ክፍለዮሐንስ አንበርብር
እንደመግቢያ
ወደ ሥራ ዓለም ከገቡ 32 ዓመታትን አስቆጥረዋል። 16 ዓመታትን በመንግሥት ተቋም ከ16 ዓመታት ወዲህ ደግሞ በግል የማማከር ሥራ ጀምረዋል። ከ32 ዓመት በፊት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሥነ ህንፃ ትምህርት አጠናቀው በመንግሥት ተቋም ሲቀጠሩ ወርሃዊ ደመወዛቸው 600 ብር ነበር።
ፊላንድ ሀገር ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አጠናቀው ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላ ደግሞ 100 ብር ጭማሪ ተደርጎላቸው ደመወዛቸው 700 ብር ደረሰ። ከመንግሥት ተቋም ሥራ ትተው ወደ ግል ሥራ ፊታቸውን ሲያዞሩ ደመወዛቸው 1ሺ200 ብር ነበር። በዚህ ደወመዝ ራሳቸውን ደጉመው ቤተሰብም ያግዙ ነበር።
ወደ ግል የማማከር ሥራ ሲገቡ በ35ሺ ብር ቀበና አካባቢ በአንድ ኬክ ቤት ‹‹ሀ›› ብለው ሥራ የጀመሩ ሲሆን፤ ከዚህ በኋላ ግን ብዙ ሥራዎች እየጎረፉላቸው መጡ። በዚህም ዓለም አቀፍ እውቅና ካላቸው ድርጅቶች ጋር እስከ መሥራት ደረሱ። ኑሮ እና እኚህ ሰው አብረው ብዙ ነገር አይተዋል።
ኑሮ እንደ ገብስ ቆሎ ፍትግ አድጋቸዋለች፤ እንደ ወራጅ ውሃ ግራ ቀኝ እያላጋች በብረቱ ድካም ፈትናቸዋለች። ግን ጥንካሬያቸው እንደ ብረት አሎሎ ነበር። እንደ እንዝርት ሾረው የተዋጣላቸው ስኬታማ ሰው ለመሆን የቻሉም ናቸው።
እንግዳችን በሀገራዊ ጥሪም ተሳትፈዋል። በ1977 ዓ.ም በመልሶ ማቋቋም ዘመቻ ወደ ጋምቤላ አቅንተው የሚቻላቸውን አድርገዋል። ዕድገት በህብረት በጣና ዙሪያ ከሚገኙ መንደሮች ደልጊ ዘምተውም ለሀገራዊ ጥሪ ምላሽ ሰጥተዋል።
ጨዋታ አዋቂ በመሆናቸው ደግሞ አቀራረባቸው ቀለል ያለና ፈገግታ ከፊታቸው የማይጠፋ ነው። ‹‹ጨዋ፣ ሰው አክባሪ፣ ለድርጅታቸው ሠራተኞች ክብር ያላቸው፣ ንግግራቸው ደርዝ ያለውና በውይይት የሚያምኑ፣ ለእውቀትና ለባለሙያ ቅድሚያ የሚሰጡ›› ሰው ስለመሆናቸውም በቅርብ የሚያውቋቸው ይመሰክሩላቸዋል።
በዚህም ይህንን ሁሉ ልምድ እንዴት እንዳካበቱት አውግተውናልና ከተሞክሯቸው ትቋደሱ ዘንድ ‹‹ ለህይወት ገጽታ›› አምድ እንግዳችን አድርገናቸዋል። የሥነ ህንፃ ባለሙያውንና በሆቴል ኢንቨስትመንት ኢንጅር ጌትነት ሳህሌን። መልካም ንባብ።
የ”ሀ፤ ሁ‘ ጅማሮ
የትውልድ ቦታቸው ጎንደር ከተማ ነው። በዕለተ ቃና ዘገሊላ ጥር 12 ቀን 1948 ዓ.ም ተወለዱ። የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ድል ተራ በአሁኑ ወቅት ህብረት በሚባለው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ያደረጉ ሲሆን፤ እስከ ስድስተኛ ክፍል ተምረውበታል። በቀድሞ አጠራሩ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ በአሁኑ ወቅት ፋሲለደስ በሚባለው ትምህርት ቤት ደግሞ ከ7ተኛ እስከ 11ኛ ክፍል ድረስ ተምረዋል።
