በጎሳ፣ በማንነትና በጎጥ የተጠናገረው ዕይታችን ፤ ከአመክንዮ ፣ ከተጠየቅና ከተዋስኦው ከፍታ አውርዶ እንደ እምቧይ ስላፈረጠን ሀገራችን የምትገኝበትን ተጨባጭና ነባራዊ ሁኔታ ሆን ብለን እየዘነጋን ጊዜያዊ ፖለቲካዊ ጥቅማችንን እያሳደድን አንድነታችን ንፋስ እየገባው መተኪያና ልዋጭ የሌላት ሀገራችንን ለአደጋ እያጋለጥናት እንገኛለን። ይህን የአኬሌስ ተረከዛችንን ያወቁ እንደ መልካም አጋጣሚ ያዩ ታሪካዊ ጠላቶቻችንና የውስጥ ተላላኪዎች ከየዋሻቸው ተጠራርተው፤ “ኢትዮጵያን የማዳከሚያው ፤ ዜጎቿን በጎሳና በሀይማኖት ከፋፍሎ የማናከሻው ጊዜው አሁን ነው። “ብለው ሌት ተቀን በአራቱም የሀገራችን ማዕዘናት እንደ አበደ ውሻ እየዛከሩ ነው።
ይሄን እኩይ አላማቸውን ለማሳካት ሸኔ_(ኦነግ)ን ፣ የህወሓት ርዝራዦችን ፣ የጉምዝ ታጣቂዎችን ፣ የጸነፉ ፖለቲከኞችንና አኩራፊ አክቲቪስቶችን በመሳሪያነት ይጠቀማሉ። ንጹሐንን በተለይ ሕጻናትና ሴቶችን ይጨፈጭፋሉ። በዚህም ኢትዮጵያውያን ወደለየለት የርስበርስ ጦርነት እንዲገቡ፤ አንዱ ብሔር ሌላውን በጥርጣሬና በጠላትነት እንዲያይ፤ ዜጎች በመንግስት ላይ እምነት እንዲያጡና ጀርባቸውን እንዲሰጡ፤ እንዲሁም የሚከሰተውን ቀውስ ሁሉ ከሴራ ጋር ያጃምሉና በአናት በአናቱ ጥርጣሬውን የሚያጠናክር ደባ ይጨምሩለታል።
የፓትሪያሪኩ ሰሞነኛ አወዛጋቢ መግለጫና የመስቀል አደባባይ ኢድ ሀይማኖትን ተገን አድርገው የተዶሎቱ ሰሞነኛ ደባዎች ናቸው። ስፖንሰር የሚያደርጓቸውና ስምሪት የሚሰጧቸው የህወሓት እርዝራዦችና የግብፅ መንግስት ሲሆኑ፣ ሱዛን ራይስ እንዳሻት ቁጭ ብድግ የምታደርጋቸው የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩና አማካሪዎች ሲሆኑ፣ የዲፕሎማሲ ጫናውንም በፊታውራሪነት ይመሩታል። ያቀናጃሉ። እንደ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያሉ አለማቀፍ ድርጅቶችና ሚዲያዎች በመናበብ ያራግቡታል።
በዶክተር ቴድሮስ አድሀኖ የሚመራው የአለማቀፍ ድርጅቶችና ዩኒቨርሲቲዎች የተሰገሰጉ የህወሓት ርዝራዦች ከዲጂታል ወያኔና ከቲኤምኤች ጋር በመቀናጀት ሀሰተኛ መረጃውን ከስር ከስር ለምዕራባውያንና ለአለማቀፍ ማህበረሰቡ በመመገብ ግዳጃቸውን ይወጣሉ። የግብጽ መንግስት በተለይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ፣ ደህንነቱና በአለማቀፍ ተቋማቱና በምዕራባውያን ዩኒቨርሲቲዎችና በምርምር ድርጅቶች ያሉ ግብጻውያን ለህወሓት ርዝራዦችና በእሱ ዙሪያ ለተኮለኮሉ ምንደኞች በታላቁ የህዳሴ ግድብ ሽፋን የዲፕሎማሲ፣ የጦር መሳሪያና የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ሳይታለም የተፈታ ነው።
