ጭርርር……ጭርር… እጅግ የምጠላው ነገር ግን ዘወትር ራስጌዬ እያደረኩት ደጋግሜ የምሰማው ማንቂያ ደወል ከሞቀው እንቅልፌ አባነነኝ። እንደ ምንም በእጄ አጥፍቼው እምር ብዬ በመነሳት መለባበሴን ጀመርኩ። በፍጥነት ወደ ስራ የሚያዳርሰኝ ሰርቪስ እንዳያመልጠኝ መሮጥ በስራ ቀን በተደጋጋሚ የማዘወትረው ተግባሬ ነው። ደመወዜ አነስተኛ በመሆኑ የቤት ኪራይ የሚቀንስበትን የኑሮ ውድነቱን ለመቋቋም እንዲረዳኝ በሚል ከመሀል ከተማ ራቅ ወዳለ አካባቢ ተከራይቼ ነው የምኖረው።
የቤቴን መስኮት ከፈት ሳደርገው ከአድማስ ብቅ ያለችው ፀሀይ አኩርፋና በጭጋግ ተሸፍና ታየችኝ። ሰማይ ለቅሶውን ሊጀምር መሆኑ ያስታውቃል። በለበስኩት ሸሚዝ ላይ ለዝናብ የሚሆን ጃኬት ከቁም ሳጥኔ አውጥቼ ደረብኩ። አልጋ ላይ ዧ ብላ የተኛችው ባለቤቴ ሜላትን ልሰናበት ተጠጋኋት። ዘወትር ማለዳ ግንባርዋን ስሜ ነው ከቤቴ የምወጣው። አይንዋን ገልጣ በትኩረት እያየችኝ መሆኑን ያወኩት ስጠጋት ነበር።
“እንዴት አደርሽልኝ ውዴ ሰርቪስ እንዳያመልጠኝ ደግሞ ልሩጥ።” ብያት ተጠግቼ ግንባርዋን ሳምኳት። በእጅዋ ያዝ አድርጋ ተመለከተችኝ። ከወትሮ ለየት ባለ መልኩ ስትመለከተኝ በማየቴ ውስጤ ጥያቄ ተፈጥሮብኛል። በድጋሚ ግንባርዋን ስሜ ከተቀመጥኩበት የአልጋ ጠርዝ ተነሳሁ። “ፍቅር” አለችኝ። ስሜ አየለ ቢሆንም እስዋ ግን አየለ ብላ የጠራችን መች እንደሆነ አላስታውስም። ሁሌ ስትጠራኝ ፍቅር እያለች ነው። እኔም ሜላት የሚለው ስሟን ማሬ ወደሚል ከለወጥኩት ሰነባብቻለሁ።
ሜላት እንከን የማይወጣላት እጅግ ውብ ናት። ከሰው ጋር የመግባባትና ቶሎ የመላመድ ባህሪዋን አይቶ ሁሉም የሚቀናባት አይነት ልጅ ናት። በጣም ግልፅና በትንሽ ነገር የምትደሰት ለሰዎች ምቹ የሆነ አመል ያላት ፀባየ ሰናይ በመሆንዋ በባለቤቴ እኮራለሁ። ብዙም የመተዋወቂያ ጊዜ ሳይኖረን ያገባኋት ይኸው ተግባቢነትዋን ወድጄው ነው። እንደ ዛሬው ቤት ተከራይቼ ከሜላት ጋር አብረን ከመሆናችን በፊት የምኖረው ከቤተሰቦቼ ጋር ነበር።
ቤተሰቦቼ በተለይ እናቴ አግባት ብለው የሚያማርጡኝና የሚያቀርቡልኝን ሴቶች መውደድ አይደለም መቅረብ የሚከብዱ ነበሩና አንዳቸውንም ቀርቤያቸው አላውቅም። ብዙ ሴቶች ላይ የሸፈተው ልቤ ሜላት ጋር ሲደርስ ተረታ። በእርግጥ ከአንድም ሁለት ጊዜ ከሴቶች ጋር ግንኙነት ኖሮኝ ያውቃል፤ ነገር ግን በዚህ መጠን ሴትን ልጅ ወድጄ አላውቅም።
