ሰርተው በድካማቸው የሚያድሩ፣ ቸርችረው ባገኙት ሽርፍራፊ ሳንቲም ኑሮዋቸውን የሚደጉሙ ታታሪ እናት ናቸው። ዛሬ ገበያ አልቀናቸውም፤ ያሰቡትን ሽጠው ጨርሰው የፈለጉትን መሸመት አልቻሉም። ድካም የበዛበት ውሎ አሳልፈው ምሽት ላይ ወደ ቤታቸው እየተመለሱ ነው። ከገበያተኛ ጋር ሲጋፉና ሲከራከሩ ውለዋል፤ የደከመ አካላቸውን ለመሸከም እንኳን ከብዷቸዋል። የዛለ ሰውነታቸው እረፍት ናፍቆታል። እግራቸውን ወደ ፊት በትግል እየወረወሩ ያዘግማሉ።
በጀርባቸው ያዘሉት እቃ የኩንታል ያህል ከብዷቸዋል። አጥብቀው ያሰሩት ሻሽ ወደ ግንባራቸው አካባቢ በላብ ርሷል። የዓለምን ፈተና የምድርን አስከፊ ገፅታ ለበርካታ ዓመታት የተጋቱ ሴት ስለመሆናቸው ፊታቸውን በጥሞና ያነበበ ይረዳል። አሳዛኝ ገጽታቸው በህይወት አስቸጋሪ ጊዜን ሲጋፈጡ መኖራቸውን ይመሰክራል። ወይዘሮ ፋጤ።
እንደ እርሳቸው በእድሜ የደከመች አህያቸው አቅም ተስኗት ከፊታቸው ሸንከፍ ሸንከፍ እያለች ትጓዛለች። አሁን አሁን ያረጀች አህያ ገበያ ለገበያ ይዘው ሲዞሩና መንገድ ሲሄዱ የተመለከቱ ስራ ፈት የሰፈራቸው ወጣቶች “የአህያዋ እናት” ብለው ስም አውጥተውላቸዋል።
መጀመሪያ አካባቢ “የአህያዋ እናት” እያለ የሚጠራቸውን ሰው ይራገሙ ነበር። አሁን አሁን ለምደውታል። አብዛኛው ሰው የሚጠራቸው “የአህያዋ እናት” እያለ ነው። ባለፈው ጎረቤታቸው እትዬ ዘነቡ “ወይዘሮ ፋጤ እንደምን ዋሉ” እንደምን አሉ ብለው ሲያናግሩዋቸው፣ ሌላ ሰው ሰላም የሚሉ መስሏቸው ወደ ኋላ ዞረው አይተው ነበር። ስማቸውን ረስተውታል።
እማማ ፋጤ ባለ ቅኔ ናቸው። ብዙውን ጊዜ ለሰዎች በተለይ ላናደዱዋቸው ሰዎች መልስ የሚሰጡት በቅኔ ነው። ውስጠ ወይራ ንግግር መታወቂያቸው ነው። በቀጥታ መናገር ብዙም አይቀናቸውም። ይልቁንም ቅኔ ባዘለ አንደበታቸው ብዙ የሚናገርን በአንድ ቃል ኩም ያደርጋሉ።
እማማ ፋጤ ቶሎ እቤታቸው ለመድረስ ተቻኩለዋል። ቤትም ደርሰው እረፍት የሌላቸው ባተሌ መሆናቸውን ፈጽሞ አይዘነጉም። እቤት ያሉ ልጆቻቸው እናታቸውን እንደሚናፍቁ ያውቃሉ። እቤት ሲደርሱ ደከመኝ ብለው አይተኙም፤ ጉልበቴ ዛለ ብለው አረፍ አይሉም። እዚያ ደግሞ ሌላ ስራ ይጠብቃቸዋል። እቤት ገብቶ ለልጆቻቸው ምግብ አብስሎ ማቅረብ የእርሳቸው ድርሻ ነው። የጉልበታቸው መዛል እጅ አሰጥቶ አያስተኛቸውም፤ ምክንያቱም እናት ናቸዋ።