ሀገራችንን ጡት ነካሾች እንደ ውጋት ሰቅዘው የያዟት ሲሆን ምዕራባውያንና ግብጽ ደግሞ ከውጭ ከበዋታል። ሌላው ሀገራችን ባለፉት ሶስት አመታት እያጨደች ያለችው ለግማሽ ክፍለ ዘመን ያህል በተለይ ላለፉት 27 አመታት ተቋማዊና መዋቅራዊ ሆኖ የተዘራውን የጥላቻና የልዩነት አሚካላና ኩርንችት መሆኑን የተጨባጭ ሁኔታው አካል አድርገን አለመረዳታችን ነው። ከሁሉም በላይ ከፍ ብሎ የተመለከቱትን የደህንነት ፣ የጸጥታ ፣ የተግባቦትና የዲፕሎማሲ ስብራቶችን አበክሮ የሚከላከል አልያም ከተከሰቱ በኋላ ወጌሻ ሆነው የሚያክሙ ተቋማት ገና በግንባታ ላይ መሆናቸውን ሆን ብለን ወይም በቅንነት አለመገንዘባችን ነው። ይሄን የሀገራችንን ነባራዊና ተጨባጭ ሁኔታ ባለመገንዘብ ወይም ችላ በማለት ለጠላቶቻችን አውቀንም ሆነ ሳናውቅ መጠቀሚያ መሳሪያ እየሆን ነው። ለመሆኑ እኛ በተለምዶ ተጨባጭ ወይም ነባራዊ ሁኔታ የምንለው ነጮች ወደ ኅልዮት ከፍ አድርገው የቀመሩት የተግባራዊ ኅልዮት/pragmatic theory /ምንድን ነው።
ተግባራዊ ኀልዮት ሰፊና ጥልቅ የፍልስፍና ጽንሰ ሀሳብ የተሸከመ ቢሆንም ለመግባባት ያህል ብቻ እንደሚከተለው እበይነዋለሁ። ነባራዊ ኀልዮት የአሜሪካውያኑ ሲ ኤስ ፒርስ እና ዊሊያም ጀምስ የፍልስፍና ንቅናቄ ሲሆን፤ በአጭሩ ሲተረጎምም ሁኔታዎችን፣ እንዲሁም የሚያጋጥሙ ችግሮችን ተጠየቃዊና አመክኖአዊ በሆነ አግባብ መከወን፣ መፍታት ነው። ከፅንሰ፣ ከንድፈ ሀሳብ ይልቅ፤ በተጨባጭ፣ መሬት ላይ ባለ እውነታ፣ በነበራዊ አውድ መመራትን የሚለፍፍ ፍልስፍና ነው። ከዚህ አንፃር አብዛኛዎቹን የሀገራችንን የፖለቲካ ልሂቃንን፣ ምሁራን፣ አክቲቪስቶችን፣ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ ብልጽግናን፣ መገናኛ ብዙኃንን፣ ወዘተ . ከኀልዮቱ አንጻር ስንቃኛቸው ውስንነት ይታይባቸዋል።
ተግባራትን በተጨባጭ ሁኔታ ላይ ተመስርቶ የመከወን፤ ችግሮችን ከነባራዊ ሁኔታ አንፃር መርምሮ የመፍታት ክፍተት፣ ድክመት የሌለበት ተቋም፣ የፖለቲካ ፓርቲ፣ ልሂቃን የለም ብል ከድፍረት እንዳይቆጠርብኝ። በስሜታዊነት፣ በግብታዊነት፣ በመንጋ ግፊት፣ በግል ፍላጎት፣ በምክንያት፣ በእውቀት፣ በአብርሆት enlightement ላይ ተመስርቶ ከማድረግ ይልቅ በዘውጉ፤ በተጨባጭ፣ በነባራዊ ሁኔታ ላይ ተመስርቶ ከመወሰን ፣ አቋም ከመያዝ ይልቅ በደመነፍስ በመነዳት ልምሻ ያልተጠቃ የለም።
