ጽጌረዳ ጫንያለው
ወይዘሮ ዘመናይ አስፋው ይባላሉ። የብዙ ልጆች፣ አረጋውያንና ሴቶች ተንከባካቢ እናት ናቸው። በሥራቸው ከ76 በላይ ሰዎችን አቅፈው እየተንከባከቡ ይገኛሉ። ይህ የሆነው ደግሞ ‹‹የሰው ለሰው ህጻናትና አረጋውያን በጎ አድራጎት›› ድርጅት በተሰኘ የበጎ አድራጎት ድርጅታቸው አማካኝነት ነው።
ለእርሳቸው “መቀበል የምትፈልጉት ስጡ” ዋነኛ መርሀቸው ነው። ለጋስነት ከተረፈው የሰጠ ሳይሆን ካለው ላይ ያካፈለ መሆኑን ያምናሉ። በዚህም ነገ ማን ተረኛ እንደሆነና የት እንደምንደርስ አይታወቅምና ሁሌም እርዳታ ለሚፈልጉ ሰዎች እጅህን መዘርጋት ውዴታ ሳይሆን ግዴታ እንደሆነ በማመን ሥራውን የጀመሩ ናቸው።
በቤተሰባቸው ቤት ውስጥ ኑሯቸውን፣ ህይወታቸውን ገብረውም ነው እየሰሩ ያሉት። ለዚህ ደግሞ ምክንያታቸው ህይወት በመደጋገፍ የተሞላች መሆኗን መረዳታቸው ነው። ስለዚህም የአገሬ ልጆች የእኔም ናቸው፤ የአገሬ እናቶች፣ አባቶች ምርቃታቸው ለእኔ ይሆናል በማለት በድርጅት ሰብስበው የተቻላቸውን ሁሉ ያደርጋሉ።
ለዚህ ደግሞ መርሀቸው በዓለም ላይ ፈልገን ፈልገን አንድ ጥሩ ሰው ማግኘት ካቃተን እኛ አንዱ ጥሩ ሰው መሆን ይጠበቅብናል የሚል ስለሆነ ነው። እናም ከእኝህ ታላቅ እናት በርካታ ተሞክሮዎችን መውሰድ ይቻላልና ለዛሬ ‹‹ የህይወት ገጽታ›› አምድ እንግዳ አድርገናቸዋል። ስለዚህም ልምዳቸውን ለመንፈስም ለስጋም ጥንካሬያችን እናድርገው ስንል ጋበዘናችሁ።
ሩህሩኋ ልጅ
የተወለዱት ጅማ ከተማ በ1965 ዓ.ም ነው። ከቤተሰባቸው ይበልጥ ጎረቤትን ፈርተውና አውቀው አድገዋል። ሲመሽና ቤተሰብ ሲቆጣቸውም ጎረቤት የሚያድሩበት ጊዜ ብዙ ነበር። ስለዚህም በአስተዳደጋቸው ጎረቤት እናትና አባት ጭምር እንደነበርም አይረሳቸውም። በተለይ ጓደኞችና የሰፈር ልጆች ጭምር ዘመድ እንደሆኑ የሚያስቡት ነገር መቼም ከአዕምሯቸው አይጠፋም።
በባህሪያቸው ብዙ ጨዋታ የሚወዱ አይነት ልጅም ስለነበሩ አብዛኛው ውሏቸው ቤተሰቤ፣ እህቴ ወንድሜ ከሚሏቸው የጎረቤት ልጆች ጋር ነው። በእርግጥ በእነርሱ ቤትም ቢሆን በርከት ያለ ቤተሰብ ነበር። እናትና አባት ሳይጨመሩ 17 ልጆች ናቸው። እንግዳችን ደግሞ ስምንተኛ ላይ ይቀመጣሉ።
ጨዋታ ወዳዷ ወይዘሮ ዘመናይ፤ ብዙ ጊዜ የማይሞክሩት የጨዋታ አይነት አልነበረም። በተለይ ሩጫ ፣ ዝላይ፣ አሎሎ ውርወራና የኳስ ጨዋታም ላይ በጣም ጎበዝ ናቸው። በዚህ ደግሞ ከትምህርት ቤት ጀምሮ እስከ ከተማና ክልል ድረስ ተወክለው አሸንፈው ያውቃሉ። የተለያዩ ሽልማቶችንም ወስደዋል።
ዋናው መለያቸው ግን ለህጻናት ልዩ ፍቅር ያላቸው መሆናቸው ነው። ለዚህ ደግሞ ማሳያው ህጻን ተጥሎ አይተው ትምህርት ቤትም ሆነ ቤታቸው ከሄዱ በኋላ አዳራቸውን ሲያለቅሱ ማደራቸው ነው። ከዚያ በኋላም ህልም አበጅተዋል። እነዚህን ልጆች አንስቶ ማሳደግ። ይህ ደግሞ በባዶ ጭምር ፍላጎታቸውን ለማሳካት እንዳነቃቃቸው ያስታውሳሉ።
በልጅነታቸው በትምህርታቸው የተሻሉ ተማሪ ቢሆኑም ይህንን እሆናለሁ ብለው አልመው አያውቁም። አበረታችም አልነበራቸውም። በዚህም ከትምህርቱ ይልቅ ጨዋታው ላይ ሰፋ ያለ ጊዜ ያሳልፋሉ።