ለተሻለ ትምህርት ፍለጋ በሚል 12ተኛ ክፍል ትምህርታቸውን አዲስ አበባ እህታቸው ዘንድ ተቀምጠው ሳሪስ በሚገኘው ንፋስ ስልክ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መማር ችለዋልም።
የ12ኛ ክፍል ውጤታቸው ለዩኒቨርሲቲ የሚያበቃ በመሆኑም 1974 ዓ.ም አራት ኪሎ በሚገኘው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ግማሽ ሴሚስተር ተማሩ። ከዚያ በኋላ እስከ ሐምሌ 1978 ዓ.ም ደግሞ ልደታ በሚገኘው ህንፃ ኮሌጅ አራት ዓመት ተኩል የሥነ ህንጻ ትምህርት አጠኑ።
ከዚያ በመጠቀል ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኮሚሽን በመንግሥት ተመድበው ለ20 ቀናት ብቻ ሰርተው ወደ ሌላ ቦታ እንዲዛወሩ ተደረገ። ከሳይንስና ቴክሎጂ ኮሚሽን በወቅቱ ኮንስትራክሽን ዲዛይን ኢንተርፕራይዝ በሚባለው እና በአሁኑ አጠራሩ ህንፃ ዲዛይን ድርጅት ተመድበው እስከ ጥቅምት 1993 ዓ.ም ድረስ ለ16 ዓመታት በዚህ ተቋም አገለገሉ።
ጉዞ ወደ ፊላንድ
ነሐሴ 1980 ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ለመማር ወደ ፊላንድ ሄልሲንክ አመሩ። 1983 ዓ.ም በወርሃ መስከረም በሥነ ህንጻ የትምህርት ዘርፍ ተመርቀውም ወደ ሀገራቸው ተመለሱ። ይሁንና ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ ፖለቲካው ምስቅልቅል ውስጥ ነበር። የፖለቲካ ሽግግር ስለነበርም ብዙ የፀጥታ ችግር ተከስቷል።
በእርግጥ ወደ ውጭ ሀገር ሲሄዱ የድጋፍ ደብዳቤ የፃፉላቸው አለቃቸው የነበሩት ኢንጅነር ካሣ ኃይሌ ‹‹ትምህርትህን አጠናቀህ ለእናት ሀገርህ እንድታገለግል በዚያው እንዳትቀር›› ብለው አሳስበዋቸው ስለነበር ይህም ቢሆን ብዙም አልፈሩም። በዚያ ላይ ‹‹እኔ ሀገሬን ስለምወድ ሳይሆን የድሃ ልጅ ስለሆንኩና ቤተሰቤን መርዳት ስላለብኝ እመለሳለሁ›› ብለው ስለነበር ወደሥራ ለመግባት ይሯሯጡ ጀመር።
በወቅቱ የቤቶች ልማት ሥራ አስኪያጅ የነበሩት ፀዳለ ማሞ፣ ፋሲል እና ስሜነህ ከሚባሉ ኢትዮጵያውያን ጋር ሆነው ወደ ፊላንድ ያመሩ ሲሆን፤ ሁሉም ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል። ቃላቸውንም አክብረዋል። ሀገር ወዳድ መሆናቸውንም በቃልም በተግባርም አስመስክረዋል።
