በ1970ዎቹ መጀመሪያ፣ የቼክ ድንበርተኛ በነበረችው የዛን ጊዜዋ ሶሻሊስት ፖላንድ ስዊድኒክ ከተማ ነዋሪዎች ሰርክ ምሽት 1:30 ላይ የመንግሥቱ ቴሌቪዥን የሚያሰራጨውን እጅ እጅ የሚል ፕሮፓጋንዳ ላለማየት በመሀል ከተማዋ ወደምትገኝ አነስተኛ መናፈሻ ውሾቻቸውን አስከትለው አየር በመቀበል ያሳልፉ ነበር። በሌላዋ የፖላንድ ከተማ ጋዳነስክም ነዋሪዎቿ የቴሌቪዥን ጣቢያውን የመንግሥት አራጋቢ መሆን በመቃወም የቴሌቪዥናቸውን እስክሪን ወደ ውጭ አድርገው መስኮታቸው ላይ በማስቀመጥ የ«አናይህም» እና «አንሰማህም» ተቃውሟቸውን ይገልፁ ነበር፡፡
በሀገራችንም ቀደም ሲል በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን በሚሰለቀው ሐሰተኛ እና ደረቅ ፕሮፓጋንዳ በመማረር ኢቲቪን ዓይንህ ለአፈር ከማለት አንስቶ፤ በጋራ መኖሪያ ቤቶች መስኮት ፤ በቤቶች ጣራ የሳተላይት ሳህኖች ተገጥግጠው እንመለከት ነበር። ሕዝቡ በቀላሉ በአንቴና ከሚያገኘው ኢቲቪ ይልቅ በሌለ አቅሙ ከልጆቹ ጉሮሮ ቀምቶ ሪሲቨርና ዲሽ ገዝቶ ሌላ የመረጃ ምንጭ ለመፈለግ የሄደበት እርቀት ባለፉት 27 ዓመታት ዜጋው በመንግሥት ሚዲያዎች እንዴት ተማሮ እንደነበረ ያሳያል፡፡
ዛሬ ለለውጥ ኃይሉና ለሕዝቡ ምስጋና ይግባቸውና ሁኔታዎች ተለዋውጠዋል ፡፡ «አምላኬ አባክህ ህይወቴን እንደ ኢቲቪ ቀይረው!» እስከማለትም ተደርሷል፡ ምንም እንኳ ዛሬም ኢቲቪ ከማዘመር፣ ከማወደስ ሙሉ በሙሉ ተፋትቶ የህዝቡን ሕጸጾች እየነቀሰ ፤ አጀንዳ እየቀረፀ ፤ የመንግሥትን አሰራር በሚጠበቅበት ልክ እየተከታተለና እየተቆጣጠረ ባይሆንም ሕዝብ በኢቲቪ ለታየው ጅምር ለውጥ እውቅና መስጠቱን ተመልክተናል፡፡
በሽብርተኝነት ተፈርጀው እንዳይሰራጩ እግድ ተጥሎባቸው የነበሩት ኢሳት እና ኦ ኤም ኤን እግዱ ተሰርዞላቸው ወደ ሀገር ቤት ገብተው በነፃነት እንዲሠሩ መደረጉ፤ የእነ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ፣ ተመስገን ደሳለኝ መፈታት፣ ተዘግተው የነበሩ በርካታ ድረ ገጾች እንዲከፈቱ መደረጉ፤ ጋዜጠኞችና ጦማሪያን እንዲፈቱ መወሰኑ፣ የፕሬስ፣ የፀረ ሽብር ሕጎችና ሌሎች አፋኝ ሕጎችን ለማሻሻል ጥረት መጀመሩ፤ ነፃ የዳኝነት አካል ለማቋቋም እንቅስቃሴዎች በይፋ መጀመራቸው ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ተቋማዊ እንዲሆን በመንግሥት በኩል ቁርጠኝነት መኖሩ፤ የኢህአዴግ ንብረት በሆነው ፋና ሳይቀር ከነውስንነቱ መሪውን ድርጅት፣ መንግሥትን የሚተቹ ዘገባዎችንና ውይይቶችን መመልከት መጀመራችን እንደ ለውጡ ማሳያ ሊወሰዱ ይችላሉ፡፡
ካለፉት 10 ወራት ወዲህ በርከት ያሉ አዳዲስ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ማለትም Arts፣ ASHAM ፣ Ahaduና Bisrat የሙከራ ስርጭት ላይ መሆናቸው፣ ፍትሕንና ኢትዮጲስን ጨምሮ አዳዲስ ጋዜጦችና መፅሔቶች መታተም መጀመራቸው ፤ መጭው ጊዜ ለጋዜጠኝነትና ለሚዲያ ኢንዱስትሪው ተስፋ ሰጭ ከመሆኑ ባሻገር ለአጠቃላይ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታም ጥሩ መደላድል ይሆናል፡፡ እንደ አራተኛ መንግሥት «the fourth power» የሚቆጠረው ሚዲያ ጠንክሮ መውጣት ለተጀመረው ለውጥ ተቋማዊ መሆን የማይተካ ሚና ስለሚኖረው፤ ይህን ታሪካዊ ኃላፊነት ለመወጣት ሚዲያው ራሱን ማዘጋጀት እንዳለበት በአክብሮት ማሳሰብ እወዳለሁ ፡፡
