አስናቀ ፀጋዬ
የዓረብ ሰላጤ አገራት የሆኑት ሳውዲ ዓረቢያ፣ ኩዌት፣ ኢራቅ፣ ባህሬን፣ኳታር፣ የተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶችና ኦማን በነዳጅ አምራችነትና ሻጭነት በዓለም አቀፍ ደረጃ የግምባር ቀደምትነቱን ስፍራ ጨብጠዋል።
አብዛኛው የነዳጅ ሀብት የሚገኘውም በእነዚሁ ሀገራት ውስጥ በመሆኑ በዓለም አቀፍ ምጣኔ ሀብታዊ እንቅስቃሴ ላይ የሚፈጥሩት ተጽዕኖም ቀላል የሚባል አይደለም።ለዓለም ገበያ የሚያቀርቡት ነዳጅ አንዴ ከፍ ሌላ ጊዜ ዝቅ ሲል የሌሎች አገራት ኢኮኖሚም አብሮ መንገራገጩ የዚሁ ተጽዕኖ ማሳያ እንደሆነ ይነገራል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንዳንድ በቴክኖሎጂ የመጠቁ አገራት ለሃይል ፍጆታቸው የሚጠቀሙበትን ነዳጅ በመቀነስ ታዳሽ ወደሆኑና ዝቅተኛ የካርበን ልቀት ወዳላቸው የኤሌክትሪክ ሃይል መጠቀም እየተሸጋገሩ መምጣታቸውን ተከትሎ የባህረ ሰላጤው አገራት የነዳጅ ገበያቸው እየተቀዛቀዘ ስለመምጣቱ ተንታኞች ይናገራሉ።በዚህም ምክንያት በነዳጅ ዋጋ ላይ ቅናሽ እስከማድረግና የምርት መጠናቸውን እስከመቀነስ ደርሰዋል።
በተለየ ደግሞ በኮቪድ ወቅት አገራት ድምበሮቻቸውን መዘጋታቸውን ተከትሎ ነዳጅን ወደተቀረው ዓለም በብዛት ሲልኩ አልቆዩም።ወትሮም ቢሆን በነዳጅ ምርት የወጪ ንግድ ላይ የተንጠለጠለው የባህረ ሰላጤው አገራት ኢኮኖሚ በኮሮና ወረርሽኝ ጣጣ ክፉኛ በመጎዳቱ ለኢኮኖሚያቸው መደገፊያ አገራቱ በተለይ ባለፈው ዓመት ዓይናቸው ወደ ብድር ማማተሩ አልቀረም።
ሆኖም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የነዳጅ ዋጋና ኢኮኖሚያቸው መሻሻል ማሳየቱን ተከትሎ አገራቱ ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው በመመለሳቸው ልክ እንደባለፈው ዓመት ሁሉ ዘንድሮ ወደ ብድር እንደማይገቡ ተንታኞችን ጠቅሶ ሲ ኤን ቢ ሲ ኒውስ ከሰሞኑ ዘግቧል።
ተንታኞቹ ለ ሲ ኤን ቢ ሲ እንደተናገሩት የባህረ ሰላ ጤው አገራት ኮቪድ ያሳደረባቸውን ተጽዕኖ ለመቋቋም ባለፈው ዓመት ከፍተኛ ገንዘብ መበደራቸውንና ዕዳቸውም ጣራ ስለመድረሱ ጠቁመዋል።ይህም እስካሁን ከነበረው የብድር ታሪካቸው ጋር ሲወዳደር ትልቅ ሪከርድ መሆኑንና ይሁን እንጂ በተያዘው የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ልክ እንደአምናው ከፍተኛ ገንዘብ የሚበደሩበት ዕድል እንደማይኖር አስታውቀዋል።
ይህም ሊሆን ያቻለው የነዳጅ ዋጋ መሻሻልና የቀጠናው ኢኮኖሚ በኮሮና ወረርሽን ከደረሰበት ተጽዕኖ ማገገሙን ተከትሎ በገልፍ ኮኦፕሬሽን ካውንስል ውስጥ ያሉ አገራት ወደቀደመው የኢኮኖሚ ሁኔታቸው በመመለሳቸው መሆኑን ተንታኞቹ ተናግረዋል።
