
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ በዓለም ላይ ከፍተኛ ነዳጅ ከሚጠቀሙ ሀገሮች መካከል አሜሪካ፣ ቻይና፣ ህንድ፣ ጃፓን በቀዳሚነት ሲጠቀሱ፤ ኢትዮጵያ ደግሞ 100ኛ ነዳጅ ተጠቃሚ ሀገር ናት። ሆኖም ኢትዮጵያ ወደብ አልባ ሀገር ከመሆኗ ጋር በተያያዘ ለነዳጅ ግዥና ማጓጓዝ ከፍተኛ ወጪ የምታወጣ ሀገር ናት። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የአዲስ አበባ ጎዳናዎች ነዳጅ ለመሙላት በሚሰለፉ ተሽከርካሪዎች ሲጨናነቁ ይስተዋላል። ህገወጥ የቤንዚን ንግድ ስለመጧጧፉም ይነገራል። ለመፍትሄም ደግሞ ዘርፍ ብዙ ሥራዎች እየተከናወኑ ስለመሆኑ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ሲናገሩ ይደመጣል። በእነዚህና መሰል ጉዳዮች ዙሪያ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የዋና ሥራ አስፈፃሚ የኦፕሬሽን ዘርፍ አማካሪ የሆኑት አቶ ደመላሽ ዓለሙ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር ያደረጉትን ቆይታ እነሆ።
አዲስ ዘመን፡– በሀገሪቱ ያለው የነዳጅ አቅርቦት ሠንሰለት ምን ይመስላል?
አቶ ደመላሽ፡– የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የመንግስት የልማት ደርጅት ሲሆን ሀገሪቱ የምትፈልገውን የተጣራ የነዳጅ ምርቶች በብቸኝነት የሚያስመጣ ነው። ድርጅቱ የሚያስመጣውን ደግሞ ነዳጅ አከፋፋዮች ይረከባሉ። እነርሱ ደግሞ ከቀጥታ ተጠቃሚዎች፣ ትራንስፖርትሮች፣ ማደያ ባለቤቶች ያቀርባሉ። በአቅርቦቱ ሠንሰለት እኛ በስፋት እናስመጣለን። እነርሱ ከወደብ ላይ ይወስዳሉ። የበፊቶቹ ማደያዎች የነዳጅ አከፋፋይ ኩባንያዎች ንብረት ነበሩ። ከዚህ በፊት የነበረው መስፈርት የላላ ሲሆን አሁን የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች እየገቡበት ነው። ነዳጅ አከፋፋይ እና ማደያዎችም በሀገር ባለሃብቶች እየተዘወሩ ነው። አሁን ያሉት ኩባንያዎች ነዳጅ አከፋፋይ እና የማደያ ባለቤቶችም ናቸው፤ ህጉ ስለሚፈቅድላቸው። በአሁኑ ወቅትም የሀገር ውስጥ ኩባንያዎች 34 ደርሰዋል። በአሁኑ ወቅት በመላ ሀገሪቱ 950 የሚሆኑ ማደያዎችም እንዳሉ ይገመታል።
አዲስ ዘመን፡– የሀገሪቱ የነዳጅ ፍጆታ አሃዝ ምን ያመላክታል?