ሜላትን ያገባኋት አንድ ወር ባልሞላ ትውውቅ ነው። በአጋጣሚ አንድ ምሽት ላይ የተዋወቅኳት ሜላት ከምችለው በላይ ተቆጣጠረችኝ። እጅግ በፈጠነውና በጠበቀው ግንኙነታችን መሃል አንድ ቀን አብረን ምሳ እየበላን መብላትዋን አቁማ ጥብቅ ብላብኝ “ እንድንጋባ እፈልጋለሁ…ወድጄሀለው” ስትለኝ ሳላስበው ደስ ተሰኘሁ።
ፊትዋን ኮስተር አድርጋ “የምሬን ነው እንድታገባኝ እፈልጋለሁ፤ ካልሆነ ወደ ውጪ አገር ለመሄድ የጀመርኩት ፕሮሰስ አለ እሱን ልቀጥለው ነው” ስትለኝ ደነገጥኩ። እሺ ሰፋ አድርገን እናወራበታለን ብዬ ሌላ ወሬ ባስጀምራትም እቤት ሄጄ በተኛሁበት ጭንቅላቴ ውስጥ ያለችኝ ሀሳብ ተመላለሰብኝ። “አግባኝ ካልሆነ ወደ ውጪ ልሄድ ነው” ማለትዋን ሳስብ ጨነቀኝ። ያን ጊዜ እጅግ እንደወደድኳት ታወቀኝ። በፍፁም ከእጄ ልታመልጥ እንደማይገባ ወስኜ ተኛሁ።
በነጋታው ደውዬ አገኘኋትና ልንጋባ እንደምንችል ነገርኳት። በደስታ አለቀሰች። ስለመጋቢያ ጊዜያችን እናስብ፤ ፕሮግራምም እናድርግ ስላት “ምንም ፕሮግራም አያስፈልግም፤ በጣም አስፈላጊ የሚባሉ እቃዎችን እንግዛና ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ አብረን እንሆናለን የሚል ሀሳብ ስታቀርብ ፍጥነቷ አስፈራኝ። በቀናት ልዩነት ደጋግማ በመወትወት አግባባችኝ። እሽታዬን ገለፅኩላት።
እሷ እንዳለችው ሳይሆን ቤት ተከራይተን ሙሉ የቤት እቃና የሚያስፈልገንን ሁሉ ገዝተን አስገባን። እሷ ምንም ስራ ስለሌላት የቤት ኪራይና እቃ ግዢው የተፈጸመው ከቤተሰቦቼ ጋር ስኖር እየሰራሁ ለዓመታት ባጠራቀምኩት የእኔው ገንዘብ ነበር። ሜላት የእቃ ምርጫ ትችላለች። ገበያ ስንወጣ የምትመርጣቸው እቃዎች ያስገርማሉ። ምንም እንኳን ውድ ውድ የቤት እቃዎች መምረጧ ባያስከፋኝም ለነጋችን የሚሆነን ብር እንዲቀር እፈልግ ስለነበር ቅር ቢለኝም፤ እቃው ሁሌም የምንጠቀምበት በመሆኑ ብዙም አልከፋኝም ነበር።
በአንድ ወር ውስጥ ሁሉ ነገር ከጨረስን በኋላ ሁሌም አግባ እያለች ትወተውተኝ ለነበረችው እናቴ ሜላትን ለማግባት ከወሰንኩ በኋላ እንደ ማፈር እየቃጣኝ ቀረብ ብዬ “እማዬ ላገባ ነው” ብዬ ስለ ሁሉ ነገር ነገርኳት። እናቴ ደነገጠች፤ ድንጋጤዋን ሳይ ፈራኋት። ጉዳዩን ቤተሰብ ሁሉ ማወቅ አለበት ብላ አሳወቀችኝ። ሁሉም ቤተሰብ አንድ ጥያቄ አነሳብኝ። ስለ ሜላት ደጋግሞ ጠየቀኝ። በተለይ እናቴ ስለጠየቀችኝ የማውቃትን ያህል ነገርኳት። ስለ ቤተሰቦችዋ ጠየቀችኝ። የአዲስ አበባ ልጅ ስለመሆንዋ ሜላት የነገረችኝን ገለጽኩላት።