ቢሆንም በአባት ህግ ከትምህርት ቤት መቅረትና የቤት ስራ አለመስራት እንዲሁም አለማጥናት ክልክል ነው። ስለዚህም ቤት ከገቡ በኋላ በእናትና አባታቸው ግፊት ይህንን ያደርጉ እንደነበር ያወሳሉ።
አባታቸው በጅማ ከተማ አንቱታን ያተረፉ ባለሀብት ነበሩ። ሆቴልና የመኪና መለዋወጫ ማከፋፈያ ሱቅም ነበራቸው። በዚህ ደግሞ ቤተሰቡ ጥሩ ኑሮ ይኖር ነበር። ነገር ግን በእቅድ ሳይሆን በገፍ ሁሉ ነገር ይከናወን ነበርና ከጊዜ ወደ ጊዜ የኑሮ ደረጃቸው ማሽቆልቆል ጀመረ። በዚያ ላይ አባታቸው ደግና ያላቸውን ማካፈል የሚወዱ መሆናቸው፣ ወድቆና ተቸግሮ ያዩትን ሰው ማለፍ አለመቻላቸው ሁሉ ነገር በኪሳራ እንዲጠናቀቅ አደረገ።
በዚህ ደግሞ ቤተሰቡ የለመደው ቀርቶ ፍላጎቱን እንኳን ማሳካት ተሳነው። በተለይ ነገሩ የተባባሰው ደግሞ የደርግ መንግስት መሬታቸውን በመውረሱና የሚሰሩበት ሁኔታ በመቆሙ እንደነበር ያስታውሳሉ።
ይሁን እንጂ ይህም መከራ ቢደርስ ደግነት ከቤት እንዳልጠፋ ይናገራሉ። እንደውም ከዚህ ቤተሰብ የወሰዱት ደግነት ዛሬ ለብዙዎች መትረፍ እንዲችሉ እንዳደረጋቸውም ይገልጻሉ።
ቤተሰብ የደረሰ ልጅ እንዲሰራ፣ ንብረትን እንዲቆጣጠር አለማድረግና ሀላፊነትን በራስ ብቻ ለመወጣት መሞከር ብዙ አደጋዎችን ያስከትላል የሚሉት እንግዳችን፤ ቤተሰቤ ባክኖ የቀረው ይህንን በዚህ ምክንያት ነው ይላሉ። ስለዚህ ቤተሰብ ልጁን ማመንና ሀላፊነት መስጠት እንዳለበትም ይመክራሉ።
በእንግዳችን በጣም ተወዳጁ ነገር አሳ ማጥመድና መዋኘት ሲሆን፤ ሙሉ ጊዜያቸውን አሳ ለማግኘት ሲዳክሩ ይውላሉ። ይህ ደግሞ ብዙ ጊዜ ያስገርፋቸዋል። ምክንያቱም ዓሳ ካላገኙ ወደ ቤት ለመመለስ ይፈራሉና ይመሽባቸዋል። ዓሳ አጥምደው ከመጡ ግን ለእናታቸው እንደ እጅ መንሻ ስለሚሰጡ ማንም አይነካቸውም። በዚህ ድርጊታቸውም ነው ይበልጥ ልጅነታቸውን የሚያስታውሱት።
ትምህርት በህጻናት ፍቅር
አባታቸው ጫናው ከባድ ባይሆንም የሚያዋጣቸው ትምህርት እንደሆነ ሁልጊዜ ይመክሯቸዋል። ያልተማሩ ቢሆኑም ልጆቻቸው እንዲማሩ ይፈልጋሉ። በዚህም ‹‹እውቀት ሁልጊዜ መንዝራችሁ የምትመገቡት የወደፊት ስንቃችሁ ነው›› የሚለው ንግግራቸው ሁሌ ከአፋቸው እንደማይለይ ያስታውሳሉ። ይህ ደግሞ ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዲከታተሉ እንዳደረጋቸውም ያወሳሉ።
ጊዜው ትምህርት ብዙም ያልተስፋፋበት ቢሆንም እርሳቸው የከተማ ልጅ በመሆናቸው እስከ 12ኛ ክፍል ከቤተሰብ ሳይርቁ በተሻለ አማራጭ እንዲማሩ ሆነዋል። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውንም በኪቶ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ጀምረዋል።
በኪቶ ከአንደኛ እስከ አራተኛ ክፍል የተማሩ ሲሆን፤ አምስተኛና ስድስተኛ ክፍልን ደግሞ መድረሻ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል። ሰባተኛና ስምንተኛ ክፍልን ደግሞ በሰጦ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምረዋል።
