አስናቀ ፀጋዬ
የኮሮና ወረርሽኝ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፈጠራቸው በጎ ያልሆኑ ተፅእኖዎች ውስጥ አንዱ በወረርሽኙ ምክንያት አብዛኛዎቹ የንግድ ተቋማትና ፋብሪካዎች መዘጋታቸውን ተከትሎ ሰራተኞች ከስራቸው በመቀነሳቸው የተከሰተው ስራ አጥነት ነው፡፡
በዚሁ ወረርሽኝ ጦስ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ያሉ በርካታ ሰራተኞች ከስራ ገበታቸው ተቀንሰዋል፡፡ እነዚህ ሰራተኞች በአብዛኛው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉና አነስተኛ ደመወዝ ተከፋይ በመሆናቸውም ለከፋ ድህነትም ተጋልጠዋል፡፡
ቦኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ብዛት ያላቸው ዜጎች ስራ አጥ ከሆኑባቸው ሀገራት መካከልም አሜሪካ በግምባር ቀደምትነት የምትጠቀስ ሲሆን 10 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎቿ ከስራ ውጪ ሆነዋል፡፡
ከሰሞኑ ቢ ቢ ሲ ባወጣው ዘገባ ባለፉት ወራት በአሜሪካ የቫይረሱ ስርጭት መቀነሱን ተከትሎና የክትባት ዘመቻ በስፋት በመጀመሩ ቡና ቤቶችና ምግብ ቤቶች ሰራተኞቻቸውን መመለስ መጀምራቸውን ገልጿል፡፡ አሰሪዎችም በየካቲት ወር ብቻ 379 ሺ የሚሆኑ ክፍት የስራ መደቦችን ማውጣታቸውን ጠቅሷል፡፡
እየወጡ ያሉ የክፍት ስራ መደቦች እድገት ተንታኞች ከጠበቁት በላይ መሆኑም በዘገባው የተመላከተ ሲሆን ሰራተኞችን ለመቅጠር የተጀመረው እንቅስቃሴ ለብቻው የስራ አጥነትን ክፍተት ሙሉ በሙሉ ሊደፍን እንደማይችልም ተነግሯል፡፡
ይህም የስራ አጥነት ቁጥሩ ከ6 ነጥብ 3 በመቶ ወደ 6 ነጥብ 2 በመቶ ብቻ ዝቅ እንዳለና አሁንም ድረስ በቫይረሱ ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ አሜሪካውያን ከስራ ውጪ ሆነው እንደሚቆዩ የሚያንፀባርቅ ስለመሆኑም ተመላክቷል፡፡
በ‹‹ፊች ሬቲንግ›› ዋና የምጣኔ ሀብት ባለሙያ የሆኑት ብራያን ኮልቶን “ይህ ቁጥር አስገራሚ ነው ፤ ነገር ግን ቁጥሩ የሚያመላክተው የስራ ገበያው ዳግም የመከፈት ከፍታ ከተጠበቀው ጊዜ አስቀድሞ መሆኑ ነው›› ሲሉ አስቀምጠዋል፡፡
ለዚህም ማህበራዊ ርቀትን የሚጠይቁ እገዳዎች መላላታቸውና በተለይ ደግሞ በግሉ ዘርፍ ያሉ የመዝናኛ እና የትራንስፖርት አገልግሎቶች ለዜጎች የሥራ እድሎችን በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ ድርሻ እንደበራቸው የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ከቡና ቤቶችና ምግብ ቤቶች ባሻገር ቸርቻሪዎችና አምራች ድርጅቶችም የስራ እድል ከፈጠሩ ዘርፎች ውስጥ እንደሚገኙበት የኢኮኖሚ ባለሙያው ገልፀው፤ ይሁንና እንደሌሎቹ ዘርፎች የኮንስትራክሽን ድርጅቶችና የአካባቢ መስተዳድር የስራ መደቦች ለስራ አጦች የስራ እድል በመፍጠር ረገድ አስተዋጿቸው ብዙም እንዳልነበር ጠቁመዋል፡፡