መጠኑ ይለያይ እንጂ ብልጽግናን ጨምሮ አብዛኛዎቹ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች መሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ፣ ነባራዊ ሁኔታ በተጠየቅ፣ በአመክንዮ መርምሮ፣ ተንትኖ ከመፍታት ይልቅ በአፈታት፣ በአቦሰጥ፣ በግብታዊነት መፍታትን ይመርጡ ስለነበር ከሶስት አመታት ወዲህ ሀገራችን የገባችበትን ቅርቃር እየተመለከትን ነው። ትህነግ ቀደም ባሉት 27 አመታት በሀገሪቱ አንሰራፍቶት የነበረውን ኢፍትሐዊነት፣ ኢ ዴሞክራሲያዊነት፣ ተቋማዊ ዘረፋ፣ ጎጠኝነት፣ ተጨባጭ፣ ነባራዊ ችግር መሆኑን አምኖ ከመቀበል ይልቅ መካድን፣ ማስተባበልን በመምረጡ ሀገሪቱንም እሱንም ይዞ ለመሞት የሄደበትን ርቀት እየተመለከትን እንገኛለን።
በአንጻሩ የለውጥ ኃይል በተሟላ መልኩ ባይሆንም ፤ ካለፉት ሶስት አመታት ወዲህ የሀገሪቱን፣ የፓርቲውን ነባራዊ ፣ ተጨባጭ ሁኔታ መርምሮ፣ ተንትኖ መፍትሔ መውሰድ በመቻሉ ዛሬ በተሻለ ተስፋና ዕድል ላይ እንድንገኝ አድርጓል ። ስጋቱ ፣ ማመንታቱና ውልውሉ እንዳለ ሆኖ። ይህ የለውጥ ኃይል በሀገሪቱ የነበረውን ተጨባጭ ሁኔታ ያገናዘበ የመፍትሔ ሀሳብ ፈለገ ካርታ ይዞ ባይመጣ ኖሩ ሊከተል የሚችለውን ቀውስ ፣ እልቂት ባሰብሁ ቁጥር ያባባኛል። ሆኖም የለውጥ ኃይሉ ፖለቲካዊ ነባራዊ ሁኔታዎችን አንጥሮ የለየውን ፣ መፍትሔ የሰጠውን ያህል ኢኮኖሚያዊ ነባራዊ ሁኔታዎች አጢኖ እንደ ፖለቲካው የሚመጥን ተጨባጭ እርምጃ መውሰድ ባለመቻሉ የኑሮ ውድነቱ ፣ ስራ አጥነቱ ፣ የዋጋ ግሽበቱ የፈጠረው ችጋር ፣ እርዛት ፣ ርሀብ ለውጡን ሙሉዕ እንዳይሆን አድርጎታል።
ፖለቲካው ላይ የታየው ተስፋ ሰጭ ለውጥ በኢኮኖሚው ቢደገም ኖሮ ለለውጡ የተሻለ ቅቡልነትን ከማስገኘት አልፎ በሕዝቡ ዘንድ የተሻለ መግባባት ፣ አንድነት ይፈጥር ነበር። ባለፉት 27 አመታት ቀን ከሌት ተቋማዊ በሆነ መልኩ ሲሰበክ በነበረ የዘውግ ፣ የማንነት ፖለቲካ የተነሳ በሕዝብ መካከል የተፈጠረውን መጠራጠር ልዩነትም ለማጥበብ ያግዝ ነበር። ከፖለቲካዊ ማሻሻያዎች ጎን ለጎን መዋቅራዊ የሆነውን የኢኮኖሚ ችግር መፍታት ለውጡን ለማስቀጠልም ሆነ ሀገራዊ አንድነትን ለመመለስ ያለው ፋይዳ እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ተቀብሎ ነገ ዛሬ ሳይባል ተጨባጭ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል ። ፖለቲካው ላይ የሚታዩ ነባራዊ ሁኔታዎችን ለይቶ የተወሰደው በኢኮኖሚው ላይ መድገም ካልተቻለ ለውጡን በሁለት እግሩ ማቆም ይቸግራል። ወደአልተፈለገ አቅጣጫ ሊወስደው ስለሚችል በጊዜ የለም ስሜት መረባረብን ይጠይቃል። ማሻሻያዎች ሁሉን አቀፍ እና መሳ ለመሳ የሚሄዱ ሆነው እንደገና መቃኘት አለባቸው።