ወደ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸው ሲዘዋወሩ ደግሞ በጅማ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዲማሩ ሆነዋል። የ12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን ያጠናቀቁትም በዚህ ትምህርት ቤት ነው። ነገር ግን ውጤታቸው ወደ ዩኒቨርሲቲም ሆነ ወደ ኮሌጅ የሚያስገባቸው አልነበረም። ስለዚህም ትምህርቱን ትተው ወደ ትዳር ገቡ።
ባለቤታቸው የተማረ በመሆኑና እርሳቸውም ከህጻናት ጋር መቀራረብ ስለሚወዱ መማር እንዳለባቸው ተወሰነ። ለዚህ ያበቃቸውም ቦታና ትምህርት ቤት ባይኖርም በረንዳቸው ላይ ህጻናትን እየሰበሰቡ ማስተማራቸውና ወላጆች ደግሞ በትምህርቱ መመሰጣቸው ነው።
በተለይ በስብዕና የተሻሉ ልጆች መሆናቸው ከነጻ ትምህርቱ በቂ ባይሆንም ወደ ገንዘብ ማደጉ፣ ማህበረሰቡም ሥራውን መውደዱ ራሳቸውን ጭምር እንዲማሩ የገፋፋቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። ተምረው በአቅም ቢያስተምሩ መልካም እንደሆነ በማሰብም ነው ለትምህርት ወደ አዲስ አበባ ያቀኑት። በዚያም በሴንጆሴፍ መምህራን ማሰልጠኛ ተቋም በመግባት በአጸደ ህጻናት መምህርነት በዲፕሎማ ሰልጥነዋል።
ቀጣዩ የትምህርት ጉዟቸው በአልፋ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ሲሆን፤ ትምህርቱን የተከታተሉት ሥራ እየሰሩ በርቀት ነው። እዚህ ሂውማን ሪሶርስ ማኔጅመንት በሚባል የትምህርት ዘርፍ በከፍተኛ ውጤት ተመረቁ። ከዚያ በኋላም በተለያየ ጊዜ የተለያዩ ስልጠናዎችን ወስደዋል።
ዘላለማዊነት ለህጻናት
የመጀመሪያ ሥራቸው የተጀመረው ህጻናትን ከመውደዳቸው ጋር ተያይዞ ሲሆን፤ በትዳር ወደ ሚዛን ቴፒ በሄዱበት ወቅት የጀመሩት ነው። በእርግጥ ይህንን ያደረጉት መልካም ትውልድ ልፍጠር በሚል በቤታቸው ውስጥ በጥቂት ልጆች በነጻ ነበር። ይሁንና ልጆች ይዘውት እየመጡ ያለው ነገር ቀላል አይደለም።
እየሆኑት ያለውም በገንዘብ የሚተመን አይደለም። ስለዚህ በነጻ ማስተማርሽ ለእኛ ምቾት አልሰጠንም ሲሉም እንዲከፍሏቸው ተማጸኗቸው። እርሳቸውም ብዙ ሳይጫኑ በአንድ ልጅ 10 ብር እየተቀበሉ ማስተማራቸውን ቀጠሉ። በ12 ልጆችም ነው ማስተማሩን ያጠናከሩት።
በወር ውስጥ እየተሳሳቡ 80 ደርሰውም የ800 ብር ደመወዝተኛ ሆኑ። ግቢው ሞልቶ ሲትረፈረፍ ደግሞ አስር ብር ያንስሻል ብለው በራሳቸው ጊዜ ጨምረው 20 ብር አደረጉላቸው። በዚህም ደሞዛቸው 1600 ብር ከፍ አለ።
ይህንን የበለጠ ለማጠናከር አዲስ አበባ በመሄድ የአጸደ ሕጻናት መምህርነትን ሰለጠኑ። ከትምህርት በኋላ የመጀመሪያዋ ሚዛን ላይ መዋእለህጻናት ትምህርትቤት የከፈቱም ሰው ሆነዋል። በእርግጥ ይህንን ለማድረግ መማር ብቻ በቂ አይደለም።
ገንዘብ ከምንም በላይ ያስፈልጋል። እናም ይህንን ገንዘብ ማግኘት ግድ ነው። ከልብ መሻት ካለ የማይቆፈር ድንጋይ አይኖርምና ብዙ ለፉ። በመጨረሻም ልማት ወዳድ ከሆኑ ጳጳስ ዘንድ ሲጠይቁ ከሀገረ ስብከቱ የሚወስዱበት እድል አመቻቹላቸው። እርሳቸውም ቢሆኑ አዲስ አበባ በሚማሩበት ጊዜ ለትምህርታቸው ከሚከፍሉት ላይ እየቀነሱ ግብዓቶችን ገዝተው ነበርና ብዙም ሳይቆዩ ወደ ሥራው ገቡ። ይህንን ያየው ቤተሰብም ከቀደመው ይበልጥ ልጁን ወደ መዋዕለጻናቱ መላኩን አጠናከረ።
