ጽጌረዳ ጫንያለው
በውሃና የአካባቢ ምህንድስና በአገር አቀፍ ደረጃ ሙሉ ፕሮፌሰርነት ያገኙ በዕድሜ ትንሹ ፕሮፌሰር ናቸው። በውሃ ሀብት አጠቃቀም አፍሪካን ለማጠናከር በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ የውሃ ማስተዳደር ልኅቀት ማዕከል (ACEWM) ከሀገር እና ከአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ ተማሪዎችን በማስተማርና በማማከር ሥራ ላይም ይሳተፋሉ።
በጅማ ዩኒቨርሲቲ በተመራማሪነት፣ በመምህርነትና በተለያዩ ኃላፊነቶች ውስጥ የሚሰሩ ሲሆን፤ እንደ አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች ላይም በተጋባዥ ፕሮፌሰርነት ሰርተዋል። አሁንም በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ላይ የማማከር ሥራዎችን ይሰራሉ፤ ያስተምራሉም። ከ100 በላይ ጥናታዊ ጽሑፎችን በዓለምአቀፍ ሳይንሳዊ መጽሔቶች ላይ ለህትመት ያበቁ፤ ከ15 በላይ ትላልቅ ዓለም አቀፍ ፕሮጀክቶች እንዲተገበሩ ያስተባበሩም ናቸው።
በጅማ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ ውጤት አምጥተው እዚያው በመምህርነት የቀሩ ሲሆን፤ ህክምና እና ምህንድስና ዘርፍን በማቀናጀት የባዮሜዲካል ምህንድስና ትምህርት ክፍል በማደራጀት ሥራ እንዲጀምርም ካደረጉ ምሁራን መካከል አንዱ ናቸው። በቅርቡ ደግሞ በሚሰሩበት ዩኒቨርሲቲ አቅራቢያ በሚገኘው በገበታ ለሀገር በሚታቀፈው የኮይሻ ፕሮጀክት ላይ ለመሳተፍ ራሳቸውን ዝግጁ አድርገዋል። ለዛሬ የሕይወት ስኬታቸውን እንዲያካፍሉን ለ‹‹ሕይወት ገጽታ›› አምዳችን የመረጥናቸው ፕሮፌሰር ዶክተር ኢንጅነር ኢሳያስ አለማየሁ ናቸው። መልካም ቆይታ።
የስለት ልጅ
እንግዳችን ምንም እንኳን ለቤተሰቡ ስምንተኛ ልጅ ቢሆኑም እርሳቸው በሚወለዱበት ወቅት የነበረው ስቃይ ዛሬ ድረስ ዳግም አምላክ አያሳየን የሚያሰኛቸው ነው። ምክንያቱም እናታቸው በወሊድ ምክንያት ምጥ ስለበረታባቸው ቤተሰቦቻቸው የሞት ስጋት ውስጥ ገብተው ነበር። ግን የቤተሰቡ እምነትና ጸሎት እንዲሁም ስለት እናትና ልጅን አቆይቶ ታሪክ ዘካሪ አድርጓቸዋል። በተለይም አባታቸው ስለታቸው ስለሰመረ እንግዳችንን ተምረው ሌላ ቦታ እንዲሆኑ አይፈልጉም። የስለታቸው ውጤት ስለሆኑ በቤተክርስቲያን ብቻ እንዲያድጉና በዚያው እንዲያገለግሉ ነው የሚፈልጉት። በዚህም ከሦስት ዓመታቸው ጀምሮ ቤት ውስጥ አድረው አያውቁም። ምግባቸውን ቤት አድርገው ውሎ እና አዳራቸው በቤተክርስቲያን እንዲሆን ነው ያደረጉት።
የትናንቱ ሕፃን የዛሬው ፕሮፌሰር ኢሳያስም የፍቅርና የሰላም ተምሳሌት እየተባለች በምትጠቀሰው በጀጎል ግንብ ሐረር ውስጥ በ1965 ዓ.ም ጤነኛ ሆነው ስለተወለዱና ቤተሰባቸውን ስለሚሰሙ የተባሉትን እያደረጉ በቤተክርስቲያን እንዲያድጉ ሆነዋል። ነገርግን አምስት ዓመት ሲሆናቸው በአካባቢው የሱማሌ ጦርነት በመኖሩ ምክንያት በዚያ ቢቆዩ አደጋ እንደሚደርስባቸው በማሰብ ሌላ ቦታ እንዲልኳቸው ግድ ሆነ። ይህ ደግሞ ለትንሹ ኢሳያስ ሌላ ዕድል አጎናጸፈው። ሙሉ ሕይወቱ ቤተክርስቲያን ብቻ ሳይሆን ዘመናዊ ትምህርትቤት ጭምር እንዲሆንም ዕድል ፈጠረለት።
