አስናቀ ፀጋዬ
በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የኮሮና ወረርሽኝ በዜጎች ላይ ስፋት ያለው ሰብአዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ አስከተሏል፡፡ በተለይ ደግሞ በወረርሽኙ ምክንያት በርካታ የግልና የመንግስት ሥራ ተቋማት ሰራተኞቻቸውን መቀነሳቸውን ተከትሎ በርካቶች ለሥራ አጥነት ተዳርገዋል፡፡ በዋናነት ደግሞ በቀን ገቢ የሚተዳደሩና የእለት ጉርሳቸውን የሚያገኙ ሰዎች የዚህ ክስተት ገፈት ቀማሽ ሆነዋል፡፡
በልእለ ሃያሏና የዓለም ምጣኔ ሃብት ቁንጮ በተባለችው አሜሪካ እንኳን 10 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች ለሥራ አጥነት ተዳርገዋል፡፡ በተመሳሳይ በእስያ፣ በአውሮፓና በአፍሪካም በርካቶች ለሥራ አጥነት ተዳርገዋል፡፡ በኢትዮጵያም በወረርሽኙ ምክንያት በርካታ የሥራ ዘርፎች መቀዛቀዛቸውን ተከትሎ ጥቂት የማይባሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ያለ ሥራ ለመቀመጥ ተገደዋል፡፡
የኮሮና ወረርሽኝ በኢኮኖሚያቸው ላይ ተፅእኖ ካሳደረባቸው የዓለማችን ሀገራት መካከል አንዷ ህንድ ስትሆን ወረርሽኙ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ በፈጠረው ቀውስ ምክንያት ባለፈው አንድ ዓመት ብቻ ከ75 ሚሊዮን በላይ የሚሆነው ህዝቧ ለድህነት መጋለጡን በሀገሪቱ የሚገኝ ‹‹ፔው›› የተሰኘ የጥናት ማእከል ያወጣውን ትንታኔን ዋቢ በማድረግ ሲ ኤን ቢ ሲ ኒውስ ከሰሞኑ ዘግቧል፡፡
እንደዘገባው ከሆነ የጥናት ማእከሉ ያወጣው ትንታኔ የኮሮና ወረርሽኝ ባይከሰት ኖሮ ሊፈጠር የሚችለውን የአገሪቱን ኢኮኖሚ መኮማተር በማወዳደር ሲሆን አሃዙ እ.ኤ.አ. በ 2020 በዓለም አቀፍ ደረጃ 60 ከመቶ የሚሆነውን የድህነት ጭማሪ ድርሻ እንደሚይዝ ትንታኔው አመላክቷል፡፡ በኑሮ ደረጃቸው ዝቅተኛ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች በቀን ከ2 ዶላር በታች ገቢ እያገኙ እንደሚኖሩም አሳይቷል፡፡
ህንድ በዓለም አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ደረጃ የኮሮና ወረርሽኝ ከታየባቸው ሀገራት ውስጥ አንዷ መሆኗንም በጥናት ማእከሉ ትንታኔ ውስጥ የተጠቀሰ ሲሆን፤ እስከ ባለፈው ዓርብ ድረስ ሀገሪቱ 11 ነጥብ 51 ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎቿ በኮቪድ- 19 መያዛቸውንና ከ159 ሺ 300 በላይ የሚሆኑት ደግሞ በቫይረሱ ምክንያት ህይወታቸው ማለፉን ለዓለም አቀፉ ጤና ድርጅት ሪፖርት ማድረጓ ተገልጿል፡፡ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም አይ ኤም ኤፍ የህንድ ኢኮኖሚ በቀጣዩ አመት 11 ነጥብ 5 በመቶ ከማደጉ በፊት በዚህ ወር መጨረሻ በ8 በመቶ እንደሚኮማተር መተምበዩም ተጠቁሟል፡፡
በፔው ምርምር ማዕከል ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ራኬሽ ኮቻር በኮቪድ ምክንያት በሕንድ እየጨመረ የመጣው ድህነት ከዚህ ቀደም የነበረውን የሀገሪቱን የእድገት ግስጋሴ በመጠኑም ቢሆን ይገታዋል ሲሉ በሪፖርታቸው ጽፈዋል፡፡