እየተደነቃቀፉ ጉዞዋቸውን ቀጥለዋል። ጭነቱን ወደ ገበያ ሲሄዱ በዚያች በደከመች አህያቸው ነበር የወሰዱት። አሁን ግን አህያዋ ገበያ መሀል እግሯ ተሰብሮባቸው ሊጭኗት አይደለም ራሷን ችላም ወደቤት ለመመለስ አስግታቸዋለች። እያነከሰች ከፊታቸው ታዘግማለች። ጭነው ሊሸጡት ከወሰዱት ድንች ግማሹን በመከራ ሸጠዋል፤ የቀረውን ደግሞ ተሸክመውታል።
መሀል ላይ ድካም ሲሰማቸው አህያዋ ላይ ለመጫን ቢሞክሩም አቅም አጥታ ስትወድቅ ራሳቸው መሸከም ግድ ሆነባቸው። እማማ ፋጤ የዛሬን ያህል ዕድል የራቃቸው ቀን የሌለ ያህል ተማረዋል። ንዴቱም ሸክሙም ግድ ሆኖባቸዋል።
እቤት ደርሰው ለልጆቻቸውን አብስለው ለማጉረስ ተጣድፈዋል። የጉልበታቸው መዛል የአቅማቸው መድከም ሳይሆን እቤት በረሀብ ተቆራምደው የእናታቸውን መምጣት የሚጠብቁ ልጆቻቸውን ደጋግመው አሰቡ።
ባላቸው ከሞተ ሁለት ዓመት አልፏል። ልጆቻቸውን የሚያስተዳድሩት በየገበያው እየዞሩ ገዝተው በሚሸጡት የተለያየ ጥራጥሬና ፍራፍሬ ነው። የማያውቁት ገበያ የለም። የማይተዋወቁት ገዢና ሻጭም እንዲሁ።
እኚህ ታታሪ እናት ሁሌም ወደገበያ በሚመላለሱበት መንገድ የሚመለከቱዋቸው ወጣቶች ዛሬም እንደሁልጊዜው እቦታቸው ላይ ቆመው ሲመለከትዋቸው በኀዘን አንገታቸውን ነቀነቁ። የወጣቶቹን ስራ ፈቶ ሁሌም እዚያ ቦታ ላይ መቆም ሲመለከቱ የልጆቻቸው የወደፊት እጣ ፋንታ ያስፈራቸዋል።
እማማ ፋጤ የነበረው ምርጥ ስማቸውም እንዲለወጥ ያደረጉት እነዚህ ወጣቶች ናቸው። ለማሾፍ ያወጡላቸው ስያሜ ፀደቀ፤ “የአህያዋ እናት” ብለው ለመሳለቂያ የደረቡባቸው ስማቸውን ውዱ ስማቸውን አስነጠቃቸው። እማማ ፋጤ ልጆቹን ባዩ ቁጥር ይበሳጫሉ።
በሚያልፉበት መንገድ ዳር ተኮልኩለው የሚውሉት እነዚህ ስራ ፈት አውደልዳይ ጎረምሶች እማማ ፋጤን ሲያዩ በማሾፍ እና በመሳለቅ ይሳሳቃሉ። እነዚያ ወጣቶች እማማ ፋጤ ላይ ብቻ ሳይሆን በዚያ መንገድ የሚተላለፈውን ሁሉ አንስተው የሚጥሉ በዘለፋቸው የሚያሸማቅቁ ናቸው።
ሰዎች በሚያልፉበት መንገድ ዳር ተኮልኩለው አላፊ አግዳሚው ላይ ቃላት እየተቀባበሉ ሳይመጠን በሚቀነባበር ዘለፋ ይሳለቃሉ። ወጣቶቹ ደሞ ይህን ተግባራቸውን “ሙድ መያዝ” ይሉታል። የሰው ሙድ እየነጠቁ ሙደኛ መባልን ተክነውበታል።