ከወንድማቸው ጋር በመሆን አጎቴ የሚሉት ሰው ጋር ለመኖር ወደ ጅማ የተጓዙት ባለታሪካችን፤ አባት ባይፈቅዱም በነበሩበት ቦታ ዘመናዊ ትምህርትን እንዲጀምሩ ሆነዋል። አጎትዬው ለትምህርት ወደ ውጭ አገር ሲሄድ ግን ወደ ቤተሰብ በመመለሳቸው እንደበፊቱ የጠነከረ ባይሆንም ከቤተክርስቲያን እንዳይለዩ ከሌሎቹ ልጆች በተለየ መልኩ ክትትል ይደረግባቸው እንደነበር አይረሱትም።
በእርግጥ ይህ መሆኑን መቼም ተማረውበት አያውቁም። ምክንያቱም ብዙ ሕይወት ሰጪ ነገሮች አሉበት። እናም እርሳቸው የተባሉትን እያደረጉና የቤተክርስቲያኑንም ሆነ ዘመናዊውን ትምህርት እየተማሩ እንዲጓዙም አድርጓቸዋል። እንደማንኛውም ልጅ በቤት ውስጥ እየኖሩ ጎረቤቱ ልዩ ፍቅር እየሰጣቸውም እንዲያድጉ መንገድ ጠርጎላቸዋል።
የስለት ልጅ መሆናቸውን ተከትሎ ከቤተክርስቲያን እንዳይርቁ የሚደረጉበት መንገድ ክትትል የበዛበት ቢሆንም በአባታቸው ዘንድ እስከ 12ኛ ክፍል ሲማሩ ነጥረው ላይወጡ ይችላሉ፤ በዚያ ላይ ዲያቆን ስለሆኑ የትም አይደርስም የሚል ምልከታ ነበርና ብዙ ነገሮችን በቸልታ ያልፏቸዋል።
ይህ ነፃነት ደግሞ በዘመናዊው ትምህርት የበለጠ ውጤታማ መሆናቸውን እንዲያሳዩ እንዳገዛቸው ያስታውሳሉ። ከዚህ ውጪ ብዙም የሥራ ኃላፊነትና ጫና አይበዛባቸውም። ቤተሰቡ ሁሉ የሆነ ነገር ይሆንብናል፤ እምነታችንን ያጎድለዋል እያሉ ስለሚፈሩ ዋና ትኩረታቸው ትምህርታቸውና ቤተክርስቲያን እንዲሆን ተደርጎ እንዲንቀሳቀሱ ያግዟቸዋል።
ፕሮፌሰር ሥራ እንዲሰሩ ባይፈቀድላቸውም እርሳቸው ግን ቤተሰቡን ለማገዝና ሥራ ወዳድ እንዲሆኑ በመፈለግ የማይሞክሩት ነገር አልነበረም። ረጅም የእግር ጉዞ ሳይቀር ሄደው ይሰሩ ነበር። በባህሪያቸው በጣም ጨዋታ አዋቂና በተለይ ኳስ መጫወት የሚወዱ ናቸው። ታዛዥ፤ የተቸገረ ማየት የማይወዱና ያላቸውን የሚያካፍሉም ናቸው። ከሰዎች ጋር በሚያሳልፉት ጊዜ አብዝተው የሚደሰቱ፤ ብቻዬ የሚሉት ነገር የሌላቸውም ናቸው። ይህ ባህሪያቸው ደግሞ ዛሬ ድረስ እየኖሩበት እንደሆነም አጫውተውናል።
እንግዳችን አራት ታናናሽ ወንድሞች እና እህት ያሏቸው ሲሆን፤ እነርሱን ዘወትር ስለሚያስጠኗቸው በልጅነታቸው እሆናለሁ ብለው የሚያስቡት መምህር ነበር። ከዚያ በተጨማሪ ህልማቸው ኢንጅነር መሆን ነው። ለዚህ ፍላጎታቸው ምንጩ አባታቸው ናቸው። አባታቸው ሹፌር ናቸው።
የራሳቸው መኪኖች ስላሏቸው ሁልጊዜ እነርሱን ሲሰሩ ይመለከታሉ። ወንድሞቻቸውም ቢሆኑ ጋራዥ ውስጥ ስለሚሰሩ ቴክኒካል ሥራዎች እንዲስቧቸው ሆነዋል። ህልማቸው አድርገውትም ቀጥለዋል። ዛሬ ሆነው ሲያዩትም በጣም የሚደሰቱበት ለዚህ ይመስላል።
እንግዳችን በጣም የሚወዱትና ዛሬም ቢደገም ብለው የሚመኙት በልጅነታቸው የነበረውን የእምነት መከባበርን ነው። ሐረር ውስጥ የመጀመሪያው መስኪድ ከእነርሱ ቤት ጎን ነው። በዚህም አባታቸው ዲያቆንና በእምነታቸው ጠንካራ ቢሆኑም መስኪዱ ውሃ ስላልነበረው ከሰባት ዓመታት በላይ ከእነርሱ በነፃ እንዲጠቀም አድርገዋል።
በዚያ ላይ ቤተሰቡ የመስኪዱን ግቢ አጽዱ ይሏቸው እንደነበር አይረሱትም። በተመሳሳይ ሙስሊሙም እንዲሁ ቤተክርስቲያንን በዚህ ሁኔታ ያይ እንደነበር አይዘነጉትም። እናም የብዙዎቹ ኢትዮጵያውያን አስተዳደግ ይህንን የያዘ በመሆኑ ዛሬም ሙሉ ለሙሉ አልጠፋምና እየኮረኮርን ትዝታ ጫሪና የቀደመ መልካም ነገራችንን መላሽ መሆን ይኖርብናል ሲሉ ይመክራሉ።
