የወራት ሽር ጉዷን ጨርሳ እንግዶቿን ስትቀበል የነበረችው የምስራቋ ፀሐይ ጅግጅጋ፤ ከትናንት በስቲያ በክልሉ ቤተ መንግሥት ራሷን በማስተዋወቅ አንድ ብላ የ8ኛውን የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም ለማስጀመር ከዋዜማ ጀምራለች፡፡ በዚህ የዋዜማ መርሃ ግብር በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲና ጅግጅጋ ከተማ አስተዳደር የጋራ ሥራ የሆነ ጽሑፍ ለውይይት የቀረበ ሲሆን፤ የጅግጅጋ ከተማ ታሪክ፣ የባህልና የቱሪዝም ሀብቶች፣ የንግድና ኢንቨስትመንት አማራጮች፣ የኢኮኖሚና ፖለቲካ ሁነቶችን፣ እንዲሁም የከተማዋን መልካም እድሎችና ፈተናዎች አስመልክቶ ለታዳሚዎች ግንዛቤ ለማስጨበጥ አስችሏል፡፡
በውይይቱ እንደተመለከተው፤ ጅግጅጋ አሁን ላይ በርካታ ለውጦች የሚታዩበት ከተማ ትሆን እንጂ፤ የእድሜዋን፣ ሰፊ የመልማት አቅሟንና እምቅ ሀብቷን ለተመለከተ ገና ብዙ ይቀራታል፡፡ አሁንም ከተማዋ ከመሰረተ ልማት ጀምሮ እስከ የሥራ እድል ፈጠራ ባለው ሂደት ብርቱ ጥረት የሚጠይቅ የቤት ሥራ አለባት፡፡ የቤት ልማት፣ የኢንዱስትሪ ፓርክ፣ የወጣቶች ማዕከልና ሌሎችም ለወጣቱም ሆነ ለህዝቡ በኢኮኖሚም ሆነ በእውቀት ሊበለጽግ የሚችልባቸው ተግባራትን ማከናወን ትሻለች፡፡እናም ጅግጅጋ ከራሷ አልፋ ለክልሉ ከተሞች አርዓያ መሆን እንድትችልም የከተማ አስተዳደሩ፣ የክልሉና የፌዴራል መንግስት ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩበት እንደሚገባም ነው የተመላከተው፡፡
የውይይት መድረኩን የመሩት የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትር አቶ ዣንጥራር አባይ እና የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፊ ሙሐመድ በበኩላቸው እንዳሉት፤ በእርግጥ ጅግጅጋ እየተለወጠች ቢሆንም ብዙ መሥራትን የሚጠይቅ ቀሪ ተግባራት መኖራቸውን ስለሚገነዘቡ የክልሉም ሆነ የፌዴራል መንግሥት ተገቢውን ሥራ ይሠራል፡፡ ሆኖም ሥራው ፍሬ የሚያፈራው የህዝቡ ተሳትፎና ባለቤትነት ሲታከልበት መሆኑን መገንዘብ ይገባል፡፡
በዋዜማው መርሃ ግብር ላይ ሀሳብ ለሀሳብ የተገናኘው የፎረሙ ተሳታፊ ትናንት ደግሞ የፎረሙን መክፈቻ ሥነ ሥርዓት ሊታደም ማልዶ በጅግጅጋ ስታዲዬም ተገኝቷል፡፡ ከወትሮው በተለይ በሕብረ ብሔራዊ ቀለም ያጌጠው ስታዲየምም፤ ህብረ ብሔራዊ በሆኑ ህዝቦችም ተሞልቷል፡፡ በክልሉ የማርሽ ባንድ የቀረበው ‹‹ተከብረሽ የኖርሺው በአባቶቻችን ደም፤ እናት ኢትዮጵያ የደፈረሽ ይውደም›› ዜማ ደግሞ ህብረ ብሄራዊውን ቀለምና ህዝብ አንድ መሆኑ የታየበት ነበር፡፡
በጅግጅጋ ከተማ ከንቲባ አቶ ጠይቡ መሐመድ የእንኳን ደህና መጣችሁ የተጀመረው ይህ መርሃ ግብርም፤ ከተሞች በጋራ ተገናኝተው በዚህ መልኩ የጋራ በዓላቸውን ማክበር ሲችሉ ከራሳቸው አልፈው ለአገር የሚተርፍ ሥራን ለማከናወን እድል የሚሰጥ፣ አንድነትን የሚያመጣላቸው እንደሆነ የሚገልጹ ንግግሮች የቀረቡበት ነበር፡፡
የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ካሳሁን ጎንፌ እንዳሉት፤ ፎረሙ በ2002 ዓ.ም ሲጀመር የከተሞችን ትስስርና አብሮነት ለማጠናከር፤ የእርስ በእርስ ትውውቅና የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ ለማስቻል፤ በከተሞች ልማትም የህዝብና የባለድርሻዎችን ተሳትፎ ለማጎልበት ታስቦ ነው፡፡ ምክንያቱም ከተሞች የእውቀትና ቴክኖሎጂ ማዕከል ብቻ ሳይሆን የኢኮኖሚው የጀርባ አጥንት እንደመሆናቸው ይሄንን ሚና መወጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በመሆኑም ፎረሙ ከተሞች ያሉባቸውን ችግሮች ለመሻገር የሚያስችሉ በርካታ ልምዶች የተለዋወጡባቸውና በዛው አግባብ እየተሰራባቸው ያሉ ሲሆን፤ በቀጣይም በሥራ እድል ፈጠራ ሆነ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ትኩረት ሰጥተው መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡
