የረመዳን በዓል ከፊት ለፊታችን ነው። የእስልምና እምነት ተከታዮች ይህን በዓል በደማቅ ስነስርዓት ከሚያከብሩባቸው መንገዶች አንዱ በአልባሳት ደምቀውና ተውበው ነው። እኛም ይህን ታላቅ በዓል አስመልክተን በዛሬው የፋሽን አምዳችን ላይ ስለ“እስላማዊ አልባሳትና” ስነስርዓቶች በስፋት ልናወጋችሁ ወድደናል። በቅድሚያ ከዚህ በፊት እንግዳችን የነበረችው ሃናን አህመድ የረመዳን በዓልን አስመልክታ ኢትዮጵያዊ ቃና ያረፈባቸው አልባሳትን በምን መልኩ ዲዛይን እንደምታደርግ ጥቂት ትለናለች።
ሃናን አህመድ
ከስድስት ዓመት የበረራ አስተናጋጅነት ቆይታ በኋላ እስላማዊ ልብሶችን ሃይማኖታዊ ስርዓቱን ሳይለቅ በባህላዊ አልባሳት ጥለት በማስጌጥ ኢትዮጵያዊ ቃናና ይዘት እንዲኖራቸው ለማድረግ እየሠራች ትገኛለች። የመጀመሪያው ሙከራዋም ተወዳጅነትና ከፍተኛ ተቀባይነት አስገኝቶላታል። ከአረብ አገራት የሚመጡ አልባሳትን ብቻ የሙስሊሙ ማህበረሰብ ከሚለብስ ኢትጵያዊ ባህል የተላበሰ ጥለቶችን በመጨመር የበለጠ የተዋበና ያማረ ለማድረግ ጥራለች።
“እስላማዊ አልባሳት ባህላዊ ይዘት እንዲኖራቸው የምጠቀመው ጥለት ነው። ሁላችንም ጥለትን ስናስብ አገራችንን እናስታውሳለን። ይህን ምክንያት በማድረግ ጥለትን ተጠቅሜ አልባሳቱን ዲዛይን አደርጋቸዋለሁ” የምትለው ሃናን፣ አባያው ላይ በዚህ መንገድ በመሥራቷ ተወዳጅ ይዘት ያለው ኢትዮጵያዊ የሙስሊም አልባሳትን ለማህበረሰቡ ይፋ ማድረግ እንዳስቻላት ነግራናለች።
ዲዛይነር ሃናን አዲስ ባስተዋወቀችው ኢትዮጵያዊ ባህልንና ሃይማኖታዊ ይዘታቸውን ያልለቀቁ እስላማዊ አልባሳት ከፍተኛ ተቀባይነት አግኝታባቸዋለች። የፈጠራ ውጤቶቿ በሆኑት የሃባያ አልባሳት በከተማ ውስጥ የሚያጌጡ ቆነጃጅትን መመልከት አሁን አዲስ ነገር አይደለም። ሆኖም የእስልምና እምነት ተከታይ ፋሽን አይከተልም በሚል የተሳሳተ አመለካከት የተነሳ አስተያየቶችም እንደሚደርሷት አልሸሸገችም። ይሄ ግን ከተሳሳተ ግንዛቤ የሚመነጭና የአብዛኛውን ማህበረሰብ ፍላጎት ያላማከለ መሆኑን ትናገራለች።
ዲዛይነር ሃናን ይህን የተሳሳተ ግንዛቤ ለመፍጠር በግሏ ጥረት ማድረጓን እንደምትቀጥል ትገልጻለች። እንደ ጅምር ዓለም አቀፍ የሂጃብ ቀን በጊዮን ሆቴል በተካሄደው ላይ በመሳተፍ ሥራዎቿንና በጎ ገፅታዎቹን ለማሳየት ሞክራለች። በተለያዩ የፋሽን ሳምንቶች ላይ የመሳተፍ ፍላጎት እንዳላት በመግለጽም የረጅም ጊዜ ልምድና ኔትወርኩ ያላቸው ዲዛይነሮች መሰል መድረኮችን ቢያመቻቹና አብረዋት ቢሠሩ እንደምትወድ አልሸሸገችም። ከዚህ ቀደም በስካይ ላይት ሆቴል በተዘጋጀ የፋሽን መድረክ ላይ ሥራዎቿን ይዛ በመቅረብም ሰፊ ተቀባይነት ከመፍጠሯ ባሻገር ግንዛቤውን ለመፍጠር ችላለች።
ኡስታዝ ፉአድ ሼህ
‹‹የሙስሊሙ አለባበስ ከሌላው ሃይማኖት አለባበስ ጋር የማይመሳሰል፣ ተቃራኒ ፆታን የማይስብም መሆን አለበት፤›› የሚሉት ኡስታዝ ፉአድ ሼሕ መሐመድ ፣በተለይ ሴቶች አለባበሳቸው ተቃራኒ ፆታን የሚስብ መሆን እንደሌለበት ይናገራሉ። ክንብንባቸው በበዛ መጠን ፈተና የመሆናቸውና ወንዶችን ዕረፍት እንዳይነሱ እንደሚሆን ኡስታዙ ይገልጻሉ። ወንዶችም የሴቶቹን ያህል ባይሆንም ገላቸውን መሸፈን ይኖርባቸዋል።
ለወንዶች ከአፍ በላይ ያለችውን ፂም አሳጥሮ ሌላውን ማስረዘም፣ ጀለቢያ መልበስ፣ ጥምጣም ማዘውተር፣ ጣቂያ ማድረግ ግዴታ ባይሆንም ‹‹የተወደደ ነው›› ይላሉ።