የሀገር በቀል ማሻሻያውና የ10 አመቱ የብልጽግና ፍኖተ ካርታ እንዳለ ሆኖ የአጭር ጊዜና ፈጣን የኑሮ ውድነት ማስተካከያ ፣ የዋጋ ግሽበትን ወደ አንድ አኃዝ ዝቅ ማድረጊያ ስልት መንደፍ እና ተጨማሪና አዳዲስ የስራ እድል ፈጠራ ላይ የመረባረብ ጉዳይ ለነገ የሚባል አይደለም ። ለተቀማጭ ሰማይ ቅርቡ ነው እንዲሉ እነዚህ አቅጣጫዎች ቀላል ናቸው ማለቴ እንዳልሆነ ልብ ይሏል። ከዘላቂ መፍትሔው ጎን ለጎን ልዩ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ለማለት እንጂ።
እንደ መውጫ
በሀገራች ዴሞክራሲና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት እንዲጎለብት ከማንነት ፣ ከዘውግ ፈለፈል shell እንዲሁም ከስሜታዊነትና ግብታዊነት ተላቀን፤ በአብርሆት ፣ በነባራዊ ኀልዮት ላይ ተመስርተን ፤ ተጨባጭ ሁኔታውን አንጥረን ለይተን፤ ተጠየቃዊና አመክኖአዊ ውሳኔ ላይ የምንደርስ ከሆነ የሰውነትን እርካብ ተቆናጠን ሀገራዊ ፣ ኢትዮጵያዊ መንበር ላይ እንደርሳለን። የሀገራችንን ነባራዊ ሁኔታ ማስቀደም እንችላለን። በዚህ ላይ ቆመን የምናሳልፈው ውሳኔ የምንይዘው አቋም ምክንያታዊና ሀገርን ያስቀደመ ይሆናል። ይህ ሳይሆን ቀርቶ ነባራዊ ሁኔታውን ሸምጥጠን ክደን ወደ ማንነት ጥፍራችን ገብተን ፤ ከተጠየቃዊነት ይልቅ ስሜታዊነትንና ግብታዊነትን የመረጠን ለታ ሰው የመሆን ፀጋችን ከመገፈፉ ባሻገር ሀገራችንን ፣ እናታችንን እናሳዝናለን። ማቅ እናስለብሳለን ፣ ትቢያ እናስነሰንሳለን ፤ በልጆቻችንም እንደተወቀስን እንኖራለን። አዎ ! ሳይመሽ ማንነት ፣ ዜግነት ወደሌለው ተጠየቃዊነት ፣ አመክኖአዊነት እንመለስ፤ በአምሳሉ የተፈጠርን ሰው ብቻ እንሁን። በዚህ እሳቤ ስንመላለስ የሀገራችንን ተጨባጭ ሁኔታ እናስቀድማለን። የዛን ጊዜ ከራሳችን ፣ ከተፈጥሮ ፣ ከጎረቤታችን ፣ ከሀገራችን ጋር እንታረቃለን።
ሀገራችን ኢትዮጵያ በሀቀኛና ጀግኖች ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር !!!
አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም(ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ግንቦት 21/2013