በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
የዓድዋ ድል በሰው ልጆች ታሪክ ወሳኝ መታጠፊያ ነው ። ወሳኝ ምዕራፍ ነው ። የቅድመ ዓድዋዋ አለም በድህረ ዓድዋ እንደነበረች አልቀጠለችም ። ታሪክ ተቀይሯል ። ተፅፏል ። ከዓድዋ ድል በኋላ በጭቆና በቅኝ ግዛት ይማቅቁ የነበሩ የሰው ልጆች ታሪክ ተቀይሯል ። ቅኝ ገዥነት ፣ እስከ አፍንጫው የታጠቀ የአውሮፓ ወራሪ በጥቁር ሕዝብ ሊረታ ሊሸነፍ እንደ ሚችል አይነ ጥላን ገፏል ። አንቅቷል ። ቀስቅሷል ። አደራጅቷል ። የአርነት ችቦን ለኩሷል ። የነጭ የበላይነትን ለመሞገት ወኔ ሆኗል። እናም ዓድዋ ከፍታ ነው ። በትውልዶች ቅብብል ከሩቅ የሚታይ እንደ ሶሎዳ ባለ ግርማ የተራራ ሰንሰለት ነው። ዓድዋ የሰው ልጆችን የተዛባ ግንኙነትና ትርክት ያረቀ እንደገና የበየነ ጀግና ነው። የጥቁር ሕዝቦች ልዕልና ነው። የሰው ልጆችን ውስብስብና ትብትብ የጎርዲዮስ ቋጠሮ የፈታ ጥበበኛ ነው። የነጻነትና የእኩልነት ከፍ ሲልም የአምሳለ ፈጣሪ ፍጡርነት ምስክር ነው ። ዓድዋ ማርሽ ቀያሪ ነው። ቀሰስተኛውን የጥቁርና የቅኝ ተገዢ ሕዝቦችን ታሪክ ወደ ነጻነትና እኩልነት ያፈጠነ ። ስለ ዓድዋ ባሰብሁና በተነሳ ቁጥር አንድ ጥያቄ ወደ አእምሮዬ ይመላለሳል። ዓድዋን ተጠቦና ተጨንቆ የሰራ መሪና ሕዝብ የጨቋኝ ተጨቋኝ የጎርዲዮስ ቋጠሮ መፍታት ተስኖት ለ122 አመታት መማሰኑና ባለበት መርገጡ ማለትም ለውጡ እስከ ባ’ተበት 2010 ዓም ድረስ መቀጠሉ እንቆቅልሽ ይሆንብኝ ነበር ። ደሙን አፍስሶና አጥንቱን ከስክሶ ነጻነትን ለዘረ አዳም ያለ ልዩነትና ስስት ያበረከተና ያደላደለ መሪና ሕዝብ በነጻነት ጠኔ ለዚህ ያህል ጊዜ መቆራመቱ እርስ በርሱ ይጋጭብኝ ነበር ።
በነገራችን ላይ የጎርዲዮስ ቋጠሮ የአስቸጋሪ ፣ የውስብስብ ነገር ተምሳሌት ሲሆን ጎርዲዮስ በዛሬዋ ቱርክ አካባቢ የፍርጂያ ንጉስ ነበር ። ቋጠሮውን ወደፊት የሚነሳ የእስያ ጠቢብ ንጉስ ይፈታዋል የሚል ሀተታ ተፈጥሮ / myth / የነበር ቢሆንም ቋጠሮውን ታላቁ አስክንድር በሰይፍ ቆርጦታል ። አልፈታውም ። ከጥበብና ከማስተዋል ኃይልንና ጉልበትን መጠቀም መርጧል ። የአፄ ምኒልክ ፣ የልጅ እያሱን ፣ የንግስት ዘውዲቱን የሀይለስላሴን አቆይተን ፤ እንደ ታላቁ እስክንድር በሰይፍ የቆረጥነውን የታህሳስ ግርግር ፣ የ66 አብዮት እና የትህነግ አገዛዝ ልብ ይሏል ። ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲንከባለል የመጣውን ቋጠሮ በጥበብ ስላልፈታነው ቋጠሮው ይብስ ተተብትቦ ለእኛ ቆይቶናል ። የዓድዋ 125ኛ አመት የድል በዓል ከቀደሙት 122 አመታት( ከለውጡ ማግስት በኋላ ያሉትን ሶስት አመታት ሲቀነሱ ፤) ወዲህ የዚችን ሀገር ቋጠሮ ለመቁረጥ ሳይሆን በማስተዋል ፣ በጥበብና በእውቀት ለመፍታት የማይተካ ሚና ባለው አሳታፊና አካታች ለውጥ ስር በሚካሄድ ምርጫ ዋዜማ የሚከበር መሆኑ የዘንድሮውን የዓድዋ የድል በዓል ልዩ ያደርገዋል ። እኛ ግን ቋጠሮን እንደ ታላቁ እስክንድር በግብታዊነት በሰይፍ መቁረጥ ስለተጋባንና ስለለመደብን በትዕግስትና በጥበብ ቋጠሮውን ለመፍታት መታገስ ተስኖን በሰይፉ የሚቆርጥ መንግስቱንና መለስን እንናፍቃለን ። ከዚህ መርገምና አባዜ ሰብረን ካልወጣን የምንመኛትን ሀገር እና የምንቋምጥለትን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ማቆም እንዳማረን ይቀራል ። ይህን ስል ለውጡ ፍጹም ነው እያልሁ እንዳልሆነ ይመዝገብልኝ ። ለነገሩ ፍጹም ለውጥ በዚች ምድር ተከስቶ አያውቅም ። አበው እማው ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ ስለ”ቋጠሮዎቻችን” ይህን ያህል ካልሁ ወደ ተነሳሁበት የዓድዋ የሕብረ _ብሔራዊነት ጉዳይ ልመለስ ።
ይህ የዓድዋ 125ኛ የድል በዓል ልዩ የሚያደርገው ሌላው ታሪካዊ አጋጣሚ ፤ ከሀዲው ትህነግ ታሪክና ትውልድ ይቅር የማይለውን ክህደት ፈጽሞ አባት ፣ አያት ቅደመ አያቶቻችን ከዓድዋ እስከ ካራማራ ደማቸውን አፍስሰው እና አጥንታቸውን ከስክሰው ያቆዩልንን ሀገር ህልውና ላይ አደጋ ደቅኖ ድባቅ በተመታበትና በተደመሰሰበት ማግስት መሆኑ ነው ። ኢትዮጵያውያንን በማንነት ከፋፍያቸዋለሁ ፣ አለያይቻቸዋለሁ፣ አራርቄያቸዋለሁ እንዲሁም ጊዜውን ጠብቆ እንዲፈነዳ በኢፌዴሪ ሕገ መንግስት ያጠመድሁትን ፈንጅ አፈንድቸዋለሁ በሚል እርግጠኝነት የተሳሳተ ስሌትና መደምደሚያ ከጀርባ ሀገራችንን ቢወጋም ፤ ኢትዮጵያውያን በአንድነት ዳር እስከዳር በመትመም ከሀዲውን ትህነግን በሕብረ _ ብሔራዊነት በዘጠኝ ቀን ድል ሊነሱት ችለዋል ። ለዛውም ሰራዊቱ በውድቅት ሌሊት በገዛ አዛዦቹና አባሎቹ ከተጨፈጨፈ እና ከነፍስ ወከፍ እስከ ከባድ የጦር መሳሪያው በተዘረፈ ማግስት። ከዓድዋው ፣ ከካራማራውና ከሰሞነኛው የትግራይ ክልል አንጸባራቂ ድል ጀርባ ህብረ _ ብሔራዊነታችንና አንድነታችን እንደ ዓድዋው አለ ። ባለፉት ሶስት አመታት ከወደቀበት ትቢያው ተራግፎ ተነስቷል ።