ትምህርትቤቱን የጀመሩት በስልሳ ብር ክፍያ ሲሆን፤ በመጫወቻም ሆነ በመምህራን ሙሉ ሆኖ አገልግሎት ይሰጣል። ነገር ግን ከዓመታት በኋላ የተሻለ አቅም ያለው ባለሀብት በመምጣቱና መዋዕለህጻናት በመክፈቱ ተማሪዎቹን ከእርሳቸው ወደ ሌላኛው ትምህርትቤት እንዲነጉዱ አደረጋቸው። አቅም ያላቸው ወላጆችም እንዲሁ ልጆቻቸውን ወደዚያ ወስደው ማስገባት ጀመሩ።
በዚህም የእርሳቸው ሥራ እንዲያከትምለት ሆነ። በዚያ ላይ በእንቅርት ላይ ጆሮደግፍ እንዲሉ የአስራ አምስት ቀን ልጅ በያዙበት ቅጽበት ባለቤታቸው በህይወት ተለያቸው። ስለዚህም ፈተናቸው ይበልጥ ከበዳቸው። በዚህም በዚያ መቆየቱን ትተው ወደ ጅማ ከቤተሰብ ጋር ለመሆን ሄዱ።
አባታቸው ወደእርሳቸው ጋር መጥተው ችግራቸውን እንዲረሱ በመጎትጎታቸውና እርሳቸውም ኑሮው እየከበዳቸው በመምጣቱ ሚዛንን የለቀቁት ወይዘሮ ዘመናይ፤ ጅማ እንደገቡ ብዙም ሳይቆዩ ተስፋ ተዋህዶ በሚባል ትምህርትቤት ውስጥ ዳይሬክተር ሆነው መስራት ጀመሩ። ይህ የሆነውም ቀደም ሲል ገንዘብ እንዲሰጣቸው ያገዟቸው ጳጳስ ተሞክሯቸውን ያውቃሉና አስፈላጊውን ሁሉ አድርገው ትምህርት ቤቱን እንዲያሰሩ በመለመናቸውና ትምህርት ቤቱ ከተጠናቀቀም በኋላ ዳይሬክተር ሆነው እንዲሰሩ በመደረጋቸው ነው።
በዳሬክተርነት በትምህርትቤቱ ለስድስት ዓመታት ከቆዩ በኋላም ሁለት ልጆችን ይዞ በትንሽ ደመወዝ መስራቱ አዋጭነት እንደሌለው ስለተረዱ ወደራሳቸው ሥራ ገቡ። ይህም ስራ የአጸደ ህጻናት መምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጅ መክፈት ነበር። ገንዘቡን ብቻቸውን ስለማይችሉትም ከጓደኞቻቸው ጋር አስር አስር ሺህ ብር አዋጥተው ጀመሩት። የመማር ማስተማሩም ሆነ የማኔጅመንቱ ተግባር የእርሳቸው ሆኖ ቀጠለ።
ነገር ግን ብዙም ሳይሰሩበት ችግር ገጠማቸውና ተዘጋ። የችግሩ መንስኤ መንግስት ያወረደው አቅጣጫ ሲሆን፤ የአጸደ ህጻናት መምህራን ማሰልጠኛ ተቋማት ይዘጉ ብሎ በማዘዙ የመጣ ነው። በዚህ ደግሞ ብዙ ጉዳት ደርሶባቸዋል። ይሁን እንጂ በህጻናቱ ተስፋ የማይቆርጡት ባለታሪካችን፤ ልምዳቸውን መሰረት አድርገው የራሳቸውን መዋዕለ ህጻናት ከፈቱና ማስተማሩን ጀመሩ።
ይህም ቢሆን መሰናክል የበዛበት ነበር። አንዱ ኮቪድ ሲሆን፤ ሌላው የቤት ኪራይ ጉዳይ ነው። እናም ከቦታው እንዲለቁ በመደረጋቸው ዛሬ ላይ ትምህርት ቤቱን በራሳቸው ግቢ የሚያሳድጓቸውን ህጻናት ወደ ሌላ ክፍል አዛውረው እንዲቀጥሉ አድርጓቸዋል።
በምንም መልኩ ተቸግሬያለሁና መፍትሄ አላገኝም የሚል ነገር የማያውቁት እንግዳችን፤ ለሚደርስባቸው ሁሉ መፍትሄ ፈላጊ ናቸው። ተስፋ መቁረጥም ለእርሳቸው ቦታ የለውም። በዚህም ነው ከአንዱ ቦታ ሲባረሩ ሌላው ላይ ሥራውን የሚጀምሩት። ገንዘብ የሚያገኙበትን ሥራም አይመርጡም።
ከማስተማሩ ጎን ለጎን ሽንኩርት መፍጨት፣ ልብስ ማጠብና መንገድ ላይ ችብስ ጠብሶ መሸጥንም ሞክረዋል። ይህ ገንዘብ በእቁብ መልክ ተጠራቅሞ የተሻለውን ህልማቸውን ከማሳካቱም በላይ ከህጻናት ጋር ያላቸውን ቁርኝትም አጠንክሮላቸዋል።
