
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ አበባ፦ የታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት ግብጽና ሱዳን በህዳሴ ግድብ ዙሪያ እንዲከራከሩ የሚያስችል የህግ መሰረት እንደሌላቸው በወሎ ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ህግ መምህር እና ተመራማሪ መምህር ደጀን የማነ አስታወቁ።
በወሎ ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ህግ መምህር እና ተመራማሪ የሆኑት መምህር ደጀን የማነ በተለይ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳስታወቁት፤ ግብጽ እና ሱዳን በህዳሴው ግድብ ጉዳይ ዓላማቸውን ለማሳካት የሚረዳቸው ዓለም አቀፍ የህግ መሰረት ተፈልጎ አይገኝም።
የ1997ቱ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ኮንቬንሽንን መመልከት ቢቻል እንኳን ሰነዱ ዝግጁ ከሆነ በኋላ ሀገራት በዚያ ስምምነት ለመገዛት ማጽደቅ ነበረባቸው፡፡ ሰነዱ ግን በውይይት ወቅትም ስምምነት ላይ የተደረሰበት ስላልሆነ እስከ 2014 ድረስ ወደ ስራ አልገባም፡፡ ህጉ ግዳጅ እንዲሆን ቢያንስ 35 ሀገራቶች መፈረም እንደነበረባቸውም አመልክተዋል ፡፡
እ.አ.አ. 2014 ላይ ወደ ስራ ቢገባም፣ ከ11ዱ የአባይ ተፋሰስ ሀገራት አንድም ሀገር የ1997ቱን የውሃ ስምምነት አልፈረሙም፡፡ በመሆኑም የዓለም አቀፍ የውሃ ህግ የሚባል ያለቀለት ህግ የለም ብለዋል፡፡
ከተፋሰሶች ጋር በተያያዘ አንዳንዶች ልማዳዊ ዓለም አቀፍ ህግ አለ ብለው እንደሚያምኑ የተናገሩት የመምህር ደጀን ገለጻ፤ አብዛኞቹ ሀገራት ፍትሃዊና ምክንያታዊ ተጠቃሚነት የሚባለውን በመርህ ደረጃ ይቀበሉታል።የተወሰኑ ሀገራት ደግሞ ጉልህ ጉዳት ያለማድረስ የሚለውን መርህ በመርህ ደረጃ ይቀበሉታል።ሀገራቱ ምን አልባት መርሆዎቹ ላይ ስምምነት ቢደረሱ እንኳን እነዚህን መርሆዎች ይዘው ለተግባራዊነቱ ሲንቀሳቀሱ አተገባበር ላይ ሲቸገሩ እንደሚታይ ገልጸዋል።
የመርሆዎች አተገባበር የታችኞቹም ሆነ የላይኞቹን የተፋሰስ ሀገራት ላያስማማ እንደሚችል ይታወቃል የሚሉት መምህር ደጀን፤ ከዚህ መረዳት የሚቻለው ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን አሁንም የሚመራው ዓለም አቀፍ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ኮንቬንሽን የሚባሉት ሳይሆን የሉዓላዊነት ህግ ነውና ግብጽና ሱዳንን የሚደግፍ የህግ ማዕቀፍ የለም ብለዋል።
እንደ መምህሩ ከሆነ፤ ስምምነቶችን በሚያስተዳድረው የቬይና ስምምነት (veinna convention on law of treaty) አንቀጽ 34 ላይ እንደተቀመጠው የሁለት ሀገራት ስምምነት የሦስተኛ ሀገርን ጥቅም የሚጎዳ ከሆነ ሦስተኛ ወገን ተሳታፊ ባልሆነበት ሁኔታ ተፈጻሚ አይሆንም የሚል ግልጽ ድንጋጌ አለ።ስለዚህ ሦስተኛው ሀገር ባልፈረመበት ስምምነት ሊገደድ የሚችልበት የሞራልም ሆነ የህግ መሰረት የለውም።ኢትዮጵያም ባልፈረመችበት የአባይ ወንዝ ጉዳይ የታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራትን የሚደግፍ አካሄድ እንደማይኖረው ጠቁመዋል።
ሁሉንም የዓለም አቀፍ ህግ ጤናማ አድርጎ የማየት የተሳሰተ ችግር አለ የሚሉት መምህር ደጀን፤ ዓለም አቀፍ ህግ በሙሉ ጤናማ ነው ብሎ ማሰብ እንደማይገባ ተናግረዋል። በተለይም ከአፍሪካ አንጻር በጣም በጥንቃቄ መታየት ያለበት ነው።ምክንያቱም እነዚህ ህጎች የውርስ ሀጢያት ያለባቸው ናቸው።የምዕራባዊያኑን የበላይነት ለማስቀጠልና የአፍሪካ የተፈጥሮ ሀብት ለመመዝበር የተፈራረሙትን ስምምነትና የውርስ ሀጢያቱ ተቀብለን መቀጠል የለብንም ብለዋል።
መምህሩ እንዳስታወቁት፤ ኢትዮጵያን የአባይ ወንዝ ከኢትዮጵያ ተራራማ አካባቢዎች ተነስቶ ድንበሯን አቋርጦ እስኪወጣ ድረስ በዚያ ውሃ ላይ የመጠቀም መብት አላት።ግብጽ ውሃውን በበላይነት ለመጠቀም በማሰብ ዓለም አቀፍ ህጎችን ትጠቅሳለች።ዓለም አቀፍ ህጎች ግን ዋስትና አይሰጡም።የዓለም አቀፍ ህግ ቋንቋ መናገር ብዙውን ጊዜ የጉልበታሞች ፍላጎት ማስፈጸሚያ ስልት እየሆነ ነው።ግብጽና ሱዳንም የዓለም አቀፍ ህግ እያሉ ውሃውን በበላይነት ለመጠቀም የሚያነሱት መከራከሪያ ውሃ የሚያነሳ እንዳልሆነ አስታውቀዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 13 ቀን 2013 ዓ.ም