‹‹2020 የተለየ ዓመት ነበር›› ሲሉ በገልፍ ኮኦፕሬሽን ካውንስል መሪ ተንታኝ የሆኑት ትሪቮር ኮሊነን ለሲ ኤን ቢ ሲ የተናገሩ ሲሆን ወደፊት ስንሄድ ልክ እንደ 2020 ተመሳሳይ የብድር ፍላጎት በአገራቱ በኩል አለ ብለን አናስብም፤ ከዚህ ይልቅ ከ2021 እስከ 2023 ድረስ የበጀት ጉድለትና የብድር ዕዳ ማስተካከያ ፖሊሲ እንደሚኖር እንጠብቃለን ብለዋል። ‹‹የበጀት ጉድለቱ ያነሰ እንደሚሆንና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴውም ጠንካራ እንደሚሆን እናስባለን›› ሲሉም ተንታኙ አክለው ገልፀዋል።
ከካፒታል ኢኮኖሚ በተገኘው መረጃ መሰረት ባለፈው ዓመት ሳውዲ ዓረቢያ፣ የተባበሩት ዓረብ ኢምሬቶች፣ ኳታር፣ ባህሬንና ኦማን ያሳወቁት አጠቃላይ ዕዳ 42 ነጥብ 1 የአሜሪካን ዶላር መሆኑን የጠቀሰው ሲ ኤን ቢ ሲ፤ ይህ አሃዝ ቀደም ሲል በ2019 ከነበረው የ33 ነጥብ 5 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ዕዳ የ25 ከመቶ ብልጫ እንዳለው ለንፅፅር አስቀምጧል።
የባህረ ሰላጤው አገራት የብድር ዕዳ ጣራ የነካው የነዳጅ ወጋ ማሽቆልቆሉን ተከትሎና የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በኢኮኖሚያቸው ላይ ያሳደረው አሉታዊ ተጽዕኖ ነው›› ሲሉ በኦክስፎርድ ኢኮኖሚክስ የመካከለኛው ምሥራቅ ዋና የኢኮኖሚ ተንታኝ ስኮት ሊቨርሞር አስታውቀዋል።
ይሁንና በአሁኑ ወቅት በተለይ በአሜሪካን ሀገር ከባዱን የክረምት ወቅት ተከትሎና የዓለም ምጣኔ ሀብትም እየተሻሻለ በመምጣቱ የነዳጅ ዋጋም አብሮ በመሻሻሉ የቀጠናው አገራት በዚህ ዓመት ወደተጨማሪ ብድር እንደማይገቡ ተንታኙ ጠቅሰዋል።እነዚህ ምክንያቶች ለባህረ ሰላጤው አገራት የበጀት ጉድለት ማሟያ ትልቅ እረፍት የሚሰጡ መሆናቸውንም ሊቨርሞር ተናግረዋል።
አሁንም ቢሆን የቀጠናው አገራት የብድር ፍላጎት የቀጠለ ሲሆን በ2021 ሀገራቱ የቦንድ ሽያጭ ጥያቄ እንደሚያቀርቡ ይጠበቃል ሲል የሲ ኤን ቢ ሲ ዘገባ ያመለከተ ሲሆን ሳውዲ ዓረቢያ በዚህ ዓመት አስቀድማ 5 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ከቦንድ ሽያጭ ገቢ ማሰባሰብ መቻሏን እና ባንኮች በተለይ የበላይ ለሆኑ የአውሮፓ ገዢዎች የቦንድ ሽያጮችን እንዲያቀርቡ ማድረጓንም ገልጿል።
በካፒታል ኢኮኖሚክስ የመካከለኛው ምሥራቅ እና የሰሜን አፍሪካ ኢኮኖሚስት ጄምስ ስዋንስተን በበኩላቸው “በባህረ-ሰላጤው ያሉ መንግሥታት አሁንም ከሌሎች የፋይናንስ ዓይነቶች ይልቅ ለዓለም አቀፍ ተቋማት ቦንድ የማቅረብን ሁኔታ ለጊዜው የሚደግፉ ናቸው” ብለዋል።ይህ ሁኔታ የዶላር ገቢ የበጀት ጉድለትንም ሆነ የወቅቱን የሂሳብ እጥረት ሊሞላ የሚችል ከመሆኑም በላይ መንግሥት በውጭ ምንዛሪ ክምችት ላይ አላስፈላጊ የዶላር ምንዛሬዎችን በተሻለ እንዲከላከል ያስችለዋል ብለዋል ፡፡