ባለማዕረጉ ተማሪ
እንግዳችን ትምህርትን ‹‹ሀ›› ብለው የጀመሩት በቄስ ትምህርትቤት ሲሆን፤ የስለት ልጅ ሆነው በቤተክርስቲያን በቆዩባቸው ጊዜያት ነው። ስለዚህም እስከ ድቁና ድረስ ትምህርቱን በሚገባ ተምረዋል። ከዚያ አጎቴ የሚሉት ሰው ጋር በመሄድ አንደኛ ክፍልን በጅማ ጀመሩ። ነገር ግን አጎታቸው ለትምህርት ወደ ውጭ አገር በመሄዳቸው የተነሳ ትምህርቱን ሳያጠናቅቁ ተመልሰዋል።
ሆኖም በጣም ጎበዝ በመሆናቸው ሐረር የአንደኛ ክፍል ትምህርታቸውን በአቡነ እንድርያስ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርትቤት እንዲቀጥሉና ብዙም ሳይቆዩ ሁለተኛ ክፍልን እንዲቀላቀሉ ተደርገዋል። ስለዚህም ሦስተኛና አራተኛ ክፍልን ጨምሮ በሁለት ዓመት ውስጥ ማጠናቀቅ ችለዋል።
ከሦስተኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ትምህርታቸውን የተከታተሉት በልዑል ራስ መኮንን ትምህርትቤት ሲሆን፤ ከዘጠነኛ እስከ 12ኛ ክፍል ደግሞ ሐረር ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ወይም በተለምዶ ሐረር ጁኒዬር ትምህርትቤት በሚባለው ነው። ድቁንናውን መማራቸውና ከዚያም በኋላ ደግሞ እናታቸውን እንዲያግዙ ተብለው ከእናታቸው ጋር መሠረተ ትምህርት መግባታቸው የበለጠ ውጤታማ ተማሪ ቢያደርጋቸውም ሁለት ዓይነት ተማሪ እንደነበሩ ግን አይረሱትም።
ከአንድ እስከ አምስተኛ ክፍል ሲማሩ አንደኝነታቸውን ማንም አይቀማቸውም ነበር። ሆኖም ከስድስት እስከ ስምንተኛ ክፍል ግን ጨዋታና ፊልም በጣም ያታልላቸው ነበርና መጨረሻ ጭምር ወጥተው እንደሚያውቁ ያስታውሳሉ። ትምህርትቤት የመግባት ሁኔታቸውም እንዲሁ የቀዘቀዘ ነበር። እንዲያውም ‹‹የአካባቢው ሰው ሁሉ ተቆጪ ስለሆነ አልጠፋንም እንጂ በዚያ አያያዛችን ዛሬ ላይ አንደርስም ነበር›› ይላሉ ጊዜውን ሲያስታውሱት።
ከዘጠነኛ ክፍል በኋላ ቀድሞ ወደ ነበረ የትምህርት አቋማቸው እንደተመለሱ የሚያወሱት እንግዳችን፤ የ12ኛ ክፍል ውጤታቸው ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባቸው አድርጓቸዋል። በእርግጥ ይህም ቢሆን ዲግሪና ዲፕሎማ በሚለው ያወዛገባቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። ምርጫቸውን የሚያደርጉት በተማሩበት ትምህርትቤት ስለነበር መጀመሪያ 3 ነጥብ እና ከዚያ በላይ ያመጣችሁ ለዲግሪ ሙሉ ተባሉ።
ቀጥለው ደግሞ ኮታው ሊሞላ ይችላልና ዲፕሎማ ጨምራችሁ ሙሉ ተባሉ። በዚህም ለዲግሪ የታሰበው ውጤት ዲፕሎማ ሆነና ወደተመደቡበት ጅማ ጤና ሳይንስ ኢንስቲትዩት የአሁኑ ጅማ ዩኒቨርሲቲ ሄዱ።
ጅማ ከገቡም በኋላ የሚፈልጉትን ትምህርት አላገኙም። ምክንያቱም ጅማ የምህንድስና ትምህርት አይሰጥም ነበር።
ስለዚህም ከምህንድስናው ጋር ቀረቤታ ያለውን የሳንተሪ ሳይንስ ትምህርት በመምረጥ እንዲማሩ ሆኑ። በወቅቱ ከፍተኛ ውጤት በማምጣትም የመጀመሪያው የዩኒቨርሲቲ ሰቃይ በዚያው ቀሪ ተማሪ ሆኑ። ይህ ደግሞ ለሌላ ዕድል አዘጋጃቸው። የመጀመሪያ ዲግሪያቸውንም በአካባቢ ጤና አጠባበቅ ሳይንስ እንዲማሩ ሆነ። ይህ ሲሆንም ከፍተኛ ውጤት በማምጣትና የዓመቱ ኮከብ ተማሪ በመሆን ነበር።