‹‹ከኢትዮጵያ ርቆ መኖርን እንኳን በእውናችን ቀርቶ በህልማችን አንዳችንም አስበነው አናውቅም ነበር›› ይላሉ ከቃል መታመንና የሀገር ፍቅር ስሜት አንጻር የተናገሩትን ሲያስታውሱ። ‹‹ያ የደግንት ዘመን ሀገራችንን እንድንወድና በአግባቡ ተቀርፀን ስላደግን እንጂ ሁላችንም በፊላንድ ሀገር የተሻለ ዕድል አግኝተን ነበር›› ሲሉም ያስታውሳሉ።
የፊላንድ ትውስታዎች
የፊላንድ ህዝብ ጥሩ ነበር። መኖሪያ ቤት እና ትምህርት ነፃ ነው። ወደ ኢትዮጵያ መጽሐፍ ገዝተው ሲመጡም ቅናሽ ይደረግ ነበር። ግን በርካታ የፊላንድ ዜጎች ጥቁር ህዝብ በቴሌቪዥን ካልሆነ በቀር በአካል አይተው ስለማያውቁ ግራ ይጋቡ እንደነበር አይረሱትም።
እኛ ኢትዮጵያውያን ከአስተዳዳሪዎቻችን ውጭ ሌላ አስተዳዳሪ አናውቅም። አስተዳዳሪዎቻችን የራሳችን ሰዎች ነበሩ። በዚህም የተነሳ እኛ ኢትዮጵያውያን አንገት አንደፋም፤ አንሸማቀቅም።
ኢንጅነር ጌትነት፤ የትምህርት መስካቸው የህንፃ ዲዛይን ስለነበር ታሪካዊ ህንፃዎችን ለማየት ወደ ጀርመን፣ ግብፅ እና ሲዊድን ሄደዋል። በዚህ ወቅት ግን አንዳንድ አይረሴ ገጠሞች ነበሯቸው። በህጋዊ መንገድ ግብፅ ለመግባት ሲሉ ኢትዮጵያውያን ላይ ክልከላ ተደርጎ ነበር። ስለዚህ የሚመለከተው አካል በአካል መጥቶ መፍቀዱን መቼም አይዘነጉትም።
ጀርመን በሄዱ ጊዜም በኢትዮጵያ በነበረው የፖለቲካ ውጥንቅጥ የተነሳ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ጥገኝነት ይጠይቁናል በሚል እሳቤ ተከልክለው ነበር። ይህንን ለማስፈቀድም ብዙ ልፋት እንደነበር ያስታውሳሉ።
ፊላንድ እያሉ ኢትዮጵያ ውስጥ በነበረው ድርቅ ገንዘብ ለማሰባሰብ የሞከሩ ሲሆን፤ በዚህም የፊላንድ ሰዎች ተባባሪ እንደነበሩ ይናገራሉ። አሁንም ባለው ሁኔታ በፊላንድ ሀገር የተማሩ የቀድሞ ተማሪዎች ማህበር አባል ናቸው።
ዛሬም ትውስታቸው ከፊላንድ ጋር እንደተሳሰረ ነው። እጅግ ከፍተኛ የሆነ በረዶ እና ቅዝቃዜም በጣም አስቸጋሪ እንደሆነና ይህን ከኢትዮጵያ ጋር ሲያስተያዩት አግራሞት እንደሚፈጥርባቸው አጫውተውናል።
ፊላንዶች በረዶ እና አስቸጋሪ የአየር ፀባይ ይዘው ሌላውን ዓለም ያግዛሉ። በኢትዮጵያ ያለው ምቹ ሁኔታ ደግሞ ሰነፍ ሳያደርገን አይቀርም የሚል ግምትም አላቸው።
የቀለሜ ልጅ!
አባታቸው መምህር ነበሩ፤ የቀለሜ ልጅ ናቸው። ቤታቸው ሰፊ ነው። እርሳቸው ለቤቱ አራተኛ ልጅ ናቸው። እርሳቸው ዩኒቨርሲቲ ሲገቡ አባታቸው ጡረታ ወጥተዋል። ለቤቱ አንጋፋ ወንድ ልጅ የነበሩት እርሳቸው ናቸው።
የመጨረሻ ወንድማቸው የተወለደው ኢንጅነር ሳህሌ ዩኒቨርሲቲ ሲገቡ ነበር። ሴቶቹ በጊዜ ትዳር ይዘዋል። የቤተሰብ ገቢ ስላልሆነና የአባታቸው ጡረታም ቤቱን ሙሉ ማድረግ ስለማይችል በችግር ውስጥም ሆነው ነው የተማሩት።
