
አዲስ አበባ፡- በትግራይ ክልል በነበረው ችግር መሠረተ ልማቱ በተለይ ድልድዮች በመጎዳታቸው ክረምት ገብቶ የሰብዓዊ ድጋፉ እንዳይቋረጥ ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ ኮማንድ ፖስት አስተባባሪ ሌተና ጀነራል ዮሐንስ ገብረመስቀል አስታወቁ፡፡
ሌተና ጀነራል ዮሐንስ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት፤ በክልሉ በሕግ ማስከበር ዘመቻው ወቅት ከተከሰተው ጉዳት አኳያ ለችግር የተጋለጡ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ እስካሁን ብዙ ርቀት የተኬደ ሲሆን የተጎዱ መሠረተ ልማቶችንም መልሶ ለመገንባት በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡
እንደ ሌተና ጄኔራል ዮሐንስ ገለፃ፤ በክልሉ በሰላም ማስከበር ሂደቱ ለጉዳት የተዳረጉ መሠረተ ልማቶችን መልሶ ወደሥራ የማስገባት ሥራዎች ተከናውነዋል፤ ለአብነትም ተቋርጦ የነበረው የባንኮች አገልግሎት በአብዛኛው ተከፍቶ እንዲሰራ ተደርጓል፡፡መብራትና ስልክም ቢሆን በተያያዥ ወደ 75 በመቶ በላይ አገልግሎት እየሰጠ ነው፡፡ይሁንና ከመንገድ ጋር የተያያዙ ብዙ ፈተናዎች አጋጥመዋል፡፡በተለይም ድልድይ ላይ የደረሰው ጉዳት በቀላሉ የሚፈታ ስላልሆነ ብዙ ነገሮችን እየገታ ይገኛል፡፡ሰብዓዊ ድጋፉ ሕዝቡ በሚፈልገው ልክ እንዳይደርስ እንቅፋት ከሆኑ ነገሮችም ውስጥ አንዱ ይህ ነው፡፡
ክረምቱ የባሰ ፈተና ውስጥ እንዳይከተን ሥራዎቹ በቀላሉ የሚፈቱበት ሁኔታ እየተመቻቸ ይገኛል ያሉት ጄኔራል ዮሐንስ፤ ጊዜው ክረምት የሚገባበት ወቅት ነው ፈጠን ብለን ይህንን የማስተካከል ሥራ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
ይህንን ችግር ለመፍታት የሚመለከታቸው የፌዴራል መንግሥት ተቋማት ከፍተኛ ርብርብ በማድረግ ላይ ይገኛሉ ያሉት ሌተና ጄኔራል ዮሐንስ፤ ድልድዮቹን ጠግኖ ወደ ሥራ ለማስገባትም ዝግጅታቸውን ጨርሰዋል ብለዋል፡፡
እንደ ሌተና ጄኔራል ዮሐንስ ገለጻ፤ አሁን የሚቀረው ክረምቱን የሚያሳልፍ ሥራ መስራት በመሆኑ እየተጣደፉም ይገኛሉ፡፡ጠንከር ያለ ቡድንም ተሰማርቶ ይህንን ለማከናወን እየሞከረ ነው፡፡ምክንያቱም ተሽከርካሪው እየተንቀሳቀሰ ያለው በመሬት ላይ በመሆኑ ክረምት ከገባ ጭቃ ስለሚሆን በቀላሉ ድጋፉን ለመጓጓዝ ከባድ ነው፡፡ስለዚህ ሥራው ክረምቱ ሳይቀድም መጠናቀቅ መቻል ይኖርበታልና በዚህ ላይ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል፡፡
ችግሩ አሁንም በብዙ መንገድ ድጋፉን ለማድረስ እየፈተነ እንደሆነ የሚገልጹት አስተባባሪው፤ በክልሉ ብዙ ተፈናቃዮች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡እነዚያ ጋር ለመድረስ ደግሞ ድልድዮች ትልቅ ሚና ቢኖራቸውም ነገር ግን እነርሱ ተስተካክለው ወደ ሥራ ካልገቡ መንግሥት ለአቅርቦቱ የሚከፍለውን መስዋዕትነት ዋጋ ያሳጣዋል ብለዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ክምችቶችን ወደሚፈለገው ቦታ በጊዜው መድረስ የማያስችል በመሆኑና የተፈናቃዩ ብዛት ብዙ በመሆኑ ጉዳቱን ከፍ ሊያደርገው እንደሚችል የገለፁት ጄኔራል ዮሐንስ፤ ይህ እንዳይፈጠር ክረምቱን መቅደም እንደሚያስፈልግም አስረድተዋል፡፡
በአቅርቦት በኩል መንግሥት 70 በመቶውን ድጋፍ ሸፍኖ ያለማቋረጥ እየሰራ እንደሆነ የሚያነሱት አስተባባሪው፤ ምግብና መድኃኒት እንዲሁም አልባሳት በተቻለ መልኩ እየተዳረሱ ይገኛሉ ብለዋል፡፡ይሁን እንጂ ካለው ከፍተኛ የተፈናቃይ ቁጥር አንጻርና ከወቅቱ ጋር ተያይዞ የመጠለያ ጉዳይ ስጋት እንደሆነባቸውና ያለው ክምችትም አንድ ቦታ ላይ በመሆኑ ሁሉም ጋር ለመድረስም አስቸጋሪ መሆኑን ጄኔራል ዮሐንስ ጠቁመዋል፡፡ስለዚህም ማዕከላትን መክፈት የውዴታ ግዴታ እንደሆነባቸው ገልጸዋል፡፡
እንደ ሌተና ጀነራል ዮሐንስ ገለጻ፤ የድጋፉ አቅርቦት ፍላጎት ለተፈናቃዮች ብቻ ሳይሆን ለጠቅላላው ነዋሪም ነው፡፡ምክንያቱም በመሠረተ ልማት ችግር ምክንያት የሚፈልጉትን በቀላሉ ማግኘት የማይችሉ አሉ፡፡ስለሆነም ለሁለቱም አካላት አቅርቦቱን ለማቀላጠፍ ከመቀሌ በተጨማሪ ክምችት የሚደረግበት ማዕከል መክፈት ያስፈልጋል፡፡ምክንያቱም ሽሬ ላይ ብቻ 600 ሺህ ተፈናቃዮች አሉ፡፡አክሱም አድዋና ሌሎችም ላይ ከዚህ ያልተናነሰ ተፈናቃይ ይኖራል፡፡
እነዚህ ላይ ለመድረስ ደግሞ ክረምቱን ለመቅደምና በቅርበት ሰብዓዊ ድጋፉን ለማቅረብ መሞከር ግድ ነው፡፡በዚህም አክሱም ላይ ማዕከሉን ለመክፈት ጥረት እየተደረገ ነው፡፡
ለትግራይ ሕዝብ የሚበጀውን የሚያስብ ሁሉ ማን ምን አለን መተውና ለደህንነቱ መስራት አለበት ያሉት ሌተና ጄኔራል ዮሐንስ፤ በተለይም ሰብዓዊ ድገፉ ላይ ክረምቱ እንዳይከፋበት መረባረብን ለመንግሥት ብቻ ከመተው ይልቅ የራስን ድርሻ መወጣትም ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ጦርነት ይህንንና ከዚህ በላይ ችግር የሚፈጥር መሆኑን በማሰብም በነግ በኔነት መስራትም እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 21/2013