ጽጌረዳ ጫንያለው
ተባባሪ ፕሮፌሰር መንግስቱ ውቤ ይባላሉ። ልጅ ሆነው ጀምሮ ስለ ተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ይጨነቃሉ፤ ለተፈጥሮ ልዩ እንክብካቤንም ማድረግ ከቤተሰቦቻቸው ተምረዋል። በተለይ ከአባታቸው ብዙ ነገር ቀስመዋል። የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን ህይወት እንደሆነ ተረድተዋል።
በዚህም በአገር አቀፍ ደረጃ የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋች ሆነው ይሰራሉ። በማማከር ስራም ቢሆን አገር ላይ የተሻለ ነገር እንዲመጣ ይደክማሉ። በእርሳቸው እሳቤ ዓለም ተለወጠ ማለት አገር ተለወጠ ነው ብለው ያምናሉ። በዚህም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሰሯቸውን ምርምሮች ውጤት በሚያመጣ መልኩ በማድረጋቸው ይታወቃሉ። በዚህ ሳያበቃም ወደ አገር መጥቶ አገልግሎት የሚሰጥበትን ሁኔታም ይፈጥራሉ።
ከዚህ ልምዳቸው አንጻርም በራሳቸው ተነሳሽነት የከተማ ግብርና እንዲጀመር ለፍተዋል። ቁምነገር ላይ በማድረስም ለአስር ዓመታት የነጻ አገልግሎት በመስጠትም አገራቸውን አገልግለዋል። በእርሳቸው መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ምስረታም ብዙዎች መለወጣቸውን በወጋችን መካከል አንስተውልናል።
ለመሆኑ ይህ ተሞክሯቸው እንዴት ዳበረ፣ የልጅነት ትዝታ ወጣትነት ላይ ከዚያም ጎልማሳነት ላይ እንዴት አረፈ የሚሉና መሰል ጉዳዮችን በማንሳት ተሞክሯቸውን እንዲያጋሩን በዛሬው የ‹‹ህይወት ገጽታ›› አምዳችን እንግዳ አድርገን ጋብዘናቸዋል። ስለዚህም ልምዳቸውን ተቋደሱ አልን።
ተባባሪ ፕ/ር መንግስቱ ተወልደው ያደጉት በጎንደር ዳዋ አቡነአረጋዊ በተባለች የገጠር ቀበሌ ውስጥ ነው። ገበያም ሆነ ከሌሎች ዘመዶች ጋር ለመገናኘት ረጅም ርቀት በእግር ተጉዘው ህይወታቸውን የሚመሩበት ቦታ ነው። እንደውም እስካሁን ድረስ ምንም አይነት መንገድ እንዳልተሰራለትም አጫውተውናል።
በዚህም እርሳቸውና መሰሎቻቸው የእግር ጉዞ ግዴታቸው ሆኖ እንዲያድጉ አድርጓቸዋል። ታናናሾቻቸው ሳይቀሩና አዛውንቱም ጭምር በዚህ መንገድ ስቃይ ሲያይ እንደኖረም ያወሳሉ።
ለመማር እንኳን ብዙ ኪሎ ሜትር በእግራቸው መጓዝ እንደሚጠበቅባቸውና በዚህ ምክንያት እርሳቸው ከቀበሌያቸው የመጀመሪያው ዘመናዊ ትምህርት የጀመሩ ልጅ እንደሆኑ አጫውተውናል። ነገር ግን በዚያው ልክ ቦታው ለአይን ከመማረኩም በላይ ለቱሪስት የሚመች ነው። ጫካ በመሆኑም በእንስሳትም ሆነ በእጽዋት ከዚያም አልፎ በፍራፍሬ የታደለ በመሆኑ ርሀብ የሚባል ነገር አይታሰብበትም። ጫካ ውስጥ ተገብቶ ተጠግቦ ነው የሚወጣው።
