በአንድ ወቅት ሦስት መናንያን ህብረት ፈጥረውና ተማሪያቸው የሆኑ ወጣቶችን ይዘው ስለሚሄዱበት ገዳም ታሪካዊ እና መንፈሳዊ ትሩፋቶች እያወጉ በጉጉት ይጓዙ ነበር፡፡ መንገዱ ረጅም ስለነበረ የሚጓዙት አንዱ አንዱን እያበረታ ነበር ። በመካከል ግን ትልቅ ወንዝ ያጋጥማቸዋል። ወንዙም መሻገሪያ ድልድይ ስላልነበረው ለመሻገር የተቸገረች ልጃገረድ ወንዙ ዳር ቆማ የወንዙን መጉደል ትጠባበቅ ነበር። ልጅቱ የሰውን መምጣት በጉጉት ትጠብቅ ነበርና የእነርሱን መምጣት ስታይ ተረጋጋች። ምክንያቱም አዝለዋት እንደሚያሻግሯት አምናለችና ከአጠገቧ ሲደርሱ እንዲያሻግሯት ተማጸነቻቸው። እነርሱ ግን ለሃይማኖታዊ ግዴታቸውን በማሰብና በዝሙት እንወድቃለን ብለው በማሰባቸው መልስ ሳይሰጧት ወንዙን ተሻግረው ጉዟቸውን ቀጠሉ። ይሁንና ከመነኮሳቱ መካከል አንድ በእድሜ የገፉ መነኩሴ ግን የዚያችን ምስኪን ልጃገረድ ተማጽኖ ትተው መጓዝ አልቻሉም።
ውስጣቸውም ትቶ መሄዱን አልቀበል አለ። ስለሆነም ወደ ኋላ በመመለስ ልጃገረዷን አዝለው ያሻግሯት እና ወደ መነኮሳቱ ተቀላቅለው ጉዟቸውን ይቀጥላሉ። ከሳምንት ጉዞ በኋላ ያሰቡት ገዳም ደረሱ። አዛውንቱ ሴቲቱን ሲረሷት ተማሪዎቹና ሌሎቹ መነኮሳት አልረሷትም። እንደተሸከሟት ሳምንት ሙሉ ቆይተዋል። ሁሉም በውስጣቸው ይህንን ለምን አደረገ? ማንነቷ አይታወቅም። ውበቷም ሆነ የተቀባችው ሽቶ ከሩቅ የሚጣራ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከዝሙት የማይተናነስ ኃጢያት እንዲሠራ ለምኞት አሳልፎ ይሰጠዋል እያሉ ውስጣቸውን ሲያስጨንቁት ሰንብተዋል። የእርሷን ውበትና ሽቶም ዳግመኛ በማድነቅ ላይ ናቸው። እናም እርሳቸው በመሸከማቸው ቀንተው ይሁን ኃጢያተኝነታቸውን ለማጋለጥ ፈልገው ውስጣቸው የሚመላለሰውን ለመናገር ይጣደፉ ጀመር። እናም ወደ አንድ በእድሜ የገፉ መነኩሴ ጠጋ በማለት «አባቴ በመነኮሳቱ መካከል ለምን እርሷን ተሸክመው አሻገሩ፤ ይህስ ከእምነታችን አስተምሮ አንጻር ኃጢያት አይደለም?» አሏቸው። መነኩሴውም « ልጄ ያቺን ልጃገረድ ተሸክሜያት አሻግሪያታለው አንተ ግን ሳምንት ሙሉ በአይምሮህ ላይ ስለዚህች ልጃገረድ ስታውጠነጥን ቆይተሃል። ታዲያ የከፋው ኃጢያት ያንተ አይደለምን?» አሉት። ‹‹እኔ ምንም ኃጢያትም ሆነ በደል አልሠራሁም፡፡ እኔ ሴትዬዋን ተሸክሜ ካሻገርኳት በኋላ ጥያት መጥቻለሁ፡፡
እናንተ ግን እስካሁን አረሳችኋትም፡፡ በውስጣችሁ ሁለመናዋ ይመላለሳል፡፡ ውበቷ ከውስጣችሁ አልራቀም፡፡ ስለዚህ በደሉ የእናንተ ነው እንጂ የእኔ አይደለም፡፡ ዓላማችንም ሰውን ማገዝ ነውና አድርጌዋለሁ፡፡ እናንተ ግን ከሁለቱም አልሆናችሁም›› አሏቸው ይባላል፡፡ በረጅም ዘመን ታሪኳ ሀገራችንም ብዙ ወንዞችን ስትሻገር ኖራለች። በዘመናት መካከልም የተለያዩ መንግሥታትን አስተናግዳለች። እነዚህ መንግሥታት ደግሞ ከወንዙ ባሻገር እንደአዛውንቱ የሚለውጥ እንደ ሌሎቹ መነኮሳትና ተማሪዎች በሰው ላይ ኃጢያትን የሚለድፉ ተግባራትን አሳልፈዋል። በተገነዘበት መጠን ሲጓዙም ቆይተዋል። ግን ለአገር ብልጽግና ጥቂቶች ሲተጉ ብዙዎች ይኮንኗቸዋል፡፡ እንደውም ስኬትን እንዳይጎናጸፉ በማደናቀፍ ይፈትኗቸዋል፡፡