የቀጣዩ የትምህርት ጉዟቸው ኔዘርላንድ ላይ የሚወስደን ሲሆን፤ ከሦስት ዓመት የሥራ ላይ ቆይታ በኋላ የውጭ የትምህርት ዕድል አግኝተው በመሄድ የተማሩበት ነው። ትምህርት ቤታቸው ኢንተርናሽናል ኢንስቲትዩት ፎር ሀይድሮኒክ ኤንድ ኢንቫይሮመንታል ኢንጅነሪንግ (IHE) ይባላል። በዚህም ሁለት ተከታታይ ሁለተኛ ዲግሪዎችን ሰርተዋል።
የመጀመሪያው እንደገቡ እንደዛሬው በቀጥታ በሳይንሱ ዘርፍ በምህንድስና ሁለተኛ ዲግሪ ስለማይሰጣቸው ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በውሃ አቅርቦት ምህንድስና (MEng) እንዲሰሩ ሆኑ። ከዚያ በሳይንሱ ዘርፍ ምህንድስናውን ለመማር ውጤታማና የጥናት ሀሳባቸው ተቀባይነት ማግኘት ይኖርበታል። እርሳቸውም ይህንንም ማድረግ ስለቻሉ በሳኒተሪ ኢንጅነሪንግ (MSc) ትምህርት በማዕረግ ተመርቀዋል።
ወደ አገራቸው ተመልሰው ለሦስት ዓመት ካገለገሉ በኋላ ዳግም ራሳቸው በፈጠሩት የውጭ የትምህርት ዕድል ለሦስተኛ ዲግሪ (PhD) ወደ ጀርመን የሄዱት ባለታሪካችን፤ በዚያ ከሮስቶክ ዩኒቨርሲቲ በውሃና አካባቢ ምህንድስና (Dr.-Ing) ትምህርት መስክ ትምህርታቸውን በማዕረግ አጠናቀዋል።
አገራቸውን የሚያስጠራ ሥራ ሰርተውና መልካም ስማቸውን ገንብተውም ነው በከፍተኛ ውጤት ትምህርቱን ያጠናቀቁት። ከዚያ በኋላ የትምህርት ጉዟቸው በሥልጠናና በሥራ የካበተ ሲሆን፤ በምርምርም ሁልጊዜ እየተማሩ እንደቀጠሉ ይናገራሉ።
ከሥራ ባልደረቦቻቸውና ከተማሪዎቻቸው ጋርም በሚሰሯቸው ሥራዎች ሁልጊዜ ተማሪነታቸው እንዳለ እንደሚሰማቸው ያወሳሉ። እንግዳችን ዲፕሎማ እየተማሩ ሳለ ሳይቀር በዘመቻም ቢሆን የውትድርና ትምህርት ወስደዋል።
ይህ የሆነው ደግሞ የመጀመሪያ ዓመት የዲፕሎማ ተማሪ ሆነው ነው። እናም ብላቴ በመግባት የተለያዩ ወታደራዊ ሥልጠናዎችን ወስደዋል። ይህ ግን መጀመሪያ አካባቢ ፍራቻ ውስጥ ከቷቸው ነበር። ምክንያቱም የሥርዓት ለውጥ ተደርጎ ደርግ ወድቆ ኢህአዴግ ገብቷል። ትምህርት ተቋርጦም ሁሉም ቤተሰቡ ጋር ነበር። እናም ዳግም ወደ ዩኒቨርሲቲ አንጠራምን እንጂ እንጠራለንን አላሰቡትም። ሆኖም ተጠርተው ገብተው ዛሬ ላይ ደርሰዋል።
በወሰዱት የውትድርና ትምህርት ብዙ ነገር እንዳገኙ የሚናገሩት ፕሮፌሰር ኢሳያስ፤ ትምህርቱ ሕይወትን በደስታ ለማሳለፍ ብዙ ስንቅ የሚያስቋጥር ነው። ጤናማ ፤ ተስፋ ያለው ሰው፤ አገር ወዳድና ስለሰው የሚጨነቅ ያደርጋል። ስለዚህም በዚህ ሥልጠና ላይ መሳተፌ በጣም ያስደስተኛልም ብለውናል።
ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ጋር የ30 ዓመት ጋብቻ
የሥራ ሀሁ የተጀመረው በ1985ዓ.ም በዲፕሎማ እንደተመረቁ ሲሆን፤ በዚያው በዩኒቨርሲቲው ለመጀመሪያ ጊዜ ሰቃይ ተማሪዎች ቀርተው ነበርና እርሳቸው አንዱ በመሆን በአካባቢ ጤና አጠባበቅ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ በማስተማር ነበር። በእርግጥ እርሳቸው በዩኒቨርሲቲው እቀራለሁ የሚል ሀሳብ አልነበራቸውም።
