አዲስ አበባ፣የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ተቋሙን በተለያዩ ዘመናት አገልግለው በጡረታና በልዩ ልዩ ምክንያቶች ለተሰናበቱ ሰራተኞችና አመራሮች እውቅና ሰጠ፡፡ ከቀደምት ሰራተኞችና አመራሮች ተሞክሮ መውሰድ ተገቢ ተግባር መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
ትናንት በድርጅቱ ቅጥር ግቢ በተካሄደው የሰራተኞች ቀን በዓል ላይ ተቋሙን በተለያዩ ዘመናት ያገለገሉ ሰራተኞችና አመራሮችን የክብር እንግዳ በማድረግ አስጠርቶ በዘመናቸው ላበረከቱት አስተዋጽኦ እውቅና ለመስጠት የምስጋና የምስክር ወረቀት አበርክቶላቸዋል።
የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጌትነት ታደሰ እንደተናገሩት፤ ማንም ተቋም ዛሬ ላይ የደረሰው የቀደሙት ሰራተኞችና አመራሮች በዘመናቸው ባበረከቱት አስተዋጽኦ ነው። ስለሆነም ሰራተኞችና አመራሮች በዘመናቸው ላበረከቱት አስተዋጽኦ ሁሉ ምስጋና መስጠትና ከእነሱም ተሞክሮ መውሰድ ተገቢ ተግባር ነው።
እንደ ዋና ስራ አስኪያጁ ገለጻ፤ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አንጋፋ የህትመት ተቋም ቢሆንም የእድሜውን ያህል የሚመጥን ደረጃ ላይ አልደረሰም። በመሆኑም ተቋሙን ወደዚያ ከፍታ ማድረስ ከተፈለገ ከቀድሞ ሰራተኞችና አመራሮች የስራ ተሞክሮ መጋራት አስፈላጊ ነው። በዚህ አግባብ መሰረትም አዲሱ አመራር የቀድሞውን ሰራተኞችና አመራሮች በማስጠራት ከምስጋና ባሻገር የሚፈልገውን ምክክር አካሂዶ ተሞክሮዎችን ቀምሯል።
በቀጣይም ተመሳሳይ መድረኮችን በማካሄድ ድርጅቱን መንግስትና ህዝብ ወደሚፈልገው ደረጃ ለማድረስ የተጠናከረ ስራ እየተሰራ መሆኑ የጠቀሱት አቶ ጌትነት፤ ከዚህ አንጻርም በጋዜጦቹ ላይ በቅርቡ የይዘትና የቅርጽ ለውጥ በማድረግ ወደ አንባቢዎቹ ማድረስ እንደሚጀምርም ጠቁመዋል።
እንደ ኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አጠቃላይ ስትራቴጂክ በሆነው እቅዱ ወደፊት ከሚሰሯቸው ስራዎች ውስጥ አንዱ ትልልቅ የሀሳብ ገበያ ሊሆኑ የሚችሉ መድረኮችን ማዘጋጀት መሆኑ የተገለጹት አቶ ጌትነት፣በነዚህ የሀሳብ ገበያ መድረኮች የፓናል
ውይይቶች ፣ታላላቅ ሰዎችና ተናጋሪዎች ፣በተለያዩ ዘርፎች ላይ ጥናትና ምርምር ያደረጉ ሰዎች የሚሳተፉበት ይሆናሉ ብለዋል፡፡እነዚህን መድረኮች ከኦን ላይን ቴሌቪዥንና ከህትመት ስራዎች ጋር ማስተሳሰር አንደኛው ቀጣዩ ስራ እንደሚሆንም አስታውቀዋል፡፡
በእለቱ ምስጋና እና እውቅና ከተበረከተላቸውና በጡረታ ከተገለሉ ሰራተኞች መካከል ድርጅቱን ከ30 አመት በላይ በፎቶ ግራፍ ባለሙያነት ያገለገሉት አቶ ክንፈሚካኤል ሀብተማርያም እንደተናገሩት፤ ከልጅነታቸው እስከ ጉልምስና ዘመናቸው ያገለገሉት ተቋም በዚህ መልኩ ጠርቶ ምስጋና ማቅረቡ ልዩ ስሜት ፈጥሮባቸዋል። በቀጣይም ድርጅቱን አቅም በፈቀደ ለማገልገል ከአመራሩና ከሰራተኛው ጋር የሚሰሩ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በተመሳሳይ ተቋሙን ለረጅም አመታት በአመራርነት ያገለገሉትና የእለቱ መርሀ ግብር ከምስጋናም በላይ እንደሆነባቸው የተናገሩት አቶ ተስፋዬ መንግስቱ እንደገለጹትም፤ አዲሱ አመራር በተቋሙ ውስጥ ያለውንም ሆነ በሌላ ቦታ ያሉትን ሰራተኞች አቅም አሟጥጦ መጠቀም ላይ በርትቶ መስራት አለበት። የዚህ አይነቱ መድረክ ደግሞ ትልቅ አጋጣሚ ስለሆነ በቀጣይ በቅርበት ተመካክሮ ለመስራት እድል ይፈጥራሉ።
