ተገኝ ብሩ
ጎህ ከመቅደዱ በፊት ነቅቶ አልጋው ላይ ጋደም እንዳለ ራስጌው ከሚገኘው የመፅሀፍ መደርደሪያ አንዱን መፅሀፍ አንስቶ ማንበብ ጀመረ፤ በእንቅስቃሴው የነቃችውን ባለቤቱን ግንባርዋ ላይ ጠጋ ብሎ ሳማት። ”ምነው ፍቅር እንቅልፍ እንቢ አለህ እንዴ?” ስትል ባለቤቱ ሳራ ጠየቀችው። “ኧረ ውዴ ፈፅሞ። ሊነጋ ነው፤ ትንሽ ላንብብ ብዬ ነው።” ብሎ በፈገግታ መለሰላት። “ምንድነው የምታነበው ? እስኪ ልስማህ፤ ለኔም አንብብልኝ” አለችው።
የመፅሀፉ ርዕስ “እውነትና ሁነት” ይላል፤ ከየትኛው ልጀምርልሽ ከእውነቱ ወይስ ሆነ ከሚባለው?” ሲል አማራጭ አቀረበላት። “ከእውነቱ ጀምር” ስትል መለሰችለት። እሺ ብሎ በመፅሀፉ የመጀመሪያው ገፅ ላይ የሰፈረውን እውነት ያነብላት ጀመር። ተመስጣ ሰማቸው። የምትሰማው እውነት ከባልዋ ስለሆነ ጥሟት አዳመጠችው። አንብቦ ሲጨርስ “ሆነ ስለተባለው ደግሞ ምሽት ታነብልኛለህ፤አሁን ቁርስ ልስራ›› ብላ ስማው ከአልጋ ወረደች።
የሰራችውን ጣፋጭ ቁርስ እየተጨዋወቱ በልተው ወደ ስራ ለመሄድ ተነሳ። “ዛሬ ፕሮግራምህ ምንድነው?” ስትል ጠየቀችው፤ ውሎና ማምሻውን አስረዳት። ክረምት ነውና ጃኬት ደርቦ፤ ልጁን አቅፎ ስሞ ለእናቱ አስረከበና የእናትዬውን ግንባር ስሞ ከቤቱ ወጣ። ወደ መስሪያ ቤቱ ሲያመራ ስልኩ የአንሱኝ ጥሪ አሰማ። “ሰለሞን በላይ” ይላል፤ በተሰላቸ ስሜት አንስቶ “ሀሎ“ በማለት ምላሽ ሰጠው። ከወዲያኛው የስልክ ጫፍ ይመጣ የነበረው ድምፅ ግን ጤነኛ አልነበረም። ፊቱን እንዲለወጥና እንዲቆጣ አደረገው።
“ብሩን ለምን አትከፍለኝም፤ በፀብ ነው እንዴ አንተን ማናገር ያለብኝ” ከሚለው ስልክ ደዋይ የሰማው ንግግር አብሽቆት ቱግ ብሎ ማውራት ጀመረ። “ሰውየው! መኪናውን የገዛሁት እኔ አይደለሁም፤ ለምን ከባለ ጉዳዩ ጋር አትጨርስም፤ እኔ አትደውልልኝ ፤አያገባኝም ብዬሃለሁ።” ብሎ ስልኩን ዘጋው።
በድጋሚ ተደወለ፤ ሳያነሳ አጠፋው። ድጋሚ ተደወለ፤ አንስቶ “አልሰማኸኝም! እኔ አያገባኝም አልኩህ፤ የሚመለከተውን አናግር” ሲል መለሰት።
“ሰምቻለሁ፤ደግሜ አልደውልብህም፤ በቅርቡ ግን መስሜያህን እዘጋዋለሁ፤ ጠብቅ!” ሲል በአጸፋው መለሰለት። ዮሀንስ ስልኩን ዘግቶ በንዴት ጦፈ “ይሄ ብሽቅ፤ ቀኔን ሊያበላሽብኝ ነው” ብሎ በብስጭት ተቁነጠነጠ።
ዮሀንስ አንድ መኪና ይፈልግ የነበረው ወዳጁን ከሰለሞን ጋር ያገናኘዋል። መኪና የሸጠው ግለሰብም ለመኪናው ያወጣለት ዋጋ እጅግ ውድ ስለነበር የዮሀንስ ጓደኛ መኪናውን ለመግዛት የሚያስችል በቂ ገንዘብ እንደሌለውና ቀሪውን በሁለት ወር ውስጥ መክፍል እንደሚችል ይነግረዋል።