አቶ ደመላሽ፡– በኢትዮጵያ አምስት የነዳጅ ዓይነት ጥቅም ላይ ይውላል። ቤንዚን፣ የአውሮፕላን ነዳጅ፣ ነጭ ናፍታ፣ ለኢንዱስትሪ የሚውሉት ደግሞ ቀላል ጥቁር ናፍታ እና ከባድ ጥቁር ናፍታ ሲሆኑ እነዚህን በሙሉ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ነው የሚያስመጣው።
ቤንዚን በተመለከተ በዚህ ዓመት ስምንት ወር ብቻ ከሃምሌ 2012 ዓ.ም እስከ የካቲት 2013 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ 428ሺ965 ሜትሪክ ቶን ገብቷል። በእርግጥ በዚህ ወቅት ውስጥ እንዲገባ የታቀደው 399ሺ261 ሜትሪክ ቶን ነበር። ይህም በተመሣሣይ ወቅት አንፃር ሰባት በመቶ ብልጫ እንዳለው ያሳያል። ባለፈው ዓመት (2012 ዓ.ም) ተመሣሣይ ወቅት አኳያ የቤንዚን አቅርቦት 16 በመቶ ብልጫ አሳይቷል።
የአውሮፕላን ነዳጅ የተመለከትን እንደሆነ ደግሞ 304ሺ445 ሜትሪክ ቶን ነዳጅ ገብቷል። እቅዱ የነበረው 446ሺ695 ሜትሪክ ቶን የነበረ ቢሆንም የኮረና ቫይረስ ስርጭት ጫና ስለፈጠረ እና በረራዎች ስለተሰረዙ አየር መንገዱ ብዙ ነዳጅ አልተጠቀመም። ካለፈው ዓመት አኳያ 508ሺ122 ሜትሪክ ቶን ነው የገባው። ከእቅድ አኳያም የተከናወነው 65 በመቶ ነው። ይህ ዘርፍ ተጎድቷል፤ እስካሁን አላገገመም። ኢትዮጵያ አየር መንገድ ካርጎ ላይ አተኩሮ ባይሰራ ይህንንም ላይጠቀም ይችል ነበር። በአጠቃላይ በዓለም ላይ ይህ ዘርፍ ተመሳሳይ ችግር ደርሶበታል።
ነጭ ናፍታ ስንመለከት ትልቅ ድርሻ አለው። በ2013 ዓ.ም ስምንት ወራት ብቻ 1 ሚሊዮን 760ሺ ሜትሪክ ቶን ታቅዶ የነበረ ሲሆን 1 ሚሊዮን668ሺ ሜትሪክ ቶን ወደ ሀገር ውስጥ ገብቷል። በዚህ ላይም የተወሰነ የኮረና ተፅዕኖ አለ። ቀላል ጥቁር ናፍታ 22ሺ603 ሜትሪክ ቶን ለማስገባት ታቅዶ ወደ ሀገር የገባው 20ሺ359 ሜትሪክ ቶን ነው። ከባድ ጥቁር ናፍታ ደግሞ 26ሺ731 ለማስገባት ታቅዶ የገባው 37ሺ802 ሜትሪክ ቶን ነው የገባው።ከጠቅላላው አቅርቦት አኳያ ሲታይ ከአምስቱ ነዳጅ ውስጥ ባለፉት ስምንት ወራት ቤንዚን 17፣ የአውሮፕላን ነዳጅ 12ነጥብ37፣ ነጭ ናፍታ 67ነጥብ8፣ ቀላል ጥቁር ናፍታ 0ነጥብ8 እና ከባድ ጥቁር ናፍታ ደግሞ 1ነጥብ 54 በመቶ ይሸፍናሉ። ባለፉት ስምንት ወራትም በአጠቃላይ ሁለት ሚሊዮን 460ሺ ሜትሪክ ቶን ነዳጅ የተገዛ ሲሆን ለዚህም 1ነጥብ079 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ተደርጓል።
አዲስ ዘመን፡– የሀገሪቷ የነዳጅ ፍጆታ እና ግዥ ምጥጥን የሚሰላው እንዴት ነው?
አቶ ደመላሽ፡– ይህ ከእቅድ ዝግጅት ይጀምራል። የዓመቱ ፍላጎት ይጠናል። ትልልቅ የነዳጅ ተጠቃሚዎች፣ ሥራ ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች፣ ወደ ሥራ የሚገቡ ፕሮጀክቶች ከግምት ውስጥ ይገባሉ። በተጨማሪም ያለፉት አራት እና አምስት ዓመታት ሁኔታዎች ይታያሉ። የአውሮፕላን ነዳጅ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ይጠየቃል፣ ቀላል እና ከባድ ጥቁር ናፍታ ፍላጎት ደግሞ ፋብሪካዎችና ኢንዱስትሪዎች ይጠየቃሉ። ሀገር ውስጥ የሚገቡ የተሽከርካሪ ብዛትም ግምት ውስጥ ይገባል። በፕላን ኮሚሽን እና ብሄራዊ ባንክ የሚያወጡት የኢኮኖሚ አመላካቾችም አሉ። በመሆኑም በእነዚህ ላይ በመመስረት ፍላጎት እና አቅርቦት የተመጣጠነ እንዲሆን ግዥ ይፈፀማል።
አዲስ ዘመን፡– ለኢትዮጵያ ሁነኛ የነዳጅ አቅራቢዎች የሚባሉት ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እነማን ናቸው?
