፤ የሚያገኟቸውን ልምዶች ቀምረውም የተሻለ ሆኖ ለመገኘት መስራት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል፡፡ የኤግዚቢሽኑ ተሳታፊዎችም፤ ፎረሙ እጅጉን እንደጠቀማቸው፤ የተሻለ ሆኖ የመቅረብ ስሜት እንዳጫረባቸውና በዛው አግባብ እየሰሩ ለውጥ እያመጡ ስለመሆናቸው የቀረቧቸውን ሥራዎች በማሳያነት እያነሱ ገልጸውላቸዋል፡ ፡ እኛም ዞር ዞር ብለን ይሄንኑ በመታዘብ ሃሳባቸውንም ጠይቀናል፡፡ ከተማቸው ስምንቱም ላይ፤ እርሳቸው ደግሞ በሦስቱ ላይ የተሳተፉ መሆኑን የነገሩን ፤ ከጅማ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የመጡት አቶ ቢያ አባ ፎኪ ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፤ ፎረሙ ከተሞች ልምድ እንዲለዋወጡና በመካከላቸው ያለውን ልዩነትም እንዲያጠቡ ዕድል የሚፈጥር፤ ህዝቦችንም አንድ ላይ የሚያመጣ ነው፡፡ ከዚህ ባለፈም ከተሞች ብቃታቸውን የሚያሳዩበት፣ የአስተዳደር አቅማቸውን የሚገመግሙበት፣ በጥቅሉ ለህብረተሰቡ ምን ያክል የተመቸ ከተማ እየፈጠሩ ነው የሚለውን በመላው አገሪቱ ከተሞች ፊት ይዘው የሚቀርቡበት፤ ልምድ አካፍለውም ተካፍለውም የሚሄዱበት ነው፡፡
እንደ አቶ ቢያ አባባል፤ ጅማ ከተማ በተሳትፎዋ የተለያዩ ከተሞችን ልምድ እያገኘችና ባገኘችው ልምድም የራሷን ግብዓት ጨምራ እየተጠቀመች ትገኛለች፡፡ በዚህም የከተማዋን መሰረተ ልማት ከማሟላትና የሥራ ዕድል ከመፍጠር ጀምሮ ለሚከናወኑ ሥራዎች ከፍተኛ ተነሳሽነትን ፈጥሯል፡፡ ይህ ደግሞ ለከተማዋ ብቻ ሳይሆን ለጅማ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ጭምር የጠቀመ ሲሆን፤ ኮሌጁ ሌሎች የቴክኒክ ኮሌጆች ይዘው የሚመጡትን በማየት ለበለጠ ሥራ እንዲነሳሳ አድርጎታል፡፡ ለዚህም ቀደም ሲል ከአራት የማይበልጥ ቴክኖሎጂ ይዘው ይቀርቡ የነበረ ሲሆን፤ በዚህ ፎረም ግን አሥር ያህል ቴክኖሎጂዎችን ይዘው መቅረባቸው በመካከላቸው ለተፈጠረው በጎ ፉክክርና ለፎረሙ ውጤታማነት አብይ ማሳያ ይሆናል፡፡ ከዚህኛው ፎረም ከሚያገኙት ልምድ ተነስተውም በቀጣይ የተሻለ ሆኖ ለመቅረብ ይሰራሉ፡፡
እናም ፎረሙ በከተሞችም ሆነ በቴክኒክ ተቋማት መካከል አንዱ ለአንዱ እውቀትና ልምዱን የሚያካፍልበት ዕድል የሰጠ ነው፡፡ ይህ የቴክኖሎጂ ሽግግርና መወራረስ ደግሞ ቴክኖሎጂው በአንድ ቦታ ተወስኖ እንዳይቀር፣ ለወጣቱ የሥራ ዕድል እንዲፈጥርና በአንቀሳቃሾች አማካኝነት አርሶ አደሩም ጭምር እንዲጠቀምበት ዕድል የሰጠ ሆኗል፡፡ ይህ ሂደት ደግሞ ግብርናው በቴክኖሎጂ እንዲደገፍ ከማድረጉም በላይ የገቢ ዕቃን በአገር ውስጥ ምርት ለመሸፈን ጭምር የአገሪቱ ኢኮኖሚ ለሚያደርገው ሽግግር ገንቢ ሚና የሚያበረክት ይሆናል፡፡
ከፎረሙ የሚጠበቀው መፎካከር ሳይሆን፤ ልምድ መለዋወጥን፣ መማማርና በጎ ውድድር ማድረግ መሆኑን የሚናገሩት ደግሞ የሐዋሳ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ስኳሬ ሹዳ ናቸው፡፡ ይህ ሲሆን እኔም እንደ ሌላው ውጤታማ የማልሆንበት ምክንያት ምንድን ነው የሚል ቁጭት ውስጥ በመግባት የተሻለ ነገር ናፋቂነትንና ይህንኑ የማድረግ ተነሳሽነትን እንደሚወልድ ያስረዳሉ፡፡
እንደ አቶ ስኳሬ አባባል፤ በፎረሙ ከተሞች፣ የመንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ የልማት ኃይሎችና ኢንተርፕራይዞች እንደየአካባቢያቸው ተጨባጭ ሁኔታና አቅም የሚያቀርቧቸው ቴክኖሎጂዎች አሉ፡፡ እነዚህ ቴክኖሎጂዎች ደግሞ በከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራና ሁለንተናዊ ዕድገት ላይ የሚኖራቸው ድርሻ ጉልህ እንደመሆኑ፤ ለራስ የሚሆንን አዲስ ቴክኖሎጂ የማግኘት ዕድል ይሰጣል፡፡ ወደፊትም ቢሆን ከተሞች ራሳቸውን የሚያስተዋውቁበት፣ የሚሸጡበትና ያላቸውን ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጭ በማቅረብም ለልማታቸው አጋዥ የሚሆን ባለሃብትን የሚጋብዙበት ነው፡፡
