ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቅርቡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ እንዳሉት፤ የመንግስት ተቋማት ያለባቸውን ኃላፊነት ያለመወጣት፤ ሚዲያዎችና የፖለቲካ ፓርቲዎች የገንዘብ አቅም ውስንነት መኖር ያልተገባና ከህግ ውጪ የሆኑ ተግባራት በህዝብ ዘንድ እንዲፈጠሩ መንስኤ ይሆናሉ። ይህ ደግሞ ስርዓት አልበኝነትና ህግ አለማክበር እንዲንሰራፋ ያደርጋል። ይሁን እንጂ ህግን በማስከበሩ ዙሪያ መንግስትም ሆነ ህዝቡ እኩል ሀላፊነት ስላለባቸው ያጠፋውን አካል በህግ መጠየቅ ያስፈልጋል።
በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ ጋሻው አይፈራም እንደሚናገሩት፤ መንግስት ስርዓት አልበኝነትን በሚገባ መቆጣጠር ያልቻለው ሁሉም መብቴ ነው የሚለው ነገር በመስፋፋቱ እና ለህግ ባለመገዛቱ ነው። በሌላ በኩል ህዝቡ የሚያምነው፣ የሚቀበለው፣ የእኔ ነው የሚለው አመራርም ሆነ ስርዓት አልተፈጠረለትም። ስለሆነም እንቢተኝነት እንዲንሰራፋበት አድርጎታል። በተለይም በህግ አውጭው፣ አስፈጻሚውና ተርጓሚው መካከል ነጻ፣ ገለልተኛና ግልጽ የሆነ አወቃቀር፣ አንዱ አንዱን የሚገመግምበት ስርዓት ያለመኖሩ ህብረተሰቡ ህጉን እንዳያምነው አድርጓል።
መምህር ጋሻው፤ ህገመንግስቱ ሁለት አይነት ምልከታዎችን ማስተናገዱ በራሱ መንግስትና ህዝብ በህገመንግስቱ ላይ ልዩነት እንዲፈጥሩ አድርጓቸዋል ይላሉ። ግማሹ የህገመንግስት ይሻሻልልን ጥያቄ ሲያነሳ ግማሹ ደግሞ ትክክለኛነቱን ብቻ ይሰብካል። በእርግጥ ለአንድ አገር ህልውና የህገመንግስት መከበር ወሳኝ ጉዳይ ነው። መመራትም ሆነ መተዳደር ያለበትም በህገመንግስቱ ነው። ያንን ላላከበሩና ላልተቀበሉ ሁሉ ህጉ በራሱ መፍትሄ ያመቻቻል። ስለዚህም ለአገር ህልውና ሲባል ሳይስማሙም መስማማት ያስፈልጋል ይላሉ።
ለህግ አለመከበሩ ሌላው ተጠያቂው ሊሂቃኑና አመራሩ ናቸው የሚሉት መምህር ጋሻው፤ ህዝቡን እንደ መሳሪያ በመጠቀም ከህግ ውጪ የሆኑ ድርጊቶች እንዲፈጸሙ ያደርጋሉ። የተለያዩ ማባበያዎችና ስሜት የሚጭሩ ተግባራትን እየነገሩ ያሰማራሉ ባይ ናቸው።
በመንግስትና በህዝብ መካከል ያሉ ሰንሰለቶች ወይ ተሰብረዋል፤ ካሉም ደግሞ ታፍነዋል የሚሉት የፖለቲካ መምህሩ፤ በመንግስት መዋቅር ውስጥ ያሉ ተቋማት ለህዝብ አገልግሎት ሰጪ ቢሆኑም በተገቢው መንገድ ኃላፊነታቸውን አለመወጣታቸው በመንግስትና በህዝብ መካከል ያለው ሰንሰለት ተዓማኒነት እንዳይኖረው አድርጎታል።
መምህር ጋሻው እንደሚሉት፤ መጀመሪያ መሰራት ያለበት ዴሞክራሲያዊና ለህዝብ አገልግሎት የተቋቋሙ ተቋማት ላይ ነው። ነጻና ገለልተኛ የፍትህ ተቋማት እንዲኖር መስራት ተገቢ ነው። የህግ ማዕቀፍ በማዘጋጀትና ተቋማዊ መዋቅር በመዘርጋት ህዝቡ እምነት የሚጥልባቸውን ተቋማት ማጠናከር ይገባል። ህዝቡ በሁሉም ተቋማት ላይ የእኔነትን ስሜት እስኪፈጥር ድረስ የተለያዩ ተግባራት መከናወን አለባቸው። በተለይም የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራው በስፋት ሊሰራ ያስፈልጋል።
በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የህዝብ አስተዳደርና ልማት መምህርና የኢትዮጵያ የህዝብ አስተዳደር ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዚዳንት ዶክተር ባጫ ከበደ እንደሚገልጹት፤ ማህበረሰቡ ከህግ ይልቅ ሽምግልናን ወይም አገር በቀል እውቀቶችን ያምናል። ስለዚህም ህግን የማክበሩን ሁኔታ ልዩ ትኩረት አይሰጠውም። የአገር በቀል እውቀቱ ደግሞ ከመንግስታዊ ተቋማት ጋር ተደጋግፎ እየተሰራበት አይገኝም።
እንደ ዶክተር ባጫ፤ ህዝቡ የሚያምንበትንና የሚገዛበትን ስርዓት መፍጠር ከምንም በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል። ከመንግስታዊ አደረጃጀትና ዴሞክራሲያዊ ተቋማት ጋር አቀናጅቶ መስራትም መለመድ አለበት። በመጀመሪያ ሊሰራ የሚገባው የስርዓት ፍተሻ ማድረግ ነውም ይላሉ። ጥሩውን በጥሩ ማስቀጠል፤ የሚሻሻለውን ማሻሻልና ህዝቡ ምን ይፈልጋል የሚለውን አጥንቶ በስርዓት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል። አስተማሪና አርዓያ የሚሆን አመራር በየደረጃው መፍጠርም ያስፈልጋል። ህዝብን ለማወያየት የሚመረጠው ሰው የተለያየ ፍላጎትን የያዘ መሆን የለበትም።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ኢትዮጵያ ውስጥ ለመገንባት፣ ስርዓቱን ለማሳደግ ዋነኛው ምሰሶ መንግስት በመሆኑ መንግስት አርቆ አስተዋይና ሆደ ሰፊ ሆኖ ዴሞክራሲን ለመገንባት ይሰራል ማለታቸው ይታወሳል። እርሳቸው እንደገለጹት፤ አገሪቱ ዴሞክራሲን መውለድ ብቻ ሳይሆን ተንከባክባ ማሳደግ አለባት። ለዚህም መንግስት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን ከሀይል በመለስ ለመፍታት ጥረት ማድረግ ይገባልም ብለው ነበር።
በቀደሙት ጊዜያት በአንዳንድ አካባቢዎች የተነሱት ግጭቶችና መፈናቀሎች ለህግ አለመከበሩ መንስኤ መሆናቸው ይታወሳል። በተለይም በቡራዩ፣ ጅግጅጋ አካባቢዎች የነበሩ ግጭቶች ሰዎችን ለህልፈት ዳርገዋል፡፡
ህግ ማክበርና ማስከበር ካልተቻለ አገሪቱ ውስጥ ሰብዓዊ መብት ረገጣ ይሰፋል፤ ስርዓት አልበኝነትም ይነግሳል። አገር መረጋጋትም አትችልም። የእርስ በእርስ ግጭቶች ይሰፋሉ። በአጠቃላይ አገር በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካዊና በማህበራዊ ቀውስ ውስጥ ትገባለች።
አዲስ ዘመን የካቲት 10/2011
ጽጌረዳ ጫንያለው