አቶ ደመላሽ፡– አሁን ያሉት ሦስት አቅራቢዎች ናቸው። አንዱ በኢትዮጵያ እና ኩዌት መንግስት መካከል የተፈፀመ የሁለትዮሽ ስምምነት ሲሆን ስሙም ኩዌት ፔትሮልየም ኮርፖሬሽን ይሰኛል። ይህ ድርጅት ነጭ ናፍታ 50 ከመቶ የአውሮፕላን ነዳጅ ደግሞ 75 ከመቶ ያቀርባል። ትራፊክ ጉራ የሚባለው ሁለተኛው አቅራቢያችን ሲሆን በኣለም አቀፍ ጨረታ ያሸነፈ ነው። ነጭ ናፍታ 55 በመቶ የአውሮፕላን 25 ከመቶ ቤንዚን ደግሞ 100 ፐርሰንቱን ያቀርባል። ሦስተኛው ቢ- ኢነርጂ የተባለው የሳውዲ ኩባንያ ሲሆን ቀላል ጥቁር ናፍጣ እና ከባድ ጥቁር ናፍጣ ያቀርባል። እነዚህ ምርቶች የሚመጡትም ከፋርስ ባህረሰላጤ እና ከሳውድ አረቢያ ነው።
አዲስ ዘመን፡– በየትኞቹ ወደቦች ነው የምንጠቀመው፤ ከሱዳን ጋር ግጭት መፈጠሩ በቤንዚን አቅርቦት ላይ ጫና ፈጥሯል?
አቶ ደመላሽ፡– ሙሉ ለሙሉ በጅቡቲ ወደብ ነው የምንጠቀመው። ሱማሌ ላንድ የተወሰኑ ጅምሮች አሉ። ከእኛ ሀገር ፍላጎት አኳያ ከተወሰኑ አመታት በኋላ ሊታሰብ ይችላል፤ አሁን ያለው ነገር ጅቡቲ ላይ ነው። ፖርት ሱዳንም ያለው አገልግሎት የተሰራው በእነርሱ ልክ ነው። የተወሰነ ትርፍ ያላቸው ቤንዚን ላይ ነው። ሆኖም ከመጋቢት 2012 ዓ.ም ጀምሮ ከሱዳን አስገብተን አናውቅም። ማዕቀብ ስለነበረባቸው በነአስተኛ መጠን ነው የሚያስገቡት። በመሆኑም ከባለፈው ወር መጋቢት ወር ጀምሮ ቤንዚንም የምናስገባው በጅቡቲ ወደብ ነው።
አዲስ ዘመን፡– አሁን የሚገባው ነዳጅ እና ግዥ ተመጣጣኝ ከሆነ በየወቅቱ የሚፈጠሩ የነዳጅ እጥረት መነሻው ምንድን ነው?
