
አዲስ አበባ፦ በኢትዮጵያ አዳዲስ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ወደ ሥራ መግባታቸው በኮንስትራክሽን ዘርፍ ለተሠማሩ አልሚዎች ምቹ አጋጣሚ እየፈጠረ መሆኑን ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ገለጹ።
ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ በድሬዳዋ ከተማ የተገነባውን የፓዮኔር ሲሚንቶ ማኑፋክቸሪንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ማስፋፊያ ፕሮጀክት መርቀዋል። በእዚሁ ወቅት ፕሬዚዳንቱ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ እና በቻይና ባለሀብቶች አጋርነት የተገነባው ፓዮኔር ሲሚንቶ ፋብሪካ ለኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ዕድገት ዘርፈ ብዙ ፋይዳ አለው።
የኢትዮጵያ እና የዓለም አቀፍ አልሚ ባለሀብቶች አጋርነት የዕውቀት ሽግግርና የካፒታል ፍሰትን እንዲሁም ምርታማነትን ማረጋገጥ የሚያስችል ሁኔታ መኖሩን የሚያመላክት መሆኑን ገልጸዋል።
ከእዚህ ቀደም የኮንስትራክሽን ዘርፉ የሚያስፈልገውን ግብዓት ለማግኘት ጥልፍልፍ መንገዶችን ይጠይቅ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡
በኢትዮጵያ አዳዲስ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ወደ ሥራ መግባታቸው በኮንስትራክሽን ዘርፍ ለተሠማሩ አልሚዎች ምቹ አጋጣሚ እየፈጠረ እንደሚገኝም አስረድተዋል።
በኮንስትራክሽን ዘርፍ ኢንቨስትመንትን ማስፋፋት ሀገር የጀመረችውን የልማት ጉዞ ከማሳለጥ በላይ አዋጭ መሆኑን መጠቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የፓዮኔር ሲሚንቶ ፋብሪካም በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በዕውቀት ልማትና ሽግግር ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑ ያስመሰግነዋል ነው ያሉት።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ረቡዕ ግንቦት 13 ቀን 2017 ዓ.ም