ሙሳ ሙሀመድ
በአሁኑ ጊዜ በጤናው ዘርፍ እየወጡ ያሉ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በደም ውስጥ የሚገኘውን የኤች አይ ቪ መጠን በመቆጣጠር ስርጭቱን መግታት እንደሚቻልና በፕሮግራም ደረጃ ተግባራዊ መደረግ መጀመሩን ነው።
የፌዴራል ኤች አይ ቪ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽ/ቤት ዋና ኃላፊ ዶ/ር ጽጌሬዳ ክፍሌ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደተናገሩት፣ ኤች አይ ቪ በደማቸው የሚገኙ ወገኖች በጤና ባለሙያዎች የታዘዘላቸውን የፀረ-ኤች አይ ቪ መድሃኒት በአግባቡ በመውሰድ የመድሃኒት ቁርኝቱን ሊያዛንፉ ከሚችሉ ድርጊቶች በመቆጠብ በደማቸው ውስጥ የሚገኘውን የቫይረስ ቁጥር ወደ ማይታይ መጠን በማድረስ ለሌላ ሰው የማስተላለፍ ዕድልን መቀነስ ይችላሉ።
ይህም ሲባል የፀረ-ኤች አይ ቪ መድሃኒታቸውን በአግባቡና ቀጣይነት ባለው መልኩ በመውሰድ የቫይረሱን መጠን ቢያንስ ለስድስት ወራትና ከዚያን በላይ በቀጣይነት ባለበት እንዲቆይ ማድረግ ከቻሉ በኤች አይ ቪ ላልተያዙ የትዳርና የወሲብ አጋራቸው ቫይረሱን የማስተላለፍ ዕድላቸው እጅጉን የተዳከመ ይሆናል።
በሌላ በኩል በደም ውስጥ የሚገኘው የኤች አይ ቪ ቁጥር የማይታይ በሚሊ ሊትር ከ200 ኮፒ በታች መጠን ከደረሰ ኤች አይ ቪ በደሙ ለማይገኝ የትዳርና የወሲብ አጋር የማስተላለፍ ዕድሉ የተገታ መተላለፍ ይሆናል ብለዋል ዶ/ር ጽጌሬዳ።ይህ ፅንሰ ሃሳብ “undetectable Equals Un-transmittable” (U=U) በመባል በፈረንጆቹ ይጠራል።የሀገራችንን ተጨባጭ ሁኔታ ከግንዛቤ በማስገባት (የማይታይ መጠን = የተገታ መተላለፍ (የ=የ) የሚል አቻ ስያሜ ተሰጥቶታል።
የማይታይ መጠን ማለት የቫይረሱ ቁጥር እጅግ አናሳ መሆኑን የሚያመለክት ሲሆን፤ የተገታ መተላለፍ ሲባል ድግሞ የመተላለፍ ሂደቱን እጂጉን መቀነሰ የሚቻለው የቫይረሱን ቁጥር በማይታይ መጠን በቀጣይነት ማቆየት ሲቻል ብቻ መሆኑን ለማስገንዘብ ነው።
ሀገራችን እ.ኤ.አ በ2030 ኤድስን ለማስቆም ባስቀመጠችው ግብ መሰረት አዳዲስ የፕሮግራም ትግበራ አገልግሎት አሰጣጥ አሠራሮችን በመፈተሽ ሀገራዊ ተጨባጭ ሁኔታን ባገናዘበ መልክ ስታከናውን ቆይታለች።ከ2013 በጀት ጀምሮም እነዚህን ፕሮግራሞች ቀድሞ ሲካናወኑ ከነበሩት የቫይረሱ መጠን ልኬትና የመድሃኒት ቁርኝት ዙሪያ የሚተገበሩ ሥራዎች ጋር በማቀናጀት ተግባራዊ ማድረግም መጀመሯን ዋና ኃላፊዎች ተናግረዋል።
ይህ ፕርግራም በ98 የዓለም ሀገሮች ተግባራዊ የሆነና 25 ሀገሮችም በሀገረኛ አቻ ትርጓሜ ሰጥተውት በመተግበራቸው ተጨባጭ ውጤት እያስገኘ መሆኑን የአሜሪካ መንግሥት በሽታ መቆጣጠሪያና መከላከል ማዕከል (ሲዲሲ) ያደረጋቸው የዳሰሳ ጥናቶች ያመላክታሉ።
ይህን ፕሮግራም በፌዴራል ደረጃ በጤና ሚኒስቴርና በኤች አይቪ/ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽ/ቤት መሪነት ኤች አይ ቪ በደማቸው የሚገኙ ወገኖች ማህበራት የጥምረቶች ጥምረት (ኤን ኢ ፒ+) ጋር በመሆንና አጋሮችን በማስተባበር የሚመራ ይሆናል።