ሻጩ ዮሀንስን ያውቀው ስለነበር ብዙም ሳይጠራጠር ሰነዱን አሟልቶ ከሁለት ወር በኋላ የቀረውን ገንዘብ እንዲያመጣለት ነግሮት አነስ ባለ ማስታወሻ ውል ይተሳሰሩና መኪናውን ያስረክባል። ከወር በኋላ ለፀቡ መንስዔ የሆነ ነገር ይከሰታል።
የዮሀንስ ወዳጅ የገዛው መኪና ሞተሩ ላይ ትልቅ ችግር እንዳለበት ይረዳል፡ “ ቀሪ ብሩን አልሰጥም፤ እንዲያውም ሙሉ ብሬን ይመለስልኝ›› ብሎ ውሉን ያፈርሳል። በዚህም ከሰውየው ጋር አለመግባባት ይፈጠራል። በእውቅና ያገናኛቸው ዮሀንስ እንዲዳኝ ቢጠየቅም ሁለቱን ማግባባት ይሳነዋል።
የሁለቱ ሰዎች ግጭት ተካሮ መኪና ሻጩ ዮሀንስን በጉዳዩ አለህበት በማለት ንትርክ ውስጥ ያስገባዋል። በዚህ መልክ የተጀመረውና የከረረው ፀብ እያደገ መጣ። መኪና ሻጩ ዮሀንስን ማስፈራራት ይጀምራል። ዮሀንስ ለባለቤቱ ርዕሱን አንስቶባት አያውቅም። መኪና ሻጩ ሲደውልለት እንጂ ለጉዳዩ ብዙም ትኩረት ሰጥቶት አሳስቦት አያውቅም። በዚህ መልክ ቀናት አለፉ።
ንፋሱ ከዝናብ ጋር አብሮ ጭለማው በቅዝቃዜ ታጅቦ አካባቢውን የዓለም ፍፃሜ የደረሰ አስመስሎታል። ጭለማው ሲታይም እንዲሁ ያስፈራል። የአየር ንብረቱን ቀድሞ አውቆ ከተፈጥሮ ጋር ታግሎ ቀኑን ለመዋል የተዘጋጀ የሚመስል ሰው እጁን በክረምት ጃኬቱ ኪስ ከቶ በፈጠነ እርምጃ ከዋናው መንገድ ታጥፎ በድንጋይ ንጣፍ ወደ ተሰራው መንገድ አመራ። የንፋሱ ሽውታና የአየሩ ቅዝቃዜ ከሚርከፈከፈው ዝናብ ጋር ተዳምሮ አካባቢው ላይ ሰው ዝር እንዳይል አድርጓታል።
ዮሀንስ ቤቱ ደርሶ ልጁንና ባለቤቱን እስኪያገኝ ቸኩሏል። እቤቱ ደርሶ “ባባ” የምትለውን ህፃን ልጁን አቅፎ ለመሳም፤ በጉጉት የምትጠብቀውን ባለቤቱን አግኝቶ በውሎው የገጠመውን ሊነግራት ተጣድፏል፤ በፍጥነት ይራመዳል። ጭለማ የወረሰው መንገድ አስፈሪ ቢሆንም፣ ዘወትር የሚተላለፍበት ነውና አላሰጋውም። ቶሎ ለመድረስ በመፈለጉ ቤቱ ርቆበት ይጣደፋል።
በድንጋይ ንጣፍ የተሰራውን መንገድ ጨርሶ ወደ ቤቱ የሚያስገባውን መንገድ ታጥፎ ሶስት እርምጃ ያህል እንደ ተራመደ “ቁም!” የሚል ድምፅ ሰማ፤እርምጃውን ገታ አደረገ። ወዲያው ድምፁ ወደተሰማበት አቅጣጫ ሲዞር ያልጠበቀው ቡጡ ሲያርፍበት ተንገዳግዶ ለመቆም ሞከረ። እዚያ ቦታ ላይ ይጠብቁት የነበሩት ተዘጋጅተው ነበርና ከበው ያሻቸውን አድርገው ጥለውት ሮጡ። ዮሀንስ የመነሳት አይደለም የመንቀሳቀስ አቅም አልነበረውም።