ሚኒስትሩ አቶ ዣንጥራር አባይ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ በኢትዮጵያ የከተሞች እድገት እየተመዘገበ ቢሆንም የከተሜነት ደረጃቸው ግን አሁንም ብዙ መሥራትን ይጠይቃል፡፡ ለዚህም መንግሥት ከተሞቹ ከዓለም ከተሞች ጋር የሚወዳደሩበትን እድል ለመፍጠር በፖሊሲና ስትራቴጂ ተደግፎ እየሠራ ሲሆን፤ ይሄን መሰል ፎረም መካሄዱ ደግሞ ከተሞች እርስ በእርሳቸው እንዲማማሩና ልምድ እንዲለዋወጡ በማድረግ በመካከላቸው የማደግ በጎ ፉክክርን በመፍጠር አጋዥ ይሆናል፡፡ አሁንም መንግሥት የከተሞች እድገትና የመሰረተ ልማት ጉዳያቸው በከተማ ካሉትም ሆነ ከተማን ሽተው ከሚገቡ ህዝቦች ፍላጎት ጋር እኩል መራመድ አልቻለም፡፡ ይሄን ችግር ለማቃለልና ከተሞች ለነዋሪዎቻቸው ምቹና ዘመናዊ እንዲሆኑ ለማስቻል ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል፡፡
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፊ ሙሐመድ በበኩላቸው እንዳሉት፤ የክልሉ መንግሥት አስደናቂ ለውጥ በማድረግ ለከተሞች ብቻ ሳይሆን ለክልሉ ሁለንተናዊ ችግር መልስ ለመስጠት እየሠራ ይገኛል፡፡ ይሄን መሰል ፎረም በክልሉ መካሄዱ ደግሞ በከተሞች ያለውን ችግር ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ውስጥ የክልሉ ከተሞች ልምድ እንዲያገኙና የመፍትሄ አካል ሆነው እንዲሠሩ እድል ይፈጥርላቸዋል፡፡
እንደ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ገለጻ፤ በክልሉ በተለይም በከተሞች ያለውን የሥራ አጥነት ችግር ለመፍታት የንቅናቄ ሥራ ተጀምሯል፡፡ ለዚህም የአመለካከትና የእውቀት ሥልጠና ከመስጠት ጀምሮ በሂደቱ የወጣቶችና ሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ እየተሠራ ይገኛል፡፡ ይሁን እንጂ የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ በዚህ መልኩ የተጀመረውን ለውጥ ለማደናቀፍ፣ በህዝቦች መካከልም ቂምና ቁርሾን ለማኖር የሚሠሩ ኃይሎች በመኖራቸው፤ ህዝቡ ከጎናቸው ሆኖ የለውጡን ቀጣይነት ማረጋገጥና ህዝባዊ መሰረቱንም ማጽናት ይኖርበታል፡፡ይህ ሲሆን የከተሞች ችግር ይፈታል፤ ለክልሉ ህዝብ ጥያቄ ምላሽ ማግኘትም የሚፈለግባቸውን እንዲወጡ እድል ይሰጣል፡፡
ጎዳና ላይ የወደቀ ወገን እያለ የከተሞች ገጽታ እንደማያምር በመጠቆም፤ ከተሞች እነዚህን ችግሮቻቸውን ለይተው መሥራት እንደሚገባቸው ያሳሰቡት ደግሞ የዕለቱ የክብር እንግዳ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ናቸው፡፡ እርሳቸው እንዳሉት፤ በጅግጅጋ ከተማ የሚታየው ለውጥ የነዋሪዎች የሥራ ውጤት እንደመሆኑ በዚህ ሥራቸው ደስ ልትሰኙ ይገባል፡፡ ይህ ፎረምም ለእንደዚህ አይነት ከተሞች የተሻለ የለውጥ ጉዞ ልምድ የሚገኝበት እንደመሆኑ፤ ከተሞች የራሳቸውን ለሌሎች ሊያስተላልፉ፣ ከሌሎችም ሊወስዱ ይገባል፡፡ ይህ ሲሆን ከተሞች በጋራ ልማትና እድገት ላይ የጋራ መግባባት መፍጠርና ከራሳቸው አልፈው አገር የምትጠብቅባቸውን ሚና መወጣት ይችላሉ፡፡
ፕሬዚዳንቷ እንዳሉት፤ በከተሞች ያለው የዘላቂ ልማት ጉዳይና የሚስተዋሉ ማህበራዊ መስተጋብሮች ለከተሞች ፈታኝ ጉዳዮች ናቸው፡፡ እነዚህን ፈተናዎች ለመሻገር ደግሞ የከተሞች ልማትና ግንባታ በእውቀት ላይ ተመስርቶ ሊከናወን ይገባል፡፡ በመሆኑም ከተሞች እንደ ከተማ፤ ህዝቦችም እንደ ህዝብ እንደ አንድ እናት ልጆች በአንድ ተቀናጅተው በአገራዊ ጉዳይ ላይ መሥራት አለባቸው፡፡ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ በሚያደርጉት ጥረትም ጊዜ እንደሌላቸው ተረድተው ያላቸውን ጊዜና በእጃቸው ያስገቡትን እድል መጠቀም ይኖርባቸዋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 10/2011
ወንድወሰን ሽመልስ