ዚፕ ሪክሪዊት በተሰኘው የስራ ፍለጋ ድረ ገፅ ዋና የምጣኔ ሀብት ባለሙያዋ ጁሊያ ፖላክ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት ስራ አጥነቱ በፍጥነት እያገገመ መሆኑን የጠቆሙ ሲሆን የየካቲት ወር የስራ ገበያ ግኝት ወጥነት ያለውና ወደ ኋላ የማይመለስ ስለመሆኑ ጠቋሚ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡ በኮቪድ ምክንያት ተቀዛቅዞ የነበረውን የሰው ሃይል ገበያ ከአንቀላፋበት የሚያነቃ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
የአሜሪካን የሰራተኞች ዲፓርትመንት ባለፉት ወራት ብቻ 10 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ስራ አጥ መሆናቸውንና ይህም ከአንድ ዓመት በፊት ቫይረሱ ስፋት ያለው ክልከላዎችንና ማህበራዊ ርቀቶች እንዲኖሩ ከማስገደዱ በፊት ከነበረው ቁጥር ጋር ሲነፃፀር እጥፍ መሆኑን ጠቁሟል፡፡ አሃዙ ሥራ መፈለግ ያቆሙ ወይም ተቀጥረዋል የተባሉትን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ያካተተ ሳይሆን በወረርሽኙ ምክንያት ስራዎችን ለማቆም የተገደዱትን የሚያጠቃልል መሆኑንም ዲፓርትመንቱ አመላክቷል፡፡
በዚህም በተለይ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙና አነስተኛ ደሞዝ ተከፋይ የህብረተሰብ ክፍሎች በከፍተኛ ሁኔታ እንደተጎዱ ገልጿል፡፡ ባለፈው ወር የአብዛኛዎቹ የስራ ዘርፎች የስራ አጥነት መጠን ዝቅ ያለ ቢሆንም የጥቁር አሜሪካውያን ሰራተኞች ስራ አጥነት መጠን ግን ከ9 ነጥብ 2 በመቶ ወደ 9 ነጥብ 9 በመቶ ማሻቀቡንም ተናግሯል፡፡
የሀገሪቱ ፌዴራል ሪዘርቭ ሊቀመንበር ጄሮም ፓውል ባለፈው ሐሙስ ሲናገሩ የቫይረሱ ስርጭት እየቀነሰ በመሄዱና የመንግስት ባለሥልጣናትም የእንቅስቃሴ ገደቦችን እያቀለሉ በመሆናቸው በሚቀጥሉት ወራቶች የስራ ቅጥር መጠን ከፍ እንደሚል ያላቸውን ግምት አስቀምጠዋል፡፡
ባለፈው ወር በርካታ የስራ መደቦች ክፍት ቢሆኑም በሆቴሎች እና በምግብ ቤቶች ውስጥ ያሉት ክፍት የስራ መደቦች ከአንድ ዓመት ቀደም ብሎ ከነበረው ጋር ሲነፃፀሩ በ 20 ከመቶ መቀነሳቸውንም ሊቀመንበሩ ተናግረዋል፡፡
ተንታኞች በበኩላቸው የየካቲት ወር የስራ ቅጥር መጨመር ባለፈው ዓመት መጨረሻ በመንግስት በኩል የፀደቀውን የ 900 ቢሊዮን ዶላር ድጎማ መጠየቂያ ውጤት መሆኑን እንደሚያንፀባርቅ ገልፀዋል፡፡
አዲሱ የአሜሪካን ፕሬዚዳንት ጆ ባይደንም ስራ አጦችንና የዘርፉን ኢኮኖሚ ለመደገፍ ሌላ የ 1 ነጥብ 9 ትሪሊዮን ዶላር የድጋፍ ፓኬጅ እንዲፀድቅ ግፊት እያደረጉ ስለመሆኑም በዘገባው ተመላክቷል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘም ሪፐብሊካን ገንዘቡ አላስፈላጊና ከፍተኛ ነው ብለው ሲከራከሩ ዴሞክራቶች በበኩላቸው ፕሬዚዳንቱ የገንዘብ ድጋፍ አቅዱን በቀጣዩ ወር አጋማሽ ላይ እንደሚያፀድቁት ተስፋ አድርገዋል ሲል የቢ ቢ ሲ ዘገባ አመልክቷል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 1/2013