ወጣቶቹ እዚያው መንገድ ላይ ተቀምጠው እማማ ፋጤን ከርቀት ሲመጡ አይተው ተጠቃቀሱ። አንዱ አፉን ወደ እሳቸው አሞጥሙጦ፤ የእርሳቸውን ክብር አዋርዶ ጓደኞቹን ሊያስቅ ተዘጋጀ። እማማ ፋጤን ወርፎ በሱ ነቆራ ሊደሰት ጓዶኞቹንም ሊያስፈነድቅ።
ጉደኞቹን ለመስማት ተዘጋጁ በሚል ትዕዛዝ በአይኑ እየጠቀሰ በወጉ ያልተገራው አፉን ሊከፍትባቸው ተዘጋጀ። እማማ ፋጤ አህያቸውን እየነዱ አጠገባቸው ሲደርሱ “እንዴት ዋሉ የአህያዋ እናት?” አላቸው፤ መልስ ይሰጣሉ ብሎ እየጠበቀ። አካባቢው በልጁ ፌዝ በታጀበው ሳቅ ተሞላ ወጣቶቹ አስካኩ “ካካካካካካካካ….ቂቂቂቂቂቂ….ሃሃሃሃሃ….”የተለያዩ ሳቆች ከተለያዩ ክፍት አፉች ውስጥ አፈትልከው እየወጡ በዚያ ያልፉ በነበሩት እናት ላይ አሽካኩ…አፌዙ…።
እማማ ፋጤ ግን ለምደውታል። የደከመ አካላቸው ይህን ሰምቶም አቅሙን አላደከመም ጠንካራ ናቸውና በሰሙት አልተብሰለሰሉም፤እንደውም ቁብም አልሰጡት።
ይልቁንም እድሜ ባስተማረው ውብ አንደበት ለልጁ መልስ የሚሆን ትልቅ አጸፌታ መልሰው አዘጋጅተው መንገዳቸውን ቀጠሉ። “እንዴት ዋላችሁ ልጆቼ?” አልዋቸው፤ ወጣቶቹ ግን ትርጉሙ ጨርሶ አልገባቸውም ፤ ምናልባትም በፍጹም የእማማ ፋጤ ንግግርን መመንዘር አልቻሉም። ሳቃቸውን የሚያደምቁበት ግልብ ስሜት እንጂ ስለ እኚህ እናት ንግግር ትርጉም መስጠት የሚችል ብልሃት አንዳቸውም ውስጥ የለም። ያሉት አልገባቸውም።
እነሱ እንደሚሉት ”መስሚያቸው ጥጥ ነው ”። አይ እማማ ፋጤ፤ እንጀት አርስ መልስ ነበር የተናገሩት። እነዚያ የሰው ክብር ላይ የሚሳለቁት ገና አልተረዱም።
“እንዴት ዋላችሁ ልጆቼ” ሲሉ መስጥረው ነበር። እኔን የአህያ እናት ብላችሁ ከተሳለቃችሁብኝ ያው እኔም ያህያ ልጆች ብዬ ሰላምታችሁን በአፀፋው ልመልስ ብለዋቸው ይበልጡን ትልቅ ውርጅብኝ እንደ ወረዱባቸው አልገባቸውም።
እንኳን ዛሬ ነገም አይገባቸውም። እነዚያ በሰው ላይ በመሳለቅ ሳቃቸው የበረታው ወጣቶች እነርሱ የቀመሱት የባሰ መሆኑን ማን በነገራቸው። እማማ ፋጤ ሌላ ቃል አልተነፈሱም ፤በራሳቸው አፀፋ ውርጅብኝ ፈገግ ብለው ሸንከፍ ሸንከፍ እያለች ከፊታቸው የምትሄደውን አህያቸውን እየተከተሉ ወደ ቤታቸው አቀኑ። እሳቸው ከቤትም ትልቅ ጉዳይ አላቸው።
… ተፈፀመ …
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ግንቦት 27/2013