አገር መቼ ትፈርሳለች ቢሉ አያገባኝም የሚል ትውልድ የተፈጠረ ዕለት ይባላል፡፡ ሀገር የመገንባት ህልማችንን እውን ለማድረግ ከሰላም ውጪ አማራጭም ሆነ አቋራጭ የለም፡፡ ልዩነትን ከሚያሰፉ አስተሳሰቦች ወጥተን በሚያጋሩን ዙሪያን አብረን መሥራት ይገባናል፡፡ አንድ ካልሆንን የትም መድረስ አንችልም፡፡ አገራችንም አሁን የሚያስፈልጋት ይህ አስተሳሰብ ነው፡፡ መቻቻል አብሮ ለመኖር መሰረታዊ ነገር ነው፡፡ አለመቻቻል ብዙ ዋጋ እንደሚያስከፍል ሩቅ ሳንሄድ በራሳችን ላይ አይተነዋል፡፡ ሁላችንም የአገሬ ጉዳይ ይመለከተኛል፤ ያገባኛል፤ ድርሻ አለኝ ማለት አለብን፡፡ እርስ በእርሳችን ሁሌም እንዲህ ያለውን መስተጋብር ማዳበር ይገባናል፡፡
ልዩነታችንን ወደጎን ትተን በሚያግባባን የህዝባችን ብሶትና መከራ ላይ አተኩረን ብንሠራ መጨረሻችን ያማረ ይሆናል፡፡ የሁላችንም ፍላጎት መሆን ያለበት ህዝባችንን እንዴት እንቀይረው የሚለው ነው፡፡ ግለሰባዊ ፍላጎት እና ግለሰባዊ አጀንዳዎች ለህዝባችን አይጠቅመውም ፡፡ እኛ መሥራት ያለብን ህዝባችንን ታላቅ ለማድረግ መሆን አለበት፡፡ ታግለን ታግሰን መጨረሻ ላይ እኛ በግለሰብ ደረጃ ታላቅ ሆነን ህዝባችን ግን እዛው የቀድሞ ቦታ ከተገኘ ተሸናፊው እኛ እንጅ ህዝባችን አይደለም፡፡
ህዝብ ከግለሰብ ይበልጣል፡፡ የህዝብ ታላቅነት ከግለሰቦች ታላቅነት ይልቃል፡፡ በዚህ ወቅት እንኳ ትልቅ የሆኑ ግለሰቦች አሉን፡፡ ህዝባችን ግን ትልቅ አልሆነም፡፡ በምሁርነታቸው በሀብታቸው በስልጣናቸው ወዘተ… አንቱ የተባሉ ግለሰቦች እንዳሉን እሙን ነው፡፡ እነዚህ ግለሰቦች በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ እና በማህበራዊ ህይወቱ የጠነከረ ማህበረሰብን መፍጠር ይኖርባቸዋል፡፡ አለበለዚያ የእነርሱ አንቱነት ከንቱ ይሆናል፡፡
በደረስንበት የዕድሜ፤ የዕውቀ ትና የአስተሳሰብ ደረጃ ታላቅ ማህበረሰብ መፍጠር አቅቶን እራሳችንን ብቻ ታላቅ ለማድረግ የምንሯሯጥ ከሆነ ብናሳካውም እንኳን አናጣጥመውም፡፡ ከህዝብ ጋር የተገኘ ታላቅነት ግን ፍሬው ያማረ ጥፍጥናው የተለየ ነው፡፡ ስለዚህም ማንኛውም ለታላቅነት የሚደረግ የግል ሩጫ ለማህበረሰብ አንዳች ጥቅም ይዞ የሚመጣ መሆን አለበት፡፡
ኢካዴፍ ከሚባል ድረ ገጽ ያነበብኩት አንድ ጽሁፍ ሀሳቤን ስለሚያጠናክርልኝ አንዳንድ ሀሳቦችን ተጠቅሜዋለው ፡፡ «እኛ ኢትዮጵያውያን አንድ የረባ የጋራ ቃል ኪዳን ሳይኖረን እየኖርን ነው። ለአንድ ህዝብ ደግሞ የተጻፈም ይሁን ያልተጻፈ ኪዳን ወሳኝ ነው። ኢትዮጵያውያን በፈጠሯቸው የፖለቲካ ቡድኖች መካከል ያንተ መሬት የኔም ነው፣ የኔ መሬት ያንተም ነው፣ እኔ የኔ የምንለው የለም ሀገራችን የእኛ ናት የሚል የረባ ቃል ኪዳን የለንም። ህገ-መንግሥታችን ኢትዮጵያን የብሔሮች ጥርቅም ብቻ ያደርግብናል።» መሬትና የተፈጥሮ ሀብት የሚያቀራምት የፖለቲካና የፌዴራል ሥርዓት ውስጥ ሆነን መገፋፋት፤ መገዳደል፤ መፈናቀል ቢኖር ልንደነቅ አይገባም።
