ኃይለማርያም ወንድሙ
የኢትዮጵያ ወንዞች ከአገር ውስጥ ወደ ጎረቤት አገሮች የሚፈሱ ናቸው፤ ከጎረቤት አገሮች ወደ አገራችን የሚፈስ ወንዝ የለም፤ ጥቁር አባይ በአገራችን የሚገኙ 19 ገባር ወንዞችን ውኃ በማጠራቀም ወደ ሱዳን ካርቱም ካለው ነጭ አባይ ጋር ተቀላቅሎ ወደ ግብፅ የሚፈስ ነው።ከኢትዮጵያ የሚመነጨው አባይ 86 በመቶው ድርሻ ይሸፍናል።የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ግንባታ ለአገራችን ዜጎች ብሔራዊ መግባባት በመጫር የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትንና የትብብር መድረክ የፈጠረ ነው።
የዛሬ 10 ዓመት በመጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም በቤኒሻንጉል ክልል ጉባ ወረዳ አካባቢ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የታላቁ ህዳሴ ግድብ የመሠረት ድንጋዩ ሲጣል 80 ቢሊዮን ብር እንደሚፈጅና 5ሺ200 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት እንዲችል ታስቦ ነበር፤ በግድቡ ሱዳንና ግብፅም ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተገልፆ ነበር።
ግድቡ ለትራንስፖርት፣ ለቱሪዝም እና ለዓሣ ልማት ይረዳል፤ በዚህም ከ10 ቶን በላይ ዓሣ ማምረት ይቻላል። በግድቡ በሚፈጠረው ሐይቅ ከ40 በላይ ደሴቶች እንደሚኖሩት ሰነዶች ያስረዳሉ። ግድቡ ሲጠናቀቅ ውሃ የሚተኛበት ሰው ሠራሽ ሐይቅ ርዝመቱ 246 ኪ.ሜ ይሆናል።
የኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ ምሁራንን ጨምሮ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ገለልተኛ የዘርፉ ምሁራን ያካተተ አጥኚ ቡድን ተቋቁሞ ለረዥም ጊዜ የወሰደ ጥናት ተደርጓል። በወቅቱ የግብፅ አጥኚዎች «ግድቡ ተፅዕኖ እንዳያሳድር ስፋትም ሆነ ቁመቱ መለወጥ አለበት» ያሉ ሲሆን፤ የግብፅ ፕሬዚዳንት የነበሩት ሙርሲ በኤክስፐርቶች የተደረገውን ጥናት በግብፅ ላይ የሚያደርሰውን ተፅዕኖ ለመገምገም በቂ አይደለም በሚል አጣጥለው ነበር።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ በግብፅ የአባይ ወንዝ ተጠቃሚነት ላይ የሚያደርሰው አንዳች ጉዳት አለመኖሩን የኢትዮጵያ መንግሥት በተደጋጋሚ የገለጸው ዕውነታ ነው። ተከዜ ሲገነባ ሱዳን ደለል ለመጥረግ የምታወጣውን 50 ሚሊዮን ዶላር ገንዘብ ማዳን ችላለች። አባይ ግድቡ ሲጠናቀቅ ደግሞ ከ20 እጥፍ በላይ ወጪዎቿን እንደሚቀንስላት የዘርፉ ምሁራን ያስረዳሉ። ግብፅ የላይኛዎቹን ተፋሰስ ሀገሮች ሁሉ ጠቅልላ ከኢትዮጵያ ጋር አለቃ መስላ ለመከራከር ስትጥር ኖራለች። በ1929 እና በ1959 በቅኝ ገዢዎች የተካሄዱት ስምምነቶች የግብፅን ተጠቃሚነት የሚያስጠብቁ ነበሩ።
ግብፆች ቢጮሁም ኢትዮጵያውያን ግድባቸውን መገንባት ቀጥለዋል፤ «ውሾቹ ይጮኻሉ፣ ግመሎቹ ግን ጉዟቸውን ቀጥለዋል» እንደሚባለው ማለት ነው፤ የታላቁ ህዳሴ ግድብ መሠረት ከተጣለ ጀምሮ የተወሰኑ መሰናክሎች ቢኖሩም ዕድገት እያሳየ ለፍፃሜ እየተቃረበ ነው፤ እነ ሜቴክ የዘረፉት ምትክ የሌለሽ ገንዘብ፣ በየቦታው የምናያቸው ግጭቶች፤ ከወያኔ ጋር የተደረገው ግጭት፣ የሱዳን ድንበር ወረራ እና ዝርፊያ እንዲሁም ባለፈው ዓመት የተነሳው እና ዓለም አቀፍ ስጋት የሆነው የኮሮና ወረርሽኝ ሁሉ ግድቡን ለማጣደፍ ለሚደረገው ያልፈጠሩት መሰናክል አልነበረም። በየዓመቱ የነበረው የግድቡ ግንባታ አፈፃፀም እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
1ኛ ዓመቱ ሲከበር ህዳሴ ግንባታው 13 በመቶ
2ኛ ዓመቱ ሲከበር ህዳሴ ግንባታው 24 በመቶ
3ኛ ዓመቱ ሲከበር ግንባታው 31 በመቶ ሲደርስ በወቅቱ በ2005 ዓ.ም የህዳሴ ግድብ ግንባታ መሠረት የተጣለበት ቀን በጉባ ወረዳ ሲከበር 400 ኪሎ ሜትር ወደ በለስ የሚዘረጋ መስመር ግንባታ መጠናቀቁ እና ከዚህ በተጨማሪም የኤሌክትሪክ ኃይል በቋሚነት ለማስተላለፍ 619 ኪ.ሜ ባለ 500 ኪሎ ቮልት የኤሌክትሪክ ተሸካሚ መስመር እየተገነባ መሆኑን በወቅቱ የወጣው አዲስ ዘመን ያስረዳል። በዚሁ ዓመት ግንቦት 20 ቀን የአባይ ውሃ አቅጣጫ የማስቀየር ሥራ ተሠራ።
4ኛ ዓመቱ ሲከበር ግንባታው 42 በመቶ
5ኛ ዓመቱ ሲከበር ግንባታው 50 በመቶ
6ኛ ዓመቱ ሲከበር ህዳሴ ግንባታው 59 በመቶ በላይ ደርሶ ነበር።
7ኛ ዓመቱ ሲከበር ህዳሴ ግንባታው 64 በመቶ በላይ ደርሶ ነበር፤ በዚሁ ዓመት (በ2010) ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅሙ ከ6ሺ450 ሜጋ ዋት ከፍ እንዲል ተደረገ።
8ኛ ዓመቱ ሲከበር (2011 ዓ.ም) ግንባታው ከ81 በመቶ በላይ ደርሶ የነበረ ሲሆን በዚህ ወቅት ከሜቴክ ውጪ የተከናወኑ የግድቡ ሥራዎች በፍጥነት እየተጠናቀቁ እንደነበር እና ከነዚህም መካከል የኮርቻ ግድብ ከ94 በመቶ በላይ የጎርፍ ማስተንፈሻ (ስፒል ዌይ) ሲቪል ሥራ 99 በመቶ ደርሶ ነበር።
በ9ኛ ዓመቱ ወቅት ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ በክረምቱ ወራት የግድቡ የውሃ ሙሌት ሥራ ተከናወነ፤
በአሁኑ ወቅት ደግሞ አጠቃላይ የግድቡ ግንባታ አፈፃፀም 79 በመቶ መድረሱን መረጃዎች ይጠቁማሉ። በዚህም መሠረት የኮርቻ ግድቡ 99 በመቶ፣ የጎርፍ ማስተንፈሻው ወይም ጎርፍ መከላከያ ግንባታ ደግሞ 97 በመቶ ደርሷል።የኃይል ማመንጫዎች ግንባታ 84 በመቶ፣ አጠቃላይ የሲቪል ሥራው ዛሬ ላይ 91.4 በመቶ ተጠናቋል፤ የኤሌክትሮ ሜካኒካልና የብረታ ብረት ሥራዎች 54 በመቶ ደርሷል።
በሌላም በኩል ግድቡ በኢትዮጵያውያን ሀብት የሚገነባ እንደመሆኑ ከዜጎች ለግድቡ ግንባታ ከ2003 ዓ.ም እስከ መጋቢት/2013 ከ15 ቢሊዮን 163 ሚሊዮን 833 ሺ,824 ብር ተስብስቧል።በዚህም መሠረት ከሀገር ውስጥ ቦንድ ግዢና ልገሳ 13,762,030,021.64 ብር፣ ከዲያስፖራ ቦንድና ልገሳ 1,068,349,251.54 ብር፣ ከልዩ ልዩ ገቢዎች ደግሞ 333,454,551.80 ብር ተገኝቷል።
