
በሞገስ ጸጋዬ
ጐንደር:-የጎርጎራን ህብረተሰብ በዘላቂነት ተጠቃሚ ለማድረግ ቱሪዝም ላይ የተመሰረተ ልማት ማካሄድ እንደሚያስፈልግ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ።
በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የስትራቴጂ ክፍል አስተባባሪ አቶ ቴዎድሮስ ደርበው እንደገለጹት፣ ጎርጎራን ወደ ቱሪዝም መዳረሻነት ለማሸጋገር የሚያስችል ሰፊ ሃብት አለ። ይህን ሀብት የህብረተሰቡን ባህልና እሴት በማይሸረሽር መልኩ መስራት ከተቻለ ዘላቂ የቱሪዝም መዳረሻ ከመሆን አልፎ ህብረተሰቡንም ተጠቃሚ ያደርጋል።
በቱሪዝም ልማት ውስጥ ዋና መሰረታዊ ጉዳይ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ መስህቦች ቢሆኑም በኢትዮጵያ በተለይ በጎርጎራ ለዚህ የሚሆን የውሃ ሀብት፣ ተራራማ ቦታዎች እና ሌሎች ማራኪ ምድራዊ አቀማመጦች፣ በርካታ ታሪካዊ መስህቦች፣ የማህበረሰቡ ባህል፣ አብያተ ክርስቲያናትና የመሳሰሉ መስህቦች ቢኖሩም ህብረተሰቡን በሚጠቅም መንገድና ጐብኚዎችን ሊያቆይ በሚችል መልኩ ማልማት ካልተቻለ መዳረሻ ቦታ ብቻውን ዋጋ አይኖረውም ብለዋል።
ጎርጎራን ትልቅ የሀብት ምንጭ ማድረግ የሚቻለው ያለውን ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ሀብቶችን ማልማት ሲቻል ነው ያሉት አቶ ቴዎድሮስ፣ በኢትዮጵያ ያለው ችግር ሀብትን ወደ ቱሪዝም መቀየር አለመቻል ነው። ያሉንን ህብቶች ማልማትና
መጠገን እንዲሁም ማስተዋወቅ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል ።
በጎርጎራ በርካታ የመስህብ አቅሞች ቢኖሩም በርካታ ችግሮችም ተለይተዋል ያሉት አቶ ሰለሞን፣ የስራ ዕድል አለመኖር፣ የትራንስፖርት አገልግሎት አለመኖር የአካባቢው መሰረታዊ ችግሮች መሆናቸውን አስታውቀዋል ችግሮች ለመፍታት በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ይሰራል ብለዋል።
ጎርጎራን የአለም አቀፍ የቱሪስቶች መዳረሻ በማድረግ በኢኮኖሚ የነቃች እንድትሆን የአግሮ ኢንዱስትሪዎችን፣ የአነስተኛና ጥቃቅን ስራዎች ማስፋፋት፣ የስራ እድል መፈጠርና የአካባቢ ማህበረሰብ ራሱን በኢኮኖሚ እንዲችል ማድረግ እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል።
ሆቴሎችን ሪዞርቶችን፣ አማራጭ ያለው የትራንስፖርት አገልግሎት በማዘጋጀት ጎርጎራን ምቹ፣ ተስማሚና ዘመናዊ ቱሪስቶችን የምታጓጓ መዳረሻ ማድረግ ያስፈልጋል። ከዚህ በተጨማሪም ዘመናዊ የጀልባ አገልግሎት፣ የጥናትና ምርምር ቦታዎችን ማዘጋጅትና ገዳማትን ለጉብኝት ዝግጁ እንዲሆኑ በማድረግ የፋሲል ቤተ መንግስትና የሞሶሎኒን ሃውልት የቱሪስቶች መዳረሻ እንዲሆኑ በማስቻል ጎርጎራን ማሳደግና ምቹ ማድረግ ይቻላል ብለዋል።
ኢኮ ቱሪዝም ጠቀሜታና ጉዳት ያለው ነው ያሉት አስተባባሪው፤ ጉዳቱ በአግባብ ካልተያዘ በአካባቢው ባህል ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ስለሚኖረው ይህንን ታሳቢ ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 12/2013