የፌዴራል ሥርዓት ትሩፋት ለዜጎች ምርጫን መጨመር ነው። ምርጫው ደግሞ ለዜጎች ሁሉ ነው። በመሆኑም ማንነትን የፖለቲካ መሣሪያ ከማድረግ አውጥተን ብሔራዊ ማንነትን ለፖለቲካ መሳሪያ ለስበት ህጎቻችን ማጠንጠኛ ማድረግ ያስፈልገናል። ይህንን ስናደርግ በማንነት ከለላ ውስጥ በሚኖሩ የፖለቲካ ቡድኖች መካከል ማንነት አጋጭ ኃይል አያመነጭም። የክልል እንዲሁም አገር ባለቤትነት ከብሔር ባለቤትነት ማላቀቅና ለብሔራዊ ማንነት የሚሰጥ የፌዴራል ሥርዓት መፍጠር ያስፈልጋል። የኢትዮጵያውያንን አዲስ ኪዳን መሰረት ያደረገ ሥርዓት መፍጠር ያስፈልጋል። በፖለቲካ ቡድኖች መካከል የሚኖር ወሰንን ከማንነት ጋር እንዳይያያዝ አድርጎ ጂኦግራፊን፣ ቋንቋን፣ አብሮነትን፣ ለአስተዳደር አመቺነትን መሰረት ያደረገ እንዲሆን ማድረግ መፈናቀልን መገፋፋትን ብሎም መገዳደልን ከስር መሰረቱ ያጠፋል።
እኛ ኢትዮጵያውያን በመረ ዳዳት እና በመደጋገፍ የምናምን የወገንን ስቃይ የማንፈልግ ነን፡፡ስሪታችን እንዲህ ነው፡ ፡ በፍቅር በታነጸ ማህበረሰብ ውስጥ ያደግን በዘር በቀለም በሃይማኖት መቧደንን የማናውቅ እኛ እንዲህ ነበርን፡ ፡ ታዲያ ቀድሞ የነበረውን የመቻቻል መልህቅ የሆነውን እውነት ማን እንዴት እንደወሰደብን ሳናውቅ በቁም ሞትን፤ ዘር ቆጠራ ገባን፣ ሃይማኖት እና ጎጥ እየመረጥን መደራጀት ጀመርን፤ ገደልን፣ ዘረፍን፣ አፈናቀልን ብዙ ለሰሚም ለተመልካችም የሚከብዱ አስነዋሪ ሁነቶች አከናወንን፤ ከመጀመሪያው እኛ ግን እንዲህ አይደለንም፤ አልነበርንም፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ ማንነት ከባድ ጉዳይ ሆኗል። በርግጥም ቡድኖች መብታቸው ሊጠበቅ ይገባል። ኢትዮጵያውያን እጅግ ብዙ እንቁ የሆኑ ባህላዊ እሴቶች ባለቤቶች ነን። ፖለቲካችን ከዘውግ ይላቀቅ ስል፣ የፌዴራል ሥርዓቱ ከብሔር ይውጣ ስል ለብሔር ጥሩ ጠገግ ሠርተን መሆን አለበት። ይህ ቤት ደግሞ ከየባህሉ የተውጣጡ የባህል ቡድኖች ተወካዮች የሚመሰረት ቤት ነው። ከፖለቲካው መንግሥት ተነጥሎ በራሱ ነጻ የሆነ ቤት ፈጥረን ባህላችንን ባህላዊ ማንነትን መጠበቅ እኩልነትን ማሳየት መከባበርን ማሳየት እንችላለን። ሰላም እርቅን ለማምጣት ይህ ቤት ይረዳናል። የጥንቃቄንም ሥራ ይሠራል። ይህ ቤት እያለ ማንነትን መሰረት ያደረገ መፈናቀል አይኖርም። በመሆኑም የውስጥ ችግሮችን ለማስቆም ብሎም አጠቃላይ ሥርዓታችንን ለማሻሻል እንዲህ ዓይነት የመዋቅር ለውጥ ማምጣት አለብን። ይህንን ቤት ስንፈጥር ዘውጎች በአንድ ጊዜና ቦታ በሰላም ማኖር የሚያስችል የመሳሰብ ህግን እናመርታለን። የህዝባችንንም ታላቅነት ለመመለስ ተባብረን ተጋግዘን ተረዳድተን ልንሠራ ይገባል፡፡ አንድ በሚያደርገን ላይ አንድነታችንን እናሳይ፡፡ አንድነት ኃይል ነውና፡፡ በየቀጣናው የሚገኙ ወጣቶችና ሌሎችም ያስጀመሩት ትግል ተደምሮ ሊቀጥል ይገባዋል፡፡ ተበጣጥሰን የትም አንደርስም ፡፡
ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተራማጅነት፣ አንድነት፣ አንጻራዊ ነጻነት እና አሰራር ምቹነት ለማጠናከር ተስፋ ሰጪ ሥራዎችን እየሠራ ነው፤ እኛም የተሰፋ ጭላጭሎችን እያየን ነው፡፡
የተጀመረውን የመድበለ-ፓርቲ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታውን ይበልጥ ለማጠናከር የፖለቲካ ምህዳሩን የማስፋት እና የዴሞክራሲ ተቋማትን የማጠናከር፣ የፌዴራል ሥርዓቱ ብሔረሰባዊና ኢትዮጵያዊ ማንነት አስማምቶ ለመሄድ የሚያጋጥሙ አመለካከት ችግሮችን መቅረፍ፣ ጠንካራ የመንግሥት ቢሮክራሲ ለመፍጠር ሴክተር ተኮር ሪፎርሞች አስፈላጊነት አጽንኦት ሰጥቶም መሥራት ያስፈልጋል።
በተጨማሪም በኢኮኖሚውመስክ እያጋጠሙ ያሉ የወጪ ንግድ መቀዛቀዝና አፈጻጸሙ ዝቅተኛ መሆን፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ የውጭ ብድር የመክፈል አቅም እየተዳከመ መሄድ፣ የገቢ መሰብሰብ አቅም ዝቅተኛ መሆን እና የኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች በቀጣይ በጥናት ላይ ተመስርቶ መፍታት እንደሚያስፈልግ ልጠቁም እወዳለሁ።
ለዴሞክራሲያዊ ሽግግር አስተ ማማኝ ድልድይ ግንባታ የሚያግዙትን የለውጥ መርሖች አንጥሮ ለማውጣት እንዲቻል፣ እሴቶቹና መርሆቻችንን ተገንዝቦ፣ ለለውጡም የሚጠበቅበትን ተሳትፎ በሚያደርግበት የዕውቀትና የተሳትፎ ልክ እንዲገኝ ለማስቻል፤ በቀጣይ እንዲረጋገጥ ለሚታሰበው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓተ መንግሥት እና ሕዝቡ የሚያደርጉት ጠንካራ ትግልና ድጋፍ እንዲቀጥል ለማስቻል የለውጡ መርሆች ላይ ቀድሞ ከተደረገው ይልቅ ጥልቅ ውይይት መደረግ ይኖርበታል።
የተጀመረው ለውጥ በሚጠ በቀው ደረጃ የተፈጸመ እንዲሆንና ህገ መንግሥታዊ መሰረት ያለው ከመሆኑም በተጨማሪ የህዝብን ፍላጎት ማዕከል ያደረገ እንዲሆን እያንዳንዱ ግለሰብ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት መወጣት አለበት፡ ፡ በያገባኛል ስሜት ከአባልነት ወደ አካልነት ስሜት በመምጣት ከእኔነት ወተን እኛነትን እናጠናክር፡፡
ስለዚህ ኢትዮጵያውያን ሁሉ አንድ ታላቅ ቃል ኪዳን ይሻሉ። እኛ ኢትዮጵ ያውያን ከፈጣሪ በታች የማንከፋፈል አንድ ህዝብ ነን የሚል ቃል ኪዳን ያስፈልገናል፡፡ ይህ ኪዳን ገፊ ነገሮችን ከፖለቲካ ቡድኖቻችን ውስጥ ያስወግዳል። መሳሳብ፣ ፍቅርና መደመር የሥርዓታችን የደም ስር እንዲሆኑም ያደርጋል፡፡ ስደተኞችን የተገፉትን ሁሉ ኢትዮጵያውያን እንደ ሚቀበሉ ቃል ቢገቡ ገፊ የሆኑ ትርክቶች እንዲሁም ሥርዓቶችን እናባርርና መሳሳብን እናዳብራለን። ይህ መሳሳብ ደግሞ ተቆርቋሪነትን ለአገር እንድናደርግ አንዱ ስለራሱ ብቻ ሳይሆን ስለሌላውም እኩል እንዲሰማው ያደርጋልና መፍትሔው አዲስ ኪዳን ለኢትዮጵያ መግባት ነው።
(ይህንን ጽሁፍ ለማዘጋጀት ከኢካዴፍ ድረ ገጽ ያገኘሁትን መረጃ ተጠቅሜያለሁ)
አዲስ ዘመን የካቲት 9 ቀን 2011
አብርሃም ተወልደ