ዘላለም የሳጥንወርቅ (የእፀሳቤቅ አባት)
ለሊት ነው ሰባት ሰዓት..ጨረቃ በዳፍንት በትር ሰኮናዋን ተብላ ከህዋው ጉያ ውስጥ ተደብቃለች።የሰኔን የሚመስል ጥቁር ጽልመት ምድርን ውጧታል።
ፍርዱ በእንቅልፍ ልቡ አልጋው ላይ ይገላበጣል..በህልሙ መላዕክ የምትመስል ቀይ ሴት እንደ ሰይጣን ቀንድ አብቅላ ጥፍሮቿን በማሾል ስታባርረው ይታየዋል።ብርሀንና ጨለማን የወረሰች እንደ የመላዕክና የአጋንንት ሁለት መልክ ያላት ቆንጆና ጋፍ ሴት እዝነ ልቦናውን አሳሩን አሳየችው።
ጠይም ፊቱ በወበቅ ተረሰረሰ..አባይና ጣና ከእሱ ሰውነት ላይ የሚቀዱ ይመስል በአንድ ጊዜ ክረምት ሆነ።እየተወራጨና እያጉረመረመ ጥቂት ደቂቃዎችን አሳለፈ።አንሶላና ብርድ ልብሱ በእግሮቹ እርግጫ ተገፍተው ወደ መሬት አዘቅዝቀዋል።አንገቱ ወደ ሰሜን አቅጣጫ አዝሟል።እጆቹ ወደ ደቡብ ጫፍ ተንጨፍረዋል።
እግሮቹ አቅጣጫቸው አይታወቅም ፤ፖሊዮ እንደያዘው ሰላላ ገላ ጥምልምል ብለው ተዛንፈዋል፡ወገቡ ሳይቀር የአቅጣጫ ለውጥ ነበረው።ቀይና ጥቁሯ ሴት እያባረረችው ነው..እጇ ላይ የኪሩቤልን የሚመስል ሰይፍ ይታየዋል።
ስልኩ ጮኸች..ከእንቅልፉ ብቻ ሳይሆን ከስቃዩም ተመነጠቀ።ፍርዱ ነቃ..።እጁን ወደ ስልኩ ሳይሰድ በእንቅልፍ ልቡ ታሳድደው ስለነበረችው ሴት እያሰበ ቆየ።ለበርካታ ዓመታት ተኝቶ አያውቅም ፤ በተለይ ለአምስት ዓመታት ርብቃን ካጣ ጀምሮ በስርዓት ተኝቶ አያውቅም።
ርብቃ ብዙ ነገሩን ነጥቃዋለች ፤ ፍቅሩን፣ ሰላሙን፣ ደስታውን ይሄን ሁሉ።ይሄ ሁሉ ጊዜ አልፎ እንኳን አልረሳትም።በህይወቱ ብዙ ቦታ ላይ አለች…አንድ ቀን ትመጣለች ሲል ለራሱ ይነግረዋል።በህይወቱ ብዙ ነገር ያጣ ሰው ነው፤ ካጣው ነገር ሁሉ ግን ርብቃን እንደማጣት የጎዳው የለም።የዓለም ብርሀን ትመስለው ነበር፣ በሳቋ ውስጥ፣ በፍቅሯ ውስጥ፣ በሴትነቷ ውስጥ ብዙ ሆኖ የሚኖር ሰው ነበር።ግን ተስፈኛ ነው፤ በህይወቱ የሚወዳቸውን ሁሉ አጥቶ ይስቃል።
ስልኩ ለሦስተኛ ጊዜ አቃጨለ።በዚህ ሰዓት ተደውሎለት አያውቅም..ኧረ ጭራሽ የሚደውልለትም የለም።ስልኩን በማንሳት ፈንታ ፈራው።
እርሱ በህይወት ያለ የዚህ ዓለም እድለ ቢሱ ሰው ነው።ከዚህ ውጪ እሱን የሚገልጽ ቃል የለም።የእሱ እድለቢስነት የሚጀምረው ከአራስ ቤት ነው፤ ገና የሦስት ቀን አራስ ህጻን ሳለ ነበር ቤተሰቡን በጎርፍ ያጣው።ቤቱ ውስጥ እሱ ብቻ ሲቀር በአንድ ምሽት ቤተሰቡን አጣ።