ሳራ ዮሀንስ የሚያስመሸበት ቀጠሮ እንዳለው ደውሎ ስለነገራት ያለወትሮው መዘግየቱ አላሳሰባትም። እራት አሰናድታ ልጅዋን እያጫወተች እስኪመጣ ትጠባበቃለች። እየመሸ ሲሄድ ግን ያሳስባት ጀመር። ደጋግማ ሰዓትዋን አይታ ስልክዋን አንስታ ደወለችለት። “የደወሉላቸው ደንበኛ ስልክ ለጊዜው ጥሪ አይቀበልም” የሚል ሆነ መልሱ፤ትንሽ ቆይታም ደግማ ደወለች፤ተመሳሳይ ድምፅ ሰማች። ትንሽ አሰብ አደረገችና ብድግ ብላ ከተቀመጠችበት ተፈናጥራ ተነሳች። ፊትዋን ቅጭም አድርጋ መጥፎ ያሳሰባትን አዕምሮዋን ወቀሰች። በሀሳብ ተውጣ ልጅዋን አባብላ አስተኛች።
ብዙ ጠበቀች፣ተቁነጠነጠች፣የምታደርገው ግራ ገባት። ከምሽቱ 5 ሰዓት ሲሆን እቤት መቀመጥ ፈፅሞ አልሆን ብሏት በሩን ከፍታ ወደ ግቢው በር አመራች። ዝናቡ ሀይል ባይኖረውም አየሩ ይቀዘቅዛል። በሩን በፍርሀት ስሜት ከፍታ የያዘችውን የስልክ ባትሪ ወደ መንገዱ አበራች። ምንም የሚታይ የለም። በሩን ዘግታ ወደ መንገዱ መታጠፊያ ተጠጋች። ከመንገዱ መታጠፊያ ጠርዝ ላይ ያየችው ነገር ልብዋን ለሁለት ከፈለው። የስልክዋን ባትሪ ይበልጥ አስጠግታ ተመለከተች። ፈፅሞ ባልገመተችው መልኩ ባልዋ መሬት ላይ ተዘርሮ ተመለከተች። “ጆዬ ጆዬ …ኡኡኡኡኡኡ” በማለት እሪታዋን አቀለጠችው።
የአካባቢው ሰዎች ተሰበሰቡ፤ተረባረቡም። ሳራ ይሄን ማመን አልቻለችም። እራስዋን ስታ ከደቂቃዎች በኋላ ነበር የነቃችው። ሰዎች አፋፍሰው ወደ ህክምና ወሰዱት፤ የዮሀንስ አስትንፋስ ግን ቀድሞ ተቋርጦ ነበር። በቦታው የነበረው ሰው ሁሉ አነባ። ጎረቤቱ በሁኔታው አዘነ። ሌቦች ደብድበው ዘርፈው ጥለውት እንደሄዱ ተገመተ።
ሳራ የባልዋን ድንገተኛ ሞት መቀበል አቃታት። በሀዘንና በተስፋ መቁረጥ የተሞሉ ቀናት አለፉ። በለቅሶ ምክንያት ይመላለስ የነበረው እንግዳ ከቤትዋ ቀስ በቀስ ቀንሶ ብቸኝነት ዋጣት። በዚያ ላይ ትተዳደርበት የነበረው የባልዋ ገቢ ቆመ። ልጅዋን በምን እንደምታሳድግ ኑሮዋን እንዴት እንደምትገፋው ግራ ተጋባች።
ባልዋ በምንና እንዴት እንደሞተ የሚያጣራው ፖሊስ ዘንድ ተመላለሰች። ከፖሊስ ምርመራ የተገኘው መረጃ ግን አጥጋቢ አይደለም። ባሏ የሞተ ሰሞን ሌቦች ደብድበው ገደሉት ከተባለው ግምት የዘለለ ምንም መረጃ ጠፋ። ዮሀንስ ከሰው ጋር ተግባቢና መልካም ግንኙነት ያለው ነው። ሳራም ሌቦች ደብድበው ጣሉት ከተባለው ውጪ መገመት አልቻለችም። ጠዋት ባሏ ስለ እውነት አንብቦላት ማታ እነብልሻለሁ ያላትን ሁነት ከእሱ ሳትሰማ በምትኩ ባልዋ ሆነ የተባለውን ሰማች። ተፈፀመ።