ብዙዎች የሰዎች መውደቅና መክሰር እርካታቸው ነው፡፡ መች ይህንን አደረገ፣ አይችለውም፣ ይህ እኮ የእርሱ ጥፋት ነው ማለትም ልምዳቸው ሆኗል። ሞክረው ሲባሉ ግን «የእናቴ መቀነት አደናቀፈኝ» አይነት ምክንያት ያቀርባሉ። በጎ ነገር ለእነርሱ መጥፊያቸው እንጂ ማደጊያቸው አይደለም፡፡ ግን አሁን አገር የሚያስፈልጋት በትውልድ መካከል ያለውን ጥላቻ እንደእኚህ ጽኑ አባት ተሸክሞት የሚሻግራት የሚታትር የለውጥ መሪ ነው። ያለፈውን አሜኬላ እንዲከስም የሚሠራ ዋና ዓላማውን እንጂ ትችትና ወሬ ሰምቶ የማያፈገፈግ ልጃገረዷን ያሻገረውን አዛውንት መሰል መሪ ያስፈልጋል። ከዚህ ጎን ለጎንም ከመሻገር ይልቅ ክፋቱና ኃጢያቱ እየታየው በሃሳብ የሚዋትት ህዝብ ሊኖር አይገባም። ከዚያ ይልቅ ያለፉ ሰዎች መልካም ታሪኮችን ማጉላት ይገባል።
የግለሰብ ድህነት የአገር ድህነት ነው ብሎ የሚያስብ ትውልድ፤ ያለፈ ጥሩ ታሪክ መነሻ፣ መጥፎ ታሪክ ደግሞ መማሪያ እንደሆነ የሚያምን ተተኪ ትውልድ አገሪቱ ሊኖራት ይገባል። አንዱ በአንዱ ላይ መረማመድ ሳይሆን ተያይዞ ማደግን መምረጥ ባህሪ ማድረግም ያስፈልጋል። ለአገር የሚያስፈልገው የአዛውንቱ አስተሳሰብ ነው። አሻጋሪ መሆን ይገባል። አጼ ምኒልክ፣ አጼ ቴዎድሮስ፣ አጼ ኃይለሥላሴና መንግሥቱ መለስና መሰሎቻቸው ጠንካራም ደካማም የአገዛዝ ሥርዓት ነበራቸው፡፡ በታሪክም ቢሆን እንዲሁ ሁለቱንም አስተናግደው አልፈዋል፡፡ አሁን ያለው ኢህአዴግም እንዲሁ በመልካምም በእኩይም የተገለጹ ተግባራትን ያከናወነ ነው። እናም እያንዳንዱ አስተዳደር ከአንዱ አንዱ መማር ያለበት ነገር እንዳለ ማመን ያስፈልጋል፡፡ ሁሉም ፈላጭ፣ ቆራጭ ነው ብሎ ማመን ለለውጥ አያበቃም፡፡
ሁሉም የበቃ ነው ማለትም እንዲሁ፡፡ ሁሉንም የቀደመ ታሪክና ልምድ አያስፈልግም ብሎ ወደጎን መግፋትም ሆነ ያለፈው ታሪክ ወርቅ ብቻ ነው ብሎ ድክመትን ለመሸፋፈን መሞከር ሁለቱም አዋጭ አይደሉም። ጥሩን ከመጥፎ ለይቶ ያለመውሰድና መልካሙን ለማስቀጠል አለመሞከር ዋጋ ያስከፍላል፡፡ በአዲስ ነገር ብቻ መጠመድና የቀደመን አለመመልከት አገርን ለወጪ ይዳርጋል፡፡ ብልሹ አሰራሮች ዳግመኛ እንዲፈጠሩም በር ይከፍታል፡፡
እናም ከቀደሙት በመማርና መልካም ነገሮችን በማወደስ ክፉውን ደግሞ ዳግሞ እንዳይከሰት መማሪያ በማድረግ ወደፊት መገስገስ ያስፈልጋል፡፡ የሰውን ኃጢያት እየተመለከቱ ብቻ መጓዝ ውድቀቱ የከፋ ነው። አዎንታዊ ምልከታ እንጂ አሉታዊ አስተሳሰብ ለአገር አይፈይድም። መሸነጋገልና የሌለ ታሪክ ማውራትም እንዲሁ ምልከታን ያበላሻል። በተለይም በብዙዎች ዘንድ የሚታየው የእኔ ብቻ ይጠቅማል ባህሪ አገርን አይገነባምና ከአስተሳሰብ ጋር መታረቅ ያሻል። ዜጎች እንደዚህ አይነት ክፉ ሃሳቦችን በአዕምሯቸው እያመላለሱ እንዳይጓዙ ማድረግ ላይ መሥራትም ይገባል።
አዲስ ዘመን የካቲት 10/2011