ለቤተሰቡ አምስተኛ ልጅ የሆኑት ባለታሪካችን፤ ከስማቸው ጀምሮ እድለኝነት እጣ ፋንታቸው ነው። ምክንያቱም እድለኛ መሆናቸው በቤተሰቡ ውስጥ ይታይ ነበር። ከአደጉም በኋላ ትልቅ ደረጃ ይደርሳል ብለው ስለሚያምኑ መንግስት የሚለውን ስም እንደሰጧቸው ይናገራሉ። ይሁንና ይህ መንግስት የሚለው መጠሪያ መንፈሳዊ ትምህርታቸውን ሲጀምሩ ተቀየረ።
ምክንያቱም መንግስት የሚለው ፖለቲካም ሊሆን ይችላል። በጊዜውም ይህንን ስያሜ መስጠት ከባድ እንደሆነ ይታሰባል። በዚያ ላይ ሃይማኖታዊ ስያሜም አይደለም። እናም ለሃይማኖቱ በሚቀርብ መንገድ አሻሻሉት። መንግስቱም ሲሉ መጥራት ጀመሩ። ከዚያም በኋላ ይህ ስም መጠሪያቸው ሆኖ ቀረ።
እንግዳችን በባህሪያቸው ታዛዥ፣ ተጨዋች እንዲሁም አይበገሬ የሆኑ ሰው ናቸው። በተለይም ያሰቡት ነገር ግቡን ሳይመታ መቼም መተው አይፈልጉም። በዚህም አንድን ነገር ደጋግሞ በመሞከር ያምናሉ፤ ያደርጉታልም። ይህ ደግሞ የበለጠ ለፈጠራ ሥራ ያነሳሳቸው እንደነበር አይረሱትም። አቅማቸውን ለማሳየትም የሚሞክሩበት ዘዴያቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። የመስራት አቅማቸውንም የተጎናጸፉት ከዚህ የተነሳ እንደሆነ ይናገራሉ።
አብዛኛውን የልጅነታቸውን ጊዜ በመንፈሳዊ ትምህርት ቤት ያሳለፉ ሲሆን፤ የግብረገብነት ትምህርቱ የበለጠ ጸባይኛ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል። ቅንና ለሰው አሳቢም አድርጓቸዋል። በሥራም ቢሆን መልካም አርአያ የሆነ ልጅ እንዲሆኑና በትምህርታቸው ማንም የማይደርስባቸው እንዲሆኑ ያገዛቸው ነው። ከዚያ ባሻገር ቤት ውስጥ ገብተው ለአልተማሩት አባታቸው እንዲያነቡላቸውና እርሳቸውም የምስጋና ቃልን እንዲሰሙ ያደረጉበት የእድገት ጉዟቸው ነበር።
ተባባሪ ፕሮፌሰር መንግስቱ ለምለም በሆነ አካባቢ በማደጋቸው በምግብም ሆነ በገንዘብ ተቸግረው እንደማያውቁ ያስታውሳሉ። ምክንያቱም እርሳቸው አትክልትና ፍራፍሬ በግቢያቸው ውስጥ በመትከልና በመንከባከብ ሲጸድቅ ወደ ገበያ በመውሰድ በቂ የሆነ ገንዘብ ያገኛሉ። ይሁንና ይህንን ገንዘብ በምንም መልኩ አያጠፉም።
ከቤተሰብ ፈቃድ ውጪ የማጥፋት ልምድም የላቸውም። ስለዚህም በቀጥታ የሸጡትን አንድም ሳያስቀሩ ለቤተሰብ ያስረክባሉ። የሚያስፈልጋቸው ነገር ካለ ቤተሰብ ራሱ ነው የሚሰጣቸው። በዚህም ሁሉም ነገር ተትረፍርፎላቸው ነው ያደጉት።
ባለታሪካችን ቤተሰብን በተለያየ መንገድ የሚያግዙ ሲሆን፤ በተለይም ከብቶችን በመጠበቅ የተለየ አገልግሎት ይሰጡ ነበር። ከዚህ ጋር ተያይዞም እረኝነትን በልዩ ሁኔታ ነው የሚገልጹት።
