
አዲስ አበባ፡- በደቡብ ክልል እስካሁን ወደ 70 በመቶ ያህል ሰው ተመዝግቦ የመራጭነት ካርዱን መውሰዱን የክልሉ ምክትል ርዕሰመስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው አስታወቁ፡፡የምርጫውን ሰላማዊነት ለማረጋገጥ 6 ሺ የሚጠጋ የፖሊስ ኃይልና ከ14 ሺ ለሚበልጥ ሚሊሻ ስምሪት መሰጠቱን ገለጹ፡፡
አቶ ርስቱ ይርዳው በክልሉ እየተከናወነ ስላለው የምርጫ ሂደትና የሰላም ሁኔታ አስመልክተው በተለይ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፤ በክልሉ 6ኛውን አገራዊ ምርጫ በክልሉ በስኬት ለማካሄድ የሚያስችል ሰፊ ሥራ በመስራት ላይ ነው፡፡
በክልል ደረጃ ወደ 113 ምርጫ ክልሎች እንዲሁም ወደ 7 ሺ 864 ምርጫ ጣቢያዎች መከፈላቸውን ያመለከቱት አቶ ርስቱ፣ እንደክልል ይመዘገባል ተብሎ ከተጠበቀው 7 ነጥብ 9 ሚሊዮን አካባቢ ሕዝብ ወደ 5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ወይም 70 በመቶ ያህሉ ተመዝግቦ የመራጭነት ካርዱን ወስዷል ብለዋል፡፡
ቀሪው 30 በመቶ በሦስትና ቀን ይጠናቀቃል ብለን እናስባለን ያሉት አቶ ርስቱ፣ የተጠቀሰው ቁጥር ከትናንት በስቲያንና ትናንትን አይጨምርም፡፡እስከ መጪው አርብ ድረስ በተሟላ መንገድ የመራጮች ምዝገባ ይከናወናል ብለው እንደሚጠብቁ አስታውቀዋል፡፡
ምርጫ ጣቢያዎች የምርጫ ቦርድ ያስቀመጠው የጊዜ ገደብ እስኪጠናቀቅ ድረስ ክፍት ሆነው እንደሚቆዩ ያስታወቁት አቶ ርስቱ፣ ምርጫው በስኬት እንዲጠናቀቅ በቁርጠኝነት እየሰራን ነው ብለዋል፡፡
እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ በዚህ ምርጫ በክልል ደረጃ የሚሳተፉ አገር አቀፍና ክልላዊ ፓርቲዎች 22 ናቸው፡፡ከእነዚህ ፓርቲዎች እስካሁን ባለው ሁኔታ የተወሰኑት እንቅስቃሴ ውስጥ ገብተዋል፡፡ምርጫውን ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ ሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ለማድረግ የጋራ መድረክ ተፈጥሯል፡፡
የጋራ መድረኩ በክልል ደረጃ ተጀምሮ ወደታችኛውም መዋቅር እየሄደ ነው፡፡እስካሁን ባለው ሁኔታ ወደ 16 የሚሆኑ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ተመሳሳይ የጋራ ምክር ቤት አቋቁመዋል፡፡ፓርቲዎች በሁሉም ደረጃ የየራሳቸውን ዝግጅት እያደረጉ ነው፡፡አንዳንዶችም ገብተው ሰፋ ያለ ቅስቀሳ በማድረግ ላይ ናቸው ብለዋል፡፡
እንደ ክልል መንግሥት ለሁሉም ፓርቲዎች ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እየሰራን ነው ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፣ በዚህ በኩል እስካሁን አልፎ አልፎ የሚቀርቡ ቅሬታዎች ካልሆኑ በስተቀር ያጋጠመን ችግር የለም፡፡የሚያጋጥሙ ቅሬታዎች ቢኖሩም በፓርቲዎቹ በጋራ ምክክር እየተደረገባቸው እየተፈቱ የመጡ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ከዚህ በመነሳትም ምርጫው ሰላማዊ ፉክክር የሚደረግበት እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