ምክንያቱም ብዙ ዲግሪና ከዚያ በላይ የትምህርት ደረጃ ያላቸው መምህራን ሰቃይ ሆነው እንኳን በዚያ መቅረት አልቻሉም። ስለዚህም እርሳቸውም የትም ብመደብ እሰራለሁ ብለው ራሳቸውን አዘጋጅተው እንደነበር አይረሱትም።
ከተማሩበት ዩኒቨርሲቲ ሳይርቁ ከመምህሮቻቸው ጋር የሚሰሩበትን ዕድል ያገኙት ፕሮፌሰር ዶክተር ኢንጅነር ኢሳያስ፤ ገና በዲፕሎማ እንደተመረቁ ነበር በፕሮጀክት ሥራዎች ላይ መሳተፍ የጀመሩት። የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ሲይዙ ደግሞ የምርምር ሥራዎች ላይ መሳተፍ ጀመሩ።
ትልልቅ የምርምር ሥራዎችንም ለትምህርት ዘርፉ እንዲያበረክቱ ሆኑ። ስለዚህም ከመማሩ እና ከማስተማሩ ጎን ለጎን የተለያዩ ምርምሮችን እየሰሩ እያማከሩም ጭምር ነው ለ30 ዓመታት በሙያው ላይ የቆዩት።
ሌላው እንግዳችን በሥራቸው ለየት የሚያደርጋቸው ነገር ለአመራርነት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን እንደያዙ ብዙ ሰዎች እያሉ እርሳቸው መመረጣቸው ነው። በዚህም ዲግሪያቸውን ይዘው ከዓመት የሥራ ላይ ቆይታ በኋላ የኃላፊነት ቦታን እንዲቆናጠጡ ተደርገዋል።
ይህም የአካባቢ ጤና ሳይንስና ቴክኖሎጂ ክፍል ኃላፊ መሆን ነበር። በዚህም ውጤታማ ሥራ ሰርተው የውጭ የትምህርት ዕድል በማግኘታቸው የማስተዳደሩን ኃላፊነት ለተወሰኑ ዓመታት አቋርጠው እንዲቆዩ ሆነዋል።
ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ጨርሰው ሲመጡም ከ1995 እስከ 1998 ዓ.ም ድረስም በአካዳሚክ አስተዳደር እንዲያገለግሉ ሆነዋል። በዚህም የዩኒቨርሲቲው የሪጅስትራል ምክትልና ዋና ኃላፊ በመሆን በወጣትነት ዕድሜያቸው የሰሩ ናቸው።
ቀጥለው ደግሞ የዩኒቨርሲቲው ኅብረተሰብ አቀፍ የትምህርት ፍልስፍና ኃላፊ ሆነውም አገልግለዋል። በአካዳሚክ አስተዳደር ዘርፍም በድምሩ ለአስራ ስድስት ዓመታት ያህል አገልግለዋል። እናም በእነዚህ ሥራዎች አንቱታን ያተረፉ በርካታ ሥራዎችን መስራት እንደቻሉ ሥራዎቻቸው ይመሰክሩላቸዋል።
በአካባቢ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዲፓርትመንት ውስጥ ገና በዲፕሎማቸው ጊዜ በመምህርነት ያገለገሉት ፕሮፌሰር፣ በተጨማሪ በውሃ እና በአካባቢ ምህንድስና መስክ ከፍተኛ አማካሪ እንዲሁም ባለሙያ ሆነውም እያገለገሉ ይገኛሉ።
በምርምር ሥራቸውም የላቁ፣ ዘላቂ እና አካባቢያዊ ተስማሚ ያላቸውን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመፍጠርም አሻራቸውን እያሳረፉ ይገኛሉ። በተለይም ለውሃ እና ለአካባቢ ጥበቃ ምህንድስና ዘርፍ የሚሰሯቸው ሥራዎች የሚያስመሰግኗቸው እንደሆኑ ይገለጻል።
በተያያዘም በአዲስ አደረጃጀት የጅማ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት (JiT) በአዲስ መልኩ ሲደራጅ ብዙ የለፉም ናቸው። እስከ ሳይንትፊክ ምክትል ዳሬክተር ድረስም እንዲሰሩበት ሆነዋል። ከዚያ ባሻገር በአገር ደረጃ የባዮሜዲካል ኢንጅነሪንግ ትምህርት ክፍልን በጅማ ካቋቋሙት መካከልም ይጠቀሳሉ።