ለአብነት ‹‹እረኝነት ለእኔ የቤተሰቤ ተልዕኮ ብቻ አይደለም›› የሚሉት አንዱ ነው። ለዚህ ምክንያታቸውን ሲያነሱ ደግሞ እረኝነት ፊደል የቆጠሩበት፣ ጥሩና መጥፎ እንዲሁም ፈዋሽ እጽዋትን የለዩበት፣ ከእንስሳት ጋር የቦረቁበትና እያንዳንዱን ነገር ማስተዳደር የተማሩበት ትምህርት ቤታቸው መሆኑን በማንሳት ነው።
ከልጅነታቸው ጀምሮ ትልቅ እንደሆኑ እየተነገራቸው ያደጉት ባለታሪካችን፤ ብዙ ነገሮች ላይ እንዲያስተባብሩና የአለቅነት ስልጣን ተሰጧቸው ነው የልጅነት ጊዜያቸውን ያሳለፉት። በዚህም በቄስ ትምህርት ቤት በሚማሩበት ጊዜ ምንም እንኳን ትንሽ ቢሆኑም ያጠፋውን አይምሩትም ነበር። በዚህም ብዙ ጊዜ አባታቸው ጋር ስሞታ ይመጣል። ነገር ግን አባት ነገሩን ስለሚረዱና ልጃቸውን ማሸማቀቅ ስለማይፈሉጉ ሰዎቹን በእሽታ ይመልሱና እርሳቸውን ግን ምንም አይናገሯቸውም። ሆኖም አመራር ምን ማለት እንደሆነ ያስረዷቸዋል። ከሰዎች ጋር መጣላት እንደሌለባቸው ይመክሯቸዋል። እንግዳችንም የሚባሉትን የሚሰሙ ስለነበሩ ያሏቸውን ተቀብለው ተግባራዊ ያደርጉ እንደነበር አጫውተውናል።
በራስ ጥረት እስከ ተባባሪ ፕሮፌሰርነት
የትምህርትን “ሀ” “ሁ” የጀመሩት በቄስ ትምህርት ቤት ሲሆን፤ እስከ ዲቁና የሚያደርሱ ትምህርቶችን ቀስመዋል። ቅኔ፣ንባብና ሌሎች የክህነት ትምህርቶችንም ተምረዋል። እድሜያቸው ለትምህርት ከደረሰ ከረጅም ዓመታት በኋላም ነው ዘመናዊ ትምህርቱን የተቀላቀሉት። ለያውም በራስ ጥረት በተደረገ ግብግብ። እንደውም በ16 ዓመታቸው ከዘመናዊው ትምህርት ጋር መተዋወቃቸውን ያስታውሳሉ።
በእርግጥ መንፈሳዊው ትምህርት ለዘመናዊው ምሰሶ ነው። ለዚህ ደግሞ ማሳያው በጣም ጎበዝና ክፍሎችን ዘለው በአንድ ጊዜ አምስተኛ ክፍልን እንዲቀላቀሉ መሆኑ ነው። በዚህም አዲስ አበባ ተፈሪ መኮንን በመግባት አምስተኛ ክፍልን የተማሩ ሲሆን፤ ይህ የተፈጠረውም በአጋጣሚ አዲስ አበባ በመጡበት ጊዜ እንደነበር አይረሱትም።
መጀመሪያ አካባቢ ዘመናዊ ትምህርት ለመጀመር ያነሳሳቸው የወንድማቸው ሚስት ወንድም ሲሆን፤ ስምንተኛ ክፍል በመውደቁ የተነሳ ከእርሳቸው ጋር እረኛ ለመሆን በትውልድ ቀያቸው መምጣቱና ከእርሳቸው የተለየ ነባራዊ ሁኔታ ማሳየቱ ነው። በተለይ የሚናገራቸው እንግሊዝኞች እርሳቸውን ይመስጣቸው ነበር። ለምን የእርሱን ያህል አቃተኝም ያሰኛቸዋል።
እናም መማር እንዳለባቸው ማሰብ ጀመሩ። ስለዚህም እንዲያስጠናቸው የተለያዩ መደለያዎችን ይጠቀሙ ነበር። ከእነዚህ መካከል ወተት መስጠቱ አንዱ ነው። ይህ ደግሞ በቃል ለሚሸመድደው የትናንቱ ህጻን የዛሬው ተባባሪ ፕሮፌሰር ቀላል ሆነላቸው። የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታቸው እንዲዳብር ሆነ።