ሰው ለሰው ምስረታ
የሶስተኛ ክፍል ተማሪ እያሉ ነበር ከአዕምሯቸው ጋር ስምምነት ላይ የደረሱት። ሰው እንዴት ይጣላል፤ እድሉን ባገኝ እነዚህን መሰብሰብ የህይወቴ መሰረት ይሆናል አሉ። ምክንያቱም በዚያ በጨቅላ አዕምሯቸው ህጻኑ በኩርቱ ፌስታል ቱቦ ውስጥ ተጥሎ የጉንዳን መጫወቻ ሲሆን እርሳቸው ደፍረው ባያዩትም ከጓደኞቻቸው ሰምተዋል።
ከክፍል ሲወጡ ግን ለማየት ሲሞክሩ አፈር ለብሶ ላይመለስ ተደፍኖበታል። ያ ጊዜ ለእርሳቸው ከባድ ነበር። እንቅልፍ የሚባል ነገር በዓይናቸው ሳይዞር ያደሩበት። ምንም ሊያደርጉለት ባለመቻላቸው ቆጭቷቸውም ለዓመታት ህልማቸውን እውን የሚያደርጉበትን ቀን ሲጠብቁ ቆዩ።
‹‹አምላክ የነገሩትን የማይረሳ የለመኑትን የማይነሳ ነው›› የሚሉት ወይዘሮ ዘመናይ፤ የዛሬ ሦስት ዓመት በቤተሰባቸው ቤት ውስጥ ከባዶ ተነስተው ስራውን እንደጀመሩት ይናገራሉ። መሄድ የሚችሉ ቀምተውም ሆነ ለምነው ይበላሉ። መሄድ የማይችሉትስ ማን ያግዛቸዋል ብለውም ህልማቸውን አውን ለማድረግ እንደገፋፋቸው ያስታውሳሉ።
ሰው ለሰውን ለመጀመር መጀመሪያ ያደረጉት በየጎዳናው እየሄዱ በዚህ ስቃይ ውስጥ ያሉ እናቶችና አባቶችን መሰብሰብ ነው። በእርግጥ ምን እንደሚያበሏቸው አያውቁም። ቢያንስ ይጠለላሉ፣ የተሻለ ልብስ ይለብሳሉ፣ ንጽህናቸውን ይጠብቃሉ፣ የህክምና አገልግሎት ያገኛሉ፣ እኔ ካለኝ ውስጥ እየተካፈሉም ይመገባሉ።
በቀን ሶስቴ ባይበሉም አንዴ ግን አላሳጣቸውም ብለው በማሰብም ነው በቅን ልቦናቸው ይህንን ያደረጉት። ግን ባዩት ነገር ሰዎች አውቀው እስኪያግዟቸው ድረስ ብዙ መፈተናቸውን አይረሱትም። በተለይ ህጻናት ድሮ እንጂ አሁን ይጣላሉ ብለው አለማመናቸውና እነርሱን ሲያዩ መሳቀቃቸው ከምንም በላይ ነገሮችን ፈታኝ እንዳደረገባቸው አይረሱትም።
አብላጫውን ስራቸውን የጀመሩት በህጻናት ፤ የአዕምሮ ህሙማን ሴቶችና አረጋዊያን ሲሆን፤ አሁን ላይ በአጠቃላይ 76 ተረጅዎችን አስጠልለው እየተንከባከቡ ይገኛሉ። የአዕምሮ ህሙማን ሴቶችን ከጎዳና ማንሳት እጅግ ፈታኝ ሆኖባቸውም እንደነበር ያነሳሉ። ነገር ግን ከእኛ ሴቶች የበለጠ የሚረዳቸው ማንም አይኖርምና በቻልኩት ሁሉ ለማገዝ ይህንን አድርጌያለሁም ብለውናል። መጀመሪያ ከመንገድ ላይ ይይዟቸውና ሰውነታቸውን ከአጣጠቡ በኋላ ወደ ሆስፒታል ይወስዷቸዋል። ወደ ራሳቸው መለስ ሲሉም በመርጃ ድርጅቱ ውስጥ እንዲኖሩ ያደርጓቸዋል። ይህ ደግሞ ብዙዎች ተስፋ እንዲኖራቸው እንዳደረገም ይናገራሉ።
33 አረጋውያን፣33 ህጻናትና 10 አዕምሮ ህሙማን ያቀፈው መርጃ ድርጅቱ፤ በርከት ያሉ ህጻናትን በጉዲፈቻ ሰጥቶ ልዩ ክትትል እያደረገ ነው። ከዚያ ባሻገር በህክምናው ዘርፍ ከመንግስት እስከ ግል ሆስፒታሎች ድረስ በህክምናው ድጋፍ እንዲደረግላቸውም ያግዛል።
በግል ደረጃ ያሉ የጤና ባለሙያዎችም የፈለጉት ላይ እንደሚረባረቡላቸው አንስተዋል። ነገር ግን መድሀኒት ላይ ሲደረስ ብዙ እንደሚቸገሩ አጫውተውናል። የአባላት ማሰባሰብ ስራ በመስራት ደመወዝና መድሃኒት መግዢያ እየተጠቀሙ መሆኑን ጠቁመው ሁሉም የተቻለውን ቢያደርግ ሳይሉም አላለፉም።