አቶ ደመላሽ፡– ይህን ችግር እንደ ነዳጅ ዓይነት ለያይቶ ማየት ይገባል። ሁሌም ሀገራዊ የነዳጅ አቅርቦት እና ፍላጎት መረጃ ተሰብስቦና ተተንትኖ ነው የሚዘጋጀው። ይህንን ያገናዘበ በመሆኑ አቅርቦት ላይ ምንም ዓይነት ችግር የለም። ወደ ስርጭት ስንመጣ ችግር አለ። ከእነዚህም መሰረታዊ ችግር እያጋጠመን ያለው በቤንዚን ላይ ነው።
ችግሩን ወደኋላ ሄዶ ማየት ያስፈልጋል። እስከ ጥር 2009 ዓ.ም ድረስ ኬሮሲን ወይንም ‹‹ላምባ›› እና ነጭ ናፍታ ልዩነት ነበረው። ነጭ ናፍታ ዋጋው ትንሽ ከፍ ይላል። ‹‹ላምባ›› ብዙ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ይጠቀሙታል ተብሎ ስለሚታሰብ ዋጋው ይቀንስ ነበር። ግን የዋጋ ልዩነቷ ጥቅም ለማግኘት ‹‹ላምባ›› እና ነጭ ነዳጅ ይቀላቅሉ ነበር። ይህ ብዙ ተሽከርካሪ ሞተር ላይ ችግር ፈጥሮ ነበር። በዚህ ላይም ብዙ አቤቱታ ይቀርብ ነበር። ከዚያ ዋጋው እኩል እንዲሆን ተደረገ። ይህ ሲሆን ህገ ወጥ ሥራው ቀረ።
የቤንዚን ሥርጭት ደግሞ ቀስ ብሎ ወደ ጥቁር ገበያ የወጣው ከዚያ በኋላ ነው። ቤንዚን ነዳጅ ማደያ ከተረገፈ በኋላ ወደ ሌላ ቦታ በተለያየ መንገድ መውሰድ ተጀመረ። ከዚህ ወቅት ወዲህ በስፋት ተጀመረ። በተለይ ከአዲስ አበባ ራቅ ሲባል ቤንዚን ከነዳጅ ማደያ ከማግኘት ይልቅ ከህገ ወጦች ማግኘት ይቀላል። ይህ ቀስ እያለ 2013 ዓ.ም ደረስን። በየጊዜው አድማሱን እያሰፋ ነው። ለመስኖ፣ ለሞተር ሳይክል በብዛት ይጠቀማሉ። ድርጅቱ የራሱን ጥናት አድርጓል። በአብዛኛው የቤንዚን ስርጭት ከመደበኛው አሠራር እንዲወጣ የተደረገው በህገ ወጥ አሰራር ነው። አንዱ ድርጅቱ ችግሩን ለማቃለል እያንዳንዷ ነጥብ ጣቢያ መረጃ እንልካለን። ከተማ ንግድ ቢሮ እና ክልል መረጃው ይላካል።
ቤንዚን በአቅርቦት ደረጃ ቢታይ 2011 ዓ.ም በወር 57ሚሊዮን 399ሺ ሊትር በወር ይቀርብ ነበር። በ2012 ዓ.ም ደግሞ 62ሚሊዮን 829ሺ ሚሊዮን ሊትር በወር ይቀርብ ነበር። በ2013 ዓ.ም የስምንት ወራት ሲታይ ደግሞ በወር 75ሚሊዮን 342ሺ ሊትር እየቀረበ ነው። ከእቅድ አኳያም ከባለፈው ዓመት አኳያ 16 ከመቶ እድገት አለ። ግን ስርጭት ላይ ችግር በመኖሩ ህዝብ ሮሮ ያቀርባል። ለዚህም ከመደበኛ አሰራር መውጣቱ ነው። በህግ ደረጃ ከነዳጅ ማደያ ውጭ ነዳጅ መሸጥ አይቻልም። ችግሩን ለመፍታት ቁጥጥሩን ማጠናከር ያስፈልጋል። ከጁቡቲ እያመጣን ያለው 75ሚሊዮን 342ሺ ሊትር ቤንዚን የመጨረሻውን አቅም ተጠቅመን ነው። ፋስሊቲውም ከዚህ በላይ አይችልም። ቤንዚን ላይ ህገ ወጡ አሰራር ካልተስተካከለ መፍትሄ አይመጣም።
አዲስ ዘመን፡– ነዳጅ ከጅቡቲ ወደብ ተነስቶ በተገቢው ቦታ ስለመድረሱ ለመቆጣጠር የሚያስችል ሥርዓትና ቴክኖሎጂ አለ?