እንግዳችን በበርካታ ዓለም አቀፍ ሁለገብ ምርምርና አቅም ግንባታ ፕሮጀክቶች ላይም ተሳታፊ ሲሆኑ፤ በመማር ማስተማሩ ሥራ ብዙዎችን ለቁምነገር ያበቁ ናቸው። ለፕሮፌሰርነት ጭምር ያበቋቸው ተማሪዎችም አሉ። እንዲያውም በአሁኑ ወቅት 19 የሁለተኛ እና ከ15 በላይ የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን በምህንድስናው ዘርፍ ያማክራሉ። በተጨማሪም የምርምር እና የአቅም ግንባታ ፕሮጀክቶችን ይመራሉ።
ግልፅ በሆነ የጋራ አስተዳደር የሚያምኑትና ባለ ራዕይ መሪ የሆኑት ባለታሪካችን፤ የድህረ ምረቃ መርሃግብሮችን፣ የምርምር ቤተሙከራዎችን እና ማበልጸጊያ ማዕከልን በፕሮጀክት ደረጃ ማቋቋም የቻሉና ዳይሬክተር በመሆን የመሩም ናቸው። በሀገረ ውስጥና ከሀገር ውጭ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥም ተጋብዘው ለሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች ያስተምራሉ።
በተለይም በውሃ ሀብት አቅም አፍሪካን ለማጠናከር በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ የውሃ ማስተዳደር ልኅቀት ማዕከል (ACEWM) ከጥር 2020 ጀምሮ ከሀገር እና ከአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ ተማሪዎች በማስተማርና በማማከር ሥራ ላይ የማዕከሉ Adujct Professor በመሆን እየተሳተፉ ይገኛሉ።
የግብጻዊቷ ንዴት በገጠመኝ
በኔዘርላንድ ሀገር የትምህርት ምርጫቸውን በተመለከተ የገጠማቸው ነው። ልጅቷ ግብጻዊት የክፍላቸው ተማሪ ናት። በግብጻውያን አካሂድ የውሃ ጉዳይ የሁሉም ዜጋ ጉዳይ ነው። ስለሆነም እያንዳንዱ ዜጋ ውሃ ላይ ጥልቅ ጥናት እንዲያደርግ ያስተምራሉ። የተሻለውን መርጠው እንዲማሩም ያግዛሉ። ከዚያም አልፈው ውሃ ላይ የሚያስተምሩና የሚያማክሩ ፕሮፌሰሮችን ጭምር መርጠው ልጆቻቸውን እንዲያገቧቸው ያደርጋሉ።
በውሃ ላይ ይነሳብናል ብለው የሚያስቡትንም በዓይነ ቁራኛ ይከታተሉታል። እነዚህ ነገሮች ደግሞ እንግዳችንን ፋታ የነሳቸው ነበር። ግብጻዊቷ የክፍል ተማሪ ‹‹ምን የትምህርት መስክ መረጥክ›› የሚል ጥያቄ ታነሳለች። እርሳቸው ደግሞ ‹‹አባይን መገደብ ስለምፈልግ የማጠናው የውሃ ምህንድስና ነው›› ይሏታል። በጣም ትናደዳለች፤ የአይቻልም ስሜቷንም በብዙ መንገድ አሳይታለች።
አንዱ ሥራዋ በወዳጇ በኩል ዕድሉን ማዘጋት ነበር። ሆኖም የፈለጋቸውን የትምህርት መስክ መምረጥ እንደሚችሉ ስምምነቱ ላይ ቢቀመጥም ወዳጇ ተማሪውን ሰብስቦ ይህ ሀሳብ እንዲቀር ለማድረግ ‹‹ከአገራችሁ በመጣችሁበት መስክ እንድትሞሉ›› አለ። እንግዳችንም እጃቸውን በማውጣት ‹‹እኔ ማጥናት የምፈልገው የውሃ ምህንድስና ነው። ይህንን መምረጥ እንደምችል ደግሞ ስምምነቱ ያሳያል። ለምን ይህ ሀሳብ ቀረበ›› ሲሉ ገለጹ።
‹‹ምን ያለበት…›› እንዲሉ ሆነና ልጅቷ አይቻልምን በአደባባይ በተማሪ መካከል ደገመችው። ባለታሪካችንም ሁኔታውን ፍርጥርጥ አደረጉት። ‹‹አባይን እንዳልገድብ ፈርተሽ ነው… ጥቅሙም የሁሉም እኮ ነው … ›› ሲሉም አሸማቀቋት። ስምምነቱ እንደማይጣስ የተረዳውና በሀሳብ መረታቱን ያወቀው ወዳጅም ሞክሩት ብሎ ተዋቸው። እርሷም እየተመናጨቀች ሄደች። በዚያ ሁኔታ መቀጠሉ ያስፈራቸው ፕሮፌሰር ዶክተር ኢንጅነር ኢሳያስም አማካሪያቸውን ቀይረው በጥበብ በአሰቡት መስክ ትምህርቱን እንዳጠናቀቁ ነግረውናል።
