
በፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ አበባ፡- የፖለቲካ ፓርቲዎች ለቅስቀሳ የተመደበላቸውን ነጻ የአየር ሰዓት በአግባቡ እንዲጠቀሙ መገናኛ ብዙሃን ጠየቁ::
በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የምርጫ ዴስክ ሰብሳቢ አቶ ሰይድ ሙሄ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን በመደበው የአየር ሰዓት ድልድል መሰረት የፖለቲካ ፓርቲዎች በኢቢሲ ስር በሚገኙ የተለያዩ ሚዲየሞች እንዲጠቀሙ የአየር ሰዓት ቢያዝላቸውም የተመደበላቸውን የአየር ሰዓት ሙሉ በሙሉ በመጠቀም በኩል ችግሮች አሉ ::
ለአብነት ያህል ከመጋቢት 30 እስከ ሚያዝያ 8 ቀን 2013 ዓ.ም በኢቲቪ ዜና ቻናል ላይ 525 ደቂቃ ተመድቦ ጥቅም ላይ የዋለው 313 ደቂቃ ብቻ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ሬዲዮ ከተመደበው 555 ደቂቃ ፓርቲዎች የተጠቀሙት 204 ደቂቃ ብቻ መሆኑን አስታውቀዋል::
ለፓርቲዎች በመደወል በዚህ ጊዜ በዚህ ሰዓት በዚህኛው ጣቢያ ላይ የአየር ሰዓት ስላላችሁ ቀድማችሁ እንድታመጡ የሚል የማስታወስ ሥራ በስፋት እየተሰራ ነው:: ይሁን እንጂ በህግ በተቀመጠው መሰረት አስቀድሞ የቅስቀሳ መልዕክቶችን በማምጣት በኩልም ችግር መኖሩን ገልጸዋል::
ለቅስቀሳ የሚውለው አየር ሰዓት ለዚህ ሥራ ብቻ የተመደበና የህዝብ ሀብት መሆኑን ያመለከቱት አቶ ሰይድ፤ ፓርቲዎች ያላቸውን የፖሊሲ አማራጭ ለማስተዋወቅ መልዕክታቸውን በወቅቱ በማምጣት በተመደበላቸው የአየር ሰዓት በአግባቡ እንዲጠቀሙበት
ጥሪ አቅርበዋል::
በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የምርጫ ዴስክ ተወካይ አቶ አሰፋ አህመድ በበኩላቸው፤ ከመጀመሪያዎቹ ሁለት ቀናት በስተቀር አብዛኞቹ ፓርቲዎች ሰዓታቸውን በመጠቀም ላይ ናቸው:: ይሁን እንጂ የተመደበውን የአየር ሰዓት አሟጦ በመጠቀም በኩል ክፍተት አለ ብለዋል::
እስከ ሚያዝያ 8 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ 1080 ደቂቃ የሚሆን ነጻ የአየር ሰዓት ተመድቦ እንደነበር ገልጸው፤ ከዚህ ውስጥ ጥቅም ላይ የዋለው ወደ 800 ደቂቃ የሚጠጋው ብቻ መሆኑን አስታውቀዋል::
በህጉ መሰረት ፓርቲዎች ከ48 ሰዓት በፊት ለሚዲያዎች መልዕክታቸውን መስጠት እንዳለባቸው
ጠቅሰው፤ የተጠቀሰውን ጊዜ አክብሮ መልዕክቱን በማምጣት በኩል ክፍተት አለ:: ነጻ የአየር ሰዓቱ ፓርቲዎች ይመርጠናል ከሚሉት ህዝብ ጋር የሚገናኙበት ትልቁ መድረክ መሆኑን በመገንዘብ መልዕክታቸውን በወቅቱ በማምጣት የተመደበላቸውን ጊዜ በአግባቡ መጠቀም እንዳለባቸው አሳስበዋል::
የዋልታ ሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን ኮርፖሬት የዜና ዋና አዘጋጅና የምርጫ ዴስክ አስተባባሪ አቶ በኃይሉ ጌታቸው በበኩላቸው፤ምርጫ ቦርድና ብሮድካስት ባለስልጣን በደለደሉት የአየር ሰዓት መሰረት በዋልታ ሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን ኮርፖሬትም የተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲዎች የተመደበላቸውን የአየር ሰዓት እየተጠቀሙ መሆኑን አስታውቀዋል::
እስካሁን ባለው ሂደት ከአንድ ፓርቲ በስተቀር ሁሉም ፓርቲዎች በተመደበላቸው የአየር ሰዓት ቅስቀሳ ማድረጋቸውን የገለጹት አቶ በኃይሉ፤ የአየር ሰዓቱን ሙሉ በሙሉ ተጠቅመውበታል ማለት ግን አይቻልም ብለዋል::
የምርጫ ዴስክ በማቋቋምና ሰው በመመደብ ፓርቲዎችን በአግባቡ የማስተናገድ ሥራ እየተሰራ መሆኑን አመልክተው፤ ለጣቢው ከተመደቡት 11 ፓርቲዎች መካከል አንድ ፓርቲ በራሱ ችግር ምንም አይነት መልዕክት ወደ ጣቢያቸው አለማምጣቱን ገልጸዋል::
የአቅም ውስንነት ያለባቸውን የፖለቲካ ፓርቲዎች ለፖለቲካ ምህዳሩና ለዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታው መስፋት ስንል በራሳችን የተወሰነ ፕሮዳክሽንና ቴክኒካል ነገሮችን እየረዳናቸው ህጉን በጠበቀ መልኩ እያስተናገዱ መሆኑንም አስታውቀዋል::
መገናኛ ብዙሃን ብዙዎችን የምናገኝበት አማራጭ እንደመሆኑ አንድ ደቂቃም ትልቅ ዋጋ አላት ያሉት አቶ በኃይሉ፤ አንዳንድ ፓርቲዎች ሶስትና አራት ደቂቃ የሚያባክኑበት ሁኔታ ስላለ በቀሪው ጊዜ ሁሉም ፓርቲዎች የተመደበላቸውን የአየር ሰዓት በአግባቡ እንዲጠቀሙ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል::
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 12/2013