አቶ ደመለሽ– አጠቃላይ ከቀጠናው ሀገራት አኳያ ሲታይ ገና ብዙ ይቀረናል። አንድ ተሽከርካሪ ጭኖ ከጅቡቲ ተርሚናል እስከ መድረሻ ያለው መቆጣጠር ላይ ድክመት አለብን። ኬንያና ሱዳን እያንዳንዱ ስቶክ፣ ማደያ ያለውን ነዳጅ በዘመናዊ መቆጣጠሪያ በመጠቀም ቢሯቸው ውስጥ ሆነው ያውቃሉ። በእኛ ሀገርም እስከ ሱልልታ፣ አዋጅ መጠባበቂያ ‹‹ዲፖ›› ያለውን እዛ ያለውን ኃላፊ ሳንጠይቅ ማወቅ እንችላለን። ይህ ወደ ሌላ ቦታ አቅጣጫ እንዳይቀይር፣ ፈጣንና ወቅታዊ ምላሽ ለመስጠትና ህገወጥ አሰራር ለመቆጣጠር ያስችላል።
በእኛ ደረጃ አስገዳጅ ህጎች ያስፈልጋሉ። ሴክተሩ ትልቅ ችግር ስላበት ብሎም መንግስት ትልቅ የውጭ ምንዛሪ ሃብት መድቦ የሚንቀሳቀስበት ዘርፍ በመሆኑ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢዎች ደርጅትን ጨምሮ ኩባንያዎች፣ ማደያዎች፣ ቀጥታ ተጠቃሚዎችን የሚቆጣጠርና መስፈርት የሚያወጣ ባለስልጣን ተቋቁሟል። በቅርቡ ሥራ ጀምሯል። የሚስተዋሉ ችግሮችም በሂደት እልባት ያገኛሉ። ወደ ዘመናዊ አሰራር መግባትም ግድ ይላል።
አዲ ዘመን፡– ከወደብ ጀምሮ ነዳጅ ታሽጎ ለመምጣቱ ለማረጋገጥ የሚያስችል አሠራር አለ?
አቶ ደመላሽ፡– ከወደብ ሲመጣ ታሽጎ ነው። ግን ተረካቢው ያንን አረጋግጦ እንዲረከብ የሚያስገድደው ህግ የለም። መጠን ብቻ ለክቶ ይቀበላል። ደረቅ ጭነት ላይ ትልቅ ጭነት አለ። አሁን የተቋቋመው ባለስልጣን አንዱ ሥራው ይህ እንደሚሆን እገምታለሁ። ከእነዚህ ሁሉ ነገሮች ግን የከፋ ችግር ያለው ቤንዚን ላይ ነው። እየባሰበት ነው የመጣው። በመሰረቱ 60 ከመቶ የቤንዚን ፍላጎትና ፍጆታ ያለው አዲስ አበባ ነው። መስኖ የሚያለሙ፣ ሞተር ሳይክል እና ባጃጅ የሚያሽከረክሩትም ደግሞ ከአዲስ አበባ ወጣ ስንል ቤንዚን የሚጠቀሙ ናቸው። ግን በአግባቡ ከተጠቀሙ ችግሩን ማቃለል ይቻላል። ቁጥጥር ሲጠብቅ ችግሩ ቀለል ይላል፤ ቁጥጥሩ ሲላላ ደግሞ ሁኔታው በተቃራኒው ይሆናል። ቀደም ሲል የቤንዚን አቅርቦት ላይ እሮሮና ችግር የነበረው ድሬዳዋ ላይ ነበር። አሁን ቁጥጥሩን ስላጠናከሩ ችግሩን ማቃለል ችለዋል። ተምሳሌት የሚሆን ሥራም እየሰሩ ነው። ይህን ተሞክሮ ማስፋት ተገቢ ነው።
አዲስ ዘመን፡– ሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት በወር 75 ሚሊዮን 342ሺ ሊትር ቤንዚን ለማቅረብ ጅቡቲ ላይ ያለው ‹‹ፋሲሊቲ›› ሙሉ አቅም እየተጠቀመች ከሆነ ቀጣይ ለሚኖረው የነዳጅ መጠቀም ፍላጎት መናር ሥጋት አይፈጥርም?