‹‹በጎነት ከራስ ሲመነጭ ፈተና ድል ይሆናል›› ብለው የሚያምኑት ባለታሪካችን፤ ሰው ለሰውን ሲመሰርቱ መንግስት ምንም አይነት ድጋፍ አላደረገላቸውም። በቤተሰቦቻቸው ቤት ውስጥ በመሆን ነው የልጅነት ህልማቸውን ለማሳካት የጣሩት። ግን መንፈሴ ሁለት አይነት ትግሎችን ያደርጋልና አሸናፊውን መርጫለሁ ይላሉ። ‹‹የሚያርፉበትን ቤት ከጨረስኩ በኋላ እናትና እህት ወንድሞቼን ሰብስቤ የማይጠብቁትን ፍላጎቴን አጋራኋቸው።
እነርሱ በሥራዬ ሁልጊዜ ስለሚገረሙ ቤርጎ የምሰራ ነበር የመሰላቸው። ሀሳቤን ስነግራቸው ግን ሁሉም ደንግጠዋል። ነገር ግን ከሀሳቤ ያፈነገጠ አንድም ሰው አልነበረም። በተለይ እናቴ ሁሉ ነገር አስደስቷት እያለቀሰች ‹‹ አንቺ እንዲህ ስታስቢ እኔ በዚህ እድሜ ላይ ሆኜ እንዴት እንቢ ማለት ይቻለኛል? ስራው ከባድ ነው እግዚአብሔር ያስችልሽ። ›› ነበር ያለችኝ።
የሚያበረታኝ ስላገኘሁ ደግሞ ይበልጥ ተደሰትኩ። ግቢ ውስጥ ቡና አፈላላሁና ተመራርቀን በነጋታው ከጓደኞቼ ጋር በመኪናዬ እየጫንኩ ለማምጣት ጎዳና ወጣሁ። ህልሜንም በአሸናፊው ድሌ አጠናቀቅሁም›› ነበር ያሉት ምስረታውን ሲያጫውቱን።
ጎዳና ላይ ያለ ሁሉ የተሻለ ነገር ያስፈልግሀል ሲባል መቼም እንቢ የሚል የማይመስላቸው ወይዘሮ ዘመናይ፤ ብዙዎቹ እዚያ ወስዳችሁ ልታፍኑን ነው፤ አንሄድም ይሏቸው እንደነበር አይረሱትም። አንሄድም ብለው የሚጮሁ ሁሉ እንደገጠማቸው ያስታውሳሉ። በዚህም ፈቃዳቸው ሳይኖር መውሰዱ ለበለጠ ችግር ማጋለጥ እንደሆነ አምነው በሦስት ሰዎች ሥራውን እንደጀመሩትም አጫውተውናል።
በዚህም እስካሁን ድረስ ከሞቱት ውጪ 132 ሰው በድርጅታቸው እንዳስተናገዱ አውግተውናል። ለጉዲፈቻ በሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ አማካኝነት የሰጡት ልጅም እንዳለና ያንንም ክትትል እንደሚያደርጉ በወጋችን መካከል አንስተውልናል።
በልጆቹ ጉዳይ ማታ የሚበላው ሲያሳስባቸው እንቅልፍ እንደሚያጡ ያጫወቱን ወይዘሮ ዘመናይ፤ አጣጥበው ካስቀመጧቸው በኋላ የሚመግቧቸው ሲጠፋ እጅግ ያዝኑ እንደነበር የሚያስታውሱት ወይዘሮ ዘመናይ፣ እኔ የማልበላበትና እነርሱ በልተው እፎይ የምልበትን ጊዜም አሳልፌ አውቃለሁ ይላሉ። ሰው መልካም ነገር ለማድረግ ጉዳዩን ነግረውት እርዱኝ ሲባል ለሰብሳቢው የሚለግስ ይመስለዋል።
በዚህ ደግሞ መጣችሁም የሚሉም አይጠፉም። ይህ በጣም የተሳሳተ ምልከታ ነው። ምክንያቱም ለመልካም ነገር መለመን የለበትም። አስቦ መስጠት ልምድ ሊሆን ይገባል ይላሉ።
በጅማ ከተማ የበጎአድራጎት ድርጅት የለም። ይህ ደግሞ በጤናው ዘርፍ ለማገዝ፣ መድሃኒት ብዙ እድሎች ነበሩት። ሆኖም የግንዛቤው ማነስ አንድ ሰው ብቻውን እንዲለፋ ያደርገዋል። እኔንም እየገጠመኝ ያለው ይኸው ነው። ስለዚህም መንግስትን ጨምሮ እንዲህ አይነት በጎ ሥራ የሚሰሩ አካላትን መደገፍ ግዴታው እንደሆነ ማሰብ ይገባልም ባይ ናቸው።