ከ2011 እስከ 2019 በህንድ በድህነት ውስጥ ያሉ ሰዎች ቁጥር ከ340 ሚሊዮን ወደ 78 ሚሊዮን እንደሚወርድ ተገምቶ የነበረ መሆኑን ተመራማሪው በሪፖርታቸው የገለፁ ሲሆን ቁጥሩ ባለፈው ዓመት ኮሮና ሳይከሰት ይበልጡኑ ወደ 59 ሚሊዮን ወርዶ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ይሁንና የኮሮና ወረርሽኝ ኢኮኖሚውን በማኮማተሩ ወደ 134 ሚሊዮን ከፍ እንደሚል የጥናቱ ትንታኔ ማሳየቱን አብራርተዋል፡፡
የሀገሪቱ የመካከለኛ የገቢ ደረጃ እድገትም በተመሳሳይ በዚሁ የኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት በከፍተኛ ደረጃ መመታቱን በጥናቱ ትንታኔ መገለፁንም ተመራማሪው ጠቁመው፤ በህንድ በመካከለኛ ገቢ ደረጃ የሚገኙና በቀን ከ10 እስከ 20 ዶላር ያገኛሉ ተብለው የሚታሰቡ ዜጎች ቁጥር ከ2011 እስከ 2019 ባለው ጊዜ ውስጥ ከ29 ሚሊዮን ወደ 87 ሚሊዮን ያደገ መሆኑንና ይህም በኮቪድ- 19 ምክንያት በ2020 ወደ 66 ሚሊዮን እንደሚወድቅ ተጠብቆ እንደነበርም አስታውቀዋል፡፡
የጥናት ማእከሉ ልክ እንደ ህንድ ሁሉ ቻይናም 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን የሚሆን ብዛት ያለው ህዝብ ያላት ሀገር ናት ሲል የገለፀ ሲሆን ይሁንና ወረርሸኙ በድህነት ላይ ያሳደረው ተፅእኖ አነስተኛ እንደነበር በንፅፅር አስቀምጧል፡፡ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት አይ ኤም ኤፍም ባለፈው ዓመት የቻይና ኢኮኖሚ በ 2 ነጥብ 3 በመቶ አድጎ የነበረ መሆኑንና በአሁኑ ዓመት ደግሞ 8 ነጥብ 1 በመቶ የሚያድግ መሆኑን ተምብየዋል፡፡
‹‹በ2020 የቻይና ኢኮኖሚያዊ እድገት በጥሩ ደረጃ ላይ ይገኝ ነበር፡፡ ከዚህ አኳያ በቻይና ያለው የድህነት ጠለል ሳይለወጥ ባለበት እንዲቆይ አግዞታል›› ሲሉ ከፍተኛ ተመራማሪው ኮቻር ተናግረዋል፡፡
በሕንድ ላይ የተደረገው ትንታኔና ከቻይና ጋር በንፅፅር የተቀመጠው ሁነት የኮቪድ -19 ወረርሽኝ በዓለም ዙሪያ የሰዎች የገቢ ደረጃዎችን እንዴት እንደነካው የፒው ምርምር ማዕከል ተቋሚ ስለመሆኑም በዘገባው የተመላከተ ሲሆን ቫይረሱ ባይከሰት የሚለው ሀሳብ ከግምት ውስጥ ገብቶ በኮቪድ- 19 ምክንያት ባለፈው አመት የዓለም ኢኮኖሚ በመኮማተሩ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጨማሪ 131 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ለድህነት እንደተጋለጡም የጥናት ማእከሉ አረጋግጧል፡፡
ሶስት እጅ ያህሉን የዓለም ህዝብ ብዛት የያዙት ቻይናና ህንድ የተከሰተው የኮሮና ወረርሽኝ አካሄድና ማገገም በዓለም አቀፍ የሰዎች የገቢ ደረጃ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያሳድራል ሲልም የጥናት ማእከሉ አስታውቋል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 15/2013