ብርቱዎች ወድቀው እሱ መቆሙ ዛሬ ላይ ይሄን ታሪኩን ሲያስብ ከማዘን ባለፈ ይገረማል።አራስ ሆኖ መዳኑ፣ ያቀፈችው እናቱ ስታልፍ እሱ መትረፉ አንዳንድ ጊዜ ከማዘን ባለፈ ፈጣሪ በእሱ ህይወት ላይ ያስቀመጠው ታላቅ ነገር እንዳለ እንዲያስብ ያደርገዋል።
ትናንትን የሚረሳባቸው ብዙ የፍሰሀ ዘላለማት ከፊቱ እንደሚጠብቁት እንዲያስብ ያበረታዋል።በመከራው ሁሉ ውስጥ..በተስፋ መቁረጡ ሁሉ ውስጥ ፈገግ እንዲል አቅም ይሰጠዋል።ከአራስ ቤት ጀምሮ በሰው እጅ ነው ያደገው።
በልጅነቱ የብዙ እናቶችን ጡት ጠብቷል።የፍየልና የበግ ወተት ጠጥቶ ያውቃል፤ ይሄም ይገርመዋል።ከመዳህ እየወጣ መራመድ ሲጀምር ጎዳና ወጣ..ስቴዲየም፣ ቦሌ፣ ሀያ ሁለት እያለ አደገ።ይሄም ይገርመዋል።
ካደገ በኋላም እድለቢስነቱ አልተወውም…በሚያፈቅራት ሴት ተቀጣ።የህይወቴ አዲስ ጀምበር ባላት ሴት ከንቱ ሆነ።በህይወቱ ከሆነው ሁሉ ይሄኛው ክፉ ነበር።ርብቃን ድንገት አጣት።ሊያገባት ሳምንት ሲቀረው የውሀ ሽታ ሆነችበት።ብዙ መከራ ብዙ መከፋት ደረሰበት።
አሁንም ግን ተስፈኛ ነው..አንድ ቀን በበደሌ ልክ ሊክሰኝ ትልቅ ነገር ይዞ ፈጣሪ ወደ እኔ ይመጣል ሲል ያስባል።አንድ ቀን በድካሜ ልክ አርፋለሁ።አንድ ቀን ባጣሁት ልክ አገኛለሁ እንዲህ እያለ።ግን ከክፉ እድል ባለፈ ወደ ህይወቱ የመጣ አንድም መልካም እድል እስካሁን የለም።ግን ተስፈኛ ነው..አንድ ቀን ሁሉም ነገር ጥሩ እንደሚሆን…..ስልኩ ለስንተኛ ጊዜ እንደሆነ እንጃ ደግሞ ጠራ..ወደ ስልኩ እያየ ‹ደሞ ምን ክፉ ነገር ይዞብኝ ሊመጣ ይሆን? እያለ በመስጋት አነሳው።ለሊት 7፡30 ላይ የህይወት ዘመኑን ድንቅ ተዓምር በስልኩ ውስጥ አዳመጠ።በቃ የእሱ ህይወት እንዲህ ነው..በተዓምር የተሞላ።
በዛ መንፈቀ ለሊት መከራውን ሁሉ የሚያስረሳ አንድ ድምጽ በስልኩ ማህጸን ውስጥ ተሰማው።ርብቃ ነበረች…ህይወቱ..እስትንፋሱ..ትርታው።ከአምስት ዓመት በፊት የሚያውቃት ርብቃ፣ ሊያገባት ሳምንት ሲቀረው ያጣት ሴት፤ ድንገት አለሁ አለችው።እውነት ይሆን? ድምጽዋን እየሰማው ራሱን ተጠራጠረው።በህይወቱ በሳቀ ማግስት እንዳለቀሰ ነው…የቱን ማመን እንዳለበት ግራ ገባው።ድምጽዋ በህሊናው ያስተጋባል ‹እኔ ነኝ…ርብቃ ነኝ..› እያለ።
በስልኩ ውስጥ ምን ነበር ያለችው? ስሟን እንደሰማ ነበር ሰመመን የዋጠው።ርብቃ ነኝ እንዳለችው ነበር ራሱን የረሳው።ነገ 10፡00 ሰዓት ብላ ምን ነበር ያለችው? ከነዓን እንገናኝ….እንዲህ ያለችው ይመስለዋል።አዎ እንደዚህ ነው ያለችው…ከእሷ ነፍስ በቀር ከነዓንን የሚያውቅ የለም።ከንዓን የጥንድ ነፍሶቻቸው የፍሰሀ ምድር ነው።
