ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአሜሪካ ገቢዎች መስሪያ ቤት የዓለም አቀፍ ጉዳዮች ኃላፊ የሆኑትን ደቪድ ሮበርት ማልፓስን የዓለም ባንክን እንዲመሩ በእጩነት አቅርበዋቸዋል፡፡ ዴቪድ ማልፓስ ለረጅም ዓመታት የዓለም ባንክን አሠራር ሲተቹ የቆዩ ሰው ናቸው፡፡ ከፕሬዚዳንት ትራምፕ ታማኝ አማካሪዎች መካከል አንዱ ናቸው የሚባሉት ማልፓስ፣ ከዓለም ባንክ በተጨማሪም የሌሎች መሰል ተቋማት አሠራር መስተካከል እንዳለበት በተደጋጋሚ ሲናገሩ የነበሩ ሰው ናቸው፡፡
ማልፓስ የዓለም ባንክን ከሚተቹባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ ባንኩ ለቻይና የሚሰጠው ብድር ነው፡፡ ‹‹ቻይና የራሷ የሆነ በቂ ሀብት ስላላት ባንኩ ለአገሪቱ የሚሰጠውን ብዙ ብድር መቀነስ አለበት›› የሚል አቋም አላቸው፡፡ ሰሞኑን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫም ባንኩን ውጤታማ የሚያደርጉትን አሠራሮች ለመተግበር ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ባንኩ የሚሰጠውን የብድር መጠን በ13 ቢሊዮን ዶላር ለመጨመር፣ ባንኩ ጠንካራ ምጣኔ ሀብት ላላቸው አገራት የሚሰጠውን ብድር ለመቀነስና ለእነዚህ አገራት የሚያቀርበውን ብድርም በከፍተኛ ወለድ ለመስጠት እንደሚሠሩም ገልጸዋል፡፡
‹‹በመላው ዓለም ፍትሐዊ ዕድገት እንዲኖርና በታዳጊ አገራት የኢኮኖሚ ዕድሎች ተፈጥረው ድህነት እንዲወገድ የሚያስችሉ መሰረታዊ ተግባራትን እንደምናከናውን ተስፋ አለኝ፡፡ ሴቶች በታዳጊ አገራት ኢኮኖሚዎች እኩል ተሳትፎ እንዲኖራቸው ማድረግ የባንኩ ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ ይሆናል›› ብለዋል፡፡
ባንኩ ለአገራት የሚሰጠው ብድር በአብዛኛው ለግል ዘርፍ ማበረታቻ እንዲውል የሚያደርግ አሠራር የመተግበርና የባንኩን የሠራተኞች ደመወዝ ጭማሬን የመገደብ እቅድ እንዳላቸውም ተናግረዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በሴቶች ላይ ትኩረት ያደረጉ ዓለም አቀፍ የልማትና የዕድገት መርሐ ግብሮችን ቀርጸው ከሚሠሩት ከፕሬዚ ዳንት ዶናልድ ትራምፕ ልጅና አማካሪያቸው ኢቫንካ ትራምፕ ጋር በቅርበት ለመሥራት ፍላጎት እንዳላቸውም ጠቁመዋል፡፡
ማልፓስ በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት የዓለም ባንክ ለቻይና የሚሰጠውን ብድር እንዲያቋርጥ ሲወተውቱ ነበር፡፡ ለዚህ ምክንያታቸው ደግሞ አገሪቱ ከባንኩ የምታገኘውን ብድር በራሷ አቅም ማሟላት ትችላለች ብለው ማመናቸው ነው፡፡ ቻይና በመሰረተ ልማት ግንባታ ስም ታዳጊ አገራትን በብድር ጫና እያስጨነቀች እንደሆነ በመጠቆም፣ ባንኩ ለአገሪቱ ብድር እንዳይሰጥ ሲያሳስቡ ቆይተዋል፡፡
