አገር አቀፉ ስድስተኛው ምርጫ በተያዘው በጀት ዓመት ለማካሄድ ዝግጅቶች ተጠናቀው ወደ ተግባር ለመግባት ስራዎች ተጀምረዋል:: ለዚህ ደግሞ ሲቪክ ማህበራት ፈቃድ ተሰጥቷቸው ህብረተሰቡን እያስተማሩ ይገኛሉ:: ከነዚህ ሲቪክ ማህበራት ውስጥ የኢትዮጵያ ወጣቶች ሰላምና ብልፅግና ተልዕኮ ሊግ ይገኝበታል:: የሊጉ ፕሬዚዳንት ወጣት ብርሃኑ በቀለ ሰሞኑን በምርጫ ዙሪያ ስለሰሯቸው ስራዎች ማብራሪያ ሰጥቷል:: እንደሚከተለው አቅርበነዋል::
ሊጉ ያከናወናቸው ተግባራት
የኢትዮጵያ ወጣቶች ሰላምና ብልፅግና ተልዕኮ ሊግ የተቋቋመው በኢፌደሪ ሲቪል ማህበረሰብ ኤጀንሲ በአዋጅ 2011 ነው:: ሊጉ የተቋቋመው በመጀመሪያ ወጣቱን በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግ ነው:: ሁለተኛው ዘላቂ ሰላም በአገሪቱ እንዲሰፍን የበኩሉን ሚና እንዲጫወት ታስቦ ነው:: ዘላቂ ሰላም የሚመጣው በፖሊስ ሀይልና በፍትህ አካላት ብቻ ሳይሆን ስለ ሰላም ግንዛቤ በመስጠትና በማስተማር ሰላም ማምጣት ይቻላል የሚል እምነት አለ:: ስለዚህ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ የኢትዮጵያ ወጣቶች ሰላምና ብልፅግና ተልዕኮ ሊግ ስለ ሰላም ወጣቱን ያስተምራል ማለት ነው::
ሰላም ሲባል የሰላም ይዘቶች ለምሳሌ የህግ የበላይነት፣ መደጋገፍ፣ መቻቻልና ሌሎችን ያካትታል:: ባህላዊ የግጭት አፈታት አንዱ የሰላም ማምጫ መንገድ ነው ተብሎ ይታሰባል:: ቀጣይነት ያለው ሰላምና ልማት እንዲመጣ ሊጉ ስራዎችን ለመስራት እቅዶች አሉት:: ቀጣይነት ያለው ልማት ሲባል በአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ወጣቱ ወደ ስራ ካልገባ ልማት ማምጣት አይቻልም::
ወጣቱ ወደ ስራ አለም እንዲገባ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ:: ለምሳሌ ወጣቱ ስራ ከመፈለግ ይልቅ ስራ ፈጣሪ እንዲሆን የስራ ፈጠራ ክህሎት ስልጠና ለወጣቱ እየተሰጠ ይገኛል:: ወጣቶቹ የስራ ፈጠራ ክህሎት ስልጠና ከወሰዱ በኋላ በጥቃቅንና አነስተኛ ከተደራጁ መንግስት ለተደራጁ ወገኖች የብድር አቅርቦትና የቦታ ማመቻቸት ይሰራል:: በተጨማሪም ኤግዚብሽንና ባዛሮች እንዲዘጋጁ ያደርጋል:: ይህ ግንዛቤ የሌላቸው ወጣቶች በብዛት ይገኛሉ::
ምርጫን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ወጣቶች ሰላምና ብልፅግና ተልዕኮ ሊግ ምርጫውን መታዘብ እንደሚችልና የመራጮች ስልጠና እንዲሰጥ ከብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ፈቃድ አግኝቶ በአሁኑ ወቅት በርካታ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል:: ሊጉ ከያዛቸው ዋነኛ ስራዎች መካከል የምርጫ ስራ አንዱ ነው:: ሌላ ደግሞ የአረንጓዴ ልማት ስራ ነው:: ከአዲስ አበባ አረንጓዴ ልማት ቢሮ ጋር በመተባበር በተያዘው በጀት አመት የተተከሉትን ችግኞች ውሃ የማጠጣትና የመንከባከብ ስራ ሊጉ ሲሰራ ነበር:: ወጣቱ ከብጥብጥና ከረብሻ እንዲሁም ወንጀል ከመስራት እንዲቆጠብ ሊጉ ጠንክሮ ይሰራል::
