
አዲስ አበባ፦ የ2013 ዓ.ም በጀት ዓመት በዘጠኝ ወራት ውስጥ 212 ቢሊዮን 473 ሚሊዮን 364 ሺህ 061 ገቢ መሰብሰቡን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ። ለስኬታማ አፈፃፀሙ ለሁሉም አካላት ምስጋና አቀረበ።
የገቢዎች ሚኒስትር አቶ ላቀ አያሌው እንዳስታወቁት፣ ሚኒስቴሩ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወር 213 ቢሊዮን 850 ሚሊዮን 048 ሺህ 262 ብር ለመሰብሰብ አቅዶ፤ 212 ቢሊዮን 473 ሚሊዮን 364 ሺህ 061 ብር መሰብሰብ ችሏል።አፈፃፀሙም ከዕቅዱ 99.36 በመቶ ነው ።
የዕቅድ አፈፃፀሙ ከ2012 ዓ.ም በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ29 ቢሊዮን 225 ሚሊዮን 528 ሺህ 145 ብር ወይም 15.95 በመቶ ዕድገት እንዳለው አስታውቀዋል።
ገቢውም ከሀገር ውስጥ ታክስ 128 ቢሊዮን 171 ሚሊዮን 912 ሺህ 306 ብር፣ ከውጭ ንግድ ቀረጥና ታክስ 84 ቢሊዮን 135 ሚሊዮን 403 ሺህ 672 ብር እንዲሁም ከሎተሪ ሽያጭ 166 ሚሊዮን 048ሺህ 082 ብር በድምሩ 212 ቢሊዮን 473 ሚሊዮን 364 ሺህ 061 ለመሰብሰብ መቻሉን አመልክተዋል።
ገቢው የተሰበሰበው ሀገሪቱ በፀጥታና በኮሮና ወረርሽኝ ውስጥ ባለችበት አስቸጋሪ ወቅት በመሆኑ የተሻለ አፈፃፀም ሊባል የሚችል እንደሆነም ገልፀዋል፡፡
ለዚህ መልካም ውጤት መመዝገብ በወቅቱ ግብራቸውን የከፈሉ ግብር ከፋዮች፤ የገቢዎች ሚኒስቴር፣ የጉምሩክ ኮሚሽን፣ የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር አመራሮችና ሠራተኞች እንዲሁም የሌሎች አጋር አካላት ሚና ከፍተኛ መሆኑን አስታውቀዋል።
ለተመዘገበው ስኬታማ አፈፃፀም ለሁሉም አካላት ምስጋናቸውን ያቀረቡት አቶ ላቀ ሁሉም አካላት የተሻለ ግብር ለመሰብሰብ እያደረጉ ያለውን ትኩረት አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 20 ቀን 2013 ዓ.ም