ከዚያ ደግሞ አክስቶቻቸው ጋር ጎንደር ሲሄዱም ከቤተሰቡ የበለጠ እየተማሩ ትምህርቱን በስፋት እንዲውቁት አገዛቸው። የፈለጉትን እያገኙ እንዲመጡም ብርታት ሰጣቸው። ሌላው የመማር ፍላጎታቸውን የጨመረው ጉዳይ በስካውት መልክ የሚመጡ ቱሪስቶች ጋር በመዋል ብዙ የትምህርት አቅማቸውን ማዳበራቸው ነው።
በዚህም በቀጥታ ዘመናዊውን ለመማር ቁርጠኛ ሆነው በ16 ዓመታቸው ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት የተቀላቀሉት። አምስተኛ ክፍል ሲገቡ በፈተና ነበር። ይህንን ፈተና ማለፍ የቻሉት ደግሞ በሁለቱ በኩል የነበረው ጥረታቸው ሲሆን፤ ፊደልን በመንፈሳዊው፣ የእንግሊዝኛ ቋንቋና ሒሳብ እውቀታቸውን ደግሞ ከተለያዩ ሰዎች ማዳበራቸው ነው። ስለዚህም ክፍሉን በቀላሉ ተቀላቅለው በደረጃ ተማሪነት ወደ ስድስተኛ ክፍል እንዲያልፉ ሆነዋል።
እስከ ስድስተኛ ክፍል በዚህ ትምህርት ቤት ከተማሩ በኋላ በየነ መርድ ትምህርት ቤትን የተቀላቀሉት ባለታሪካችን፤ ሰባተኛና ስምንተኛ ክፍልን በትምህርት ቤቱ እንዲማሩ ሆነዋል። ቀጣዩን ክፍል ደግሞ ካቴድራል ትምህርት ቤት የተከታተሉ ሲሆን፤ 11ኛ ክፍልን ብቻ ሴንጆሴፍ ትምህርት ቤት ተምረዋል።
በእነዚህ የክፍል ደረጃዎች ታዲያ የማታ ተማሪ ነበሩ። ምክንያቱም ቀን ሳይሰሩ መማር አይችሉም ነበር። እናም አንዳንድ ቀን ብቻ ሲፈቀድላቸው ከቀኖች ጋር ይማራሉ እንጂ በቋሚነት ትምህርታቸውን ያጠናቀቁት በማታ የትምህርት መርሃ ግብሩ ነው።
በትምህርታቸው ጎበዝ በመሆናቸው በክፍል ጓደኞቻቸው እሳቱ፣ ነበልባሉ፣ ታከለና አበባው እየተባሉ የሚጠሩ ሲሆን፤ በዚህም የበለጠ ታታሪ እንዲሆኑ እንዳገዛቸው ይናገራሉ። በተጨማሪ አባታቸው ምንም እንኳን ያልተማሩ ቢሆኑም በራስ መተማመንን እንዲያዳብሩና ትኩረታቸውን ትምህርታቸው ላይ እንዲያደርጉ ማበርታታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ እንዳደረጋቸው ያወሳሉ። በተለይም ከትምህርት መልስ እንዲያነቡላቸው በየቀኑ መጎትጎታቸው አንባቢነታቸው እንዲጨምር ያደረጋቸው እንደነበርም አይረሱትም። መጸሐፍ ማንበብ የመውደዳቸው ምስጢርም እርሳቸው እንደነበሩ ያወሳሉ።
የእርሳቸው ባህሪ በብዛት አንድ ጊዜ አንብበው በቃላቸው መሸምደድ ነበር። ሆኖም አንብብልኝ ስለሚባሉ ለእርሳቸው ሲሉ ከመማሪያ መጽሐፍት ውጪ ሳይቀር የሚያገላብጧቸው መጽሐፍት እንዲበዙ አድርጓቸዋል። በዚህም በትምህርት ጉዟቸው ይህንን ዘዴ ተጠቅመው ከክፍል ክፍል ተዛውረዋል። በተለየ መስክም እውቀታቸውን አጎልብተዋል።
በዚህም አዲስ አበባ በመንፈሳዊ ትምህርቱ የተሻሉ የሆኑትና በአለማዊውም ውጤታማ ይሆናሉ የተባሉ ተመርጠው በቤተክህነት ስልጠና እንዲወስዱ መጡ። ስልጠናውም ለዓመት ያህል የተለያዩ የትምህርት አይነቶችን ያቀፈ ስለነበር ወሰዱ። በዚህም ከሁሉም የተሻሉና ውጤታማ ስለነበሩ ሌሎቹ በቀጥታ በተለያየ መስክ መስራት ሲጀምሩ እርሳቸው ግን በአዲስ አበባ ቀርተው ዘመናዊ ትምህርትን ጀመሩ። እንዲህ እንዲህ እየተባለም 12ኛ ክፍል ተጠናቀቀ።