ሌላው በዚህ ወቅት በወጣቶች ላይ እየተስተዋለ የመጣውን ሱሰኝነት ነው:: ወጣቱ በሱስ ተጠምዶ በሺሻ ቤትና በጫት ቤቶች ተቀምጠው በመዋላቸው ሂወታቸው እየተበላሸ ይገኛል:: ከዚህ ነገር ውስጥ እንዲወጡ ወጣቶችን የማስተማርና የማንቃት ስራ ለመስራት ዝግጅቶች ተደርገዋል:: ለወደፊት የሱስ ማገገሚያ ቦታዎችን ለማዘጋጀት እቅዶች አሉት::
ሊጉ ለምርጫው ያከናወነው ስራ
በዘንድሮ ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ የኢትዮጵያ ወጣቶች ሰላምና ብልፅግና ተልዕኮ ሊግ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በአፋርና በደቡብ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል የመራጮች ስልጠና እንዲሰጥ ከብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ፈቃድ ተሰጥቶታል:: በሁለት ዋና ዋና ክልሎች ተጨባጭ የሆነ ስራ መስራት ተችሏል:: ለምሳሌ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከአስራ አንዱም ክፍለከተማ ለተውጣጡ ወጣቶች ስልጠና ተሰጥቷል::
ለወጣቶች ብቻ ሳይሆን ለሴቶችና ለአካል ጉዳተኞች ስልጠናው እንዲሰጥ ተደርጓል:: ስልጠናው በተጨባጭ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ለአርባ አምስት ሺህ ወጣቶች፣ ሴቶችና አካል ጉዳተኞች የተሰጠ ሲሆን በሌላ በኩል ለሁለት ሺህ አምስት መቶ ወጣቶችም እንዲሰጥ ተደርጓል። በኦሮሚያ ክልል አዳማ፣ ቡራዩ እንዲሁም ወሊሶ ከተማዎች ለ35 ሺ ወጣቶች ስልጠና እንዲሰጥ ተደርጓል። በአጠቃላይ እስካሁን ድረስ ለዘጠና አምስት ሺህ ዜጎች የገፅ ለገፅ ስልጠና ተሰጥቷል።
የገፅ ለገፅ ስልጠና ሲባል ፊት ለፊት በተደረገ ግንኙነት ማለት ሲሆን ስልጠናው በመገናኛ ብዙሀን እንዲዘገብ ነው የተደረገው። ሊጉ በተደጋጋሚ ዜጎች ካርድ እንዲወስዱ ግንዛቤ እየሰጠ ይገኛል። በመሆኑም የመራጮች ምዝገባ የተጠናቀቀ በመሆኑ የተደረጉ ቅስቀሳዎች ውጤታማ ናቸው ብሎ መውሰድ ይቻላል። በአገር አቀፍ ደረጃ ከ36 ሚሊዮን ህዝብ የመራጭነት ካርድ መውሰዳቸው ይታወቃል። በኦሮሚያ ክልል 15 ሚሊዮን ህዝብ በላይ ካርድ አውጥቷል። ከሌሎች ክልል በተሻለ በኦሮሚያ መራጮች በአግባቡ ተመዝግበዋል።
ሊጉ የሰጣቸው የምርጫ ስልጠናዎች ይዘት የመጀመሪያው የፖለቲካ ፓርቲዎች ስነምግባር አዋጅን ነው። አዋጁ እያንዳንዱ ፖለቲካ ፓርቲ ማንፌስቶ፣ ፖሊሲና ስትራቴጂ የመግለፅ መብት አለው። የፖለቲካ ፓርቲዎች ስነምግባር መጣስ የለባቸውም። ዜጎችን ከዜጎች የሚያጋጭ ንግግር፣ ሃይማኖትን ከሀይማኖት የሚያጋጭ ንግግር እና ብሄርን ከብሄር የሚያጋጭ ንግግር ማድረግ የተከለከለ ነው። ምክንያቱም የግጭቱ ምንጭ እነሱ ስለሚሆኑ ነው። በአገሪቱ ማንኛውም ፖለቲካ ፓርቲ ከገዥው ፓርቲ ጋር እኩል ተወዳዳሪ ናቸው። ነገር ግን የፖለቲካ ፓርቲ እርስበርስ መሰዳደብ ሳይሆን ችግሮቻቸው ላይ አተኩረው መነጋገር ይችላሉ። ከመሰዳደብ ፖለቲካ ፓርቲዎች መታቀብ አለባቸው። አንዳንድ ፖለቲካ ፓርቲዎች በመገናኛ ብዙሀን በኩልና በሲቪክ ማህበራት በኩል ችግሮቻቸውን እንዲያስተካክሉ ተደርገዋል።
