
ሀዋሳ፡- በሀዋሳ ከተማ ያለው የመሬት አቅርቦትና የአስተዳደር ሥርዓት የተሻለ እንደሆነና በአግባቡ እየተመራ መሆኑ የሀዋሳ ከተማ ምክትል ከንቲባና የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ ሃላፊ አቶ ሚልኪያስ ብትሬ አስታወቁ።የሀዋሳ ሀይቅን የመጠበቅና የመንከባከብ እንዲሁም የሀይቅ ዳርቻዎችን የማልማት ሥራ በሰፊው ለመሥራት ትልቅ ግብ ተቀምጦ እየሠራ እንደሚገኝ ገለፁ።
የሀዋሳ ከተማ ምክትል ከንቲባና የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ ሃላፊ አቶ ሚልኪያስ ብትሬ በተለይም ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፤ ከተማ አስተዳደሩ ውስንና የጋራ ሀብት የሆነውን መሬት በአግባቡ ተጠቅሞ እያስተዳደረ ይገኛል።
በከተማዋ የተሻለ የመሬት አቅርቦት ከመኖሩ ጋር ተያይዞ በርካታ የመሬት ፍላጎቶች ይቀርባሉ።ያለውን ሰፊ ፍላጎት ተከትሎም ከተማ አስተዳደሩ መመሪያና አሠራሩን በመከተል በተለያየ መንገድ መሬት እያዘጋጀ ለሚፈለገው አገልግሎት እያቀረበ የሚገኝ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በከተማዋ ጤናማ የሆነ የመሬት አስተዳደር ለመኖሩም በከተሞች የተጀመረው ካዳስተር ምክንያት ሆኗል ያሉት አቶ ሚልኪያስ፤ የከተሞች የመሬት ምዝገባና መሬት ነክ ንብረቶችን በቴክኖሎጂ መዝግቦ መያዝ መቻሉ እጅግ አስፈላጊና ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው አሠራር እንደሆነ አስታውቀዋል።
የመሬት አያያዝን ለማዘመን በከተሞች የተጀመረው ካዳስተር በሀዋሳ ከተማ በአምስት ክፍለ ከተሞች ተግባራዊ ለማድረግ መሞከሩን አመልክተው፣ ሌሎች ከተሞችም ወደ ከተማዋ መጥተው ልምድ የሚወስዱበት ሁንታ እንደነር አመልክተዋል።
በአካባቢው ተፈጥሮ በነበረ የፀጥታ ችግር ምክንያት ሥራው ተቀዛቅዞ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ሚልኪያስ፤ በአሁን ወቅት ሌሎች ሁለት ተጨማሪ ክፍለ ከተሞችን በመጨመር የካዳስተር ሥራው የቀጠለ መሆኑን ጠቁመዋል።
የካዳስተር ሥራ በዋናነት መብት ፈጣሪ ከሆነው ማለትም የከተማዋ መሬት ማኔጅመንትና መሬት ልማት የሚመጣውን መረጃ እና ባለንብረት ነኝ የሚለው አካል የሚያቀርበውን መረጃ አመሳክሮ ማረጋገጥ ነው።የተረጋገጠው መረጃም በሥርዓት ተደራጅቶ ወደ መረጃ ቋት ውስጥ ይገባል።በዚህ ጊዜ ፋይል ጠፋ፣ የዕገሌ ይዞታ ትክክል ነው አይደለም ወዘተ… የሚሉ ቅሬታዎች አይነሱም ብለዋል።
አጠቃላይ የመሬት አስተዳደር ሥርዓቱ በሥርዓት መመራት ይችላል ያሉት አቶ ሚልኪያስ፤ ቴክኖሎጂው በከተማዋ ያለውን መሬት ማወቅና በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችል ከመሆኑም በላይ ከተማዋ ምን ያህል ገቢ ማግኘት እንዳለባት የተጣራ መረጃ ይሰጣልም ብለዋል።ከዚህ በተጨማሪም ሕገ ወጥነትን መከላከል የሚያስችል መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በከተማዋ የካዳስተር ሥርዓትን በመከተል መሬትን በዘመናዊ መንገድ ከመያዝ ባለፈም የሊዝ አዋጁን በመከተል በዋናነት መሬት በሁለት መንገድ የሚተላለፍ መሆኑን ምክትል ከንቲባ አቶ ሚልኪያስ ገልፀዋል።የሚተላለፈው መሬት በተለይም የሥራ ዕድል በመፍጠር ለከተማዋ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከት የሚችሉ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለተሰማሩ ባለሀብቶች እንደሆነም ጠቁመዋል።
በከተማዋ በዓመት ሁለት ጊዜ መሬት በጨረታ እንደሚቀርብ የጠቆሙት አቶ ሚልኪያስ ፣ ከሌሎች ከተሞች በተለየ መልኩ ሀዋሳ ከተማ ላይ መሬት በከፍተኛ ዋጋ የሚጫረት እንደሆነ ጠቁመዋል። ይህም ከተማዋ ምን ያህል ተፈላጊና ለኑሮ ምቹ እንደሆነች የሚያመላክት ነው ብለዋል፡፡
በዋናነት መሬት ለባለሀብቶች ከሚተላለፍባቸው ሁለት መንገዶች በተጨማሪም በማህበር ተደራጅተው ለሚመጡ አቅምና ፍላጎት ያላቸው ነዋሪዎች የመኖሪያ ቤት መገንባት የሚያስችላቸውን ቦታ በማዘጋጀት የሚቀርብ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘም ለከተማ ግብርና፣ ለማኑፋክቸሪንግ፣ ለኢንዱስትሪና ወጪ ቆጣቢ ለሆኑና ከተማ አስተዳደሩ ለሚያስገነባቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶችም እንዲሁ መመሪያና አሠራሩን በመከተል መሬት ይዘጋጃል ብለዋል።ባለፉት ዘጠኝ ወራትም ከተማ አስተዳደሩ ከዕቅዱ በላይ መሬት አዘጋጅቶ ያስተላለፈ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
በሀዋሳ ከተማ ያለው የመሬት አቅርቦትና አስተዳደሩ የተሻለ መሆኑን ጠቁመው፤ በከተማዋ ከ40 ሺህ የሚበልጥ ቁራሽ መሬት መኖሩን አስታውቀዋል። እስካሁን በካዳስተር ሥርዓት ውስጥ የተካተተው መሬት ስምንት ሺህ ያህሉ እንደሆነ ም አመልክተዋል። ከተማ አስተዳደሩ በቀጣይ ብዙ ሥራ የሚጠበቅበት እና በዛው ልክም እየሠራ መሆኑን ገልፀዋል።
የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከተማዋን በምሥራቅ አፍሪካ አሉ ከሚባሉ ከተሞች መካከል አንዷ የማድረግ ራዕይ ሰንቆ እየሠራ ባለበት በዚህ ወቅት በተለይም የከተማዋ ትልቅ ሀብት የሆነውን ሀዋሳ ሀይቅን የመጠበቅና የመንከባከብ እንዲሁም በቀጣይም የሀይቅ ዳርቻዎችን የማልማት ሥራ በሰፊው ለመሥራት ትልቅ ግብ አስቀምጦ እየሠራ እንደሚገኝም አመልክተዋል።
ፍሬህይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 20 ቀን 2013 ዓ.ም