ከ12ኛ ክፍል በኋላ በቀጥታ ዩኒቨርሲቲ አልገቡም ነበር። ምክንያቱም በቴሌኮሙዩኒኬሽን ውስጥ ይሰሩ ነበርና ወደ ምክንያቱም በቴሌኮሙዩኒኬሽን ውስጥ ይሰሩ ነበርና ወደ ውጪ አገር ለመሄድ ተጻጽፈዋል። በዚህም በጓደኛቸው ግብዣ አማካኝነት ወደ እስራኤል አቀኑ። በእርግጥ እስራኤል መኖር አይፈልጉትም።
ሆኖም መሸጋገሪያ እንደሚሆናቸው ያውቃሉና ግብዣውን ተቀብለውታል። እዚያም ከገቡ በኋላ ለተወሰኑ ዓመታት በስራ ላይ ቆዩ። መማር ህልማቸው በመሆኑም የልጅነት ፍላጎታቸውና የወቅቱ ምርጫ እንግሊዝ በመሆኗ እዚያ ለመሄድ አሁንም መጻጻፍ ጀመሩ። ነገር ግን ወደዚያ መሄድን ትተው ስውዲን ጥገኝነት ጠይቀው ሄዱ። ለስድስት ወር ያህል ፈቃዱን እስኪያገኙ መንግስት እየተንከባከባቸውም ቆዩ።
ከ11 ወር ቆይታ በኋላ ጥገኝነቱ መልስ በማግኘቱ ቋንቋ እንዲማሩ ሆኑ። በዚያው እድል ቀናቸውና ኦብሳላ ዩኒቨርሲቲን ተቀላቀሉ። የመጀመሪያ ዲግሪያቸውንም በዩኒቨርሲቲው ጀመሩ። ትምህርቱን ሲማሩ በብድር ሲሆን፤ ይህም ቢሆን መመለስ ይችላል ብሎ ካልታመነና ውጤታማ መሆን ካልተቻለ አይፈቀድምና እርሳቸው የሰሩባቸው ቦታዎች፣ የ12ኛ ክፍል ውጤታቸው ታይቶ ብድሩ ተፈቀደላቸው። እናም የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በማህበራዊ ሳይንስ ዘርፍ ትምህርት እንዲመረቁ ሆኑ።
ብዙም ሳይቆዩ በዚያው ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን የጀመሩት ተባባሪ ፕሮፌሰር መንግስቱ፤ በህብረተሰብ ሳይንስ ወይም በጆኦግራፊ ትምህርት መስክ ተምረው በጥሩ ውጤት ከዩኒቨርሲቲው ሊመረቁ ችለዋል። አሁንም ቢሆን የነበራቸው ውጤት ቀጣይ እድል የሚያሰጥ ነበረና የሦስተኛ ዲግሪያቸውን በእርሻ ትምህርት መስክ እንዲመረቁ ሆነዋል።
ሌላው የተማሩት ትምህርት የፖስት ዶክትሬት ትምህርት ሲሆን፤ የተማሩበት ዩኒቨርሲቲ አግሪካልቸራል ዩኒቨርሲቲ ይባላል። ያጠኑት የትምህርት መስክ ደግሞ ግብርና እና ባዮ ጆኦግራፊ የትምህርት መስክ ሲሆን፤ የተሻለ ውጤት ይዘውም ነው የተመረቁት።
እያንዳንዱ ትምህርት ሙሉ እስኮላር ሽፕ ተሰጥቷቸው የተማሩት ሲሆን፤ ለዚህ ደግሞ በተለይም ለኢትዮጵያ በተለያዩ መንገዶች የሚያግዘው ሲውዲሽ ኢንተርናሽናል ዴቭሎፕመንት የሚባል ድርጅት በብዙ ነገር እንደደገፋቸው ይናገራሉ።
የተባባሪ ፕሮፌሰርነታቸውን ሲያገኙም ቢሆን ይህ ድርጅት ጥናትና ምርምሮቻቸውን በውጤታማ መልኩ እንዲያጠናቅቁ ከፍተኛ ሚና እንደተጫወተም ያስታውሳሉ። የተባባሪነት ፕሮፌሰርነት ማዕረጉን ያገኙት ከሲውዲን አብሳላ ዩኒቨርሲቲ ሲሆን፤ ከ20 በላይ ጥናቶችን ሰርተውና በአለማቀፍ ሳይንሳዊ መጽሔቶች ላይ አሳትመው እንዲሁም ዩኒቨርሲቲዎች ላይ አስተምረውና ሌሎች መስፈርቶችን አሟልተው ነው።