ማሳሰቢያው በደረቁ እንዳይሆን፤ መጀመሪያ በራሱ በፋና የ1ኛ ዓመት ምስረታ በዓል ሻማ ፀዳል ፋናን እንመልከትና በመቀጠል አብዛኛዎቹ ሚዲያዎቻችን ከጭራነት፣ ከጭፍ ራነት፣ ከተከታይነት፣ ከአሸርጋጅነት ወጥተው፣ እንዴት መሪ፣ አጀንዳ ቀራጭና ተቆጣጣሪ እንደሚሆኑ፤ የዓመቱ የሚዲያ ክስተት ሆኖ ስለወጣው ፋና ቴሌቪዥንም የግል ምልከታዬን ላውሳ ፡፡ የመደበኛ ሚዲያን mainstream media ፦ የቴሌቪዥን፣ የሬዲዮና የጋዜጣን፣ ተመልካች ፣ አድማጭና አንባቢ ብዛት እያጠና የትኛው የቴሌቪዥን ጣቢያ ብዙ ተመልካች ፤ የትኛው ሬዲዮ ጣቢያ ደግሞ ከፍ ያለ አድማጭ፤ የትኛው ጋዜጣ በአንባቢዎቹ ይበልጥ ተነባቢ እንደሆነ በየጊዜው የሚያጠናና ደረጃ የሚሰጥ ገለልተኛ ተቋም Rating Agency ቢኖር ከቴሌቪዥን ፋናን፣ ከሬዲዮ ሸገር ኤፍ ኤም 102 . 1 ፣ ከጋዜጣ ሪፖርተርን፣ ከመፅሔት ፍ_ት_ሕን በቀዳሚነት ሊያስቀምጥ ይችላል ብዬ እገምታለሁ፡፡
የቴሌቪዥን ስርጭትን በሀገሪቱ አሀዱ ብሎ የጀመረ እንደ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ያለ ጣቢያ እና የ54 ዓመት ታሪክ፣ ልምድ፣ የደለበ የምስልና የድምፅ ክምችት ያለው፤ በ«ዘመናዊቷ» ኢትዮጵያ ግንባታ ሂደት በበጎም ሆነ በመጥፎም ጡብ ያቀበለ ተቋም ከተቋቋመ አንድ ዓመት ባላለፈው እንግዳ ፣ አርፋጅ ቴሌቪዥን ፤ በተመልካች ብዛት፣ በስርጭት ጥራት፣ በቅርፅ format፣ በይዘት content፣ በብዙ እጥፍ ተበልጦ ተከንድቶ ማየት እንደኔ ላለ ሀገር ወዳድ ዜጋ በመንፈሳዊ ቅናት ቆሽት ያሳርራል፡፡ ጨጓራ ይልጣል ፡፡ ፋና ቴሌቪዥንን ለማቋቋም ገና ከማለዳው ከአምስት ዓመታት በፊት የተመልካች ፍላጎት የዳሰሳ ጥናት ሲደረግ የተዘጋጁ መጠይቆች የመመልከት አጋጣሚ ተፈጥሮልኝ ስለነበረ የሙከራ ስርጭቱን አጠናቆ መደበኛ ስርጭቱን ሲጀምር ደግሞ በአመዛኙ በሬዲዮ ቅርፁ format ተፅዕኖ ስር ወድቆና በሬዲዮ ጋዜጠኞቹ የተዋቀረ ስለነበር ፋና ኤፍ ኤም 98 .1 እንዳለ ምስል ብቻ ጨምሮ የመጣ እስኪመስለኝ ቴሌቪዥንነቱን ለመቀበል ተቸግሬ ስለነበር ፤ ፋና ኤፍ ኤም በምስል እያልሁ ከባልጀሮቼ ጋር መሳለቅ ሁሉ ጀምሬ ነበር ፡፡
ሌላው ከትጥቅ ትግሉ አንስቶ የትህነግ / ኢህአዴግ ልሳን፣ ደጋፊና ንብረት ስለሆነ ከጭፍን ድጋፍና የፕሮፓጋንዳ መሳሪያነት ይወጣል ተብሎ ስላልተጠበቀ እንዲህ በአጭር ጊዜ ለዛውም በ365 ቀናት በኢትዮጵያ የሚዲያ መልክዓ landscape ላይ እንዲህ አንፃራዊ ልዩነት አምጥቶ ቀዳሚ ይሆናል የሚል ዕምነት አልነበረኝም፡፡ የአብዛኛው ተመልካች የመጀመሪያ ግምትም ከዚህ የተለየ እንደማይሆን ይሰማኛል፡፡ታዲያ ፋና ቴሌቪዠን በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዴት እንደዚህ የሆነበት ሚስጥሩ ምንድነው ?