ድርጊቴ አግባብ እንዳልሆነና የልጅትዋን ቤተሰብ በደንብ አውቀህና ሽማግሌ ልከህ ካልሆነ ማግባት የለብህም አለችኝ። ነገር ግን እኔና ሜላት ቀድመን ሁሉን ነገር ጨርሰን ነበርና አብሮ ለመሆን መወሰኔን ለእናቴ አሳወቅኋት። ብዙ መከረችኝ። ቀድሞ ማወቁና መተዋወቁ ይሻላል ብላ የእናትነት ምክሯን ለገሰችኝ።
ምክሯና ማሳሰቢያዋን ችላ ብዬ ከሜላት ጋር ተጠቃልዬ ገባሁ። ለሜላት ስለ ቤተሰቦችዋ ደጋግሜ ስጠይቃት የደሴ ልጅ መሆኗና እዚያ እንደሚኖሩ ከመንገር ውጪ ምንም አውርታኝ አታውቅም። “ባልሽ ሆኛለሁ፤ ሚስትህ ነኝ” ከተባባልንበት የጋራ ቃል ኪዳናችን ውጪ እኔና እስዋ በተለየ መልኩ ያስተሳሰረን አንዳችም ነገር የለም። የቤተሰብ ትውውቅም በመሀላችን ባይኖርም ውሎ ሲያድር ወደዚያ እናመራልን ብዬ በማሰብ ኑሮን ከጀመርን ይኼው ሁለት ወር ሞላን።
ዛሬ አለወትሮዋ በጠዋት የነቃችው ባለቤቴን ተሰናብቼ ከቤት ልወጣ እየተሰናዳሁ ነው። እዚያው በተኛችበት “እወድሀለሁ እሺ። አንተ መልካም ሰው ነህ ” ስትለኝ ከቅድሙ አስተያየቷ በላቀ ግራ መጋባቴ ይበልጥ ጨመረ። እንዳይረፍድብኝ ከቤት ፈጥኜ መውጣት ስላለብኝ እኔም እንደምወዳት ነገሬያት ወጣሁ። ሁኔታዋ ግን ለየት ብሎብኝ ስለነበር ወደኋላ እስዋን እያሰብኩ ተጓዝኩ።
ቀን 8 ሰዓት ቢሮ ስራ ላይ ሆኜ ስልኬ አቃጨለ፤ ሳየው የምወዳት ባለቤቴ የሜላት ነው። ፈገግ ብዬ “ሀሎ ማሬ አንዴት ነሽልኝ “ አልኳት። ሳግ በተናነቀው ድምፅ “ፍቅር መቼም አታገኘኝም፤ እንዳትፈልገኝ ሄጃለሁ፤ መልዕክት እቤት ትቼልሀለሁ። አታገኘኝም እንዳትፈልገኝ። ቻው እወድሀለሁ።” ብላኝ ስልኩን ስትዘጋው የምትቀልድብኝ መስሎኝ ነበር። መልሼ ስደውል ስልኳ ሲዘጋ መደንገጥ ጀመርኩ። ከቢሮ እቤት ታክሲ ይዤ በፍጥነት ሄድኩ። በር ከፍቼ ስገባ አንድ የተጣጠፈ ወረቀት ጠረጴዛው ላይ ተቀምጦ ተመለከትኩ። እጄ እየተንቀጠቀጠ አንስቼ ማንበብ ጀመርኩ።
“በቅድሚያ ይቅርታ አደርግልኝ። ሁሉን ነገር ያልነገርኩህ ሳላስበው ወድጄህ ስለነበር እንዳላጣህ ሰግቼ ነው። ቤተሰቦቼ አስገድደው ያጋቡኝ ባሌ ዘወትር ይፈፅምብኝ በነበረው ግፍ ተማርሬ ገድዬው ከፖሊስ ተደብቄ ከአገር አገር እየተሰደድኩ የምኖር ወንጀለኛ ነኝ። ፖሊሶች ተከታትለው ሊደርሱብኝ መሆኑን ስለሰማሁ አሁንም ወደማይታወቅ ቦታ ሄጃለሁ። በህይወት ዘመኔ የምመኘው ፍቅርን ለአጭር ጊዜም ቢሆን ስለሰጠኸኝ አመሰግናለሁ፤ ልብህን ስለሰበርኩት ይቅርታ።” የሚል ነበር። በተቀመጥኩበት ደንዝዤ ቀረሁ። አበቃ
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 29/2013