
በጌትነት ተስፋማርያም
አዲስ አበባ፦ የህዳሴ ግድቡን በሚመለከት ከዚህ ቀደም በግብጽ ተይዞ የነበረው ገታራ አቋም አሁን ላይ የተለሳለሰ በሚመስል መልኩ እየቀረበ የሚገኘው የግድብ ውሃ ሙሌት እንደማይቀር በመረዳታቸው እንደሆነ የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ አስታወቁ ። ግብጽ በግድቡ ጉዳይ የተለሳለሰ አቋም ስላሳየች በኢትዮጵያ በኩል ትጥቅ ማላላት እንደማያስፈልግ አመለከቱ።
አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ የግብጽ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚ ሽኩሪያ ለሀገራቸው ፓርላማ ቀርበው ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌቱ አይጎዳንም ማለታቸው ግብጾች የህዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌት ሂደት እንደማይቀር መረዳታቸውን ያሳያል።
<<የህዳሴው ግድብ ግንባታ መሬት ላይ የወረደ እውነታ ነው>> ያሉት አምባሳደር ዲና፤ የግብጽ ባለሥልጣናት የግድቡ ውሃ ሙሌት በምንም አይነት መልኩ እንደማይቀር ልቦናቸው ያውቀዋል። ውሃ ሙሌቱ እንደማይጎዳቸው ቢያውቁም እንኳን መቀበል ስላልፈለጉ ተቃራኒውን ለህዝባቸው ሲያስረዱ መቆየታቸውን አመልክተዋል።
ያንኑ መረጃ ሲቀበል የነበረው ህዝባቸው ደግሞ ሁለተኛ ዙር ውሃ ሙሌቱን ኢትዮጵያ ስታከናውን እንዳያኮርፍባቸው በማሰብ አሁን ላይ የተለሳለሰ አቋም በመያዝ የማረጋጋት ስራ እየሰሩ ስለመሆናቸው ፍንጭ ሰጭ እንደሆነ ገልጸዋል።
እንደ አምባሳደር ዲና ገለጻ፤ ግብጾች በግድቡ ጉዳይ ህዝባቸውን በህይወታችሁ ላይ የመጣ መጥፎ ግንባታ ነው በማለት አስበርግገውት እና ፍርሃት ውስጥ ከተውት ነበር። ረጅምና አሰቃቂ የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ በግድቡ ጉዳይ ነዝተው ነበር መልሰው የተደናገጠውን ህዝባቸውን ለማረጋጋት ውሃ ሙሌቱ እንደማይጎዳ በመናገር የተለሳለሰ አቋም እያሳዩ ነው። በህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት የተነሳ የውሃ ጉድለት እንኳን ቢከሰት ጉድለቱን የምንሞላበት አማራጭ ዝግጅት አድርገናል ማለታቸው የህዝቡን ይሁንታ ለማግኘት አስበውም ማድረጋቸውን ያሳያል ያሉት አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ፤ ያም ሆነ ይህ ኢትዮጵያ የውሃ ሙሌቱን በተያዘለት ጊዜ እንደምታከናውን ተረድተዋል፣ ለዚህም ለዘብ ያለ አቋም እንዲይዙ ተገደዋል ብለዋል ።
ሱዳንም ተለዋዋጭ አቋም በመያዝ እና የግብጽን አጀንዳ በመከተል የውሃ ሙሌቱ እንደሚጎዳት ስታሳውቅ መቆየቷ ያስታወቀት አምባሳደር ዲና ፣ ግብጾች በግድቡ ጉዳይ የተለሳለሰ አቋም መያዛቸው
በነሱም ላይ ተጽእኖ ማሳደሩ እንደማይቀር አስታውቀዋል። ግብጽ በህዳሴው ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ላይ ለህዝቧ ባስተላለፈችው መልዕክት ስለተለሳለሰች ኢትዮጵያ ውስጥ ትጥቅ ማላላት እንደማያስፈልግ ጠቁመዋል።
ግብጽ የተለሳለሰ አቋም ብታሳይም አሁንም በኢትዮጵያ እና ግድቡ ላይ የሚያከናውኑት ሸር እና ደባ ሊቀጥል ይችላልና የተባለውን ብቻ መስማት አያስፈልግም የሚል ሃሳብ የሚያነሱ ሰዎች መኖራቸውን የተናገሩት አምባሳደር ዲና ፣ይህ ማሳሰቢያ እውነታነት ሊኖረው እንደሚችል ማሰብ እንደሚገባ ገልጸዋል። ማሳሰቢያ አዘል ሃሳቡ ሊናቅ የሚገባው ጉዳይ እንዳልሆነም አስታውቀዋል።
<<በእኛ በኵል ያለው ነገር ያለመዘናጋት እና ሁሉን ነገር በንቃት የመከታተል ስራ ያስፈልጋል። ዋናው አላማችን የግድቡን ውሃ መሙላት እና ግንባታውን መጨረስ ነውና ስራችንን አጠናክረን መቀጠል ይገባል።በሌላ በኩል ከውጭ የሚመጡ ተጽእኖዎችን እንደተለመደው ሁሉ በዲፕሎማቲክ፣ በፖለቲካ እና በሌሎች አግባቦች መከላከል ላይ ማተኮር ያስፈልጋል>> ብለዋል።
ግብጾች የእራሳቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ ከተገኘ በሚል ድርድር ላይ ጠንከር ብሎ የመቅረብ ሁኔታ አለ። በተቃራኒው ደግሞ የውስጥ ጉዳያቸውን ለማረጋጋት የተለየ መልዕክት ያለው ሃሳብ ይዘው ለህዝባቸው ይቀርባሉ። ይህ የተለመደ አሰራር እና የተለያዩ መንግስታት የሚጠቀሙበት ጥቅምን የማስከበር ሂደት መሆኑን አመልክተዋል ። በኢትዮጵያ በኩል በግንባታውም ሆነ በዲፕሎማሲው እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ሲከናወኑ የነበሩ ስራዎችን በተደራጀ እና በተጠናከረ መልኩ እንዲቀጥሉ ማድረግ እንደሚገባ አስታውቀዋል ።
የግብጹ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚ ሽኩሪ ሰሞኑን ለሀገሪቱ ፓርላማ የአፍሪካ ጉዳዮች ኮሚቴ በሰጡት ማብራሪያ ፣የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውኃ ሙሌት ግብጽን አይጎዳትም ማለታቸው የሚታወስ ነው።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 12/2013