የሕይወት ፍልስፍና
ሕይወት ብዙ ፈተናዎች የማይለያት ነች። ሆኖም አጋጣሚዎችን ሁሉ መልካም ማድረግ የሚቻልበትን መንገድም ትጠቁማለች። ግን ሰውዬው ምን ዓይነት ጠንካራና በችግር ውስጥ መልካሙን ማየት ይፈልጋል የሚለውን ትፈልጋለች። ለዚህ ዝግጁ ከሆንን ከባድ ችግሮች ቀላል ይሆናሉ። መልካሙን ሁሉም እናገኛለን።
በተለይም የመፍትሄ አካል መሆን የምንችልበት ሁሉ ይከፈትልናል የሚል አመለካከት አለኝ የሚሉት ባለታሪካችን፤ አራት የሕይወት ፍልስፍና አቅጣጫ እንዳላቸውና እንደሚከተሉት ይናገራሉ።
የመጀመሪያው ሰው ብቻዬን ሰራሁ፤ ብቻዬን ውጤታማ እሆናለሁ የሚለው ነገር ስለማይመቻቸው የእኔ ለውጥ ምንጩም፤ ውጤቱም አብሮ መስራትና አብሮ መጠቀም ነው የሚለው ነው። ሌላው ጊዜ ልዩ ዋጋ እንዳለው ማመናቸው ሲሆን፤ እንደርሳቸው አገላለጽ ‹‹ጊዜ ወርቅ ሳይሆን ለእኔ ሕይወት ነው›› የሚለው የፍልስፍና መርሃቸው ነው።
ቀጣዩ የሕይወት ፍልስፍናቸው ‹‹መስጠት መሰጠት ነው›› የሚለው ሲሆን፤ የተቸገረን ረድተው በእርሳቸው መፍትሄ አግኝቶ ፊቱ ላይ ፈገግታ ሲያዩ በሕይወታቸው ላይ አንድ ዓመት ያህል እንደጨመሩ እንደሚሰማቸው አጫውተውናል።
የመጨረሻው የእውቀት ማማ ላይ ደርሻለሁና ‹‹ትምህርት ይበቃኛል›› የሚል አካል ሊኖር አይገባም የሚለው ነው። እንደእርሳቸው ፍልስፍና እውቀት ነፃ የሆነ የአምላክ በረከት ሲሆን፤ ከሁሉም የሚገኝ ለሁሉም የሚሰጥ ነው።
ማንም ሊሸሽገውና ይፋ ካልወጣ ደግሞ የማይገለጠው ዓይነት ስጦታም ነው። በዚህም ፕሮፌሰር ሁልጊዜ የተማሪዎቹ ተማሪ መሆኑን ሊያምን ያስፈልጋል ይላሉ። በራሱ ተኮፍሶ ብቻውን የሚራመድና የሚሰራ ከሆነ ግን ለእርሱም፣ ለተማሪዎቹ እንዲሁም ለአገሩ የሚያበረክተው ነገር አይኖረውም እምነታቸው ነው።
ሽልማት
እንግዳችን በአበረከቱት አስተዋፅጾ እኤአ ከ1998 ፣ 1999 ፣ 2001 ፣ 2007 ፣ 2013 ፣ 2014 እና 2016 ላደረጉት የላቀ የአካዳሚክና ምርምር ውጤቶች ከተቋማቱ በርካታ ተቋማዊና አገራዊ ሽልማቶችን አግኝተዋል። ከሁሉም ግን የሚልቅባቸው ከተማሪዎች ወርቅ እና የተለያዩ ሽልማቶች በተደጋጋሚ የሚበረከትላቸው እንደሆነ ይናገራሉ።
በሚማሩባቸው ዩኒቨርሲቲዎችም እንዲሁ ሰቃይ ስለሆኑም የተለያዩ ሽልማቶች ተበርክቶላቸዋል። ከእነዚህ ውስጥ ዲግሪያቸውን ሲመረቁ በተከታታይ አራት ነጥብ በማምጣታቸው የዓመቱ ኮከብ ተብለው የተሸለሙት አንዱ ነው። በባዮሜዲካል ኢንጅነሪንግ በሰሩት የምርምር እና የአካዳሚክ ፕሮጀክቶች (የAIHA ፕሮጀክት, የNICHE ፕሮጀክት…) ውጤታማነት የተሸለሙትም እጅግ የሚደሰቱበት እንደሆነ አጫውተውናል።
ቤተሰብ
ስለ ባለቤታቸው ተናግረው አይበቃቸውም። እርሷም ብትሆን እንዲሁ ‹‹እርሱ ለእኔ›› ብላ መግለጽ ሲያቅታት እንባ ነው የሚተናነቃት። እናም መዋደዳቸው ከልባቸው መሆኑን የሚያስረዳልን ሁለቱም ስለ ትዳራቸው ሲያወሩ ቃላት ማጣታቸው ነው። በተለይ ባለታሪካችን ስለእርሷ ሲያነሱ በትምህርት ወደ ውጭ አገር በሚሄዱበት ጊዜ እናትም አባትም ሆና ልጆቹን መንከባከብ መቻሏ ሁሉ ነገሬ መሆኗን የሚነግርልኝ ነው ይላሉ።