እነርሱም በፎረሙ ያስተምራሉ ያሏቸውንና የአቅማቸውን ይዘው ቀርበዋል፡፡ ከሌሎች በርካታ ነገሮችን ለመውሰድም ተዘጋጅተዋል፡፡ በተለይ ከሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር በተያያዘ ቴክኖሎጂን ከማፍለቅ አኳያ ከልማት ኃይሎች በሀሳብ ደረጃ ያሉ በርካታ ቴክኖሎጂዎች በእነርሱም ሆነ በሌሎቹ ዘንድ እንደመኖራቸው ዕድሉን በአግባቡ ለመጠቀም አቅደዋል፡፡
ለምሳሌ፣ እነርሱ ጋር ውጤታማነታቸው የተረጋገጠና የፈጠራ ባለቤትነት ማረጋገጫ የተሰጣቸው ተፈጥሯዊ የሆነ የፍሳሽ ማዳበሪያ እንዲሁም የትኋን መግደያ አይነት የቤት ውስጥ ምርቶች አሉ፡፡ እነዚህ ደግሞ ገቢ ምርቶችን በመተካት የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ቴክኖሎጂዎች ስለሆኑ፤ በቀጣይ እነዚህ ምርቶች እንዴት መስፋት እንዳለባቸው ነው መታሰብ ያለበት እንደመሆኑም፤ ፎረሙ ቴክኖሎጂና ገበያን ለማስተሳሰርም ጉልህ ድርሻ አለው፡፡
ሐዋሳ ከተማ በርካታ የልማትና ኢንቨስትመንት አቅም ቢኖራትም፤ ያላትን ሀብት ያክል ተጠቃሚ መሆን አልቻለችም፡፡ በዚህ ፎረምም ልምድ ከመስጠትና ከመቀበል ባለፈ ዋና ሥራቸው የሚሆነው የከተማዋን የኢንቨስትመንት ዕድል በማስተዋወቅ የኢንቨስትመንት ዕድል መፍጠር ነው፡፡ በአንጻሩ ከሥራ ዕድል ፈጠራና በተለይም ከአረንጓዴ ልማትና ጽዱ ከተማን በመፍጠር ሂደት ከሌሎች የሚወስዷቸው ልምዶች ይኖራሉ፡፡ በመሆኑም ፎረሙ እስካሁን እንደነበረው የመማማርና የስራ መንፈስ ማነሳሻ መድረክነቱ ከዛሬው የተሻለች ሐዋሳን ዕውን ለማድረግ በካፒታልና ቴክኖሎጂ ፈጠራ ላይ ሁሉም የሚሰራ ይሆናል፡፡
የፌዴራል የከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘነበ ኩሞ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ በፎረሙ በዋናነት በጥቃቅንና አነስተኛ የተደራጁ ኢንተርፕራይዞች ምርትና አገልግሎቶቻቸውን ይዘው የሚቀርቡበት እንደመሆኑ በከተሞች ለሚከናወነው የሥራ ዕድል ፈጠራ ተግባር አጋዥ ግብዓት የሚገኝበት ነው፡፡ ከዚህ ባለፈም ለኢንተርፕራይዞቹ ምርታቸውን ለማስተዋወቅና የገበያ ዕድል ይፈጥርላቸዋል፤ እርስ በርስ ልምድ ይለዋወጡበታል፡፡ መንግሥትም በኤጀንሲው አማካኝነት የሚሰጠው አገልግሎትም የገበያ ትስስር መፍጠር አንዱ ሲሆን፤ ምርትን ማስተዋወቅ፣ አዳዲስ የሥራ ዕድል ፈጠራ ሃሳቦችን ለማግኘት፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማድረግና ልምድ ለመለዋወጥም እገዛው የጎላ ነው፡፡
ለምሳሌ፣ በጎንደር በተካሄደው የከተሞች ፎረም ልምድ ያገኙ ኢንተርፕረነሮች በዚህኛው የራሳቸውን የፈጠራ ውጤት ይዘው ቀርበዋል፡፡ ይህ ደግሞ ከራሳቸው አልፈው ለሌላው የሥራ ዕድል እንዲፈጥሩ መንገድ የሚጠርግ፣ የድህነት ደረጃንም የሚቀንስ ተግባር ነው፡፡ ምክንያቱም በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ተነድፎ ወደሥራ ሲገባ በከተማ ያለው ድህነት ምጣኔ ወደ25ነጥብ7 በመቶ ሲሆን፤ የሥራ አጥነት ደግሞ 16ነጥብ5 በመቶ እንደመሆኑ ይሄንን በግማሽ የመቀነስ ግብ ተቀምጦ ነው እየተሰራ ያለው፡፡ ስለዚህ በፎረሙ የሚገኙ ልምዶች የሥራ ችግር ከመቅረፍም ሆነ በልቶ ከማደር አኳያ ያሉ ችግሮችን ለማቃለል በኤጀንሲው የሚከናወኑ ተግባራት ወደ ውጤት እንዲደርሱ የጎላ ድርሻ እየተወጣ ይገኛል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 11/2011
ወንድወሰን ሽመልስ