በ2005 ዓ.ም ለአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ አዲስ አበባ መጥተው የነበሩት የግብፁ ፕሬዚዳንት መሐመድ ሙርሲ «የህዳሴውን ግድብ ግብፅ ትደግ ፋለች፤ ለመተባበርም ዝግጁ ነኝ» ብለው ነበር። ነገር ግን ይህን በተናገሩበት ምላሳቸው ሀገራቸው ሲገቡ አንዲት ጠብታ ውሃ በደም ትመነዘራለች የሚል ንግግር አደረጉ።
ኢትዮጵያ ለሰኮንድም ቢሆን የግድቡን ግንባታ አታቋርጥም የሚል ዓላማ ይዛ ግድቡን እያጣደፈችው ትገኛለች።ግድቡን እየገነባች ያለው ዓለም አቀፍ ሕጎችንና ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ሕግ በመከተል ነው። ዘንድሮም ሁለተኛው የግድቡ ውሃ ሙሌት በክረምት ወራት ይከናወናል ተብሎ ይጠበቃል። በአንድ ወቅት ጠ/ሚ አብይ እንደተናገሩት፣ ስግብግብ ብንሆን ኖሮ በበጋ ወራትም ግድቡን መሙላት እንችል ነበር። አገራችን ክረምትን ተንተርሳ የውሃ ሙሌት ሥራ የምታከናውነው በበጋ ወራት ወንዞች ስለሚጎድሉ ግብፅንና ሱዳን እንዳይቸገሩ በማሰብ ነው።
ግብፅ አገራችን የአባይን ውሃ እንዳትጠቀም እና እንዳትነካ ስታስፈራራ ቆይታለች፤ አገራችን እየፈሩ የሚያስፈራሩትን አትፈራም፤ የሌሎች አገሮችን መብትና ሉዓላዊነት አንዳፈርም ማንም ኃያል ነኝ የሚል አገር ቢያስፈራራትና ቢዳፈራት ታዋርደዋለች።ምንም ብቀጥን ጠጅ ነኝ እንደሚለው የአገራችን ብሂል ድሆች ብንሆንም ክብራችንን የሚዳፈር እንጥለዋለን።
በህዳሴ ግድብን የውሃ ሙሌትና አለቃቀቅ ላይ ባለፉት ስምንት ዓመታት ከስምምነት ሊደረስባቸው በሚችሉ ጊዜያት ሁሉ፣ የግብፅ ተደራዳሪዎች በተጠናና ስልታዊ በሆነ መልኩ ጥቅማቸውን በሚያስጠብቅ መንገድ ለመደራደር ሲጥሩ ቆይተዋል። ኢትዮጵያ ግን ሁልጊዜም የነበራትና ያላት አቋም ውሃውን ፍትሐዊ በሆነ መልኩ እንጠቀም የሚል ነው።
ኢትዮጵያ የዜጎቿን 50 በመቶ ኤሌክትሪክ ማዳረስ አልቻለችም። የህዳሴ ግድብ የአገራችንን የኤሌክትሪክ እጥረት ቀርፎና አዳርሶ ለጎረቤት አገራትም ጭምር የሚተርፍ በረከትና የገቢ ምንጭ የሚሆን ነው። ከዓመት በፊት የአረብ ሊግ ባካሄደው ስብሰባ ከግብፅ ጎን ተሰልፈው ኢትዮጵያን ለማውገዝ ቢሞክሩም በስብሰባው ላይ የነበረችው ሱዳን ግን ተቃውማለች፤ ህዳሴ ሲጠናቀቅ የቅርብ ተጠቃሚ የምትሆንበት መንገድ ስላወቀች ነው። አሁን ላይ ደግሞ ከግብፅ ተለጥፋለች፤ ወደ ድንበር አካባቢም ሠራዊት ልካ ወረራ አካሂዳ ሕዝብ አፈናቅላለች። በህዳሴው ግድብ ሱዳን ተጠቃሚ እንደምትሆን ማንም ተርታ ሰው የሚያቀው ሀቅ ነው፤ አሁን ላይ መንግሥታቸው እየወሰደ ያለው አቋም ግን ዜጎቻቸውን የሚጎዳ መሆኑን ሊገነዘቡ ይገባል። ግድቡ በሱዳን አቅራቢያ መገንባቱ ዜጎቻቸው ኤሌክትሪክ ተጠቃሚ እንዲሆን የሚያግዝ ነው።