ዜጎች የሚደግፉትን ፓርቲ በምን መልኩ መደገፍ እንዳለባቸው የተቀመጡ ህጎች አሉ:: ዜጎች ድጋፋቸውን ሲያደርጉ ወደ ብጥብጥና ወደ ግጭት በሚያመራ መልኩ መሆን የለበትም:: እያንዳንዱ የፖለቲካ ፓርቲ ደጋፊ ዜጎች ድጋፋቸውን ሲያደርጉ ከማንኛውም ግጭት የሚቀሰቅስ ተግባር መፈፀም የለባቸውም:: አሁን አገሪቱ ባለችበት ሁኔታ ግጭት ቀስቃሽ ንግግር የተከለከለ ነው:: ገዥው ፓርቲ ሁለት ኃላፊነት አለበት:: የመጀመሪያው ህገ መንግስቱንና የህገ መንግስቱን ኃላፊነት ማስከበር ነው:: ሁለተኛው ገዥው ፓርቲ በራሱ ተፎካካሪ በመሆኑ ኃላፊነቶችን ሊወጣ ይገባል::
ግንዛቤ ለህብረተሰቡ በሚሰጥበት ጊዜ ትኩረት የሚደረገው በምርጫው ሂደት ላይ ነው:: የምርጫ ሂደት ሲባል ቅድመ ምርጫ፣ ምርጫውና ድህረ ምርጫ ናቸው:: ቅድመ ምርጫ የሚያካትተው የእጩ ምልመላ፣ የፖለቲካ ፓርቲ ቅስቀሳ እና የመራጮች ካርድ መውሰድ ናቸው:: እጩ ምዝገባ ላይና መራጮች ምዝገባ ላይ ወጣቶች፣ ሴቶችና አካል ጉዳተኞች ፖለቲካ ፓርቲዎች ሴቶችን በእጩነት አሳትፈዋል ወይ ተብሎ ሲታይ አነስተኛ ነው::
አብዛኛው ፖለቲካ ፓርቲ በሚገባ ሴቶችን፣ ወጣቶችንና አካል ጉዳተኞችን አላሳተፉም:: በመራጮች ምዝገባ ወቅት ደግሞ ሂደቱ እንዲታወክ የሚሰሩ አካላት ነበሩ:: በሽብር የተፈረጁ ፖለቲካ ፓርቲዎች ምርጫው እንዲስተጓጎል ጠንክረው እየሰሩ ናቸው::
በምርጫው ወቅት ደግሞ የምርጫ ድምፅ አሞላል ላይ እውቀት ለሌላቸው ዜጎች ግንዛቤ ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ ነው:: በድህረ ምርጫ ወቅት ደግሞ ችግሮች እንዳይከሰቱ ጥረት ይደረጋል:: በተለያዩ አገራት ከምርጫ በኋላ ብጥብጥ የሚነሳው ውጤትን ካለመቀበል ጋር በተያያዘ ነው:: በዚህም ወጣቱ ወደ ብጥብጥና ወደ ግጭት እንዲያመራ የሚያደርግ ነው:: ይህ እንዳይሆን የማስተማር ስራዎች ይሰራሉ::
በምርጫው ውጤት ወጣቱም ሆነ ማንኛውም ማህበረሰብ ክፍል መቀበል ያለበት ከብሄራዊ ምርጫ ቦርድ መሆን አለበት:: ከምርጫ በኋላ ለሚፈጠሩ ችግሮች ቅሬታ ማቅረቢያ መንገዶችን መጠቀም የግድ ይላል:: ወጣቱ ቅሬታ ካለው ከብጥብጥ በራቀ መልኩ ቅሬታ ማቅረብ አለበት:: ምርጫውን የሚከታተል ገለልተኛ ፍርድ ቤት በመቋቋሙ በዛ መንገድ መቅረብ አለበት:: በሊጉ የመራጮች ካርድ እንዲወጡ ለማድረግ 97ሺህ 500 ለሚሆኑ ወጣቶች የግንዛቤ ስልጠና ሰጥቷል::
በምርጫ ስራው ያጋጠሙ ችግሮች
ሊጉ በውስጡ ያቀፋቸው አባላቱ የተማሩ በመሆናቸው ሌሎችን ለማብቃት ስልጠና እየሰጡ ናቸው:: ነገር ግን የግብዓትና የበጀት ችግር በመኖሩ የታሰበውን ያህል መስራት አልተቻለም:: በዚህም ከአዲስ አበባና ከኦሮሚያ ክልል ውጪ ስልጠና ለመስጠት አልተቻለም:: ስልጠና በሚሰጥበት ወቅት የገንዘብ አቅም አስፈላጊ ነው:: በአዲስ አበባ ከተማና ኦሮሚያ ውስጥ የወጣው ወጪ ከፍተኛ ነበር:: የገንዘብ ድጋፍ ከተገኘ በሌሎች ክልል ለመንቀሳቀስ እቅድ አለ::