አባታቸው ጎንደር ከተማ በሚገኘው በቀዳማዊ ኃይለስላሴ የአዳሪ ትምህርት ቤት ከፈረንጆች ጋር ያስተምሩ ነበር። አማርኛ መምህርም ነበሩ። ያኔ! ጎንደር፣ ጎጃም ያሉት የመንግሥት ሠራተኞች የክረምት ትምህርት ወደ አስመራ መምህራን ማሰልጠኛ ሄደው ይማሩ ነበር።
አባትዬውም በዚህ ወቅት ወደ አስመራ ሄደው ተምረዋል። ብዙ ነገር አካብተዋልም። ለልጃቸው ጌትነት ብዛት ያላቸው መጽሐፍት ይገዙላቸው የነበረውም ከዚህ የተነሳ እንደሆነ ያስባሉ። በተለይ የፊዚክስ፣ ኬሚስትሪና ሌሎች የሳይንስ መጽሐፍትን 20 ብር ድረስ አውጥተው ይገዙላቸው ነበር። በወቅቱ ይህ ገንዘብ እጅግ ብዙ የሚባል ነው።
አባትየው ልጃቸው በትምህርት ታታሪ እንዲሆን ፅኑ ፍላጎት አላቸው። ይህ ፍላጎት እውን እንዲሆን ደግሞ ዓለም አቀፍ ዝናን ያተረፉ መጽሄቶችን ይገዙላቸው ነበር። በክረምት ወራት ደግሞ ሥራ ልጃቸው እንዲለምድ በማሰብ አንዳንዴ በጋራዥ ቤት፣ አናፂነትና ሌሎች ሥራዎችን እንዲሰሩ ያደርጉ ነበር።
ይህ ሁኔታ በእርሳቸው ላይ የጥንካሬ ምንጭ እንደሆነ ይናገራሉ- ኢንጅነር ጌትነት። 1966 ዓ.ም በነበረው የለውጥ እንቅስቃሴ 11 ኛ ክፍል ትምህርታቸውን አቋርጠው ነበር። በዚህ ዕድገት በህብረት ጎንደር ጣና ጥግ በሚገኘው ደልጊ በሚባል ስፍራ ዘምተው ሁለት ዓመት አገልግለዋል።
የልጅነት ትዝታ
በአብዛኛው ሕይወታቸው በቤተክርስቲያን ውስጥ ያለፈ ነው። ለጥምቀት በዓል ደግሞ ልዩ ትዝታ አላቸው። ዲያቆንም ስለነበሩ ብዙ! ብዙ! ነገር አይተዋል። እስከ ስምንተኛ ክፍል በነበራቸው ቆይታውም ቤተክርስቲያን በድቁና አገልግለዋል። ከሃይማኖት ጋር ያላቸው ትስስርም እስከዛሬም ድረስ በእጅጉ ይመስጣቸዋል፤ በትዝታ ይወሰውሳቸዋል። ዝማሜው፣ የፅናፅሉ ደምጽ አሁንም በጆራቸው ላይ ያቃጭላል።
በወቅቱ የነበረው የበዓል አከባበር ቱሪስትን ማዕከል ያደረገ ሳይሆን ቀኖናው ላይ ያኮረ ብሎም በተመረጡ ካህናት የሚመራና የሚወደስ ስለነበር ነገሩ ሁሉ አይረሴ ሆኖባቸዋል። ቅኔ ለመዝረፍና ለማስመስከርም የነበረው ዝግጅት ሁሉ ዛሬም ይገርማቸዋል። ያኔ የነበራቸው ትውስታ እስከዛሬም ድረስ አብሯቸው ይጓዛል።
1961 ዓ.ም እስከ አ1966 ዓ.ም በትምህርት ቤቶች በየጊዜው ሰልፍ ነበር። በዚህም ትምህርት ይቋረጥ ነበር። ግን ደግሞ ተማሪዎች በህብረት የማጥናት ባህል ነበራቸው። በተለይም ቤተክህነት አካባቢ ያሉ ልጆች በትምህርት ብዙ ስኬታማ ነበሩ ይላሉ። እርሳቸውም ልጅነታቸውን በዚህ አካባቢ ማሳለፋቸው እንደጠቀማቸው ይናገራሉ።
ምንም እንኳ ልጅነታቸውን ያሳለፉት ጎንደር ቢሆንም እስከ 2000 ዓ.ም ጎንደር የመሄድ ልምዳቸው አናሳ ነበር። አዲስ አበቤ ሆነው ነገሩን ረስተውት ነበር። ግን በአጋጣሚ ጎንደር ከተማ የጀመሩት ኢንቨስትመንት በየዓመቱ ከተማዋን እንዲጎበኙት ዕድል ሰጥቷቸዋል።