ፕሮግራሙ በዋናነት ትኩረት የሚደረግባቸው የቫይረሱን መጠን ልኬት ፍለጎት መጨመር፣ የፀረ-ኤች አይ ቪ መድሃኒት ቁርኝትን ማሻሻል፣ የጤና ስርዓት ማሻሻል፣ የጥምር የኤች አይ ቪ መከላከል ሥራን ማጠናከር እና የኤች አይ ቪ ምክርና ምርመራን ማጠናከር መሆናቸውን ነው ሲሉ ዶ/ር ፅጌሬዳ በዝርዝር ተናግረዋል፡፡
የጽ/ቤት ኃላፊዋ በእያንዳንዱ ሲያብራሩም የቫይረሱን መጠን ልኬት ፍለጎት መጨመር (Demand creation for viral load testing)፣ ፀረ-ኤች አይ ቪ ህክምና እየወሰዱ የሚገኙ ወገኖች የቫይረስ መጠን ልኬትን የጤና ባለሙያዎች በሚያዟቸው መሰረት እንዲያሠሩ፣ ግንዛቤ የማሳደግ ሥራ ይሠራበታል።
የመድሃኒቱ ተጠቃሚዎች ጥቅሙን በሚገባ ተረድተውና በደማቸው የሚገኘው የቫይረስ መጠን መውረድ ያለውን ፋይዳ በተቃራኒው ድግሞ የቫይረስ መጠን መጨመሩ የሚያስከትለውን ችግር በማወቅ አግባብነት ያለው የአኗኗር ዘይቤን የማስተማር ሥራ ተጠናክሮ የማስቀጠል ሂደት ነው።ይህም ይቀጥላል።
የፀረ-ኤች አይቪ መድሃኒት ቁርኝትን ማሻሻል (Promoting Adherence to ART) ለቫይረሱ መጠን መቀነስ ዋነኛ ምክንያት በጤና ባለሙያ የታዘዙ የፀረ-ኤች አይ ቪ መድሃኒቶችን በአግባቡ መውሰድ ስለሆነ፣ ወጥነት ያለው የመድሃኒት ቁርኝት እንዲኖር የሚያደርጉ ሥራዎችን መሥራትን አጠናክሮ ማስቀጠል ነው፡፡
የጤና ስርዓትን ማሻሻል፡- ይህ ስርዓት የቫይረስ መጠን ልኬት አሠራር እንዲሁም የፀረ-ኤች አይ ቪ መድሃኒት ቁርኝት ዙሪያ የሚከናወኑ ሥራዎች ላይ የሚያጋጥሙ የጤና ስርዓት ችግሮች እንዳይከሰቱ የጤና ስርዓቱን የማሻሻል ሥራ ማለት ነው፡፡
የጥምር የኤች አይ ቪ መከላከል ሥራን ማጠናከር፡- ኤች አይ ቪን የመከላከል ሥራው በአንድ አገልግሎት ብቻ ውጤታማ የሚሆን ሳይሆን የቅድመ መከላከልን መሰረት በማድረግ ባህሪያዊ፣ መዋቅራዊና ባዮ ሚዲካል መሰረት ያደረጉ የመከላከል ሥራዎችን ጎን ለጎን ተጠናክረው የሚቀጥሉበት አሠራር ነው።
የኤች አይ ቪ ምክርና ምርመራን ማጠናከር፡- የፀረ-ኤች አይ ቪ ህክምና የሚያስገኘውን ጥቅም በመረዳት በተለይም ኤች አይ ቪ በደማቸው የሚገኙ ወገኖች ላይ የሚደርሰውን መድሎና መገለልን በማስቀረት ኤች አይ ቪ በደማቸው መኖሩን ላላወቁ ሰዎች፣ በምርመራ ራሳቸውን እንዲያውቁ የሚያደርገውን የማስተማር የምክርና ምርመራ አገልግሎት ማጠናከር ነው።ይህ ፕሮግራም አንዱ የትኩረት አቅጣጫ ነው።
በመሆኑም ጽንሰ ሃሳቡን በጥልቀት በመረዳት ኤች አይ ቪ በደማቸው የሚገኙ ወገኖች መድሃኒታቸውን በሀኪም ትዕዛዝ መሰረት በትክክል መውሰድ በዚህ ፕሮግራም ተጠቃሚ መሆን እንዲችሉ የጤና ባለሙያዎች እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት እና አጋር ድርጅቶች፣ የህብረተሰብ የላቀ ተሳትፎን በማቀናጀት የሚሠራበት አሠራር ነው፡፡
የዛሬ 18 ዓመት ገደማ እ.ኤ.አ 2003 የፀረ ኤች አይ ቪ/ኤድስ መድሃኒት በሀገራችን መሰጠት ሲጀምር በሀገር አቀፍ ደረጃ 1.5 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎቻችን ኤች አይ ቪ በደማቸው ይገኝ እንደነበር የጽ/ቤቱ ዋና ኃለፊ ዶ/ር ፅጌሬዳ አውስተዋል።