ማህበረሰቡም ቢሆን ካለው ላይ አንድ በመቶውን ማካፈል ቢለምድ ብዙዎችን መታደግ ይቻላል። እናም ይህ ነገር ቢታይ ይላሉ። እኔ ዛሬ ጀምሬያለሁ ጨራሹ ነገ የሚመጣው ትውልድ ነው። ትውልዱን ደግሞ መስጠት ካላስተማርነው ምንም ሊያደርግ አይችልም። ስለሆነም በተለይ ቤተሰቦች ይህንን ሀላፊነት መወጣት ቢችሉ አገርን ከችግር ማላቀቅ እንችል ነበርም ብለውናል።
በጎነትን ከአባት
‹‹ ነገ ሌላ ቀን ናት፤ ዛሬን አይታችሁ ሰውን እንዳትበድሉ። መጥፎ ነገርም እንዳትሰሩ። ፖሊስ ይህንን ያደርገኛል ብላችሁም የወደቀን ረግጣችሁ አትለፉ። ምክንያቱም ያንን ሰው ታድጋችሁት ዛሬን ታሻግሩት ይሆናል። ለዚህ ደግሞ አምላክ እንደሚያግዛችሁ እመኑ። ኪሴ ባዶ ይሆናል ብላችሁም በፍጹም አትጠራጠሩ።
ክፍያውን ከአደረጋችሁት በላይ ታገኙታላችሁና።›› ከልምዳቸውና ከሚያደርጉት ነገር ለልጆቻቸው ዘወትር የሚመክሩት ነገር ነበር። እንግዳችንም በዚህ እምነት አላቸው። ምክንያቱም ለዛሬ እዚህ መድረሳቸው ይህ ምክር ገንብቷቸዋል። ሰዎችን በተለየ አይን እንዲያዩም ረድቷቸዋል። ከምንም በላይ ደግነት ከቤተሰብ የሚወሰድ መሆኑን አሳይቷቸዋል። ስለዚህም ሰዎችም እንደርሳቸው ቢሆኑ ይመኛሉ። ለልጆቻቸውም ይህንን ያስተምራሉ።
ፈተና
እንግዳችን በየጊዜው የተለያየ ፈተናን አሳልፈዋል። ነገርግን እንደ ሁለቱ የሆነባቸው ነገር እንደሌለ ያነሳሉ፤ የባለቤታቸው ከዚያም የአባታቸው ሞት እና የሚያሳድጓቸው አራት ህጻናት በአንድ ጊዜ መታመም። ነገሩ እንዲህ ነበር። የባለቤታቸው ሞት በገንዘብ እጦት እንዲሰቃዩና የጀመሩትን ትምህርት ቤት ዘግተው ብን ብለው እንዲወጡ አድርጓቸዋል። ከዚያም አባታቸው ጋር ለመኖር እድሉን አግኝተው ገና ሳይጠግቧቸው እርሳቸውንም ሞት ነጥቋቸዋል።
በዚህም የመኖር ምስጢራቸውን ሁሉ የተፈታተነው ነበር። ጠንካራ ሆነው እንዳይቀጥሉ አድርጓቸዋል። ሆኖም ጥንካሬያቸውን በቀላሉ መመለስ የሚችሉና ተስፋ የማይቆርጡ በመሆናቸው በእናታቸው ቁጣና በእህትና ወንድሞቻቸው ድጋፍ እንዲሁም በጓደኞቻቸው ብርታት ሰጪነት ዳግም ብርቱ ሴት ሆነው ቀጣዩን ጉዟቸውን ጀምረዋል።
ሌላው ፈተና የሚያሳድጓቸው ህጻናት ታመውና ተርበው ማየት ሲሆን፤ በተለይ አንድ ጊዜ ያለቀሱትን መቼም አይረሱትም። ይህም አራት ህጻናት በአንድ ጊዜ የታመሙባቸው ነበር። ከሁሉም ደግሞ አንዱ ለማስታመምም አስቸጋሪ ነበር።
ምክንያቱም ጭንቅላቱ ከሰውነቱ በላይ በመሆኑ ህክምና እንዲያገኝ ማድረግ በጣም ከባድ ነው። አራት ቀን ሙሉ ከእቅፋቸው ሳይለይም ነበር ህክምና ሲሰጠው የቆየው። ጭንቅላቱ የተለያዩ ፈሳሾችን እያመነጨ ስለሚፈስ ሽታውና መጠራረጉ ስለሚከብዳቸው ሞግዚቶች ደግሞ በፍጹም ሊነኩት አልወደዱም።
ከህክምና በኋላም ቢሆን ለማቀፍ እንኳን የሚያግዝ ሰው አልነበረም። እንዴት እንደሚድንላቸውም ያሳስባቸው ጀመር። ከሁሉም በላይ ደግሞ የት አድርገው እንደሚንከባከቡት ግራ ገብቷቸው ያውቃል። ህጻናቱ ጋር እንዳይገባ በጣም ያስፈራል። ከጭንቅላቱ በላይ ሰውነቱ ጭምር መፈንዳት ጀምሯል። ስለዚህም ሌሎቹ ላይ ችግር እንዳይፈጥር በማሰብ ሊቀላቅሉት አልወደዱም።
ሞግዚቶችን በእንክብካቤ አግዙኝ ሲሏቸው ይበልጥ ሥራ እየለቀቁ ሄዱ። ስለዚህም ያላቸው አማራጭ ራሳቸው ጋር አድርገው መንከባከብ ነው። ሶስት ወር ሙሉም ይህንን ስቃይ አሳለፉ። ግን ለእርሳቸው ሳይሆን ለእርሱ ነበር ያሰቡት። በመጨረሻ ህይወቱ አለፈ።