• ከለውጡ ጋር መገጣጠም ፦ የፋና ቴሌቪዥን የሙከራ ስርጭት በጀመረ ሁለት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የሚመራው የለውጥ ኃይል በለውጥ ፈላጊው አንጋሽነት ወደ ዙፋኑ መምጣቱ እና የፖለቲካ ምህዳሩን የሚያሰፉ ጠርማሽ disruptive ተከታታይ እርምጃዎችን መውሰዱ፤ ህወሀት ለሁለት በተሰነጠቀ ጊዜ በእነ አለም ሰገድ ጎራ አባልነት ተፈርጆ በእነ በረከት ሲኮረኮም ለኖረው የፋና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሠርግና ምላሽ የሆነለት ይመስላል ፡፡
በለውጡ ከልብ በማመን ይሁን ቂሙን ለመወጣት ያለምንም ማቅማማትና ማመንታት በድፍረት ከትህነግና ከእነ በረከት ጥርነፋ ባፈነገጠ መልኩ በድፍረት 360 ዲግሪ ተከርብቶ የለውጡ ለፋፊ ፣ እምቢልታ ነፊ ፣ ነጋሪት ጎሳሚ መሆኑ በተመልካቹ ዘንድ ሞገስን እንዳስገኘለት ይታመናል ፡፡ የትህነግ / ኢህአዴግ የመንፈስም፣ የቁስም ልጅ የነበረው ፋና ፤ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ እንደ ኢቲቪ ፈራ ተባ ሳይልና ሳያመነታ፤ በጀግንነት የለውጡ ልሳን ሆኖ መውጣቱ ዛሬ ለተቆናጠጠው የሚዲያ እርካብ አብቅቶታል፡፡ የኢቲቪን ፍርሀት እንደምቹ ዕድል ተጠቅሞም ብኩርናውን birthright ሊነጥቀው ችሏል ፡፡ ዛሬ ወደድንም፣ ጠላንም ፋና ቴሌቪዥን ከእነ ውስንነቶቹ በሀገራችን ቀዳሚና ተመራጭ ቲቪ ከመሆኑ ባሻገር እነ ኢቲቪንም ይዞ ወጥቷል ማለት ይቻላል፡፡ አጋጣሚን ሳያባክን በአግባቡና በድፍረት መጠቀሙ ከፍሎታል፡፡
• የደለበ ካዝናው ፦ ፋና ባለፉት 27 ዓመታት እንደ ኤፈርት ኩባንያዎች ፖለቲካዊ ጡንቻውን በመጠቀም ያለማንም ከልካይና ተፎካካሪ በእስፖንሰር፣ በአየር ሽያጭ፣ በሌሎች የገቢ ማስገኛ ስልቶች ካዝናውን ማድለቡ ዛሬ ለደረሰበት አቋራጭ «ስኬት» ተጠቃሽ ነው፡፡ ከመንግሥት የልማት ድርጅቶች፣ ከታዳጊ ክልሎች ፣ «ከልማታዊ ባለሀብቶች» በተለያዩ ስልቶች ተዝቆ የማያልቅ ጥሪት ማፍራቱና በነፃነት እንዲጠቀምበትም መፈቀዱ ዛሬ በሀገራችን ካሉ የመንግሥትም ሆነ የግል ሚዲያዎች
ሀብታም ሚዲያ አድርጎታል ፡፡ ይህ ፈርጣማ አቅሙ በሀገሪቱ የመጀመሪያውን «የግል» ሚዲያ ኮምፕሌክስ እንዲገነባ፤ ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ኢንቨስትመንት እጅግ ዘመናዊ የሆነ ስቱዲዮ፣ ካሜራ፣ የፕሮዳክሽን መሳሪያዎች ከመደራጀቱ ባሻገር በአንፃራዊነት ሠራተኛውን ጠቀም ባለደመወዝና ጥቅማ ጥቅም መያዙና ከውጭም ልምድ ያላቸውን ጋዜጠኞች ከሌሎች ሚዲያዎች ማስኮብለሉ፤ ከመንግሥት ሚዲያ ይልቅ ከተባባሪ አዘጋጆች