ሀሳባቸውና ቁርጠኝነታቸው ለሥራ ያነሳሳል፡፡ ውስጣዊ ጥንካሬያቸውን ስኬታማነታቸውን ይመሰክራል፡፡ ብዙዎቹ ለውጫዊ ውበታቸው ቦታ አልሰጡም፣ አልተሸቀረቀሩም፡፡ ሴቶቹ ፊታቸውን የሚያቀላ ሜካፕ፣ ዓይናቸውን የሚያጎላ ኩል
አልተኳሉም፡፡ የሽቷቸው መአዛ ታዋቂ (ብራንድ) አይደለም፤ አለባበሳቸው ከሩቅ የሚጣራ ቀለማቱም ታስበውባቸው የተናበቡ አይደሉም፡፡ ነገር ግን ንፁህና መንፈሰ ጠንካራ ናቸው፡፡ ስለ ንግድ ሥራቸው ሲናገሩ ሌላው ሰው ራሱን ተኝቶ እንደሚበላ ሰነፍ እንዲቆጥርና በቁጭት እንዲነሳሳ ያስገድዳሉ፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት በዕለተ አርብ በአዳማ ከተማ የአነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ማስፋፊያ ባለሥልጣን ከክልል ለተውጣጡ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ላይ ተሰማርተው ስኬታማ የሆኑ ሴቶችን ጋብዞ አወያይቷል፡፡ በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩት ሴቶች በመድረኩ እንዲናገሩ ሲጋበዙ በብዙ ስብሰባዎች ላይ እንደሚታየው አብዛኛዎቹ ለመናገር
አይፈሩም፡፡ የብዙዎቹ ሃሳብ ለማካፈል ወደኋላ የማይሉ ደፋሮች እንደሆኑ የሚያሳይ ነው፡፡
ከታዳሚዎቹ መካከል ዕድሜዋ በሰላሳዎቹ መጀመሪያ የሚገመት የመንግሥት ሠራተኛ ሆና ሁለት ልጆች ከወለደች በኋላ ባለቤቷ ማረፉንና ልጆቿን ለብቻዋ ለማሳደግ እንደተገደደች ብዙ መከራዎችን እንዳሳለፈች ለተሰብሳቢው መግለጽ ጀመረች፡፡ የብቸኝነት ኑሮ ሲከብዳት ከአዲስ አበባ ወደ አዳማ መግባቷን
ተናገረች፡፡ አያይዛም የተለያዩ ሥራዎች ላይ ተሰማርታ እንደነበር፤ በመጨረሻም ገንዘብ ስታጣ አጎቷ ቤቱን አስይዞ ተበድሮላት ወደ ዶሮ እርባታ መግባቷን አብራራች፡፡ አሁን ላይ ዕዳ ከመክፈል አልፋ የተሻለ ሕይወትን በመምራት ላይ መሆኗን ስትናገር፤ ተሰብሳቢዎቹ ባለቤቷ በሞት ቢለያትም ልጆቿን የእናትነትን ብቻ ሳይሆን የአባትነትን ግዴታ ጨምራ በመወጣት ኑሮን ታግላ አሸናፊ ለሆነችዋ ጠንካራ ሴት አጨበጨቡላት፡፡
‹‹ሴቶች ብድር አትፍሩ፤ ዋናው እሰራለሁ ብላችሁ ካሰባችሁ የተበደራችሁትን ትመልሳላችሁ፡፡›› ብላ፤ እርሷ በብድር እየሰራች አትርፋ እንደምትመልስ ነገር ግን በሥራ ውጣ ውረዷ የባለሥልጣናት የገንዘብ አምጪ (የሙስና) ጥያቄ ያማረራት መሆኑን
ተናገረች፡፡ ‹‹እኔ ለማገኘው መንግሥታዊ አገልግሎት ለማንም ገንዘብ አልሰጥም›› በማለቷ ብዙ ነገር እንዳጣች፤ አንዳንድ ባለሥልጣናትም ጉዳይ ለማስፈፀም ገንዘብ ካልሰጠች አገልግሎት ባይሰጧትም፤ እስከ አሁን በሥራዋ ጥንካሬ ታግላ ማሸነፍ መቻሏን ያጋጠማትን ክስትት ተናግራለች፡፡