በእስልምና ንፅሕና ከምንም በላይ ነው። በቀን አምስት ጊዜ ሲሰገድ አምስቱንም ጊዜ መታጠብ የግድ ነው። በአጋጣሚ ቆሻሻ ቢነካባቸው እንኳ ሳያውቁ እንዳያልፉ ሁሉን ነገር ወለል አድርጎ የሚያሳይ ነጭ ልብስ መልበስም ተመራጭ ነው።
ሴቷ ፀጉሯን በሒጃብ ትሸፍናለች። ፊቷ ሲቀር ሙሉ ሰውነቷን የሚሸፍነውን አንድ ወጥ ጨርቅ ጅልባብ ትለብሳለች። ዓይኗን ብቻ አስቀርታ መላ ሰውነቷን በኒቃም ከዕይታ ትደብቃለች። ወንዱም ፂሙን አስረዝሞ፣ ሱሪውን ያሳጥራል፣ ጀለቢያ ይለብሳል፣ በአናቱ ጣቂያ በትከሻው ደግሞ አማይማ ይደርባል። እነዚህ ሃይማኖቱ ተከታዮች እንደ አተያያቸው ከሚከተሏቸው የአለባበስ ዓይነቶች ዋና ዋናዎቹ ናቸው።
እነዚህን የአለባበስ ደምቦች መሠረት ያደረጉ ፋሽን አልባሳትን የምትሸጠው ሐያት ፈድሉ አብዛኞቹን ዕቃዎች ከዱባይ ነው የምታመጣው። ቋሚ ሱቋ መርካቶ አንዋር መስጊድ አካባቢ ነው።
‹‹ምርጡ ኢንተርኔት የሚባለው የጨርቅ ዓይነት ነው፤›› ትላለች እንደ ኢንተርኔት ባሉ ዘመንኛ ጨርቆች የሚሠሩ አባያዎች እስከ 2,800 ብር ድረስ እንደሚሸጡ እየነገረችን። ከፋሽን መድረኩ እየወረዱ የሚሳሳቡ (ስትረች የሚያደርጉ) ጨርቆች በአንፃሩ በርካሽ ዋጋ ይሸጣሉ። ‹‹እነዚህ በፊት ምርጥ የሚባሉ ነገር ግን ፋሽናቸው ያለፈባቸው ዕቃዎች ናቸው፤ እስከ 550 ብር ድረስም ይሸጣሉ። ሰዎች አሁን ላይ ስትረች መልበስ አይፈልጉም፤›› አለች። የጨርቁን መሳሳብ ለማሳየት በእጇ ሳብ ሳብ እያደረገች።
ሒጃቦችም እንደየ ዓይነታቸው ዋጋቸው የተለያየ ነው። ከ150 ብር ጀምሮ የሚሸጡ ሲሆን፣ ምርጥ የሚባሉት ካሽካ (የብራንድ ዓይነት ነው) እና የቱርክ ሒጃቦች እስከ 500 ብር ድረስ ይሸጣሉ።
በነጋዴዎች መካከል የሚኖረው ፉክክር የዕቃዎች ዋጋ አንፃራዊ ቅናሽ እንዲኖር የሚያደርግ ቢሆንም የተጠየቀውን ከፍሎ የሚሄድ ደንበኛ አይኖርም። በመርከሱ እየተደመመም ቢሆን ቀንሱልኝ ብሎ መከራከሩ አይቀርም። ዓይን አዋጅ የሚሆንበትን ያንንም ይህንንም ያነሳል በዋጋ ክርክር ይገጥማል። ‹‹የቱን ብገዛ ይሻለኛል›› በሚል ከራሳቸው ጋር የሚከራከሩ ብዙ ናቸው።
አንዲት ሴት ልጅ ከሰባት ዓመቷ ጀምሮ ሒጃብ መከናነብ አለባት። ሙስሊም ሴት ሁሉ ግዴታዋ እንደሆነም ታሰምራለች። ረዥም ቀሚስ መልበስና ሌሎችም ሃይማኖቱ የሚያዛቸውን ነገሮች መተግበር እስላማዊ ግዴታ ከመሆን ባሻገር የሕይወት መርህም ነው ትላላች። በገበያ ላይ ምርጥ የተባለ አባያ በ250 ብር ይሸጥ ነበር። አሁን ግን ከዚያም በላይ ዋጋው ጭማሪ አሳይቷል። ማንኛውም ልብስ እንደሚወደደው ሁሉ የአባያ ዋጋ ከፍ ዝቅ ይላል። ዛሬ በሺሕ ቤት ቢሸጥም ፈላጊ ግን አይጠፋም። ዋጋው በጣም ውድ የሚባል አለመሆኑን ነው አንዳንድ በገበያው ላይ ለብዙ ዓመታት የሚሳተፉ የሃይማኖቱ ተከታዮች የሚናገሩት።
እስላማዊ አለባበስ እንደ ያስሚን ባሉ ወጣቶችና በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ ማኅበረሰቦች መካከል የተለያየ ነው። ሃይማኖታዊ አለባበሱ ከየአካባቢው ባህል ጋር የሚፈጥረው የመቀላቀል ሁኔታ ይታያል። በምሥራቁ ክፍል ሰፋፊ ድርያዎችን በሻርፕ መልበስ ያዘወትራሉ። ወደ ሰሜኑ ደግሞ በተለይም በትግራይ ከባህላዊ አለባበሱ እንዳለ ሆኖ በሹሩባቸው ላይ ስስ ሻሽ ሸብ ማድረግ የተለመደ ነው።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ግንቦት 2/2013