ጋር ለመሥራት ቀላል፣ ምቹ አሰራርና አደረጃጀት መዘርጋቱ እንደ ‘ፈታ ሾው’ ፣ ‘ያሉ ዝግጅቶችንና ፕሮዲውሰሮች ቀልብ መማረኩ ለተመራጭነቱ ሌላው ምስጢር ነው ፡፡ እውነት ለመናገር የፋና እንዲህ የለውጡ አቀንቃኝ ሆኖ መምጣት ዛሬ ድረስ እንቆቅልሽ እንደሆነብኝ ነው፡፡ በፋና ወጊነት በለውጡ ሂደት ከፊት መሰለፍን ፈራ ተባ ሲል፣ ሲያመነታ የነበረውን ኢቲቪንና ሌሎች ሚዲያዎችንም በተወሰነ ደረጃ አጀግኗል ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ለዚህ ነው የሚዲያ ተንታኞች የፋና በጎ ተፅዕኖ ከቅጥሩ የተሻገረ ከመሆኑ በላይ አገር አቀፋዊ አንድምታ አለው የሚሉት ፤ ፋናን ለስኬት ያበቁት ምስጢሮች እነዚህ ብቻ ባይሆኑም በዚህ ላቀዝቅዝና በፋናም ሆነ በሌሎች ሚዲያዎች ስለታዘብኩትና አሁንም ስለሚታዩ ውስንነቶች ትንሽ ልበል ፤
• የጭፍራና ጭራነት አባዜ ፦ ፋና ቴሌቪዥንም ሆነ የሌሎች ሚዲያዎች ትልቁ አባዜ መጠኑ ቢለያይም የመንግሥት ፣ የአክቲቪስቶች፣ የተፎካካሪዎች፣ የአድማጭ ተመልካቹ፣ የአንባቢው ጭፍራ፣ ጭራ፣ ተከታይ፣ ምርኮኛ መሆናቸው ነው፡፡ ተመልካች አድማጩ የአውሮፓ የእግር ኳስ ሊጎችን ስለሚያመልክ ሚዲያው ሁሉ አንጥፎ ካዳሚ መሆን፤ ድራማ ስለወደደ የአየር ሰዓቱን በሞላ በድራማ መሙላት ፤ የተሰጥኦ ውድድር ስለወደደ ሁሉም ቴሌቪዥን ሳይጨምር ሳይቀንስ ባለ አይዶል ቮው መሆን፤ ጆሲ የሀገር ባለውለታዎችን በየጉራንጉሩ እያፈላለገ ስለሚጠየቅ ፤ ቴሌቪዥኑ በሞላ ደረት ደቂ ፤ ወዘተ… መሆን የሚዲያው ትልቁ ፈተና ነው ፡፡ የአድማጭ ተመልካችን ፣ የአንባቢን ፍላጎት ፣ ምስ እያነፈነፉ ማቅረብ የተመልካቹን ፣ የአድማጩንና የአንባቢውን ቁጥር ከፍ ያደርጋል ፡፡ በዚህም የማስታወቂያና የስፖንሰር ገቢ ሊያድግ ይችላል ፡፡ ይሁንና ከፍተኛ ተመልካች ማፍራትም ሆነ አትራፊ መሆን እንደኛ ባለሀገር ላለ ቴሌቪዥን የመጨረሻ ግብ ሊሆን አይገባም ፡፡ አዎ ! ሚዲያዎቻችን አጀንዳ እየቀረፁ ፣ የማህበረሰቡን ህፀፅ እየነቀሱ፣ የመንግሥት ተቋማት ፈር ሲለቅቁ፣ ፈር እያሲያዙ፣ እንደ ነብይ አደጋን ፣ ስጋትን ፣ ድልን ፣ ወዘተ… አበክረው የሚያሳዩ ፣ የሚያነቁ ሆነው፣ ሀገርን ሕዝብን የሚመሩ፣ የሚያሻግሩ፣ እንጅ የአድማጭ ተመልካቹ፣ የአንባቢው ጭፍራ ሊሆኑ አይገባም፡፡