የዕቁብ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂስ መስራች እና ዋና የቴክኒክ ኃላፊ ዮሃና ኤርሚያስ እንደምትገልፀው በዕቁብ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂስ ይፋ የሆነው ይህ መተግበሪያ ባህላዊው የቁጠባ ስርዓታችንን ማህበረሰባዊነቱን በጠበቀ መልኩ ወደ ዘመናዊ አሰራር የሚቀይር ነው። ዕቁብ ላይ የሚከናወኑ ተግባራትን አስመስሎና የበለጠ ተጠያቂነት፣ የአጠቃቀም ቅለት እንዲሁም እቁቦቹ በሌሎች ሰዎች ይበልጥ እንዲገኙ እንዲያስችል ተደርጎ የተሰራ ነው።
በኢትዮጵያ ለሚካሄደው የፋይናንስ ቴክኖሎጂ እና ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ትልቅ አስተዋፅዖ እንደሚያበረክት ስለሚታመነው መተግበሪያ ዮሃና እንደምትገልፀውም በመተግበሪያው እቁቦቹ ልክ እንደ ባህላዊ ስርዓቱ ሁሉ ከዕቁብተኞች የሚላከውን ገንዘብ የሚቆጣጠር የየራሳቸው ሰብሳቢ ሲኖራቸው የዕቁብ አወጣጡም እንዲሁ በእጣ የሚወሰን ይሆናል። ለአስተማማኝነቱ ሲባል መተግበሪያውን ለመጠቀምና ዕቁብተኛ ለመሆን ሥም፣ አድራሻ እና የመታወቂያ ካርድ ማቅረብ እንደ ግዴታ ተቀምጧል። መመዝገብ የሚፈልግ ማንኛውም ተገልጋይም፣ የትውልድ ቀን፣ የሚኖርበት ቦታ፣ መታወቂያ፣ ፎቶ፣ ጨምሮ የተለያዩ የግል መረጃዎቹን መስጠት አሟልቶ መቅረብ ግድ ይለዋል።
በመተግበሪያው መሰረት አንድ ዕቁብ አሊያም ዕቁብ ሰብሳቢ መሆን ፍላጎት ያለው ሰው በመተግበሪያው ላይ ዕቁብ መፍጠር ይችላል። የሚፈልጋቸውን በተለይ በቅርብ የሚያውቃቸውን ሰዎቹ መጥራት ይችላል። እያንዳንዱ ዕቁብም ፍላጎትን መሰረት ባደረገ መልኩ የሰፈር አሊያም የካምፓኒ ስም መለያ ሊሰጠው ብሎም ሊካተትበት ይችላል።
መተግበሪያው በበይነ መረብ አማካኝነት ሲሰራ ዕቁብተኞቹ ክፍያዎችን ከመከታተልም ባሻገር መረጃ እንዲለዋወጡ የሚያስችላቸው ይሆናል። እቁባቸውን በጊዜው ይጥሉ ዘንድ ማስታወሻ የሚልክላቸው መተግበሪያው በጊዜ የሚጥሉትንም ኋላ ላይ ማበረታቻ የሚሰጥ ይሆናል። በተጨማሪም ማን እቁቡን እንደጣለና እንዳልጣለ፤ ማን ዘግይቶ ገንዘቡን እየላከ እንደሆነ መረጃ እንዲሰጥና በአካባቢያቸው ያሉ ሌሎች እቁቦችንም መፈለግ እንዲችሉ ሆኖ የተሰራ ነው።