እ.አ.አ በ2017 በውጭ ግንኙነት ካውንስል (Council on Foreign Relations) አዘጋጅነት በተካሄደ ጉባዔ ላይ ‹‹ቻይና ከዓለም ባንክ በከፍተኛ ደረጃ ከሚጠቀሙ አገራት መካከል አንዷ ናት፡፡ ብዙ ሀብትና አቅም ላለው አገር ብድር መስጠት ተገቢ አይደለም›› ብለዋል፡፡ በጉዳዩ ላይም ከወቅቱ የባንኩ ፕሬዚዳንት ጂም ዮንግ ኪም ጋር መነጋገራቸውን ገልጸው ነበር፡፡ በሌላ በኩል ማልፓስ አሜሪካና ቻይና በሚያደርጉት የንግድ ድርድር ውስጥም ተሳታፊ ከሆኑ ግለሰቦች መካከል አንዱ ናቸው፡፡
ታዲያ ማልፓስ ለዓለም ባንክ እጩ ፕሬዚዳንት ሆነው ሲቀርቡ ‹‹ተቀናቃኝ ይገጥማቸዋል ወይ?›› የሚለው ጥያቄ ለብዙዎች ግልጽ አይደለም፡፡ ባለሙያዎች እንደሚሉት አሜሪካ በባንኩ ላይ ያላት ተፅዕኖ ከልክ ያለፈ ነው የሚሉ አገራት ማልፓስን የሚፎካከር ሁነኛ ዕጩ ማቅረብ መቻላቸውን ይጠራጠራሉ፡፡
የባንኩን 16 በመቶ ድርሻ የያዘችው ልዕለ ኃያላኗ አሜሪካ ያቀረበችው ዕጩ መሾሙ አይቀርም የሚል አመለካከት ቢኖርም እንደየአቅማቸው የባንኩን ድርሻ የያዙ የሌሎች 188 አገራት የአሜሪካን ዕጩ አሜን ብለው ይቀበላሉ ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ፈጣን የምጣኔ ሀብት ዕድገት እያስመዘገቡ የሚገኙ አገራት አሜሪካ ያቀረበችው ዕጩ ግለሰብ የባንኩ ፕሬዚዳንት ሆኖ የሚሾምበት ያልተጻፈ ሕግ እንዲለወጥና ብቃትን መሰረት ያደረገ ምደባ እንዲከናወን ድምፀቸውን ማሰማት ጀምረዋል፡፡ ጂም ዮንግ ኪም እ.አ.አ በ2012 ከኮሎምቢያና ከናይጀሪያ የገጠማቸው ተቃውሞም የዚሁ ማሳያ ሳይሆን እንደማይቀር ይገመታል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአሜሪካ የገቢዎች መስሪያ ቤት የቀድሞ ኃላፊዎች የማልፓስን ዕጩነት ተቃውመዋል፡፡ ማልፓስ ባንኩን ለመምራት የሚያስችል ብቃት እንደሌላቸው ባለስልጣናቱ ገልጸዋል፡፡
የደቪድ ማልፓስ ዕጩነት በባንኩ የሥራ አስፈፃሚ ቦርድ ከፀደቀ እ.አ.አ ከ2012 ጀምሮ ባንኩን በፕሬዚዳንትነት ሲመሩ የቆዩትንና የኃላፊነት ጊዜያቸውን ለማጠ ናቀቅ ሦስት ዓመታት እየቀራቸው በባንኩ የሀብት ምንጮችና በአየር ንብረት ለውጥ ጉዳዮች ላይ ከፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር በፈጠሩት አለመግባባት ምክንያት ባለፈው ወር ኃላፊነታቸውን የለቀቁትን ጂም ዮንግ ኪምን የሚተኩ ይሆናል፡፡
ባንኩን እንዲመሩ በፕሬዚዳንት ትራምፕ ዕጩ ሆነው የቀረቡት ዴቪድ ሮበርት ማልፓስ በፕሬዚዳንት ሮናልድ ሬገን አስተዳደር ምክትል የገቢዎች መስሪያ ቤት ኃላፊ፣ በፕሬዚዳንት ጆርጅ ኸርበት ወከር ቡሽ አስተዳደር ደግሞ ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል፡፡ በ2016ቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳ ንታዊ ምርጫ ወቅት የዶናልድ ትራምፕ የኢኮኖሚ አማካሪ በመሆን ከትራምፕ ፕሬዚዳንታዊ የምርጫ ቅስቀሳዎች ጀርባ ከነበሩ ግለሰቦች መካከል አንዱ ነበሩ፡፡ በመቀጠልም እ.አ.አ በ2017 አሁን እየሠሩበት ባለው በአሜሪካ ገቢዎች መስሪያ ቤት የዓለም አቀፍ ጉዳዮች ኃላፊ ሆነው ተሾመዋል፡፡
