አውደ ዓመት በተቃረበ ቁጥር በተለያዩ ምርቶች እና አገልግሎቶች ላይ የዋጋ ጭማሪን ማስተዋል የተለመደ ከሆነ ዋል አደር ብሏል ። ሊከበር ጥቂት ቀናት በቀሩት ፋሲካ በዓል ገበያ የሚስተዋለውም ተመሳሳይ ይመስላል ። በዓሉን ምክንያት በማድረግም የተለያዩ ምርቶች ዋጋ ጨምሯል ። በተለይ የቅቤና የማንጠሪያው ቅመማ ቅመም ዋጋ ከመቼውም ጊዜ በላይ መጨመሩ በርካቶችን እያነጋገረ ይገኛል።
እኛም በተለያዩ የአዲስ አበባ ከተማ የንግድ አካባቢዎች ተዘዋውረን ባደረገው የገበያ ቅኝትና ከቅቤና የማንጠሪያው ቅመማ ቅመም ሻጭ እና ገዢዎች ባገኘነው አስተያየት የዋጋ ጭማሪ ስለመኖሩ አረጋግጠናል።
በዋናው ገበያ መርካቶ ቅቤ ተራና በተለያዩ የከተማዋ የቅቤ መሸጫ ቦታዎች የአንድ ኪሎ ቅቤ ዋጋ ከ400 እስከ 700 ብር እየተሸጠ መሆኑን ለመረዳት ችለናል።
ዋጋው በየዕለቱ ብቻም ሳይሆን በጠዋትና ከሰዓት እንዲሁም በሰዓታት ልዩነት ጭማሪ እንደሚያሳይ ተረድተናል። ያነጋገርናቸው ገበያተኞችም የምርቱ ዋጋ እስከ በዓሉ እለት አንድ ሺህ ብር ሊደርስ እንደሚችል ግምት እና ስጋታቸውን ገልፀውልናል።
ወይዘሮ የውብዳር አስማረም በመርካቶ ገበያ ጎጃም በረንዳ የቅቤ መደብር ፣አንደኛ ደረጃ የሚባለውን የጎጃም ቅቤ ሲገዙ ነው ያገኘናቸው።
የዋጋ ጭማሪን በሚመለከት ላቀረብንላቸው ጥያቄ ወይዘሮ የውብዳር እንደሚገልፁት፣ ባሳለፍነው ረቡዕ ቅቤ የገዙት በአራት መቶ ብር ነበር ። በማግስቱ ሐሙስ ሳይወደድ ልጨምር ብለው ሲመጡ ግን ዋጋው 500 ብር ሆኖ ቆያቸው።
ዋጋው በመጨመሩ ይዘው የመጡት ብር አንሷቸው ገንዘብ ይዘው ለመምጣት መሳለሚያ ወዳለው ቤታቸው ደርሰው እስኪመጡ ዋጋው ወደ 550 ብር ከፍ ብሎ ጠበቃቸው።
በዋጋው አስገራሚ ጭማሪ ተበሳጭተው ይቀንስላቸው ዘንድ እየተከራከሩ ባሉበት አጋጣሚ ወረፋ ሲበዛ ሻጩ የቅቤ ዋጋ ከነማንጠሪያው አልቀመስ ብሏል፤
ቅቤ ከሚያቀርብለት ነጋዴ ጋር ስልክ ተደዋውሎ ሲነጋገር ማድመጣቸውን የሚያስታውሱት ወይዘሮ የውብ ዳር፣አቅራቢው ተጨማሪ ቅቤ እንደሌለው መግለፁን ተከትሎም ሻጩ የአንዱን ኪሎ ቅቤ ዋጋ ወደ 600 ብር ከፍ እንዳደረገው ነው የገለፁት።
‹‹ዶሮ ወጥ ያለ ቅቤ አይሆንም››የሚሉት ወይዘሮ ቀነኔ ቦንሳ፣መርካቶ ላሉ ቸርቻሪዎች ከሚያስረክቡ አርሶ አደሮች የሚፈልጉት ቅቤ በቀጥታ የመግዛት ዕድል የገጠማቸው ናቸው ። ‹‹አንድ ኪሎ ቅቤ የገዛሁት 700 ብር ነው›› የሚሉት ወይዘሮ ቀነኔ፣ጥራቱ አስተማማኝ ቢሆንም ዋጋው በተለይ አቅም ለሌላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች የማይደፈር መሆኑን ይናገራሉ።
‹‹ከቅቤው የማንጠሪያው ይባስ››የሚሉት ደግሞ በአጎዛ ገበያ ቅቤ ማንጠሪያ ቅመማ ቅመም ዋጋ ሲያጠያይቁ ያገኘናቸው ወይዘሮ ቦጋለች ይመር ናቸው ። ወይዘሮ ቦጋለች እንደሚገልጡት፣ለቅቤ ማንጠሪያ ዋናው ኮረሪማ ነው ። ይሁንና የአንድ ኪሎ ኮረሪማ ዋጋ 150 ብር ፣ጥቁር አዝሙድ 300 ብር ፣ ጅንጅብል 50 ብር ፣የተደለዘ ነጭ ሽንኩርት 250 ብር ደርሷል ። ትንንሾቹ የቅቤ የማንጠሪያ ቅመማ ቅመሞች ዋጋቸው በእጅጉ ጨምሯል።ዋጋው ከእርሳቸው አቅም ጋር የሚመጣጠን ባለመሆኑም ቅቤ የመግዛት ሃሳባቸውን ለመሰረዝ፣ ዶሮውንም በዘይት ለመሥራት እስከመወሰን ተገደዋል ።