መተግበሪያው በዕቁብተኞቹ መካከል መተማመን እንዲኖር ለማድረግ ያስችሉኛል ያላቸውን ለየት ያሉ ገፅታዎችንም ይዟል። በቴክኖሎጂው በሚስጥር አጠባበቅ ረገድ ጠንካራ አሰራሮችን የተዘረጉለት ስለመሆኑ አፅንዖት የሚሰጡት መስራቿ፣ ‹‹ተጠቃሚዎቹ ሌሎች እቁቦችን በሚቃኙበት ሰዓት እቁቡ የስንት ብር እንደሆነ ከማስመልከትና ለመቀላቀል ጥያቄ እንዲያቀርቡ ከማመቻቸት በቀር ሌሎች የዕቁብ ቡድኑን መረጃዎች በሚስጥር ይጠብቃል። በመተግበሪያው አሰራር ማንኛውም ሰው እቁቡ ወርሃዊ ነው ሳምንታዊ ነው እንዲሁም ባለ ስንት ነው የሚለውን ከመመልከት ውጭ የሌሎችን የግል ሚስጢር መመልከት አይችልም›› ነው ያሉት።
መተግበሪያው በዚህ በሳምንት አሊያም ወር እቁቡን ያሸነፈው ማነው የሚለውን በቂ መረጃ ይሰጣል። እቁቡ ስለተጣለባቸው ዙሮች እንዲሁም እቁቡን ሳይጥሉ ያሳለፉ ዕቁብተኞች ስለመኖራቸው የሚያሳዩ መረጃዎችን የሚያቀርብ ስለሆነም ተጠቃሚዎቹ የተሻለ ተዓማኒነት ያላቸውን እቁቦች ለይተው እንዲቀላቀሉ ያስችላል ተብሎለታል።
ከአገር በተጓዳኝ ባህር በመሻገር በመላ ዓለም የሚገኙ ዲያስፖራዎችን ተደራሽ በመሆን ረገድ ሰፋፊ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ያስገነዘቡት መስራቿ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ ከባለድርሻ አካላት በጋራ ለመስራት የሚያስችሉ የግንኙነት ስራዎች እንደተጠናቀቁም በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዘመናዊውን ዕቁብ እንዲቀላቀል በሩ ይከፈትላቸዋል ተብሏል። በዚህ ረገድም የተለያዩ ማበረታቻዎች እየተዘጋጁ ስለመሆኑም ለማወቅ ተችሏል።
ዕቁብ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂ መተግበሪያውን ከባንክ አገልግሎት ጋራ ለማስተሳሰር እና የገንዘብ ልውውጡንም ቀላል ለማድረግ ያስችል ዘንድ ከተለያዩ የባንክ ዘርፉ ባለድርሻዎች ጋራ እየተነጋገሩ መሆኑን ታውቋል። ዕቁብ ፔይ የተሰኘ ገፅታን በውስጡ ማካተቱንም ለማወቅ ተችሏል። መተግበሪያው ይፋ ከተደረገበት ዕለት አንስቶ ባሉት ቀጣይ ሦስት ወራት ውስጥ 30 ሺህ ተጠቃሚዎችን ለመሳብ አልሟል።
ከሳምንት በፊት በጉግል አፕ ስቶር ላይ እንዲቀመጥ የተደረገው መተግበሪያው በእስካሁኑ ቆይታው ከ500 ጊዜ በላይ ዳውንሎድ ለመደረግ በቅቷል። ድርጅቱ መተግበሪያውን የሚጠቀሙ ዕቁብተኞችን ታላሚ አድርገው ከሚሰሩ ማስታወቂያዎች ገቢ የሚያገኝ ይሆናል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 3/2013