አትክልተኛው አማካሪ
‹‹ለእኔ ስራን ያለማመደኝ የገጠሩ አስተዳደግ ሁኔታዬ ነው›› የሚሉት ባለታሪካችን፤ የማህበረሰቡ እና የቤተሰቤ ሁኔታ ከስነልቦና ጀምሮ እስከ ኢኮኖሚውና ማህበራዊው ነገራቸው ብዙ አስተዋጽኦ የነበረው እንደሆነ ያነሳሉ። እርሳቸው በስራ የተገነቡት ማህበረሰቡና ቤተሰቦቻቸው በሚያደርጉላቸው እንክብካቤና ሰርቶ መለወጥ እንዴት እንደሚቻል ማስተማር ነው።
በዚህም አትክልተኛ ሆነው፣ ነግደው ገንዘብ አግኝተዋል። እናም የስራ መነሻቸው ያ እንደነበር ያወሳሉ። ከዚያ ቀጣዩ የሥራ ቦታቸው አዲስ አበባ ለመማር ወስነው እያለ የጀመሩት ሥራ ሲሆን፤ ይህም መንገድ ላይ በተዋወቁት አንድ ሰው አማካኝነት የመጣው በኢትዮጵያ ቴሌኮሙዩኒኬሽን ቦርድ በዛሬው ኢትዮ ቴሌኮም ተቀጥረው የሰሩት ነው። ስራው በኮሚሽን የሚከናወን ሲሆን፤ አሰሪያቸው በወር 100 ብር እየከፈላቸው ነበርም የሚሰሩት።
በዚህ ቦታ ለዓመታት ያገለገሉ ሲሆን፤ ገንዘብ ያዥ ሆነው ያውቃሉ። ከዚያ እድገት አግኝተው ሱፐርቫይዘር ሆነው መስራት ችለዋል። በመቀጠል ደግሞ ሰፊ የመስራት አቅም ፈጥሮላቸው እስራኤል ውስጥ በእንግዳ ተቀባይነት ኤላት ከተማ ውስጥ በጣም በታወቀ ሆቴል ማለትም በናሮብ ሆቴል ተቀጥረው ለአምስት ወር ያህል ሰሩ። ሆቴሉ ውስጥ በታማኝነት በማገልገላቸው የተነሳ ሆቴሉ የወር ፈቃድ ሰጥቷቸው እስራኤልን ሙሉ እንዲጎበኙ አድርጓቸዋል። ይህ አጋጣሚ ደግሞ ከሌሎች ጋር እንዲገናኙ እድል ፈጥሮላቸዋል።
ወደ ሆቴላቸውም ቢሆን የሚመጡት ትልልቅ ባለስልጣናትና ባለሀብቶች ካልሆኑ አይችሉትምና እዚያም እንዲሁ ብዙዎችን ተተዋውቀው ነበር። በዚህም ከእንግሊዝ፣ ከፈረንሳይና መሰል ቦታዎች እንውሰድህ የሚላቸው በዝቶላቸው እንደነበር አይረሱትም። እርሳቸው ግን አሻፈረኝ አሉ። ምክንያቱም ከመስራት በላይ መማሩ የበለጠ እንደሚጠቅማቸው ያውቃሉ።
በዚህም ሁሉንም ትተው ወደ ስውዲን አቀኑ። ስውዲን የገቡት በጥገኝነት ሲሆን፤ ወዲያው ግን ፈቃዱን ማግኘት አልቻሉም ነበር። በዚህም ወቅቱን የተረዳው የስውዲን መንግስት ኢትዮጵያን በተለያየ መንገድ ያግዝ ስለነበር እርሳቸውንም በዚያ ልክ ተቀብሎ አስተናገዷቸዋል። ምንም ሳይጎልባቸውም ለወር ያህል በሆቴል እየኖሩ ተቀምጠው መታወቂያው ተሰጣቸው።
