አዲስ አበባ /ፋና/፣ እውቁ አርቲስት በረከት መንግስትአብን ጨምሮ 55 አባላት ያሉት የኤርትራ ፐብሊክ ዲፕሎማሲና የባህል ቡድን ልዑኩ ባህርዳር ገባ፡፡ የፐብሊክ ዲፕሎማሲና የባህል ቡድኑ የጉብኝቱ አላማ የኢትዮጵያና ኤርትራ ታሪካዊ እና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ለማጠናከር ያለመ ነው ተብሏል። ይህ ልዑክ ከኢትዮጵያ የባህል ቡድን ጋር አዲስ አበባን ጨምሮ በክልል ከተሞች የሁለቱ ሀገራትን የደም ትስስርና የማያቋርጥ ግንኙነት የሚያንፀባርቁ የባህል ሙዚቃዎችና ልዩ ልዩ ዝግጅቶችን ያቀርባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በኢትዮጵያ በሚኖረው ቆይታ በተለያዩ ዝግጅቶች ተሳታፊ ይሆናል። ልዑኩ ዛሬ የካቲት 9 ቀን በባህርዳር፣ የካቲት 10 በአዳማ፣ የካቲት 12 በሀዋሳ ዝግጅቱን የሚያቀርብ ሲሆን፣ በመጨረሻም የማጠቃለያ ዝግጅቱን የካቲት 14 ቀን 2011 ዓ.ም 25 ሺህ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ያቀርባል ፡፡
የኤርትራ ፐብሊክ ዲፕሎማሲና የባህል ቡድን ልዑክ የካቲት 17 ቀን 2011 ዓ.ም ወደ ኤርትራ የሚመለስ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲና የባህል ቡድንም ለተመሳሳይ ዓላማና ዝግጅት ከአንድ ወር በኋላ ወደ ኤርትራ አስመራ እንደሚጓዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ቃል አቀባይ አቶ ነቢያት ጌታቸው ተናግረዋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 9/2011