ለ28 አመታት በኢትዮጵያን ሄራልድ የሠሩት አቶ ስምረቱ ተገኝ በበኩላቸው፣ ‹‹ይህንን ሰርተሃል እና ለሰራኸው ስራ እናመሰግናለን መባል ቀላል ነገር አይደለም፡፡በህይወትም የሌሉ በተለያየ መንገድ ያልተገኙና ይችን ቀን ያላዩ ሰዎች ይኖራሉ፡፡ነገር ግን ለሰራኸው ስራ እውቅና ከመሰጠት በላይ የሚያስደስት ነገር የለም›› ብለዋል፡፡
ተቋሙ ጋዜጦችንም ሆነ መጽሄት ለማተሚያ ቤት እየከፈለ እንደሚያሳትም ጠቁመው ፣በዚህም ከፍተኛውን ሀብት የሚያወጣው ለህትመት ነው ብለዋል፡፡ስለሆነም በተቋሙ ውስጥም በሚሰሩበት ጊዜያቶች የብዙው ሰራተኛ ሃሳብ የነበረው ፕሬስ የራሱ ማተሚያ ቤት እንዲኖረው ስለሆነ አዲሱ አመራር ቁርጠኛ አቋም ወስዶ መንግስትን ማሳመን እንዳለበት መክረዋል፡፡
በይዘቱ ዙሪያ ድርጅቱ ሚዛናዊ ሆኖ ከወገንተኝነት በጸዳ ፣ ለሀገር ጠቃሚና አስተማሪ በሆነ መልኩ ማቅረብ አለበት ያሉት አቶ ስምረቱ ፣ ይህም ድርጅቱን ተአማኒ፣ አስተማሪ፣ ተወዳጅ እና ለሀገር ጠቃሚ እንዲሆን እንደሚያደርገው አመልክተዋል፡፡
ወይዘሮ ሙሉወርቅ አማረ ከ30አመታት በላይ በእርምና በጋዜጣው የተለያዩ አምዶች በመጻፍ መስራታቸውን ጠቅሰው፣‹‹ድርጅቱ እውቅና ሰጥቶ በዚህ ፕሮግራም ላይ መገኘቴ ፍጹም ደስታ ተሰምቶኛል››ብለዋል፡፡
የእውቅና አሰጣጥ መድረኩ አዲሱ አመራር የተሻለ ነገር እንደሚሰራና ተስፋ ያለው መሆኑን የሚያሳይ ነው ያሉት ወይዘሮ ሙሉወርቅ፣ በድርጅቱ የመልካም አስተዳደር ችግር እንዳይኖር ልመክር እወዳለሁ ብለዋል ፡፡አመራሩ ስራ የሚሰራና የማይሰራ ለይቶ ማወቅ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ድርጅቱ የራሱ ማተሚያ ቤት እንዲኖረውም አዲሱ አመራር መትጋት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጀት ስራ አስኪያጅና የአዲስ ዘመን ዋና አዘጋጅ ዋና ጸሃፊ በመሆኑ ለ32 አመታት ያገለገሉት ወይዘሮ ሂሩት ጎይታይ በበኩላቸው ፣ በአዲሱ አመራር አስታዋሽ አግኝተን ጥሪ መደረጉ በጣም ደስ ብሏቸዋል፡፡
ድርጅቱ የህትመት ሚዲያ እንደመሆኑ መጠን ከሌሎቹ ማንኛውም የመገናኛ ብዙሀን በተሻለ የፎቶና የህትመት ውጤቶቹ መረጃ በመሆኑ ህትመቶች በሚፈለገው ጥራትና መጠን እንዲሰሩ የራሱ ማተሚያ ቤት እንዲኖረው አዲሱ አመራር መንግስትን የማሳመን ስራ መስራት አለበት ብለዋል፡፡
ጋዜጦቹ እና መጽሄቱ ተጠናክረው ዘመኑን ተላብሰው መሄድ አለባቸው፣ ትኩስ የሆነውንም ወጣቱ ሀይልን በማሳተፍ ለወደፊት የተሻለ መስራት ይጠበቅባቸዋል፣ ሀሳብን በማፍለቅ ቶሎቶሎ አነጋጋሪ ስራዎች እንዲሰሩም አመራርና ሰራተኛው መጠንከር ይገባቸዋል ሲሉ መክረዋል፡
በእለቱ በተካሄደው መርሀ ግብር ላይ ድርጅቱን ለበርካታ አመታት አገልግለው በተለያዩ አመታት በጡረታ ለተሰናበቱ 30 ሰራተኞቹ የምስጋና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 10/2011
ሶሎሞን በየነ