ፊዚክስ፣ ቢዝነስ አስተዳደርና ዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ያጠኑት ማልፓስ፣ ቻይና በዓለም አቀፍ ፖለቲካና ምጣኔ ሀብት ላይ የምታደርገውን እንቅስቃሴ በአንክሮ የሚከታሉና የቻይናን ዕርምጃዎች አጥብቀው የሚኮንኑ ሰው እንደሆኑ በተደጋጋሚ ይነገራል፡፡ ቻይና ከአሜሪካና ከጃፓን በመቀጠል የዓለም ባንክን ሦስተኛውን ትልቅ ድርሻ (4.5 በመቶ) የያዘች አገር ናት፡፡
የዓለም ባንክን ታሪክ ወደኋላ መለስ ብሎ ለተለመለከተ ሰው የደቪድ ማልፓስ ዕጩነት በባንኩ የሥራ አስፈፃሚ ቦርድ መፅደቁ እንደማይቀር ግልጽ ይሆንለታል፡፡ ከዓለም ባንክ ብዙ ድርሻ ያላት አሜሪካ የባንኩ ፕሬዚዳንት የሚሆነውን ሰው እያቀረበች ስታሾም ኖራለች፡፡ እስከአሁን ድረስ ባንኩን በፕሬዚዳንትነት ከመሩት 12 ሰዎች መካከል አስሩ አሜሪካውያን ሲሆኑ ሁለቱ ደግሞ የአሜሪካ ጥምር ዜግነት ያላቸው ናቸው፡፡
እ.አ.አ በ2012 በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዕጩ ሆነው ቀርበው የባንኩ ፕሬዚዳንት ሆነው የተሾሙት የጂም ዮንግ ኪም ከኃላፊነት መልቀቅ አሜሪካ መቀመጫውን ዋሺንግተን ዲ.ሲ ባደረገው ግዙፉ ገንዘብ አበዳሪ ተቋም ላይ ያላት ተፅዕኖ ከልክ ያለፈ ነው የሚሉ ሌሎች አገራትን ከፕሬዚዳንት ትራምፕ አስተዳደር ጋር አለመግባባት ውስጥ ከትቷ ቸዋል፡፡
ባለፈው ወር መጨረሻ ከባንኩ የፕሬዚ ዳነትነት ኃላፊነታቸውን መልቀቃ ቸውን ያሳወቁት ጂም ዮንግ ኪም፣ በመላው ዓለም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ልዩ ትኩረት ስለሚፈልጉ የዓለም ባንክ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ጥንካሬ እንደሚያ ስፈልገው ተናግረው ነበር፡፡
ደቡብ ኮሪያ ተወልደው አሜሪካ ያደጉትና በዳርማውዝ ኮሌጅ፣ በሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲና በዓለም የጤና ድርጅት በተለያዩ ኃላፊነቶች የሠሩት የ60 ዓመቱ ሐኪምና አንትሮፖሎጂስት ጂም ዮንግ ኪም የዓለም ባንክ ፕሬዚዳንትነት ኃላፊነታቸውን መልቀቃቸውን ተከትሎ የባንኩ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ክሪስታሊና ጆርጊየቫ ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት ሆነው እየሠሩ ይገኛሉ፡፡
የዓለም ባንክ የሥራ አስፈፃሚ ቦርድ በሚቀጥለው ሚያዝያ ወር በዋሽንግተን ዲ.ሲ ከሚካሄደው የዓለም ባንክና የዓለም የገንዘብ ድርጅት (International Monetary Fund_-IMF) ስብሰባ በፊት አዲሱን የባንኩን ፕሬዚዳንት ይፋ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ምጣኔ ሀብታቸው በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የተጎዳባቸውን አገራት ለመርዳት በ1937 ዓ.ም የተመሰረተው የዓለም ባንክ፣ 189 አባል አገራት ያሉት ሲሆን፤ ባለፈው ዓመት ለታዳጊ አገራት 64 ቢሊዮን ዶላር ብድርና ዕርዳታ ሰጥቷል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 1/2011
አንተነህ ቸሬ