ግብፅ የተለያዩ ዲፕሎማሲ ጫናዎችን በማድረግ አባይ እንዳይገደብ ስትጥር ቆይታለች፤ ግድቡ ሲገነባ ደግሞ የማመንጨት አቅሙ ከ6ሺ ወደ 1ሺ400 ሜጋ ዋት እንዲቀንስ የግድቡ ርዝመትም ከ145 ሜትር ወደ 90 ሜትር ዝቅ እንዲል ጠይቃ ነበር።በግል ይሄ አንድ ድል ነው። በድርድሮቹ አዳዲስ ሐሳቦችን ይዛ የምትመጣው ግብፅ፣ በስተመጨረሻ ከህዳሴ ግድቡ የሚለቀቀውን ውኃ ከ40 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ እንዳያንስ፣ በግብፅ የሚገኘው ትልቁ የአስዋን ግድብ የውኃ መጠን ከባህር ወለል በታች 165 ሜትር ከወረደ በአፋጣኝ ውኃ ከህዳሴ ግድቡ እንዲለቀቅላት፣ የህዳሴ ግድብ ከ12 እስከ 20 ዓመታት ባላነሰ ጊዜያት እንዲሞላ፣ እንዲሁም የግድቡ ሙሌትና የውኃ አለቃቀቅ በየዓመቱ በሚኖረው የድርቅና የአየር ንብረት ሁኔታ ላይ የተመረኮዘ እንዲሆን የሚሉ ነጥቦችን አንስታለች።
ሀገራችን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ባለፈው ዓመት የመጀመሪያውን ሙሌት ማካሄዷ በራሱ ታሪካዊ ድል ነው። የውጪ ርዳታ ብድር እየጠበቁ እጃቸውን አጣምረው ለተቀመጡ የአፍሪካ ሀገሮች ምሳሌ መሆን የምንችልበት ድህነትን የምንዋጋበት ልማትንና ብልፅግናን የምናስፋፋበት ሌላ የአድዋ ድል ተደርጎ የሚቆጠርበት ይሆናል፡፡
ግብፅ ለዘመናት በአባይ ወንዝ ላይ ያላት አመለካከት እኔ ብቻ ልጠቀም የሚል ነው። ይህ ደግሞ የሌላ ሰው ዕቃ ይዘው አለቅም የኔነው ብለው እንደሚያለቅሱ ባልበሰሉ ሕፃናት ያለ አመለካከት ነው ማለት ይቻላል።
የኢትዮጵያን መንግሥትና ሕዝብ ሊወጋ የሚችል አካል ሲፈጠር መሣሪያ ገንዘብ እና ሥልጠና በማመቻቸት ግብፆች ተባባሪዎች ናቸው። ይኸውም ኢትዮጵያውያን እርስ በእርስ ሲጋጩ አባይን ያለ ስጋት ለመጠቀም ያስችለናል በሚል እሳቤ ነው።
ደርግ ሥልጣን ሲይዝና የእርስ በእርስ ግጭትና ጦርነት በሰሜንና በምዕራብ አካባቢዎች ሲወጠር ኢትዮጵያን ለማዳከም ወሳኝ ጊዜ ተገኘ በሚል የሶማሊያውን ዚያድ ባሬን ጦር በመርዳትና በማስታጠቅ የውክልና ጦርነት አካሂደዋል። በዚሁ ወቅት አባይን ከነካችሁ ወዮላችሁ ትል እንደነበረ ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ በአንድ ወቅት ገልፀዋል። በወቅቱ ግብፅ በሱዳን 30ሺ ጦር አስፍራ ነበር። የተፈራውን የሶማሊያ ጦርነት ወታደራዊው ደርግ በአጭር ጊዜ ሥልጠና ድምጥማጡን አጥፍቶ ግብፅና ሌሎች የዚያድ ባሬ ጦር አጋሮች ሀፍረትን ተከናንበዋል።
ሀገራችን ከላይ የጠቀስናቸው የተወሰኑ ግጭቶች መነሻቸው ምንም ይሁን ምንም በውክልና የተከፈተ ግጭት ነበር፤ ይህም ኢትዮጵያ ከተረጋጋች፣ አባይን ትገድባለች በሚል ፍራቻ ነው። በውክልና ጦርነት ሲከፍቱብን የነበሩት ወዳጆቻችን አንጀታቸውን ቆርጠው ይቀመጣሉ፤ የኢትዮጵያንም በወንዙ የመጠቀም መብት ሳይወዱ በግድ ያረጋግጣሉ። አገራችን ዘላቂ ሰላም የምታገኘው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ተገድቦ ኢትዮጵያ ለዘመናት ሳትጠቀምበት የነበረችውን አባይን ከዘፈን ባለፈ የሀገር አድባር፣ የሀገር ሲሳይ ስታደርገው ነው። ግድቡን ከግቡ ለማድረስ ዜጎች ቦንድ በመግዛትም ሆነ በመርዳት ዜግነታዊ ግዴታቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል፤ በዚህም ዘለቄታዊ ብልፅግና ማምጣት እንችላለን፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 24/2013