አኩሪው የጥቁር ሕዝቦች ድል ዓድዋ የተመዘገበባቸው በርካታ ምክንያቶቸ አሉ ። ዘመን የተሻገረ የሀገረ መንግስት ልምምድ ፣ የሀገር ፍቅር ፣ የአፄ ምኒሊክና የእቴጌ ጣይቱ የመሪነት ብቃት ፣ የአፄ ምኒልክ ስሪተ መንግስት ብዝሀነትና ሕብረ_ብሔራዊነት ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እና የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ሕብረ _ ብሔራዊነት እና የአገናኝ ድልድይነት ፣ ወዘተረፈ ዋና ዋናዎች ናቸው ። አፄ ምኒልክ የሰርጸ ድንግል የልጅ ልጅ የሆኑት የንጉስ ሳህለስላሴ ልጅ የንጉሥ ሀይለመለኮት ልጅ ናቸው ። በዚህ ማንነት ውስጥ ከሰለሞን የሚመዘዝ አይሁድነትና ከንግስት ሳባ የሚመዘዝ ኢትዮጵያዊነት የሚቀዳ ሕብረ _ብሔራዊነት አለ ። የኦሮሞና የአማራ ማንነትም ተንሰላስሎ ሳይጣላ በአንድ ላይ አለ ። አፄ ምኒልክ አማራና ኦሮሞ ሲሆኑ እቴጌ ጣይቱ የኦሮሞና የእስልምና የኋላ ማንነት አላቸው ። የንጉሱን ሹማምንት ብንመለከት ፤ ሼህ ሆጅሌ ጉምዝ/በርታ ፣ አፈ ንጉስ ነሲቡ ኦሮሞና አማራ ፣ ፊትአውራሪ ገበየሁ የአብቹ ኦሮሞና የቡልጋ አማራ ፣ ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ ኦሮሞና ጉራጌ ፣ ደጃዝማች ባልቻ ሳፎ ኦሮሞና ጉራጌ ፣ ወዘተረፈ ሁለትና ከዚያ በላይ የጎሳ ማንነት ነበራቸው ። እንግዲህ የአፄ ምኒልክ መንግስት ሕብረ_ብሔራዊ ከነበረ ፤ ወዶ ገቡ 100ሺህ የገበሬ ጦሩም የዚህ ብዝኃነትና ሕብረ _ ብሔራዊነት ድምር ውጤት መሆኑ አያጠያይቅም ። ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ ፣
“የኢትዮጵያ ታሪክ 1847_1983” ፤ በተሰኘው መጽሐፋቸው ገጽ 85 ላይ ፣ “የምኒልክ ጦር…ድፍን ኢትዮጵያን የወከለ በመሆኑም ልዩ ትኩረት የሚሰጠው ነበር ። ለንጉሠ ነገሥቱ ነጻነትና የአገር ድንበርን የማስከበር ጥሪ ጦር ያልላከ የአገሪቱ ክፍል አልነበረም ።” እንዳሉት በዚህ አኩሪ ድል ያልተሳተፈ ጎሳ አልነበረም ።
የኢትዮጵያ የጦር አበጋዞችን ስብጥር ስንመለከት ጦርነቱ በሕብረ_ብሔራዊነት የተመራና የተፋለሙለት መሆኑን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል ። ራስ ሚካኤል ከወሎ ፣ ራስ መኮንን ከሐረር ፣ ራስ አሉላና ራስ መንገሻ ከትግራይ፣ ንጉሥ ተክለሀይማኖት ከጎጃም ፣ ራስ ወሌ ከየጁ ፣ መንገሻ አቲክም ከጎንደር ፣ ፊታውራሪ ጌጃ ከከምባታ፣ ወዘተረፈ የተውጣጡ ነበሩ ። በስራቸው አማራ ፣ ኦሮሞ ፣ ትግራይ፣ አገው ፣ ቆቱ ፣ ሀረሪ ፣ ሶማሌ ፣ ጉራጌ ፣ ወላይታ ፣ ሲዳማ ፣ ጎፋ ፣ ሀድያ ፣ ከምባታ ፣ ከፋ ፣ ሸካ ፣ ጉምዝ ፣ ሽናሻ ፣ ጋምቤላ ፣ ወዘተረፈ ተሰልፏል ። ከሀይማኖት አንጻር ሲታይ ክርስቲያን ፣ እስላምና እና እንደ ዋቄ ፈና ያሉ የሌሎች እምነት ተከታዮች በስብስቡ ነበሩ ። የድሉ ሚስጥር ይህ ሕብረ_ብሔራዊነት ነው ። ይህ አንድነት ነው ። የሀይማኖት አባቶችን ፣ ሴቶችን ፣ በገና ደርዳሪዎችን ፣ አለም አጫዋቾችን
/አዝማሪዎችን/ ፣ ነጋሪት ጎሻሚዎችን ፣ መለከት ነፊዎችን ፣ አቀንቃኞችን ፣ አቅራሪና ፈካሪዎችን እና ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎችን ያሳተፈ በመሆኑ ባለ ፈርጀ ብዙ ብዝኀነትም ነበረው ። እንዲህ በአግባቡ የሚጠቀምበት አስተዋይና ብልህ መሪ ሲገኝ ሕብረ_ብሔራዊነትና ብዝኀነት ኃይል ጉልበት ይሆናል ። በአንጻሩ እንደ እፉኝቱ ትህነግ ለልዩነት ፣ ለጥላቻ ፣ ለፈጠራ ትርክትና ለከፋፍሎ መግዛት ከተጠቀሙበት መጨረሻው የማያባራ ቀውስና ግጭት ይሆናል ።
በዚህ ሕብረ_ብሔራዊነት ደምቆ በተንጸባረቀበት ጦርነት 100ሺህ ሰዎችና ከ25ሺህ በላይ ፈረሶችና ሌሎች የጋማ ከብቶች ተሳትፈዋል ። በአምባላጌ ፣ በመቐለና በዓድዋ በሺህዎቹ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ደም ፈሷል ። አጥንት ተከስክሷል ። የዛሬው ነጻነታችን እና የዛሬዋ ኢትዮጵያ በአማራው ፣ በኦሮሞው ፣ በትግራዩ፣ በአገው ፣ በአፋር ፣ በሱማሌ ፣ በጉራጌ ፣ በወላይታ ፣ ወዘተረፈ ደም ተቦክታ በአጥንት ተማግራና ተገድግዳ በስጋ ተለስና የተሰራች ናት ። ካርል ማርክስ ፣ “ ታሪክ ራሱን መጀመሪያ በአሳዛኝ ሁኔታ በማስከተል በአስቂኝ ሁኔታ ይደግማል “ እንዳለው ፤ ከጥቅምት 24 እስከ ሕዳር 19 ቀን 2013ዓም ሕግን ለማስከበርና የሀገርን ህልውና ለማስቀጠል በተካሄደው ዘመቻም ከሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የተውጣጡ ኢትዮጵያውያን ደማቸው ፈሷል ። አጥንታቸው ተከስክሷል ። በሱማሊያ ፣ በግብፅ፣ በደርቡሽ ፣ በቱሪክ ወረራ ጊዜም የኢትዮጵያውያን ደም ያለልዩነት ፈሷል ። የህይወት መስዋዕት ሆነዋል ። ተወዳጇ አርቲስት እንዳለቸው የዛሬው ነጻነታችን ህይወት ተከፍሎበታል ። የአማራው ፣ የኦሮሞው ፣ የትግራዩ ፣ ወዘተረፈ ህይወት ።
በዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር የሆነው ሬይሞንድ ጆናስ ፤” አፄ ምኒልክ እና የዓድዋ ድል “ በተሰኘ ግሩም ድንቅ መጽሐፉ የዓድዋን ድል ትምህርት ፣ አንድምታ ፣ ጥልቀት ፣ ከፍታ ፣ ንዑድነትና ትርጉም በሚያስደንቅ ሁኔታ እንዲህ ይገልፀዋል ፦ “ …ምኒልክ እና ጣይቱ ወደ ሰሜን የዘመቱት ስልጣናቸውን በፅኑ መሰረት ላይ ለመገንባት ብቻ አልነበረም ። …የትግራይ፣ የሸዋ ፣ የኦሮሞ ፣ የወላይታ እና የሌሎች ሕዝቦችን ውስጣዊ አንድነት በደም አስተሳስረው በጋራ ጠላት ላይ በመዝመት የጋራ አገር ለመገንባት እንጅ ፤ የሕዝቦች ጥብቅ ትስስር የሚፈጠረው በእያንዳንዱ ሀይማኖት ፣ ማንነት ብሔር ላይ ተመስርቶ ሳይሆን የጋራ ነፃነትን ለመቀዳጀት በሚከፈል መስዋዕትነት ነው ። ይህ አይነቱ መተሳሰር ብቻ ነው የኢትዮጵያ የነፃነት ከፍታ መገለጫ ፤ የዓድዋ ትምህርትም ይኸው ነው ። …”
እንደ መውጫ
ስንወረር ፣ ስንጠቃና ስንደፈር ቀፎው እንደ ተነካ ንብ በአንድነት እንደምንተመው ሁሉ ፤ ለእድገት ፣ ለብልጽግና ለዴሞክራሲ በአንድነት እጅ ለእጅ ተያይዘን ካልቆምን በእጃችን ደም አለ ። ከንቱ ያደረግነው የአያት ቅድመ አያቶቻችንና የአባቶቻችን ደም ። በጥላቻና በዘረኝነት እየተመላለስን እንደ ጲላጦስ ከደሙ ንጹህ ነኝ ልንል አንችልም ። ይቅር በመባባል በመፋቀርና በመግባባት የእጃችንን ደም ልንታጠብ ይገባል ። ይህን ስናደርግ ነው የአባቶቻችን መስዋዕትነት ከፍ ያለና ዘላቂ ትርጉም የሚኖረው ። የዚህ ጊዜ ነው ሕብረ_ብሔራዊነታችን ጌጥና መዋቢያ የሚሆነው ። የግጭት፣ የጥላቻና የመለያየት ምንጭ ከሆነ ግን እርግማን አድርገነዋል ማለት ነው ። በዓድዋ ሶሎዳ ተራራዎች ላይ ከፍ ብሎ የተውለበለበው ፤ በካራማራ ላይ በኩራት የተውለበለበው ፤ በአትሌቶቻችን ድል በአሸናፊነት ከፍ ብሎ በእነ ሮም አደባባዮች የተውለበለበው ሰንደቃችን ባንዲራችን ፤ የአፍሪካና የካሪቢያን ሀገራት በአንድም በሌላ በኩል ሰንደቃቸው ያደረጉት አረንጓዴ ቢጫና ቀይ ባንዲራችን ከፍ እንዳለ እንደተከበረ ሊኖር የሚችለው ከተረጅነትና ከተመጽዋችነት ነጻ ስንወጣ ነው ። ይህን ታላቅነት የሚመጥን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ስናቆም ነው።
ዘላለማዊ ክብር ለዚች ሀገር ሉዓላዊነትና ነጻነት በዱር በገደሉ ለተሰው ጀግኖች ኢትዮጵያውያን !!!
አሜን ።
አዲስ ዘመን የካቲት 22 ቀን 2013 ዓ.ም