በውይይቱ ላይ የተሳተፉ ብዙዎቹ ሴቶች እንደርሷ ተመሳሳይ ጋሬጣዎች እንዳጋጠሟቸው፤ የመንግሥትን ቅርብ ድጋፍ ባያገኙም ጠንካራ ዓላማ በመያዛቸው ያሰቡበት መድረሳቸው እንደማይቀር ገለፁ፡፡ ተሰብሳቢዎቹ አንዳንዶቹ የራሳቸውን ኑሮ ከማሸነፍ አልፈው በአሥር የሚቆጠሩ ዜጎችን ቀጥረው እየሰሩ አገርን በመጥቀም ጉልበታቸውንና ጊዜያቸውን በአግባቡ ሥራ ላይ እያዋሉ ህልማቸውን እውን ለማድረግ የማያቋርጥ ትግል ውስጥ መሆናቸውን ተናገሩ፡፡ ነገር ግን ብዙዎቹ እንደገለፁት ፈተና የሆነባቸው በየቢሮው የሚያጋጥማቸው ለአገልግሎቱ ገንዘብ ስጡን የሚሉ የሌብነት ጥያቄዎች ናቸው፡፡
በስብሰባው ላይ ከሀዋሳ እንደመጡ የተናገሩት ግለሰብ፤ በተለያየ መልኩ ጨረታ በወጣ ቁጥር የሚፈፀሙ አሻጥሮች እና ሕግን ያልተከተሉ አካሂዶች ዕድገታቸውን እየጎተቱባቸው መሆኑን በመግለፅ፤ አንዳንዴ ሕይወታቸው ሳይቀር ለአደጋ የተጋለጠበትን አጋጣሚ በመጠቆም ያለፈውን አስታውሰው ሴቶች በኢትዮጵያ ሰርተው ለማደግ ያለባቸው ፈተና ከባድ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አንዳንዴ የሚሰሩ አሻጥሮች ‹‹ሕይወትሽን አጠፋዋለሁ›› እስከሚል ዛቻ ይደርሱ እንደነበርም ገልጸዋል፡፡
ሴቶቹ በቤተሰብ በኩልም የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን አልሸሸጉም፡፡ አንዲት ሴት ምንም እንኳ ተበድራ ሰርታ ራሷን መለወጥ ለሌሎች ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ብትፈልግም ባሎችም እንቅፋት እንደሚሆኑ
አንስተዋል፡፡ በተለይ የብድር አቅርቦት ለማግኘት ባሎች ጭምር የብድሩ ጥያቄ ላይ መፈረም ቢኖርባቸውም ሴት ሰርታ ስኬታማ ትሆናለች የሚለውን ስለሚጠራጠሩ ፈቃደኛ የማይሆኑበት ሁኔታ መኖሩን ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪ ብድር ሲፈለግ የወለድ መጠን ከፍተኛነት እና የማስያዣ ጥያቄ እንዲሁም ሂደቶቹ እጅግ ከባድ
ናቸው፡፡ ነገር ግን ሁሉንም እናልፈዋለን በሚል ፅናት እየታገሉ በመሥራት ላይ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡
‹‹ሴት የምትፈልገውን መጠየቅ እስከቻለች ድረስ መስራት እንጂ በየቢሮ እየሄደች ችግር ሲያጋጥማት እያለቀሰች ተስፋ ቆርጣ መሸሽ የለባትም፡፡›› ያሉት ተሰብሳቢዎቹ፤ እርስ በእርስ መደጋገፍ አንዱ ያላወቀውን ሌላው ማሳወቅ አገርና ሕዝብን መደገፍ እንጂ በድካም መዛል የማይታሰብ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በእርግጥም እነዚህ ሴቶች የጥንካሬ ተምሳሌቶች ናቸው፡፡ ብዙዎቹ ከስኬታቸው ጀርባ የሚታየው የእነርሱ ትጋት ነው፡፡ ነገር ግን