አስናቀ ፀጋዬ
የደቡብ ምስራቅ እስያዋ ደሴቲቱ ሀገር ሲንጋፖር በሰማይ ጠቀስ ህንፃዎቿና በከተማ ፅዳቷ ይበልጥ ትታወቃለች፡፡ በነፃ፣ በፈጣራ ስራ፣ በተለዋዋጭነቱና በንግድ ተስማሚነቱ የሚጠቀሰው ኢኮኖሚዋም በተለይ የውጪ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ለእድገቷ ጉልህ ሚና ተጫውቷል፡፡
ሲንጋፖር ስሟ እንዲህ ከፍ ብሎ ቢጠቀስም ኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ በተወሰነ መልኩ በኢኮኖሚ ዕድገቷ ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል፡፡በቫይረሱ ከ59 ሺ በላይ የሚሆኑ ዜጎቿ መያዛቸውንና 29 ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ መሞታቸውን ለዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት አድርጋለች፡፡
ወረርሽኙ ባስከተለው የዓለም ምጣኔ ሃብት እኤአበ2020 በጥልቅ መኮማተር ውስጥ እንደነበርና እድገቱም ከዜሮ በታች 4 ነጥብ 4 ከመቶ ማሽቆልቆሉን የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት በቅርቡ ማሳወቁ ይታወሳል፡፡የሲንጋፖር ኢኮኖሚም በተመሳሳይ ሁኔታ መኮማተሩን ድርጅቱ አስታውቋል::
ቢዝነስ ስታንዳርድ ከትናንት በሥትያ ባወጣው መረጃ ቸር ወሬ አሰምቷል፡፡እንደመረጃው የዓለም አቀፍ ምጣኔ ሃብት አወንታዊና አሉታዊ እድገቶችን በመመዘን ሲንጋፖር ኢኮኖሚዋ በኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ከደረሰበት አስከፊ ድቀት ማገገም ችሏል፡፡
ሀገሪቱ ኢኮኖሚዋ ከነበረበት 4 ከመቶ ወደ 6 ከመቶ፣እንዲሁም የተጣራ የሀገር ውስጥ ምርት ደግሞ በ6 ነጥብ 3 ከመቶ እንደሚያድግ ዘገባው ያመለከተ ሲሆን፣ዕድገቱ እኤአ ከ2011 ወዲህ የተሻለ እንደሆነ ሀገሪቷ መግለጿን ዘገባው ጠቅሷል፡፡
ዓለም አቀፍ የምጣኔ ሃብት አሉታዊና አወንታዊ እድገቶችን በመመዘንና ያለፈው ዓመት የህዳር ወር ትምበያ ላይ በማተኮር የሲንጋፖር ኢኮኖሚ በዚህ ዓመት ከ4 ወደ 6 በመቶ እንደሚያድግ የሀገሪቱ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚንስቴር ጠቅሶ ዘገባው ቢያመለክትም በ2020 ሁለተኛው ሩብ ዓመትኢኮኖሚው በ13 ነጥብ 3 ሲኮማተር ከነበረው ጋር ሲነፃፀር የዚህ አመት የኢኮኖሚ እድገት ፍጥነቱ አነስተኛ እንደነበረም በንፅፅር አስታውሷል፡፡
የሲንጋፖር ኢኮኖሚ በተለይ በ2020 በኮሮና ወረርሽኝ ሲመታ ሚኒስቴሩ የመጨረሻ ትምበያውን ያስቀመጠ መሆኑን ዘገባው ጠቅሶ፣ኢኮኖሚው በ5 ነጥብ 4 በመቶ መኮማተሩንና ይህም ሀገሪቱ ነፃነቷን ካገኘች በኋላ አስከፊው የኢኮኖሚ ድቀት እንደሆነ መግለፁንም በዘገባው ተመላክቷል፡፡