ይህ ስቃይ ግን ብዙ ትምህርት ሰጥቷቸው እንዳለፈ ያምናሉ። በተለይ ሁኔታው የገጠማቸው መጀመሪያ አካባቢ መሆኑ የሥራውን ክብደት እንዲረዱ እንዳገዛቸው ይናገራሉ።
ምስጋና
የጅማ ዩኒቨርሲቲ ግብርና ኮሌጅን በጣም ያመሰግኑታል። ምክንያቱም ከምስረታው ጀምሮ ከዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ በተጨማሪ ኮሌጁ እየተሳተፈ ብዙ አግዟቸዋል። ልክ እንደቤታቸው የሚሰሩ አባላትን ብቻ ሳይሆን ለአፓረንት የሚወጡ ተማሪዎችንም ይመድብላቸዋል። በዚህም ተረጂዎቹ ሙሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርገዋል።
አትክልትና ፍራፍሬ በመትከል ፣ ዶሮ በማርባትም ሙያዊ ድጋፍ እያደረጉ ሁሉም ውጤታማ እንዲሆን ለፍተዋል። እናም አምላክ ለውለታቸው ይክፈላቸው ይላሉ። ከቦርድ አባልነት እስከ ሌላ ድጋፍ ድረስ የሚሳተፉ አካላትም ምስጋና ይግባቸውም ብለዋል።
መልዕክት
ሰው ለሰው ያልኩበት ምክንያት የሰው ልጅ ለሰው መኖርም፣ መሞትም አለበት ብዬ ስለማምን ነው። ሰው ብቻውን ይኖር ዘንድ መልካም አይደለም እንደተባለ ሁሉ ሰው ለሰው እየሆነም ሊኖር ይገባዋል። ከፍጥረታት ሁሉ ትልቁ ሰው በመሆኑ እርስ በእርስ መከባበርና መድሃኒት መሆንም አለበት። ስለዚህም ይህንን እምነቴን ለማሳየት ድርጅቱን መስርቼዋለሁ የሚሉት እንግዳችን፤ ሰዎች ቆራጥ ቢሆኑ ደስ ይለኛል።
አንዴ በአዕምሮ ውስጥ የተሳለና በአላማ የተቆመበት ነገር ሳይፈሩ ከገቡበት ለስኬት የማይበቁበት አንድም ነገር አይኖርም። ለዚህ ደግሞ ደፋርም መሆን ያስፈልጋል የመጀመሪያ ምክራቸው ነው።
የምንፈልገውን ነገር ለብዙ ሰው ማማከር አይገባም። ምክንያቱም ከአላማ የሚያሰናክል ብዙ ሀሳብ ይመጣል። ስለዚህም ከዚያ ይልቅ ቆራጥ መሆንና ትግስትን ከጽናት ጋር አስተባብሮ መያዝ ከሁሉም በላይ ያስፈልጋል። የሚሰሩት ነገር ጥሩ መሆኑን ማመንም ይገባል። ሰው እንዳቅሙ እንደሚሰራ ማሰብም ተገቢ ነው። እናም አላማ ሲኖር ተቃዋሚ ይበዛልና ያንን ለማሸነፍ ጠንካራ መሆን ከሁሉም ይጠበቃል። የተሻለውን እንደሚያገኙ እያመኑ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል ምክራቸው ነው።
ላለምነው ነገር አይቶ እንዳላየ ማለፍ፣ ችግር ሲመጣ ተስፋ አለመቁረጥ፣ እችላለሁ ብሎ ማመንና ግቡንና ወደፊት የሚሰጠውን መልካም ውጤት እያዩ መስራትም ይገባል። ለእንቅልፍ ጊዜ አለመስጠትም ዋናው ነገር ነው። ምክንያቱም ብዙ ድሎት ካለ ብዙ ውጤት ማፈስ አይቻልም። ትውልዱ ከራሱ አካፍሎ ለሌላው መስጠትን እንዲለምድ ማስተማርም ግድ ነው። በተለይ በዚህ ወቅት ብዙ ነገሮች በቆሸሹበት ፤ መቼ እንደምንሞት በማናውቅበት ጊዜ ምሳሌ መሆን ከምንም በላይ ያስፈልገናልም ይላሉ።
ይቺ ዓለም ለሁሉም እኩል ናት ። ዛሬ ብትሰጠን ነገ ታሳጣናለች። ዛሬ ብታሸንፈን ደግሞ ነገ እናሸንፋታለን። ስለሆነም ለሁሉም ጊዜ አለው በማለት በጎነታችንን እናብዛ። መልካምነት ዋጋ ያስከፍላልና ሁሌም ፍጹም መልካም ሰው እንሁን የማሳረጊያ ምክራቸው ነው።
አዲስ ዘመን የካቲት 28/2013