‹‹የሀገር ውስጥ ባንኮች በዓለም አቀፍ ገበያዎች ላይ ማዘንበላቸው የመንግሥት ቦንዶችን አይገዙም እንደማለት ነው›› ሲሉም ኢኮኖሚስቱ ተናግረው የብድር ወጪዎች ዝቅተኛ እንደሆኑ እና በቀጠናው ያሉ መንግሥታት የብዝሃነት መርሃግብሮችን ለመደገፍ ቦንድ ማቅረብ እንደሚችሉ ጠቅሰዋል።አገራቱም ቢሆኑ ይህ ተስማሚ መሆኑን ከተረዱ የዳበረ ዕዳን እንደገና በገንዘብ ለመደገፍ ወደ ገበያ መምጣትን ሊመርጡ ይችላሉ ብለዋል።
የመንግሥት ዕዳ በባህረ ሰላጤው አገራት በአንፃራዊነት አነስተኛ ነው ሲሉ ገልፀዋል።አጠቃላይ የብድር ዕዳው በአግባቡና በድጋሚ የገንዘብ ድጋፍ መሰተካከል ከቻለ የገልፍ ኮኦፕሬሽን ካውንስል መንግሥታት በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ቀድሞው የኢኮኖሚ ሁኔታቸው ይመለሳሉ ሲሉም ሊቨርሞር ጨመርው ተናግረዋል።
የካፒታል ኢኮኖሚክስ ተንታኙ ስዋንስተን የኦማንና የባህሬን ጉዳይ ቢያሳስባቸውም ከፍተኛ የብድር ዕዳ በቀጠናው ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ላይ የሚያሳድረው የከፋ ተጽዕኖ እንደማያሳድር ጠቁመዋል።
የዕዳና ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ጥመርታ የአገራት የህዝብ ዕዳን የማስመለስ ብቃት መለኪያ ነው ያሉት ስዋንስተን የዚህ ጥመርታ ከፍተኛ መሆን ምን አልባት አገራት የውጭ የብድር ዕዳዎቻቸውን ለመከፍል መቸገራቸውን ማሳያ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በነዚህ ዓመታት የመንግሥት የዕዳ መጠን በሁለቱ አገራት በከፍተኛ ደረጃ አሻቅቧል ያሉት ስዋንስተን ሁለቱም አገራት የመንግሥት ፋይናንስን ለማስተካከል የፊስካል ፖሊሲያቸውን ማጥበቃቸውን ገልፀዋል።ሆኖም የበጀት ጉድለቶችን እና የሕዝብ ዕዳን ለመቆጣጠር ረዘም ላለ ጊዜ የሚቆይ የበጀት ቅነሳ በመንግሥታቶቻቸው በኩል ማድረግ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
እንደ ኤስ ኤንድ ፒ ገሎባል ሬቲንግ ከሆነ ደግሞ የባህሬን መንግሥት ዕዳና አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ጥምርታ በዚህ ዓመት 115 ከመቶ እንደሚሆን የተጠበቀ ሲሆን የኦማን ደግሞ እስከ 84 ከመቶ ሊደርስ እንደሚችል ተተንብለዋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 24/2013