ከአምስት ዓመት በፊት የንጹህ ልቦቻቸው ማረፊያ ስፍራ እንዲህም ነበር።ራሱን እየሳቀ..እያለቀሰም አገኘው።ከደረቀበት አቆጠቆጠ…ከጠወለገበት አለመለመ።ህይወቱ ባዶ ነበር፣ ለምን እንደሚኖር አያውቅም ነበር።ታሪኩ ካቆመበት ቀጠለ።ለሊቱን ተቀምጦ አደረ።
ጠዋት እንገናኝ ወዳለችው ቦታ ሲሄድ በህይወቱ ተሰምቶት በማያውቅ ደስታ ነበር።አይኖቹን ለፍለጋ ሲያማትር ከመንገዱ
በወዲያ ጥግ ናፍቆት ያገረጣት አንድ ሴት ቆማ አየ።ምን ነበር የሆነው? አያስታውሰውም…በደስታው ቀን ሁሌ እንዳዘነ ነው ከህልም እንዳይባንን እየፈራ ስቃ ወደምትጠብቀው ሴት ተራመደ።ፈገግ ብላ ቆማለች።የሚያውቀውን የሆነ ነገር ፊቷ ላይ አጣው..ግማሽ ውበቷ በቦታው የለም…ደብዝዛለች…እንዳይከፋው በግድ የምትስቅ ይመስለዋል።ልቡ ተላወሰ..
ርብቃ እሱ ከሆነው በላይ ሆና ጠበቀችው።በነፍሷም በስጋዋም እየሳቀች ተጠጋችው…ከህልሟ አንዱ እሱን ማየት ነበር ሆነላት።ብዙ ነገር ታወራዋለች።ከአምስት ዓመት በፊት ሊጋቡ አንድ ሳምንት ሲቀራቸው ለምን እንደጠፋች እያለቀሰች ትነግረዋለች።
አሁንም ከሰላሳ ደቂቃ በላይ በህይወት መቆየት እንደማትችል ይሄንንም እያለቀሰች ትነግረዋለች።አሁንም የመጣሁት ለዘላለም በምወድህ በአንተ ክንድ ላይ መሞትን ፈልጌ ነው ስትል ይሄንንም እያለቀሰች ትገልጽለታለች።በመጨረሻም እንደምታፈቅረው ነግራው ትሰናበተዋለች።
ካንሰር አለባት…ከአምስት ዓመት በፊት ወደ እሱ ስትመጣ ወደቀች…ከአልጋዋ ላይ እስከተነሳችበት የትናንትናዋ ቀን ድረስ በህክምና ላይ ነበረች።ተስፋ የሌላትንና ነገ የምትሞትን ሴት ሚስቱ ማድረግ የለበትም ፤ሌላ ጤነኛ ሴት ማግባት አለበት ስትል ነበር ራሷን ደብቃ ስትታከም የቆየችው።
ግን ቶሎ መሞት አልቻለችም…ድኜ አገበዋለሁ ስትል ብዙ ተስፋ ነበራት፤ በመጨረሻ ግን ከሁለት ወር በላይ እድሜ እንደሌላት በሀኪሟ ተነገራት።አላገኘውም ብላ ነበር..ግን አልቻለችም ፤ለመሞት አንድ ቀን ሲቀራት ትናንት ለሊት ደወለችለት ፤ይሄው ዛሬ ተገናኙ።ለመሞት ሰላሳ ደቂቃ ሲቀራት ወደምታፈቅረው ሰው ህይወት ዳግሞ መጣች።
ሲገናኙ ሁለቱም በናፍቆት እያለቀሱ ነበር…በመጨረሻዋ በእድሜዋ ማምሻ ላይ በምታፈቅረው ሰው ጉያ ውስጥ ራሷን አገኘችው።
እነግረዋለሁ ያለችውን ሳትነግረው…ክንዱ ላይ ወደቀች።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 15/2013