የምርጫው መራዘምና ፈቃድ አሰጣጥ በነበረ መዘግየት በሊጉ ላይ ተፅዕኖ ፈጥሯል:: ፈቃድ ከምርጫ ቦርድ ሲሰጥ በወቅቱ ባለመከናወኑ ችግር ፈጥሮ ነበር:: አሁን ደግሞ የድምፅ መስጫ ካርድ መውሰጃው ቀን ተራዝሟል፤ በዚህ ጉዳይ ዜጎች እንዲጠቀሙ ታስቦ የተደረገ መሆኑን ሊጉ ይረዳል:: ዜጎች ካርድ እንዲወስዱና በበቂ ሁኔታ የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲሰፋ ታስቦ የተደረገ በመሆኑ በበጎ ጎን ይታያል::
ዜጎች ስለሚመርጡት ፓርቲ ጊዜ ወስደው እንዲያስቡ መራዘሙ ይረዳቸዋል:: ስራዎች ውጤታማ የሚሆኑት ዜጎች የፈለጉትን ፓርቲ መምረጥ ሲችሉ ነው:: የሚፈልጉትን ፓርቲ የሚመርጡት ደግሞ በካርዳቸው ነው:: ካርድ ካልወሰዱ መምረጥ ስለማይችሉ መራዘሙ ትክክለኛ ውሳኔ ነው:: ነገር ግን የመራጭነት ካርድ ማውጫ ቀን በመራዘሙ ብዙ ነገሮችን ወደ ፊት እንዲገፉ ያደርጋል:: ነገር ግን የምርጫው ቀን መራዘሙ እንደ አጠቃላይ ችግር ላይፈጥር ይችላል::
ከገለልተኛነት ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ ወጣቶች ሰላምና ብልፅግና ተልዕኮ ሊግ ከማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ተፅዕኖ ገለልተኛ የሆነ ተቋም ነው:: ምርጫው ዴሞክራሲዊ፣ ሰላማዊና ተዓማኒ እንዲሆን ገዥው ፓርቲ ከፍተኛ የሆነ ኃላፊነት አለበት:: በምንም አይነት መንገድ የህግ ማስከበር ከሌለ ምርጫው ውጤታማ መሆን አይችልም:: ገዥው ፓርቲ አሁንም ቢሆን ህግን የማስከበር ግዴታ አለበት:: በእጩ ምልመላ ላይ የሴቶች ተሳትፎ በተመለከተ በተደረገ ጥናት አብዛኛው ፓርቲ ሴቶችን በመጠኑ ነው ያሳተፈው::
በጥናት እንደተገኘው ከሆነ በምርጫ ጣቢያዎች በመዞር ነዋሪው ለምን እንዳልተመዘገበ ሲታይ በአንድ ምርጫ ጣቢያ ውስጥ አንድ ሺህ አምስት መቶ መራጭ ብቻ የሚመዘገብ በመሆኑ ነው:: ከዚህ አንፃር ያጋጠመው ነገር አንድ ሺህ አምስት መቶ ተመዝጋቢዎች በአንድ ቦታ ይመዘገባሉ:: ከዛም የመራጭነት ካርድ አልቋል ይባላል:: ነገር ግን ወዴት ሄደው መመዝገብ እንዳለባቸው አይነገራቸውም:: በዚህም ነዋሪው ወደየቤቱ እንዲመለስ ይደረጋል:: ይህ ሁኔታ እንዲስተካከል በመደረጉ ነዋሪው እንዲያወጣ ተደርጓል::
ሌላው ችግር የነበረው የምርጫ አስፈፃሚዎች ደመወዝ አለመከፈሉ ነው:: በተጨማሪም የምርጫ አስፈፃሚዎች በተቀመጠላቸው ሰዓት አለመግባታቸው ሌላኛው ችግር ነበር:: ሊጉ ተዘዋውሮ በተመለከተባቸው ምርጫ ጣቢያዎች አስፈፃሚዎች በጊዜ ገብተው የመራጭነት ካርድ መስጠት ላይ ክፍተቶች ተስተውለዋል:: ዜጎች ካርድ ለመውሰድ ተሰልፈው ካርድ የሚሰጥ ሲጠፋ ሁሉም ወደየቤቱ ይመለሳል:: ይህ ሁኔታ መስተካከል አለበት:: በተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩ የፀጥታ ችግሮች መራጮች ካርድ እንዳወጡ እንቅፋት ፈጥሮ ነበር:: በተደረጉ ስራዎች ነዋሪው ካርድ ማውጣት ችሏል::
መርድ ክፍሉ
አዲስ ዘመን ግንቦት 13/2013