አቶ ደመላሽ፡– ይህን ለማሳደግ በጅቡቲ ተርሚናል ሥራዎች እየተሰሩ ነው። ለመናገር የፈለኩት ያለውን ‹‹ፋሲሊቲ›› አሟጠን ተጠቅመን እየሰራን ነው። በድርጅታችን ጥናት የቤንዚን መሰረት ሙሉ ለሙሉ አሟጠን አቅማችንን አልተጠቀምንም። በእርግጥ የተደራጀ ጥናት ይፈልጋል። መስኖን ጨምሮ ከመደበኛው ውጭ ቤንዚን የሚጠቀሙ አሉ። ይህን በተሽከርካሪ ቁጥር ብቻ ሳይሆን ሞተር ሳይክልን ጨምሮ የሌሎችን ፍላጎት ማወቅ ይገባል። የፍላጎት መጨመር ቢኖር እንኳን አቅርቦት እና ፍላጎት ይህን ያህል የተራራቀ አይደለም። ይህን ለማረጋገጥ በየትኛውም ከተማ ስንሄድ ቤንዚን አጥቶ የቆመ ተሽከርካሪ አሊያም ባለ ሦስት እግር ባጃጅ የለም። ቤንዚኑን የሚገዙት ከሌላ አቅጣጫ እንደሆነ ያመላክታል። አሰራሩን ለማጥበቅ በአጭር ጊዜ የቁጥጥር አድማሱን ማጠናከር ነው። ይህ ከሆነ ወደ ሌላ አቅጣጫ እንዳይሄድ ያደርጋል። ነዳጅ ማደያ የሚጠቀሙት ትክክለኛ ተጠቃዎች ናቸው። ነገር ግን በጀሪካንና እና ሌሎች የሚገዙት አግባብ አይደለም። ይህን የፈጠረው ጥቁር ገበያው ነው። ገቢዎች ሚኒስቴር እንደሚቆጣጠረው ‹‹ካሽ ሪጅስተር›› ማሽን አይጠቀሙም። በቀጣይ ይህን እንዲጠቀሙ ወደዚህ እየሄድን ነው። አስገዳጅ ነገሮች ወደ ሥራ ሲገቡ ቢያንስ ብዙ ነገር ይስተካከላል።
አዲስ ዘመን፡– ቀደም ሲል የዱቤ አገልግሎት መቆም ጫና እንደፈጠረ ይነገራል። ይህን ድርጅቱ እንዴት ይመለከተዋል?
አቶ ደመላሽ፡– እኛ በቀጥታ ግንኙነት ያለን ከነዳጅ አከፋፋይ ኩባንያዎች ጋር ነው። ነዳጅ አከፋፋይ ኩባንያዎች ደግሞ ከትራንስፖርተሮች እና ከማደያዎች ተጠቃሚዎች ጋር ውል ተፈራርመው ያቀርባሉ። በአብዛኛው ነዳጅ ማደያ ከፍለው ነው ነዳጅ የሚቀርብላቸው። አሁን እጅ በእጅ ሽያጭ ሽግግር የከፍተኛ ነዳጅ ሽያጭ ላለፉት 55 ዓመታት በዱቤ ነበር። ይህ ደግሞ በገንዘብ በፍጥነት አለመሰብሰብ፣ የኩባንያዎች ቁጥር በየጊዜው መበራከትና ሌሎች ምክንያቶች ጋር ተያይዞ የድርጅቱ የቦርድ አባላት አምነውበትና ተወያይተውበት ነው። ይህ መንግስትም አምኖበት ያዘጋጀው የመውጫ መንገድ ነው። ቀድሞውኑ ነዳጅ አከፋፋዮች ከነዳጅ ማደያዎች ጋር ያላቸው ግንኙነት እጅ በእጅ ሽያጭ ነው። አሁን የተጀመረውም የቅድሚያ ክፍያ 10 በመቶ ከፍያ ነው። ሁለተኛው ምዕራፍ 25 በመቶ ይከፍላሉ። ሦስተኛው ምዕራፍ ደግሞ 50 መቶ ይከፍሉና 50 ከመቶ ዱቤ ይሆናል። በአራተኛው ምዕራፍ ወይንም መጋቢት 2014 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በክፍያ ይፈፃማል ማለት ነው። በመንግስት እቅድም በአንድ ዓመት ነው ሙሉ ለሙሉ እጅ በእጅ ሽያጭ ለመውጣት የታሰበው።
አዲስ ዘመን፡– የነዳጅ መሸጫ ዋጋ ከቦታ ቦታ መለያየት ለኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅቱ እና ማደያዎች ሥራ የቅሬታ ምንጭ አልሆነም?
