ግርማ መንግሥቴ
የሰዓት አቆጣጠር ጉዳይ እንደየግለሰቡና ተግባሩ ይለያያል፤ ይወሰናልም። ተኝቶ የሚውል ምንም የሚቀጥረው ሰዓትም ሆነ ለጥቅስ የሚበቃ ድርጊት የለውምና ዝም እንጂ ሌላ ምንም የሚለውም ሆነ የሚቆጥረው ነገር፤ የሚለካው ውጤት የለውም። በሁሉም ዘርፍ እንዲሁ ነው።
ወደ ምርጫ ስንመጣም ያለው ሁኔታ ያውና ተመሳሳይ ነው፤ የሚወዳደር የሚቆጥረው ሰዓት አለው፤ የማይወዳደር የማይቆጥረው ሰዓት አለው። በቃ – በሁለቱ መካከል ያለው ልዩነት የመቁጠርና ያለመቁጠር ነው።
ይህን እንበል እንጂ በመቁጠርና ባለ መቁጠር መካከል ግን ሰፊ ልዩነት የለም እያልን አይደለም፤ በጣም አለ። ልክ በሚተኛና በሚሰራ መካከል እንዳለው ልዩነት ባይ(ቢ)ሆንም ማለት ነው። (በኋላ እንመለስበታለን።)
ሰዓት ግኡዝ ግን ደግሞ ረቂቅና ሀያል ነገር ነው። ይሁን እንጂ እኛ (እንደ)ፈለግነው ልንቆጥረው፤ ልናሽከረክረው እንችል ዘንድ ፈጣሪ በእኛ ቁጥጥር ስር አድርጎታል።
ስንፈልግ በአቅጣጫው ልንከተለው፤ ሳንፈልግ በአቅጣጫችን ሊከተለን ሁለታችንም መብት አለን። ጉዳዩ በእነዚህ ሁለት የተለያዩ የተጠቃሚነት መብቶች መካከል ያለው የአጠቃቀም ፍላጎትና እውቀት ነው። (እውነት በምርጫ ሰዓት አቆጣጠር አሁን ሰዓቱ ስንት ነው??)
የኢትዮጵያውያን ጥልቅ ፍልስፍና ከሚገለጽባቸው ብልሀቶች አንዱና ምናልባትም ዋናው ሥነቃል ሲሆን “ሰርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ” ያለ በቂ ምክንያት የተሰደረ፤ ወይም የተደረደረ፤ በዜማና ስልት የተዋቀረ አባባል አይደለም። ዋጋ ያለው፤ ትርጉም የሚሰጥና ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው እጅግ የላቀና ከሰላ አእምሮ የፈለቀ አገላለፅ ነው – ሰርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ።
የአገራችንን ምርጫ ከኋላ ጀምሮ ለተመለከተውም ሆነ ትንሽም ቢሆን የግል ምርምር ብጤ ላደረገ ሰው እውነታው ይሄው “ሰርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ” አይነት ነው። ሁል ጊዜ ዝግጅታችን የግብር ይውጣ ነው፤ ሁል ጊዜ እንቅስቃሴያችን ያላዋቂ ነው፤ ሁል ጊዜ እንቅስቃሴያችን የስልጣን ጥምን ለማርካትና እግረ መንገዳችንንም ለመጠፋፋት ነው። በቃ – ሌላ “አለ” የሚል ካለ ሊጨምርበት እንጂ ከዚህ የተሻለ ሊያመጣ አይቻለውምና እንዳማረበት አርፎ ይቀመጥ። “አልቀመጥም” ካለ መከራከር ይቻላልና መግጠም ነው።
“ሰርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ” ሲባል ያለ ምክንያት ሳይሆን ሳቢያና ውጤት ባለው መልኩ የተከናወነን አሳዛኝ፤ የሰነፍ ተግባር መኖሩን ለማመላከት ነው። ተግባሩም ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊ ወዘተ ጉዳዮችን በአንድ አጣምሮ የያዘ ስለመሆኑ “ሰርገኛ” እራሱን የቻለ ማረጋገጫ ነው። (“ሰርግ” እና “ሰርገኛ”ን “ምርጫ” እና “መራጭ”ን ምን አገናኛቸው ካልተባለ በስተቀር ለእኔ አንድ ናቸው።)
የአካሄዳችን ዳር ዳርታ ግልፅ ነው። በተለይ ካለንበት የምርጫ አየር ጠባይና የተመራጭ አመል ጠባይ አኳያ ለተመለከተው፤ ለመዘነው ሁሉም ግልፅ ነው።
ያለንበት ወቅት ከምርጫ አኳያ ሰዓታችን ወደ ታች፤ ወደ ዜሮ እየቆጠረ በመሄድ ላይ ይገኛል። ሰዓታችን በየሰከንዱ፣ በየደቂቃው፣ በየሰዓቱና በየቀኑ በፍጥነት እየቀነሰና ወደ ዜሮ እየተጠጋ፤ ዜሮ ሊያደርግ የተዘጋጀውንም ዜሮ ለማድረግ፣ ያንዱን ዜሮም በማጣፊያው የሂሳብ ስሌት መሰረት አጣፍቶ ሌላኛውን መቶ በመቶ (96.9 %ም ሊሆን ይችላል) በማድረግ ሁለቱንም ወደ የተገቢ ስፍራዎቻቸው ለመሸኘት ሰዓታችን በፍጥነት እየገሰገሰ በመቀነስ ላይ ነው።
ይህ እየገሰገሰ በመቀነስ ላይ የሚገኛው የምርጫና ሰዓታችን ጉዳይ እንዲህ አሁን በወረቀት ላይ እንደምንፈላሰፈው አይደለም። ምናልባትም ሄዶ ሄዶ ወደ ግጭት ሊያመራ ይችላል፤ የንፁሀንን ህይወት ወደ መቅጠፉ ሊያመራ ይችላልና በጉዳዩ ላይ ከወዲሁ አጥብቆ ማሰብ ያስፈልጋል። ይህን ስንል ሟርት ሳይሆን የህይወት ልምዳችንን፤ በተለይም ታሪካዊው 97 ያስተማረንን መነሻ አድርገን ነውና ሀሳባችንን የሚጋሩ ብዙዎች ስለመሆናቸው አንጠራጠርም።
ምርጫ ሲደርስ “የእናቴ መቀነት አደናቀፈኝ” ማለት ያው “ሰርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ” ከሚለው የማይለይበት አንድ አቢይ ነጥብ ቢኖር ሁለቱም አስቀድመው የሰሩት ስራ አለመኖሩ ሲሆን፤ ሁለቱም ለአቅመ ሰርግና ለአቅመ ምርጫ አለመድረሳቸው ነው። “ለአቅመ ሰርግም ሆነ ለአቅመ ምርጫ (ከደረሱ በኋላ) አለመድረስ” ማለት ደግሞ መጨንገፍ ነው። በተለይ ሰዓቱ ወደ ታች እየቆጠረ፣ በፍጥነት እየቀነሰና ወደ ዜሮ እየተጠጋ በሄደ ቁጥር የጨንጋፊዎች መጠነ መጨንገፍ እየጨመረና በፍጥነት ወደ ላይ በመገስገስ ፍጥነት ጭንጋፌያቸውን እያጣደፈው የመሄዱ ጉዳይ ያሳስባልና አሁንም ጊዜ አለ ለማለት ነው።