አቋራጭ መንገድን የሚጠቀሙ ዋልጌዎች በመንገዳቸው ጋሬጣ ሆነው ከማደናቀፍ አልፈው በአፍጢማቸው ሊደፏቸው ይጥራሉ፡፡ በቅድሚያ በብዙ ፈተናዎች መካከል ማለፏን የገለፀችዋ ሴት እንደተናገረችው፤ የቦታ ይሰጠኝ ጥያቄ ለማቅረብ ወደ አንድ ቢሮ ብዙ ምልልስ ካደረገች በኋላ፤ ‹‹በእግርሽ ሳይሆን በእጅሽ ነይ…›› የሚል የባለሥልጣን መልስ ተሰጣት፡፡ የእርሷ መልስ ‹‹ምንም ነገር በጉቦ ማግኘት አልፈልግም፤ በሐቅ ሊሰጠኝ የሚገባ የልማት መሬት እንደማንኛውም ዜጋ ይሰጠኝ፤ ያለበለዚያ
አልፈልግም፡፡›› አለች፡፡ በመጨረሻ ባለሥልጣኑ የሰጣት መልስ ‹‹ ድሃ ሆነሽ ትቀሪያለሽ›› የሚል ነበር፡፡ ነገር ግን እርሷም ‹‹አላማ ያለው ድሃ አይደለም፡፡ ድሃም
አይሆንም፡፡›› ካለች በኋላ፤ አሁን ከድህነት ወጥቻለሁ ብላለች፡፡
ጠንካራዎቹ በማኑፋክቸሪንግ ላይ የተሰማሩት ሴቶች በተለያየ መልኩ ‹‹ቤት አሰሪልኝ፤ ግንብ አሳጥሪልኝ›› ከሚል ጀምሮ እጅግ የተጋነነ ብር እስከ መጠየቅ የሚደርሱ ባለሥልጣኖች እና ባለሞያዎች መኖራቸውን በመግለፅ፤ አገር የምትለወጠው በዚህ መንገድ ባለመሆኑ ‹‹ እባካችሁ ጉቦም ሆነ ሙስና ጉርሻም ሆነ ቅምሻን በማቆም በእውነት ሰርተን ስለዕውነት አገራችንን እናሳድግ ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በግል ካጫወትኳቸው ሴቶች መካከል አንደኛዋ የቅባት እህሎችን ወደ ውጪ የምትልክ መሆኑን በመግለፅ፤ መጋዘን በአንድ መቶ ሰማኒያ ሺህ ብር ተከራይታ እንደምትሰራ የመሬት ጥያቄ ስታቀርብ ‹‹በባንክ የሒሳብ ቁጥርሽ ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ ከሌለሽ ሊሰጥሽ አይችልም›› ተብላ መከልከሏን ነግራኛለች፡፡ ከላኪነት ጋር ተያይዞም በአሠራሩ ላይ ትልቅ ክፍተት አለ፡፡ ሆኖም ‹‹ህልሜ ትልቅ በመሆኑ ከአሰብኩበት እንዳልደርስ የሚያግደኝ ምንም ነገር የለም›› ስትል ገልጻለች፡፡
በእርግጥም ሴቶቹ ግንባራቸው ላይ ትልልቅ ዓላማ እንዳላቸው ይነበባል፡፡ ጠንካራና ቀልጣፋ ናቸው፡፡ ከራሳቸው አልፈው ለቤተሰባቸው ብቻ ሳይሆን ለአገር የሚተርፉት እነዚህ ሴቶች በተለያዩ ተልካሻ ምክንያቶች ወደ ኋላ እንዳይቀሩ አሠራሮች ሕጋዊነትን የተከተሉ መሆን አለባቸው፡፡ በየመንገዱ እየተደነቀሩ የሚያደናቅፉ ሙሰኛ ባለሥልጣናት አደብ እንዲገዙ ማስቻል አስፈላጊና ተገቢም ነው፡፡ የአንዲት ጠንካራ ሴት ሕይወት ስኬት የብዙ ቤተሰቦች ሕይወት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ስለሚኖረው ጠንካራዎቹን ሴቶች መደገፍ ሲገባ ማደናቀፍ ተገቢ አይደለም፡፡
ምህረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ግንቦት 18/2013