አቶ ደመላሽ፡– የነዳጅ ዋጋ በየከተማው ነው የሚወሰነው። ወደ ጅቡቲ እየረቀብን ስንሄድ እየቀነሰ ወደ አዲስ አበባ ስንመጣ ደግሞ እየጨመረ ይሄዳል። ይህ ከትራንስፖርት ጋር የተያያዘ ነው። አዳማ እና አዲስ አበባም ይለያያል። አንዱ ችግር የትራንስፖርት ማጓጓዣ ታሪፍ ንግድ ሚኒስቴር ሲያወጣ ከመሸጫ ዋጋው ጋር አብሮ ነው የሚወሰነው። ግን ትራንስፖርተሮች የሚያነሱት ቅሬታ አስፋልትና ጥርጊያ መንገድ በሚል መወሰኑ አግባብ አይደለም የሚል አቋም አላቸው። ግን የመሬት አቀማመጥ ተራራ እና ሜዳ ታሳቢ ይደረግ የሚል ነው። እነዚህ ችገሮችን ታሳቢ በማድረግም አዲስ የተቋቋመው ባለስልጣን ለእነዚህ ሁሉ መፍትሄ እንደሚሰጥ ይታመናል። የመጨረሻ ተጠቃሚ የሆነው ህዝብም እንዳይጎዳ ከፍተኛ ጥንቃቄ በማድረግ እየተሰራ ነው። ወደፊት ደግሞ በቴክኖሎጂ በመታገዝ መሰራት እንዳለበት እናምናለን።
አዲስ ዘመን፡– ቀደም ሲል ‹‹ኢታኖል›› ከቤንዚል ጋር ቀላቅሎ በመሸጥ የነዳጅ እጥረት ለማቃለል ታስቦ የነበረው ፕሮጀክት አሁን የውሃ ሽታ ስለመሆኑ ይነገራል። ይህ የሆነው ከምን የተነሳ ነው?
አቶ ደመላሽ፡– ኢታኖል የስኳር ተረፈ ምርት ነው። ይህም ሲደረግ የነበረው አዲስ አበባ ላይ ብቻ ነበር። ከዚያ የሚገኘውን ነበር የሚቀላቀለው። ይቀላቀል የነበረው አምስት በመቶ ነበር። መሆን የነበረበት 10 ከመቶ ኢታኖል መቀላቀል ነበር። የተወሰነ ጊዜ ተሰርቶበት ነበር። ግን በሂደት ሲታይ የኢታኖል ማጓጓዣ፣ ኢታኖል ምርት መጠን ማነስ፣ አጠቃላይ ያለው ሂደት ወጪ ጨመረ። ዋጋ ትመና ላይም ቅሬታ ነበር። ለወጪ ማካካሻም የተመደበውም ገንዘብ በቂ አይደለም የሚል ቅሬታ ነበር። የስኳር ፋብሪካዎች ኢታኖል አቅርቦት ማነስና የመሳሰሉት ሥራው በታሰበው መጠን እንዳይቀጥል አድርጓል። ከሁለት ዓመት ተኩል ወዲህ ይህ ነገር ተቋርጧል። በግንባታ ላይ የነበሩ ፋብሪካዎችን ታሳቢ ያደረገም ነበር። እነዚህ ወደ ሥራ ሲገቡ 10 በመቶ ኢታኖል የመቀላቀል እቅድም ነበር። ግን ስኬታማ መሆን ሳይቻል ቀርቷል። ስኬታማ ቢሆን ኖሮ የውጭ ምንዛሪ ለማዳንም ያግዝ ነበር።
አዲስ ዘመን፡– መንግስት በጅቡቲ የፈሳሽ እና ደረቅ ወደብ መገንባቱ ይታወሳል። ይህ አስተዋፅኦ እያበረከተ አይደለምን?
አቶ ደመላሽ፡– ይህ እኛ ሀገር መግቢያ ላይ ተሰርቷል። ከጅቡቲ ወደብ አስፈላጊ 260 ኪሎ ሜትር በጣም የተጎዳ በመሆኑ ምሬት ይቀርባል። በዚህ መንገድ በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ ያለው በጣም የተሻለ መንገድ ነው። የነዳጅ ምልልሱ ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል። ቡታጁራ ወደብ አዲስ መንገድ እየተሠራ ነው።
አዲስ ዘመን፡– የመንግስት የልማት ደርጅት እንደመሆኑ መጠን ትርፋማነቱ እንዴት ይገለፃል?