ገና በጠዋቱ “በምርጫው አልወዳደርም” ማለት ገና በምርጫ ላይ ግፍ መዋል ብቻ ሳይሆን ሀጢያትን መፈፀም ነው። ሲጀመር ምርጫ የትም አገር አልጋ ባልጋ ሆኖ አያውቅም፤ በሰለጠነው አለምም ከሞት በመለስ ሁሉንም አይነት ዋጋ ያስከፍላል። ምናልባት ልዩነቱ ፈረንጆቹ “የአፍሪካ ምርጫ” (African Election) በማለት የሚሳለቁበት የአፍሪካ ምርጫ ነፃነትን በማያውቁ ነፃ አውጪዎች እጅ መግባቱና “ነገ ስልጣን ይዘው ያሳልፉልኛል፤ ካለሁበት መከራና ስቃይ ያወጡኛል” በማለት በተስፋ የሚጠብቋቸውን ንፁሀንን ደም እስከ ማፍሰስና ህይወት እስከ መንጠቅ ድረስ መዝለቁና ሁል ጊዜም ዲሞክራሲ ወደ ኋላ ሲጓዝ መታየቱ ነው። (አዎ በአፍሪካ ከምርጫ በኋላም የዲሞክራሲው ሰዓት የሚቆጥረው ወደ ኋላ ነው። ወደ ኋላ – – -)
አሁን ባለንበት ሁኔታ “በምርጫው አልወዳደርም” ማለት ሞት ነው – ፖለቲካዊ ሞት። ምህዳሩ ለሁሉም አንድ ሆኖ ሳለ “የእናቴ መቀነት አደናቀፈኝ” ማለትን ምን አመጣው? ይህ፤ እንደዚህ ፀሀፊ እምነት ለአገራችን የምንፈልገውን ዲሞክራሲን አያመጣም፤ ያለችውንም ያዳፍናል እንጂ ምንም አይነት ጭላንጭል አያሳይም።
ምህዳሩ ለሁሉም እኩል፤ ለሁሉም አንድ አይነት ሆኖ ሳለ ሌላው ለምርጫው ተፍ ተፍ ሲልና ላገሩ የሚችለውን ሁሉ ሊያደርግ ሲታትር “በምርጫው አልወዳደርም” ማለት በደጋፊዎች ስነ ልቦና ከማላገጥ፤ በጊዜና ገንዘብ ከመጨማለቅ፤ በኋላ “ምርጫው ተጭበርብሯል”፣ “ኮሮጆ ተገልብጧል” ከሚል ጠብ አጫሪነት የተለየ አይደለምና ከሁሉም በፊት አሁንም ጊዜ አለ ለማለት ነው። (ጊዜ አለ እንበል እንጂ አሁንም ጊዜው ወደ ታች፣ ወደ ዜሮ ቲክ ቲክ ሲል እየታየ ነው።)
በፖለቲካ አለም ብቻ አይደለም በዛሬዋ አለማችን ምርጫ የሁሉም ነገር መሽከርከሪያ ምህዋር ነው። ያለ ምርጫ እራሱ “ነፃ ምርጫ” (Free will) የሚባል ነገር የለም። ያለ ምርጫ ወደ ኋላ እንጂ ወደ ፊት የሚወስድ መንገድ ፈፅሞ የለም። ያለ ምርጫ ጭለማ እንጂ ብርሀን አይኖርም።
በዛሬዋ አለማችን “ምርጫ” የምርጫ ጉዳይ ብቻ አይደለም፤ የምርጫ ጉዳይ የህልውና ሁሉ ጉዳይ፤ የፖለቲካ፣ ማህበራዊ፣ ሀይማኖታዊ፣ ባህላዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ወዘተ ጉዳይ ሁሉ ነው። የዛሬው ምርጫ ከዛሬው ባለፈ የነገው ትውልድ ህይወት ሁሉ የሚወሰንበት፤ የአገርና ህዝብ እጣ ፈንታ የሚሰፈርበት፤ የማን ማንነቱ የሚለይበት፣ ፍሬው ከገለባው የሚበጠርበት ወዘተ ሁሉ ነውና ማንም በምርጫ ሊያሾፍ አይፈቀድለትም።
መጪውን ምርጫ የሰላም፣ የፍቅር፣ የአንድነት፣ የመፎካከር ያድርግልን።
አዲስ ዘመን መጋቢት 23/2013