አቶ ርስቱ እንዳሉት፤ በመጀመሪያዎቹ አካባቢዎች አንድ ፓርቲ ዕጩ ታስሮብኛል የሚል ቅሬታ አቅርቦ ነበር ዕጩው በወንጀል ተጠርጥሮ በሕግ ቁጥጥር ስር የዋለበት ሁኔታ ነበር፤ ለፍርድ ቤት ጉዳዩን በማቅረብ ዕጩ ተወዳዳሪ መሆኑ ተገልጾ ክሱ ለጊዜው እንዲቆይና ወጥቶ ምርጫ ሥራው ላይ እንዲሳተፍ በክልሉ መንግሥት በኩል ጥረት ተደርጓል፡፡
ከዚህ ባለፈ ይህ ነው የሚባል ቅሬታ የለም ያሉት አቶ ርስቱ፣ ነገር ግን ፓርቲዎችም አንዳንድ ቦታዎች ደጋፊዎቻቸው ስለደረሰባቸው ተጽዕኖ በጋራ የሚያነሷቸው ጥያቄዎች እንደነበሩና ይህንንም በጋራ ወርደው እንደሚፈቱ አስታውቀዋል፡፡
ለምሳሌ ጋሞ ዞን ላይ እንዲህ ዓይነት ጥያቄዎች ቀርበው የነበረ ሲሆን፣ የፓርቲ አባላቱና ምርጫ ቦርዱ በጋራ በመሆን ታች ድረስ በመውረድና ችግሩን በማየት የተባለው ነገር መሬት ላይ አለመኖሩን አሳይተዋል፡፡ቅሬታ ያቀርቡ ፓርቲዎችም ተወዛግበው ስህተት አለመኖሩን አረጋግጠው መመለሳቸውን አመልክተዋል፡፡
አልፎ አልፎ በገዥው ፓርቲም በኩል የሚነሱ ቅሬታዎች መኖራቸውን የጠቀሱት አቶ ርስቱ፣ ለአብነትም ፖስተር ተቀደደብኝ፤ ሌላ ፓርቲ በእኔ ፖስተር ላይ ደረበብኝ የሚሉና መሰል ቅሬታዎች መኖራቸውን ገልጸዋል። እነዚህንም ቅሬታዎች በመነጋገር መፍታት የሚገባው በጋራ ምክር ቤት በመሆኑ በዚሁ አግባብ በመሰራቱም በእስካሁኑ ሂደት የጎላ ችግር እንዳልገጠማቸው አስታውቀዋል፡፡
ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ቀደም ሲል በክልላቸው የጸጥታ ችግር መኖሩን አስታውሰው፤ አሁን ባለው ሁኔታ ግን መላ ሕዝባችንና የመንግሥት አካላት በየደረጃው ባደረግነው ጥረት በተነጻጻሪ የተሻለ ሰላም ያለበት ክልል ነው ብለዋል፡፡በክልሉ በሁሉም ጥግ ምርጫውን በሰላማዊ መንገድ ማድረግ አለብን በሚል ዝግጅት በማድረግ ላይ ነው፡፡በምርጫው ችግር ያጋጥመናል የምንላቸውን አካባቢዎች በመለየት አስቀድመን የጸጥታ ማስከበር ሥራ እየሰራን እንገናለን ብለዋል፡፡
በሁሉም ምርጫ ጣቢያዎች የምርጫውን ደህንነትና የምርጫ ቁሳቁስን ደህንነት የሚከታተል የጸጥታ ኃይል ስምሪት አድርገናል ያሉት አቶ ርስቱ፣ ወደ 6 ሺ የሚጠጋ የፖሊስ ኃይል ለይተን ስምሪት ሰጥተናል፡፡ከዚህ በተጨማሪ ከ14 ሺ በላይ የሚሊሻ ኃይል ስልጠና ወስዶ ምርጫውን እንዲያግዝ መሰማራቱን ጠቁመዋል፡፡
ከጸጥታ አኳያ ችግር እንዳይኖር ሁሉም ዜጋ የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ ያቀረቡት አቶ ርስቱ ያለምንም ሰላም መደፍረስ ምርጫውን እናደርጋለን ፤ ለዚህም በቂ ዝግጅት አድርገናል ብለዋል፡፡
ምርጫውን ለማካሄድ ሰላም እጅግ አስገፈላጊ ነው፡፡ሰላም ከሌለን መምረጥም መንግሥት ማቋቋምም ሆነ የየዕለት ኑሯችንን ማስቀጠል አንችልም፡፡ከሁሉ በላይ ደግሞ አሁን አገራችን ካለችበት ተጨባጭ እውነታ አንጻር ማንም ያሸንፍ ማን ሕዝቡ የሚሰጠውን ውሳኔ ለመቀበል የትኛውም ፓርቲ ዝግጁ ሊሆን ይገባዋል ብለዋል፡፡
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 21/2013