የከተማ እመቤት
አርክቴክት ጌትነት ጎንደር እና ሐረር ከተማን ለየት አድርገው ይመለከቷቸዋል። ጎንደር ከተማ ከሆነች ዘመናትን ያስቆጠረች ከተማ ናት። ጎንደር እና ሐረር የተለየ ባህሪ አላቸው። ዘር፣ ሃይማኖትና ሌሎች ችግሮችን አይነኳኳቸውም። ከተሞቹ ጥንታዊ ከመሆናቸው የተነሳ ሜትሮፖለቲያን ባህሪ ተላብሰው የመጡ በመሆናቸው ይህን ነገር እርግፍ አድርገው ትተውት መጥተዋል የሚል እምነት አላቸው።
ጎንደር በኢትዮጵያ በ16ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የእሳት አጥፊ ብርጌድ ያላት ከተማ ነበረች። በወቅቱ ከተማዋ እሳት ያስቸግራት ስለነበር ሁሉም ሰው የማይጠጣ ውሃ በየበራአፉ ላይ በማሰሮ እንዲያስቀምጥ ይደረግ ነበር።
ከዚያ እሳት የተነሳ እንደሆነ ሁሉም ሰው ውሃውን ይዞ እሳት ወደተነሳበት ሥፍራ ያመራና እሳቱን ያጠፋ ነበር። ሐረርም በኢትዮጵያ ታሪክ አሸራዋ ትልቅና በብዙ መንገድ ተምሳሌት እንደሆነው ይናገራሉ የሥነ ህንፃ ባለሙያው- ኢንጅነር ጌትነት።
በእርግጥ እርሳቸው የጥንት ከተሞችን ማድነቅ ብቻ ሳይሆን የጥንት ካህናትና ሃይማኖት አባቶች ትውውቅ፤ መከባበርና መተባበር አሁንም ይገርማቸዋል። ካህናቱእርስ በርስ ይተዋወቁ ነበር። ጎንደር፣ አክሱም፣ እና ወሎ ያሉ ካህናትና የሃይማኖት አባቶችም ይተዋወቃሉ፤ ይከባበራሉ። መጀመሪያ መስከረም 21 ላይ ግሸን ሄደው ያከብራሉ።
ከዚያን በህዳር 21 ወደ አክሱም ያቀኑና አክሱም ፅዮንን ያከብራሉ። በመቀጠል ደግሞ ወደ የገና በዓል ላሊበላ ያከብራሉ። በመጨረሻ ጥር ጎንደር ላይ ተገናኝተው ጥምቀትን በደመቀ ሁኔታ ያከብራሉ።
ያኔ ከአንዱ ቦታ ያለው ካህን ከሌላው ጋር ተያይዞ ወደ ሌላ ቦታ እየሄዱ ያከብሩ ነበር። ከዚያን ከጥር ወር በኋላ ወደየቤታቸው ተመልሰው ምርታቸውን ሰብስበው እርሻቸውን ያቀላጥፋሉ።
ወደ ግል ሥራ
ከመንግሥት ተቋም ወጥተው የግል ሥራ ለመጀመር የወሰኑት ፊላንድ ሆነው ነው። እዚያ ሀገር በአንድ አማካሪ ቢሮ እስከ 200 ሰዎች ይቀጥራሉ። ታዲያ ይህን ልምድ ከዚያ ቀስሙ። የግል ሥራቸውን ለመጀመርም ቀጣይ ስንቅ ሆናቸው።
ከዚያም ከ1993 ዓ.ም ጀምሮ በግል መንቀሳቀስ ጀመሩ። ከዚያም የመንግሥት ሥራ ላይ እያሉ የግል ፈቃድ ለማውጣት ሞከሩ። ቀን ቀን የመንግሥት ሥራ አከናውነው ማታ ማታ ደግሞ ወደ ግል ሥራቸው ያመራሉ።
በመንግሥት ተቋም ሥራ እንደጀመሩ የመጀመሪያ ሥራቸው ዘመቻ መምሪያ ካፌ እና ቡራዩ ጡብ ፋብሪካ ሼድ ነበር የሰሩት። ከፊላንድ እንደተመለሱ ደግሞ የድሬዳዋ አውሮፕላን ማረፊያን ሰርተዋል።
ከዚያ በግል የሰሩት የመጀመሪያ ሥራ ደግሞ ቀበና አካባቢ የሚገኘው ‹‹ሊዲያ ኬክ ቤት›› የተሰኘው ነው። በዚህ ወቅትም በ35ሺ ብር የኤሌክትሪካል፣ ሳኒተሪ፣ ቢል ኦፍ ኳንቲቲ፣ ዲዛይኑንና ሌሎች ሥራዎችን በሙሉ ሰሩት። ይህን ሥራ ካከናወኑ በኋላ የትውውቅ አድማሳቸው እየሰፋ ልምዳቸውም እየዳበረ መጣ።