አሁንም ይህ አኃዝ ባለፈው ወር ከተሰጠው የ 5 ነጥብ 8 በመቶ ግምት በላይ መሆኑንና በታህሳስ ወር ከተሰጠው ከ 6 ነጥብ 5 እስከ 6 በመቶ የትበያ ክልል ካለው በአማካይ በ6 ነጥብ 25 በመቶ ከፍ ያለ መሆኑም በዘገባው ተጠቁሟል፡፡
እንደዘገባው ይህ ሊሆን የቻለው ኢኮኖሚው በአራተኛው ሩብ ዓመት መጀመሪያ ከተገመተው በታች በመሆኑና ከዓመት ዓመት በ 2 ነጥብ 4 በመቶ በመቀነሱ ብሎም በሦስተኛው ሩብ ዓመት ከነበረው የ 5 ነጥብ 8 በመቶ መቀነስ መሻሻል በማሳየቱ እና የ 3 ነጥብ 8 በመቶ ቅናሽ ካለው የቅድመ ግምት ከፍ ያለ ሆኖ በመገኘቱ ነው:: በየሩብ ዓመቱ በተሰራው ወቅታዊ ማስተካከያ መሰረትም የሲንጋፖር ኢኮኖሚ በተለይ ደግሞ በአራተኛ ሩብ አመት ላይ በ 3 ነጥብ 8 በመቶ አድጓል ሲልም የሲንጋፖር ዕለታዊ ዘገባ ያስረዳል::
በታህሳስ ወር 2020 መጨረሻ ላይ የሲንጋፖር የኢኮኖሚ ሰርቬይ ከተሰራ ጀምሮ በብዙ የአለም ምጣኔ ሃብቶች ውስጥ የተረጋገጡ የኮቪድ 19 መከላከያ ክትባት እየተዋወቁ መሆናቸውን ተከትሎ በኮቪድ 19 ክትባት ልማትና ስርጭት ላይ መሻሻል መኖሩን የሀገሪቱ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚንስቴር ጠቅሷል፡፡
ምንም እንኳን የክትባት ስርጭት ፍጥነት ከሀገር ሀገር ቢለያይም እንደ አሜሪካ እና በዩ ሮዞን አካባቢ የሚገኙና የላቀ ኢኮኖሚ ያላቸው ሀገራት ክትባቱን በዚህ አመት አጋማሽ ለህዝቦቻው የማቅረብ ሲፊ አድል ያላቸው መሆኑንና ይህ ደግሞ በምላሹ ኢኮኖሚያቸው በፍጥነት እንዲያገግም በእጅጉ እንደሚረዳም ሚንስቴሩ አስታውቋል፡፡በአንፃሩ የወረርሽኙ ስርጭት ዳግም በማገርሸቱ በቀጠናው በሚገኙ ማሌዢያና ኢንዶኔዢያ በመሰሉ ሀገራት የኢኮኖሚ አድገት ተስፋው ሊዳከም እንደሚችልም አስቀምጧል፡፡
የሚኒስቴሩን መገልጫ ጠቅሶ የወጣው ሪፖርት “ሚዛናዊ በሆነ ሁኔታ ፣ ቁልፍ በሆኑ ውጫዊ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የተገኙት አዎንታዊ ለውጦች አሉታዊውን የሚያካክሱ በመሆናቸው ፣ ከሦስት ወር በፊት ከነበረው ጋር ሲነፃፀር የሲንጋፖር የውጭ ፍላጎት አተያይ በጣም ተመሳሳይ ነው” ሲል አመልክቷል፡፡
በወረርሽኙ ምክንያት በአለም ምጣኔ ሃብት መልሶ ማገገም ላይ ጥርጣሬዎችና አደጋዎች መኖራቸው ከግምት ውስጥ መግባት እንዳለበትም ሚንስቴሩ ጠቅሶ፤ የሲንጋፖር የኮቪድ 19 ሁኔታ በቁጥጥር ስር ውሎ የክትባት ፕሮግራሙ እየተካሄደ ቢሆንም፣ በዓለም ዙሪያ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ዳግም እየጨመረ መሄደ እና ይበልጥ ተላላፊ የሆኑ የቫይረሱ ዝርያዎች መከሰታቸው የድንበር መልሶ መከፈቱን ፍጥነት እንደሚያዘገየው መታሰብ እንዳለበትም አመልክቷል፡፡
እነዚህ ችግሮች እንዳሉ ሆነው ታዲያ የሲንጋፖር ኢኮኖሚ በዚህ ዓመት ቀስ በቀስ እያገገመ እንደሚሄድ ሚንስቴሩን ጠቅሶ የወጣው ሪፖርት እንደሚያሳይም በዘገባው ተጠቅሷል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 10/2013