የኮቪድ 19 ወረርሽኝ የአገራችንና የዜጎች ስጋት መሆኑን ቀጥሏል።የጤና ሚኒስቴር ተከታታይ መረጃዎችና ማሳሰቢያዎችም የወረርሽኙን እየተስፋፋ መምጣት በሚገባ ያመለክታሉ። ከሚያዝያ 6 እስከ 8 ቀን 2013 ባሉት ሦስት ተከታታይ ቀናት ከወጡት የጤና ሚኒስቴር መረጃዎች መረዳት እንደሚቻለው፤ በአገራችን በኮቪድ ወረርሽኝ 72 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።ከ6 ሺ በላይ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል።የጽኑ ህሙማን ቁጥርም ከአንድ ሺ በላይ ዘሏል።ይህ በራሱ በሽታው በአሳሳቢ ሁኔታ እየተስፋፋ መምጣቱን ያመለክታል።
በሽታው እስከ አለፈው አርብ ድረስ ከ3ሺ300 በላይ ዜጎችን ሕይወት ነጥቋል።በአሁኑ ወቅትም ከ57 ሺ 590 በላይ ሰዎች ቫይረሱ ይገኝባቸዋል።
አገራችን ያሏት የመተንፈሻ መሣሪዎች ውስን እንደመሆናቸው የኮቪድ ጽኑ ህሙማን ቁጥር እየጨመረ መምጣት ችግሩን አሳሳቢ እንደሚያደርገው መገመት አይከብድም።መሣሪያዎቹ በኮቪድ ጽኑ ህሙማን የሚያዙ ከሆነ ደግሞ በሌላ ህመም ምክንያት መሣሪያው የሚያስፈልጋቸውን ዜጎች ለመርዳት የማያስችል ሁኔታ ይፈጠራል።የበሽታው እየተስፋፋ መምጣት ችግሮችን በከፍተኛ ሁኔታ እያወሳሰበ ይሄዳል።
መንግሥት የችግሩን አሳሳቢነት በሚገባ ተገንዝቦ አስቀድሞም በመከላከሉ ላይ በትኩረት ሲሰራ መቆየቱ ይታወሳል።አገራችን ህሙማንን ማከም የሚያስችል አቅም እንደሌላት ታምኖበት የሚበጀው መከላከል ብቻ መሆኑ አጽንኦት ተሰጥቶት እየተሰራበት ነው።
ኅብረተሰቡም የመንግሥትን መመሪያና ማሳሰቢያ በመከታተል ሲተገበር ቢቆይም፣ ጥረቱ በመዘናጋት ተጠልፏል።መዘናጋቱ ዋጋ እንዳያስከፍል ነበር ስጋቱ።ይህን ተከትሎም በሽታው እየተስፋፋ ነው።
መንግሥት አሁንም ወረርሽኙን ለመከላከል ለሚያስችሉ ሥራዎች በትኩረት መስራቱን ቀጥሏል።ከ430 ሺ በላይ የሚመለከታቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ክትባት ወስደዋል።ተጨማሪ ክትባት ወደ አገር ቤት ለማስገባትም እየተሰራ ነው።ሕዝቡ ርቀቱን በመጠበቅ፣ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ማስክ በአግባቡ በመጠቀም የመከላከል ሥራውን አጠናክሮ እንዲቀጥል የተለያዩ ተግባሮች እየተከናወኑ ናቸው።
ሕዝቡ መረጃዎችን እንዲያገኝ እየተደረገ ነው፤ ማሳሰቢያዎች እየተሰጡም ናቸው፤ አዳዲስ መመሪያዎች ወደ ትግበራ ገብተዋል።ሁሉም በጥሩ ጎናቸው የሚጠቀሱ ናቸው።ክትትልና ቁጥጥር ላይ ግን ብዙ ጉድለት