ቀጣዩ የሥራ ቦታቸው ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሲሆን፤ ሲዳ እየከፈላቸው ለሁለት ዓመታት የአየር ጥበቃና አግሪካልቸር ኢንቫይሮመንት በነጻ አስተምረዋል። በተመሳሳይ በምርምርም የሰሩባቸው ቦታዎች አሉ። ከእነዚህ መካከል እስቶኮልም እስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ ውስጥ ለ10 ዓመት ያህል በተመራማሪነት ሰርተዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ለፖስት ዶክተራል ምርምር ስራ በመሄድ የሰሩ ሲሆን፤ በሙቹካን ስቴት ዩኒቨርሲቲ ለሁለት ዓመታት ምርምሩን እየሰሩ ቆይተዋል። በስተመጨረሻ መቀጠርን ትተው በራሳቸው ባዮዲ ፉድ አሶሴሽን የሚባል ግብረሰናይ ድርጅት አቋቁመው መስራት ጀመሩ። ይህ የሆነው ደግሞ አገራቸውን ለማገልገል ባላቸው ፍላጎት ነው። እናም በዚህ ሥራ ላይ 10 ዓመታትን አገልግለዋል።
ይህ ድርጅት ዋና ትኩረቱ የከተማ ግብርናን ማስፋፋት ሲሆን፤ የተቸገሩ ሰዎች በከተማ እርሻ ላይ ሰርተው ምርታማ ሆነው እንዲጠቀሙ ማስቻል ነው። በዚህም ራሳቸው በገዙት 2ሺህ ካሬ ሜትርና መንግስት በሰጣቸው አንድ ሺህ ካሬ ሜትር ላይ የተለያዩ አትክልትና ፍራፍሬዎች እንዲሁም የእንስሳት እርባታን በመክፈትና በመሸጥ አካውንት ተከፍቶላቸው እየቆጠቡ እንዲለወጡ አድርገዋል።
በሌላ በኩል ከሌሎች ተጨማሪ ድርጅቶች ጋር አንድ ላይ በመሆን ደግሞ የምግብ ስራ፣ የኮምፒዩተርና መሰል ስልጠናዎችን ወስደው ራሳቸውን እንዲለውጡም ተደርጓል። ይህንን ያደረጉትም በማማከር ስራ ከሚሰሩት ገቢ ራሳቸውን እያስተዳደሩ በነጻ አገልግሎቱን የሚያገኙበትን ሁኔታ በማመቻቸት እንደሆነ አጫውተውናል።
ይህ ደግሞ አብዛኞቹን ሴቶችና ወጣቶችን የራሳቸው ድርጅት እስከማቋቋም ያደረሰ እንደነበርም ይናገራሉ። ነገር ግን የበጎ አድራጎት ማህበራት ህግ የሚያሰራ ባለመሆኑ ከዓመት በፊት ራሳቸውን እንዳገለሉ ሆኖም ሥራው ግን ሌሎች ድርጅቶች ይዘውት እንደቀጠሉ አጫውተውናል። ነገር ግን ያለስራ መቀመጥን አይወዱምና ‹‹ዋንዛ ኢንተርናሽናል ኮንሰልቲንግ›› የተባለ ድርጅት በመክፈትም በአካባቢ ጥበቃ ዙሪያ የማማከር ሥራዎችን እየሰሩ አገራቸውን እያገለገሉ ይገኛሉ።
የአገር አበርክቶ
በአብዛኛው የሲውድን መንግስትና አንዳንድ ድርጅቶች ቢረዷቸውም በአገራቸው ግን አንድም ሥራ እየተከፈላቸው አለማገልገላቸው አንዱ መሆኑን ያነሳሉ። በተለይ በማስተማርና በግብርና ዙሪያ የሰሯቸው ስራዎች ለአገሬ አበረከትኩት የሚሉት እንደሆነ ይናገራሉ።
በተጨማሪ አትክልትና ፍራፍሬ በሰፈር ውስጥ ቆሻሻ ቦታን በማጽዳት ተክለውና ተንከባክበው ማህበረሰቡ እንዲጠቀምበት መፍቀዳቸው አንዱ ነው። ጥላ እንዲሆንና ቦታው ውብ የሚሆንበትን መንገድ በመፍጠርም እንዲሁም ማድረግ ወጣቶችን የእረፍት ጊዜያቸውን የሚያሳልፉበት ምቹ ቦታ መፍጠራቸውም ሌላው እንደሆነ አጫውተውናል።
ቤተሰብ