አቶ ደመላሽ፡– የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት በትርፍ ህዳግ ነው የሚሰራው። ጀቡቲ ላይ እያንዳንዷ ሊትር በስንት እንደገባ ይታወቃል። ድርጅት የተመደበለት የትርፍ ህዳግ አለ። እኛ በዓለም ዋጋ ደረጃ ነው ነዳጅ የምንገዛው። መንግስት ደግሞ መጠነኛ ጭማሪ አድርጎ ነው ዋጋ የሚወጣው። ብዙ ጊዜ ማስተካከያ የሚደረገው በአውሮፕላን ነዳጅ ላይ ነው። ሌላው ላይ የብዙዎችን ሕይወት ስለሚያናጋ ብዙም አይከለስም። በዚህም ነዳጅ አቅራቢዎች፣ ነዳጅ ማደያዎች፣ የትራንስፖርት ድርጅቶች፣ የተመደበ የትርፍ ህዳግ አለ። የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የሚገኘውም በሽርፍራፊ ሳንቲሞች የሚቆጠር ቢሆንም ከዚህ በሚያገኘው ሥራዎችን እያከናወነ ነው። መንግስት የሚያደርገው ድጎማ አለ። ሆኖም የመሸጫ እና አቅርቦት ዋጋ ልዩነቱን በዚያ ልክ አያስተካክልም። ልዩነቱን ራሱ ይሸከማል። በዋጋ ልዩነት ያለው እ.ኤ.አ 2017 ጀምሮ ባለው ጊዜ ወደ 27 ቢሊዮን ብር ደርሷል። በዚያ ልክ ዋጋው ቢስተካከል የቤንዚን ዋጋ 40 ብር ይደርስ ነበር።
አዲስ ዘመን፡– የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት መሰረታዊ ችግሮች ምንድን ናቸው?
አቶ ደመላሽ፡– ዋንኛው የመሰረተ ልማት አቅርቦት ችግር ነው። ኢትዮጵያ ወደብ አልባ ሀገር ናት። ጅቡቲ ላይ ያለው ሆራይዘን ተርሚናል ሰኔ 1998 ዓ.ም ነው ሥራ የጀመረው። ያኔ ሥራ ሲጀምር በወቅቱ በነበረው የሀገራችን ፍጆታ ማዕከል አድርጎ ነው። ግን ፍጆታው በጣም እየጨመረ ነው። አሁን በተርሚናሉ ላይ የተወሰኑ ማሻሻያዎች ከማድረግ በቀር መሰረታዊ የማስፋፋት ሥራ አልተከናወነም። ይህ ትልቁ ማነቆ ነው። ነጭ ናፍታ እና አውሮፕላን ላይ መሰል ችግር የለም። ግን ወደፊት ወደዚህ እየመጣን ነው። ለእኛ እና የጅቡቲ መንግስትም የምንጠቀም 75 ሚሊዮን ሊትር መያዝ የሚችል የቤንዚን የነዳጅ ማጠራቀሚያ ጋን ነው ያለው። ከሀገራችን እድገት አኳያ የከፋ እየሆነ የመጣው ደግሞ በቤንዚን ላይ ነው። በመሆኑም በሱማሌ ላንድ እና በኤርትራ ወደቦች ለመጠቀም የመግቢያ በሮችንና አማራጮችን ሰፋ ማድረግ ይፈልጋል።
ሁለተኛው የነዳጅ አቅርቦት ሰንሰለት ላይ ችግር አለ። እቅድ ተይዞ የሀገሪቱ ነዳጅ ፍላጎት በየወሩ ተተንትኖ እየቀረበ ቢሆንም ከመረከቢያ ወደብ እስከ ተጠቃሚ በአግባቡ መድረሱን የሚረጋገጥበት አስገዳጅ አሠራር የለም። በአሁኑ ወቅትም ቤንዚን ላይ ያለው ችግር የዚህ ውጤት ነው። አስገዳጅ ሁኔታዎችን መተግበሩ እንዳለ ሆኖ ደግሞ የተለየ ኢንቨስትመንት የሚጠይቅ ሥራ አለ። ነዳጅ በጣም ብዙ ነገር የሚነካ እና ሁላችንም ቤት የሚነካካ በመሆኑ በጣም ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው።
አዲስ ዘመን፡– ለሰጡኝ ማብራሪያ በጣም አመሰግናለሁ።
አቶ ደመላሽ፡– እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 23/2013