ታይቷል።ይህም በተማሪዎች ምረቃ፣ የስብሰባ መድረኮች፣ በሰርጎችና ለቅሶዎች፣ በሃይማኖት በዓላት፣ ወዘተ ላይ በግልጽ ታይቷል።በእነዚህ መድረኮች የኮቪድ መከላከል መመሪያዎችን የሚጥሱ ተግባሮች የተፈጸሙበት ሁኔታ ታይቷል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህም ኅብረተሰቡን ከአደጋው ለመታደግ በጤና ሚኒስቴር በተዘጋጀው መመሪያ ቁጥር 30 ትግበራ ላይ እየተሰራ ነው።መመሪያውን አክብረው በማይንቀሳቀሱት ላይም ቁጥጥር እየተደረገ ይገኛል።ወደ እርምጃ የተገባበት ሁኔታ ስለመኖሩም መረጃዎች ይጠቁማሉ።ይህም የተጠቀሱትን ክፍተቶች ለመሙላት ይጠቅማል።
ወረርሽኙ እየተዛመተ እንደመሆኑ ወደ እርምጃ መገባቱ ትክክልና ተገቢም ነው።ወረርሽኙ እያደረሰ ያለውን ጉዳት ለመቀልበስ የትኛውንም አማራጭ መጠቀም ይገባልና እርምጃው ተጠናክሮ መቀጠልም ይኖርበታል።
ቀደም ሲል በመከላከሉ ላይ ጥሩ ግንዛቤ ተይዞ እንደነበር ይታወቃል።ይህን ተከትሎም ነበር ወደ መደበኛ እንቅስቃሴው የተገባው።እርምጃው ለውጥ ማምጣት አስችሎ ወደነበረው ወደዚህ መስመር ይመልሳል።
በመከላከያ መንገዶቹ ተግባራዊነት ላይ ክትትል ማድረግም ተጀምሯል።በዚህም ማስክ የሚያደርጉ ሰዎች ቁጥር መጨመሩንና ያለጥንቃቄ የሚደረጉ መሰባሰቦች መቀነሳቸውንም የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ በቅርቡ አስታውቀዋል።የጥንቃቄ መንገዶችን ተላልፈው በተገኙትም ላይም የማስተማሪያ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ተናግረዋል።ይህ አንድ ለውጥ ነው።
መንግሥት ኮቪድን ለመከላከል እየተወሰደ ያለውን እርምጃ መከታተልና መቆጣጠር ውስጥ መግባቱ ለውጥ ለመምጣቱ አንድ እርምጃ ተደርጎ ይወሰዳል።አሁን ታየ የተባለው ለውጥ በራሱ አንድ እርምጃ ወደፊት እንደመሄድ ይቆጠራል።ይህን ለውጥ ማስቀጠል፣ ለውጡን ወደኋላ ሊመልሱ ከሚችሉ ተግዳሮቶች መጠበቅም ይገባል።ለእዚህም ሁሉንም ባለድርሻ አካላት አሳትፎ መስራት ያስፈልጋል።
መመሪያውን በሚጥሱ ግለሰቦች ላይ ብቻ ሳይሆን ተቋማትና የመንግሥት ኃላፊዎች ላይ ጭምር ቁጥጥርና ክትትሉ መካሄድ ይኖርበታል።ተጠያቂነት እስከ አለ ጊዜ ድረስ ለውጦች እንደሚመጡ ጥርጥር የለውም።
ይህን ለውጥ ማስቀጠል ላይ አሁንም ዋናው ባለቤት ኅብረተሰቡ ነው።ኅብረተሰቡ የመከላከል እርምጃውን ከአዩኝ አላዩኝ ማውጣት አለበት።አሁን ያለው የመከላከል ሥራ የአዩኝ አላዩኝ ነው።ለፖሊስና ሌሎች ተቆጣጣሪ አካላት ሲል አይደለም ማስክ ማድረግ ያለበት።
ለራሱ፣ ለቤተሰቡ፣ ለሥራ ባልደረቦቹ፣ ለጓደኞቹ፣ ወዘተ ሲል ነው።እነዚህን መጠበቅ ካልቻለ ሕዝቡንና አገሪቱን መጠበቅ አይችልም።ኅብረተሰቡን ራሱን ከመዘናጋት ቢያወጣ መልካም ነበር፤ አሁን የክትትልና ቁጥጥር ሥራ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።በዚህ ሥራም የተወሰነ ውጤት ታይቷልና የቁጥጥርና ክትትል ሥራውን ያለ ምንም ወጣ ገባ አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 11/2013