የሦስት ልጆች አባትና የስድስት አያት የሆኑት ባለታሪካችን፤ ሁሉንም አስተምረዋል። ሆኖም ሁሉም በተማሩበት ሙያ እየሰሩ አይደለም። አንዱ አዲስ አበባ ላይ የራሱን ንግድ ስራ እየሰራ ይገኛል። ሁለቱ ደግሞ ውጪ አገር በመሄድ የተለያዩ ስራዎች ላይ ተሰማርተው እየሰሩ ይገኛሉ። ከባለቤታቸው ጋር የተገናኙት በጓደኛቸው አማካኝነት ሲሆን፤ ዛሬ ላይ ተግባብተውና ተናበው እንዲሁም ተከባብረው የሚኖሩ ናቸው። ይህ የጀመረው ደግሞ ገና ከጋብቻቸው ጀምሮ እንደነበር ያስታውሳሉ። ሰርግ በስፋት አይደገስም ተብሎ በአነስተኛ ድግስ ጋብቻቸውን እንዳከናወኑም ያስረዳሉ።
መልዕክት
ኢትዮጵያ ውስጥ በሽታ የበዛው የሀኪሙና የህመምተኛው ተግባቦት በትክክል ያለመናበብ እንጂ በሽታው ከባድ ሆኖ አይደለም። እናም በማንኛውም ጉዳይ ላይ የስነልቦናን ማጥናትና መናበብ መፍትሄውን ያመጣልና ሰዎች እነዚህ ነገሮች ላይ በስፋት ቢሰሩ የልማት አገርንም መፍጠር መቼም ከባድ አይሆንም የመጀመሪያው መልዕክታቸው ነው።
ሌላው ያነሱት ነገር ለማንኛውም ነገር ዋጋችን ገንዘብ ከሆነና ጥቅማችን ላይ ብቻ ካተኮርን ከጨዋታ ውጪ እንሆናለን የሚለው ሲሆን፤ ለነገሮች ዋጋችን ክፍያ ከሆነ የሚሰራው ሥራ ስኬታማ መሆን አይቻልም። ለዚህም ማሳያው በተፈጥሮ የማይደሰት ፍጡር ማንም አይኖርም። ግን የሚከፍለው ክፍያ የለም። ይህ ግን በገንዘብ ቢተመን ማንም ለመክፈል አቅሙ አይኖረውም። ምን ያህል ገንዘብም ባወጣ ነበር። ስለዚህም ነገሩ ለእግዚአብሔር የኦክስጅን እየከፈሉ መኖር ነውና ከዚህ አንጻር የሰው ልጅ ለተፈጥሮና ለሰው የሚሰጠውን ዋጋም ማየት አለበት።
ማንም ሰው የሚያውቀውን ካላስተማረ፣ ከሌሎች ለመማር ዝግጁ መሆን ከሌለ ራስም ሆነ አገርን መለወጥ አዳጋች ነው። መሰልጠን የሚባል ነገርም አይኖረውም። ስለዚህም የሚያውቀውን ማሳወቅ የማያውቀውን ደግሞ ትዕቢቱን አስወግዶ ከሌሎች ለመማር ዝግጁ መሆን ይገባል መልዕክታቸው ነው።
እኛ የአካባቢያችን ውጤት ነን የሚል እምነት ያላቸው ባለታሪካችን፤ “በአካባቢያችን የስብዕና ለውጥ ይመጣል፤ መማርና ማስተማርም እውን ይሆናል። በተመሳሳይ የሥራ ሰውና የእውቀት ልኬትም የሚታየው ከዚህ ነው። ከሁሉም በላይ የተፈጥሮ ሰው የሚኮነው በአካባቢ ውስጥ መኖራችንን ስንረዳ ነው። እናም ሁሉም ሰው እኛ የማህበረሰባችን፣ የአካባቢያችን ውጤት መሆናችንን መረዳት ይገባዋል” ይላሉ።
በመጨረሻም የአንድ ወቅት ችግር የቀሪ ሕይወትህን ደስታ እንዲያበላሸው አትፍቀድለት፤ ሕይወትንም ባስቸጋሪው ወቅት በነበረህ መነፅር አትያት፤ በአንድ ክፉ አጋጣሚ ወክለህም አትመልከታት፤ ይልቁንም በአስቸጋሪ ጊዜ ነገም ሌላ ቀን ነው ብለህ ጽና፤ የተሻለው ጊዜ እንደሚመጣ እርግጠኛ ሁን። «በጥሩ ሁኔታ ላይ መሆንህን ስትረዳ መጥፎ ነገርን ፍራ፤ በመጥፎ ሁኔታ ላይ መሆንህን ስታውቅ ደግሞ ጥሩ ነገርን ተስፋ አድርግ” በማለት ይመክራሉ።
አዲስ ዘመን የካቲት 21/2013