የስርጭት ምጣኔውም በከተሞች 12.6 በመቶ፣ በገጠር 2.6 በመቶ እንደነበር በወቅቱ የወጡ መረጃዎች ያሳያሉ።በተከታዩ እ.ኤ.አ 2004 ዓመትም በአንድ ዓመት ብቻ 105,454 ሰዎች በዋና መዲናችን አዲስ አበባ ብቻ ሲያዙ፣ 90,000 የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ በኤድስና ተያያዥ በሽታዎች ህይወታቸው አልፏል።በወቅቱ 265,358 በላይ የሚሆኑ ኤች አይ ቪ በደማቸው ይገኝ የነበሩ ዜጎች የፀረ-ኤች አይ ቪ ህክምናው የሚያስፈልጋቸው እንደነበሩም ያሳያል፡፡
በዚህ 2004 ዓ.ም የጤና ሚኒስቴር፣ የመድሃኒት አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣንና የፌዴራል ኤች አይ ቪ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽ/ቤት በመተባበር የፀረ-ኤች አይ ቪ ሀገራዊ መመሪያ በማዘጋጀት፣ ለጤና ባለሙያዎች ማሰልጠን እንደጀመረም ከፌዴራል ኤች አይ ቪ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡
በስልጠናውም በመጀመሪያ ዙር 390 ሀኪሞችን፣ ነርሶችን፣ ፋርማሲስቶችንና የላብራቶሪ ቴክኒሻኖችን በ58 የስልጠና ማዕከላት እንዲሰለጥኑ በማድረግ በዚያው 2004 ዓመት 10,400 ህሙማን ህክምናውን እንዲወስዱ ተደረገ። በዚህ መልኩ የጀመረው የኢትዮጵያ ኤች አይ ቪ መድሃኒት ህክምና 18 ዓመታትን ዘልቆ አሁን ላይ በሀገራችን በይፋ የተጀመረውን የማይታይ መጠን= የተገታ መተላለፍን (የ=የ)ፕሮግራም አስጀምሯል።
በደማቸው ኤች አይ ቪ ቫይረስ የሚገኝባቸው ወገኖች በህይወት ኖረው፣ ጤናማና አምራች እንዲሆኑ ስልጠናውም ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል።በዚያን ወቅት የተጀመረው ስልጠና በደማቸው ኤች አይ ቪ የሚገኝባቸው ወገኖች ከኤች አይቪ ነፃ የሆነ ልጅ እንዲወልዱም አስችሏል።እንደ ሰደድ እሳት ሀገር ምድሩን እያጠፋ፣ ዜጎችን በኀዘን ካባ ያለበሰው፣ በፍርሐትና ጭንቀት ህዝቡን እንዳላመሰ፣ አሁን ይህ ስልጠና ተስፋና ብሩህ ዘመን እንዲፈነጥቅ አዲስ ምዕረፍ ከፍቷል፡፡
እንደ ሀገር ያለው ስርጭትም በአሁኑ ወቅት በሁሉም የዕድሜ ክልል 62,2626፣ በላይ የሚሆኑ ዜጎች ኤች አይ ቪ ቫይረስ በደማቸው ይገኛል።በየዓመቱ 11,715 በላይ የሚሆኑ ዜጎች በኤች አይ ቪ እንደሚያዙ ይታመናል።ከ12,687 በላይ የሚጠጉ በኤድስና ተያያዥ በሽታዎች ህይወታቸውን ያጣሉ። በሌላ በኩል 500,000 የሚጠጉ ዜጎች የፀረ-ኤች አይ ቪ መድሃኒት ህክምና በመውሰድ ላይ የሚገኙ ናቸው።
በተሠራው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራም ሰፊው ማህበረሰባችን የባህሪ ለውጥ ከማምጣት በተጨማሪ እራሳቸውን ከኤች አይ ቪ ኤድስ እንዲከላከል በማድረግ ረገድ የተለያዩ አካላት የሚያበረክቱት ድርሻና ርብርብ ትልቅ ትርጉም አለው። ሆኖም ግን ቅሉ የፀረ-ኤች አይ ቪ መድሃኒትና ህክምና አሁን ለተገኘው ሀገራዊ ስኬት ጉልህ ድርሻ አለው፡፡
ዓለም በስዓታት ውስጥ ብዙ ለውጥ ታስተናግዳለች። አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችና የቴክኖሎጂ ውጤቶች ይፈጠራሉ። ትላንት ያረጅና ዛሬ አዲስ ቀን ይመጣል። ዛሬ ደግሞ አዲስ ዓለም ይሆናል። የህክምና ሳይንሱም በነዚህ ሁኔታዎች ውስጥ ማለፍ የግድ ይለዋል።ሁሉም ነገሮቻችን በሂደት ውስጥ ይለወጣሉ።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 14/2013