ከዘንድሮው አንፃር ባለፈው ዓመት አንድ ኪሎ ቅቤ የተሸጠበት 280 ብር ዋጋ እጅግ የተሻለ መሆኑንም የሚያስታውሱት ወይዘሮ ቦጋለች፣ከዋጋ መናር ባሻገር ዶሮ በዘይት አጣፍጠው ለመሥራት ያስገደዳቸው ሌላው ምክንያት በውድ እየተሸጠ ያለው ቅቤ ጥራት ሁኔታም አስግቷቸው መሆኑን አልሸሸጉም።
ወይዘሮዋ እንደሚሉት በተለይ አውድ ዓመት በደረሰ ቁጥር ቅቤ ከዋና ዋና ገበያዎች ውጪ በየአካባቢው፣ በየቤቱ፣ በየጉራንጉሩና በየቢሮው ሳይቀር ይሸጣል።
በዚህ አጋጣሚ እንደ ሙዝ፣ድንች፣ሳሙና የመሳሰሉ ባዕድ ነገሮችን የሚጨምር አይጠፋም።ሆኖም ጥራቱና ደህንነቱ ላይ መንግስት ወይም የሚመለከታቸው አካላት ቁጥጥርና ክትትል ሲያደርጉ አይታይም ። በመሆኑም ሕብረተሰቡ አደጋ ላይ እንዳይወድቅ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርበታል።
ሌላው ያነጋገርናቸው በቅቤ ንግድ የተሰማሩት አቶ መካሻ ዓለሙ ፣ከሁለት ሳምንት በፊት አንድ ኪሎ ቅቤ በ350 ብር ነበር መሸጣቸውን ያስታውሳሉ ። በማግስቱ እስከ ቀትር ድረስ ደግሞ 400 ብር ሸጠዋል ። ከቀትር በኋላ 450 ብር የሸጡበት ሁኔታ አለ።
በዓሉ እየቀረበ ሲመጣ ዋጋውን የበለጠ የመጨመር አዝማሚያ እንዳለው የሚናገሩት አቶ መካሻ፣ እሳቸውም በገዙት ዋጋ ላይ ትርፋቸውን አስልተው እንደሚሸጡ ይናገራሉ ። አሁን አንድ ኪሎ ቅቤ የገዙት በ400 ብር ስለሆነ እና ያመጡት ደግሞ ከዋድላ ደላንታ በመሆኑ የትራንስፖርት ወጪያቸውንና ሌሎች ትርፋቸውን አስበው የሚሸጡ መሆኑን ይገልፃሉ።
‹‹እስካሁን ባመጣሁት ዋጋ ላይ ትንሽ ትርፍ አክዬ የምሸጠው እጄን ሳፍታታ ቆይቼ በዓሉ እየቀረበ ሲመጣ ጨመርመር አድርጌ በመሸጥ ኪሳራዬን አካክሳለሁ ብዬ በማሰብ ነው።››ይላሉ።
ለእርሣቸው የዘንድሮው የዋጋ ጭማሪ ምክንያት አለው። ባሳለፍነው አመት 280 ብር ሲሸጥ የነበረው ዝናብ ስለነበረና ላሞቹ ስለተመቻቸው ቅቤ በመኖሩ ነው። ዘንድሮ ግን የበልግ ዝናብ ባለመኖሩ ድርቅ ነው ። እጅግ ከፍተኛ የቅቤ እጥረት አለ ። ዘንድሮ ዋጋ የጨመረውም ለዚህ ነው ብለዋል ።
አንዳንድ ያነጋገርናቸው የሕብረተሰብ ክፍሎችም ሆኖ ሸማቾች እንደነገሩን፤ የቅቤ ዋጋ በዘንድሮ የትንሳኤ በዓል ሊያሻቅብ የቻለው በቸርቻሪዎች ምክንያት ነው ። በየአካባቢው ያሉ ቸርቻሪ ነጋዴዎች ከዋና ዋናዎቹ ነጋዴዎች ቅቤ እየዞሩ የሚሰበስቡበትና የሚያከማቹበት ሁኔታ አለ ። ይሄን የሚያደርጉት አንድም ከዝናብ ጋር ተያይዞ እጥረት በመኖሩ መጪውም የሰርግ ወቅት በመሆኑ በዛ ወቅት በከፍተኛ ዋጋ ለመሸጥና ለመጠቀም ነው ። በመሆኑም ጉዳዩ የሚመለከተው አካል ሊጎበኛቸው ይገባል የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 22/2013