በአዲስ አበባ ከተማ አራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 እሪ በከንቱ በተባለው ስፍራ በላስቲክ መጠለያ ይኖሩ የነበሩና ቦታው ለልማት ሲፈለግ እንዲለቁ የተደረጉ ግለሰቦች ያነሱትን ቅሬታና አቤቱታ አዳምጦ መልስ መስጠቱን ክፍለ ከተማው አስታወቀ፡፡
የክፍለ ከተማው ም/ዋና ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ አበባ እሸቴ ጉዳዩን አስመልክተው ዛሬ ከሰዐት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በቦታው ይኖሩ የነበሩና መመሪያው በሚፈቅደው መሰረት ወደ ሌላ መጠለያ እንዲዛወሩ የተደረጉ ግለሰቦች መኖራቸውን ጠቅሰው ህጉ የማይፈቅድላቸው የተወሰኑ ተከራዮች በገዛ ፈቃዳቸው ቦታውን መልቀቃቸውን ተናግረዋል፡፡
እንደ ወ/ሮ አበባ ገለፃ 117 ገደማ የሚሆኑት ግን መመሪያው ስለማይፈቅድ ቦታውን እንዲለቁ ተነግሯቸው ነበር፤ ነገር ግን መሄጃ ስለሌለንና አቅማችንም ስለማይፈቅድ መንግስት ይደግፈን በሚል በተደጋጋሚ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
ቅሬታቸውን በመመርመር 117 ወገኖች በቦሌ ክፍለ ከተማ ቦሌ ቡልቡላ በመገንባት ላይ ባለው የአራዳ ክፍለ ከተማ የድሀ ድሀ መጠለያ ፕሮጀክት ካለፈው አርብ ጀምሮ መግባታቸውን ወ/ሮ አበባ ተናግረዋል፡፡
እነዚህ ወገኖች መመሪያ ባይፈቅድላቸውም ያለባቸውን ችግር ክፍለ ከተማው ከከተማ አስተዳድሩ ጋር በመነጋገር በሰፊው ከተወያየ በኋላ በመጠለያው እንዲስተናገዱ ተደርጓል ተብሏል፡፡
የተገነቡት ቤቶች መሰረተ ልማት እስኪሟላላቸው ድረስ በትዕግስት እንዲጠብቁ ለተነሺዎቹ ቢነገራቸውም ካለባቸው ችግር አንፃር ከነጉድለቱም ቢሆን እንገባበታለን በሚል ጥያቄ በማቅረባቸው ተስተናግደዋል፤ አሁን ክፍለ ከተማው መሰረተ ልማቶችን የማሟላት ስራ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡
ቤቶቹ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቀው በኪራይ መልክ ለእነዚህ ግለሰቦች ከተላለፉ በኋላ በቦሌ ክፍለ ከተማ ስር እንደሚተዳደሩ በመግለጫው የተነገረ ሲሆን የኪራይ መጠንን በተመለከተም ሁለቱ ክፍለ ከተሞች በመመካከር የሚወስኑት ይሆናል ተብሏል፡፡
በቦታው ላይ መስፋፋት በማድረግና ከሌሎች አካባቢዎች በመምጣት የይገባኛል ጥያቄ እያቀረቡ ያሉ ግለሰቦች መኖራቸውን የተናገሩት ወ/ሮ አበባ ይህንን መሰሉን ህገወጥ ድርጊት ለመከላከል ህብረተሰቡ እንዲተባበር ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በድልነሳ ምንውየለት