ሸገር ኤፍ ኤም 102. 1 በተወሰነ ደረጃ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው ፡፡ ብዙዎቹ የፕሮግራሞቹ ይዘትም ሆነ ቅርፅ የአድማጩ ተከታይ፣ ጭፍራ ሳይሆኑ በተቃራኒው አድማጩን ተከታይ ማድረግ የቻሉ ናቸው፡፡ ስለሀገር ፣ ስለታሪክ፣ ስለባለውለታዎቻችን፣ ስለየሕግ የበላይነት፣ ስለፍትሕ፣ ስለዴሞክራሲ፣ ስለማህበራዊ ህፀፆቻችን፣ ወዘተ… የሚናገርም፣ የሚያደምጥም ጠፍቶ በነበረበት ባለፉት ዓመታት፤ ሸገር በተንገረበበችዋ በር ገብቶ በድፍረት፣ በመላ፣ በጥበብ ገብቶ ሀገርንም፣ ትውልድንም ለመታደግ በጭፍራነት ሳይሆን በመሪነት የመጣ፤ የክፉ ቀናችን መውጫ ሚዲያ ነው ፡፡ ዛሬ የተንገረበበችዋ በር ብርግድ ብላ ብትከፈትም፤ እንደ ሸገር የሚመራን ሚዲያ ግን ገና አልተወለደም ፡፡ ከፊታችን ከተደቀነው አደጋ ታድገው የሚመሩን፤ የምንከተላቸው ሚዲያዎች ይበዙ ዘንድ ከሚከተሉት ዋና ዋና ሦስት ሚናዎች አንፃር ራሳቸውን ቢያዩ ፦
1ኛ . የዘብነት፣ የአቃቢነት ሚና ( Watch dog ) ፦ ሚዲያዎች መንግሥት ፣ ማህበረሰቡ ፣ የሲቪል ተቋማት ሚዲያዎች እራሳቸውን፣ ሕግን፣ ሥርዓትን፣ እሴትን እንዳይተላለፉ የመከታተል ተላልፈው ሲገኙ ተጠያቂ ማድረግና የመንግሥትን ሦስቱን አካላት ማለትም ሕግ አውጭውን ፣ ተርጓሚውንና አስፈፃሚውን የመከታተል ሚናቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡
2 ኛ . አጀንዳ የመቅረፅ ሚና ( Agenda setter ) ፦ ሚዲያዎች ለፖሊሲ ሀሳብ አፍላቂዎችም ሆነ አርቃቂዎች ግብዓት የሚሆኑ አዳዲስ ሀሳቦችን ፤ መፍትሔ የሚሹ ችግሮችን ከስር ከስር እየተከታተለ ማመላከት፡፡ 3 ኛ . መድረክ የመሆን ሚና ( Civic forum)፦ ለሕዝቡ፣ ለአክቲቪስቶች፣ ለፖለቲካ ፓርቲዎች የመወያያ፣ የመነጋገሪያና የመከራከሪያ መድረክ ሆኖ በገለልተኛነት ማገልገል፣ ከላይ በ2ኛም ሆነ በ3ኛ ነጥብ የተመለከቱት ሚናዎች በአንድነት የመጨረሻው ግባቸው መምራት፣ ማሳየትና መጠቆም ስለሆነ Guide dog በመባል የሚታወቀው የሚዲያ ባህሪ ሆነው ሊወሰዱ ይችላሉ፡፡ ሆኖም ዛሬ በሀገራች ያሉ ሚዲያዎች ከሞላ ጎደል በአብዛኛው የመንግሥትን ስህተት፣ ድክመት እየፈለጉ ከመተቸት፣ ከማጥቃት፣ ከመናከስ Attack Dog ከመሆን አልያም ለመንግሥት አጎብዳጅ በመሆን ሁለት ተፃራሪ ዋልታዎች ላይ ከመቆም ይልቅ ወደ መሀል የመምጣት አዝማሚያ እያሳዩ ቢሆንም ሙሉ በሙሉ ጨክኖ መውጣቱ ላይ ግን ብዙ ይቀራቸዋል፡፡ ክቡር ጠ/ሚ እንደሚሉት ከዋልታ ረገጥነት በሂደት ወጥተው የተቆጣጣሪነት አልያም የመሪነት ሚና ለመጫወት ሚዲያዎቻችን በተለይ አቅሙ ያላቸው ልዩ ዘጋቢዎችን በተለይ ፖለቲካን ፣ ቢዝነስንና ኢኮኖሚን ፣ ችሎትን ፣ ኪነ ጥበብን ፣ ወዘተ… የሚዘግቡ ጋዜጠኞችን ማብቃት ይጠበቅባቸዋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 8/2011
ቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)