የሁለቱ ትውውቅ የጀመረው ሰፈር ውስጥ ሲሆን አብረው ነው ያደጉት። በትምህርትቤትም አብረው ተምረዋል። ሆኖም በትዳርና በፍቅር ሕይወት ተሳስበው አያውቁም። የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን እንደተመረቁ ግን ማግባት እንደሚፈልጉ ለቤተሰቦቻቸው አስረዱ። እነርሱም ምርጫቸውን እርሷ ላይ አደረጉ።
በዚህም ቤተሰቡም እርሳቸውም መርጠዋት የትዳር አጋራቸው እንድትሆን አጯት። አግብተዋትም የዛሬ የአራት ልጆቻቸው እናት አደረጓት። በዚህም ደስተኛ ሕይወት እንዲመሩ ሆኑ።
እንግዳችን በተደራራቢ ሥራ ምክንያት ለቤተሰቡ ብዙ ሰዓት ባይሰጧቸውም እቤት በገቡ ቁጥር ግን አባትነታቸውን በሚገባ ለልጆቻቸውም ሆነ ለባለቤታቸው ያሳያሉ። እንዲያውም ከልጆቻቸው ጋር እግርኳስ ሳይቀር እንደሚጫወቱ ልጆቻቸው በአንደበታቸው ይናገራሉ።
በተመሳሳይ ለባለቤታቸውም ቢሆን ልዩ ፍቅር ይሰጣሉ። አሁን የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪ በመሆኗ በትምህርትም ቢሆን በሚገባ ይደግፏታል። ያስጠኗታል። ይህ ደግሞ ትስስራቸውን ይበልጥ እንዳጠነከረላቸውና ደስታቸውን እንደጨመረላቸው አጫውተውናል።
መልዕክተ ኢሳያስ
ሰዎች ቢኖራቸውና እነርሱም ቢኖሩበት የምለው የመጀመሪያው መልካምነት ነው። ችግሮችን ጭምር ወደመልካም መቀየርና መልካሙን አጉልተው ክፉውን ቀንሰው ቢሄዱ ሁሉ ነገራቸው ስኬታማ ይሆናል ብዬ አምናለሁ። ስለዚህ ሰዎች በዚህ አስተሳሰብ ቢመሩ ይላሉ። ሌላው ያነሱት ነገር ሰዎች ጥበበኛ ቢሆኑ የሚለው ሲሆን፤
በኢትዮጵያዊነት ብቻ የሚገኝ፤ የትም የማይገኝ ሀብት እንዳለ ሰዎች ቢያውቁ ደስ ይለኛል። ይህም ልንቀማ ተሞክሮ ያልተቀማነው፣ ብዙ ሴራ ተሰርቶበት የተሸረሸረ ቢመስልም ሰዎች ቢገለጡ የሚያሳዩት ነገር አብሮነት ነው። እናም ኢትዮጵያ ብለን የምናነሳውን፣ መልካም እሴት የገነባንበትን በማሰብ ወደፊት መጓዝ ይገባናል።
ምክንያቱም የትናንቷን ኢትዮጵያ የተረዱና የኖሩ፣ የሚነግሩን ብዙ አባቶችና እናቶች አሉንና እነርሱን ተጠቅመን ከዘመኑ ጋር እየዋጀን አሁን ያለውን ትውልድ ከመገብነው የትናንቷ የአብሮነት ኢትዮጵያ፤ ስሟ የገነነውና በመልካም እሴቶቿ የምትታወቀው ኢትዮጵያ በእድገት ትመነጠቃለች። ተስፋችንም እርሱ ነውና ይህንን እናድርግ ሲሉ ይመክራሉም።
እንደ አገር አሁን የሚታዩ ችግሮች በአምስት መሠረታዊ ተግባራት ሊፈቱ ይችላሉ። እነዚህም መጀመሪያ ችግሩ ችግር መሆኑን መቀበልና ማወቅ ነው። ከዚያ ችግሩ ለምን ተፈጠረ፣ የሚያባብሰው ምንድነው? እንዳይመጣ የሚያደርገውስ ምን ሊሆን ይችላል ብሎ ምንጩን መለየት ያስፈልጋል።
በመቀጠል ደግሞ ወደ መፍትሄው መሄድ ነው። በዚህ ሳናቆም መፍትሄው ምን ያህል ዘላቂ ነው፤ ምንጩ ደርቋል ወይ የሚለውንም ማረጋገጥ ይገባል። ከዚያ በመጨረሻ መደረግ ያለበት በችግሩ የተጎዳውን የማከም ሥራ መስራት ነው። ይህ የሚሆነው ደግሞ በእውቀት፣ በክህሎት፣ በአመለካከት ቅየራ ነውና ይህ ተግባራችን ይሁን ሲሉ መልዕክታቸውን ቋጭተዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 14/2013