በግል ከሰሯቸው ነገሮች ሁሉ ለየት የሚልባቸው በሳር ቤት አካባቢ የሰሩት ‹‹አዳምስ ፓቪሊዮን›› የተሰኘው ህንፃ ነው። ባለሃብቱ ደውለው አንድ ሥራ ሥራልን ይሏቸዋል። ግን አቶ ጌትነት ሦስት ጉልቻ ለመመስረት ሩጫ ላይ ስለነበሩ ሁለት ሳምንት እንዲታገሷቸው ጠየቁ። ይህኔ ታማኝነትህና ግልጽነትህ ያስደስታል እሽ እንታገሳለን አሏቸው። ታዲያ አቶ ጌትነትም የዋዛ አልነበሩምና ሠርጋቸው ላይ እንዲገኙ የጥሪ ካርድ ሰጧቸው።
እርሳቸውም ‹‹ጠሪ አክባሪ›› ነው ብለው በማመናቸው ከአቶ ጌትነት ሠርግ ላይ በክብር ተገኝተዋል። ከሠርጉ በኋላ ሥራውን ተዋወሉና በ100ሺ ብር ሰሩላቸው። ከዚያን በኋላ ግን ገበያው ይጎርፈላቸው ጀመር። በመቀጠል 140ሺ ብር ዋሽንግተን ሆቴልን ዲዛይን ሰርተው አስረከቡ።
ይህ ደግሞ ሌላ ገበያ፣ ሌላ ዕድል አመጣ። ኢንጅነሩ መጀመሪያ በመንግሥት ተቋም ሲቀጠሩ ወርሃዊ ደመወዛቸው 600 ብር ነበር። ማስተርሳቸውን አጠናቀው ሲመጡ ደመወዛቸው 700 ብር ደረሰ። ከመንግሥት ቤት ሲወጡ ደግሞ ደመወዛቸው 1ሺ200 ብር ነበር። ግን በግል ሥራቸው ቆጥረው የማያውቁትን ብር ቆጠሩ። እናም ሥራቸውን እያጠናከሩት እያሰፉት ሄዱ።
በግል የማማከር ሥራ ከጀመሩ ወዲህ ሐዋሳ ጊዮርጊስ ቢራ ፋብሪካ፣ ካስትል ወይን ፋብሪካ፣ ሐረር ሒንከን ቢራ ፋብሪካ ቆሻሻ ማስወገጃ፣ ሀበሻ ቢራ ፋብሪካ፣ ዳሽን ቢራ ፋብሪካ፣ ዘቢደር ቢራ ፋብሪካ ላይ አሻራቸው ካረፈባቸው የምግብ ፋብሪካዎች ውስጥ በዋናነት ይጠቀሳሉ። በዚህም ከዓለም አቀፍ አማካሪዎች ጋር የመሥራት ልምድና አጋጣሚዎችን አካብተዋል።
በሆቴሎችና በርካታ መንግሥት ተቋማትን ዲዛይን ሰርተዋል። ለአብነት የማኔጅመንት ኢንስቲትዩት፣ አምስት ኪሎ፣ ስድስት ኪሎ የሚገኙ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥም ብዙ ሥራዎችን አከናውነዋል።
ፖለቲከኛው ልብስ
ኢንጅነር ጌትነት ሥራ በጀመሩበት ወቅት ጊዜውና የፖለቲካ ሥርዓቱ እንደሚያስገድደው እንደ ማንኛውም የመንግሥት ሠራተኛ ዩኒፎርም መልበስ ነበረባቸው። በደንቡ መሰረት በራሳቸው ወጪ አንድ ዳለቻ ካኪ እና አንድ ሰማያዊ ሙሉ ልብስ ማሰፋት ነበረባቸው። ግን በወቅቱ ቤተሰብ የማገዝ ኃላፊነት ስለነበረባቸው ብር አልበቃ አላቸው። በወቅቱ የኢሰፓ ፀሐፊ የነበሩት አቶ አዲስ ይባሉ ነበር።
እርሳቸው ዘንድ ቀርበው ችግራቸውን አስረዱ። በወር እጄ ላይ የሚደርሰው 450 ብር ነው። ኃላፊነት አለብኝ ቤተሰቤን አግዛለሁ። በዚህ ላይ የእናት ሀገር ጥሪ እና ትራንስፖርት ተቆርጦም አይበቃኝም ሲሉ ችግራቸውን አስረዷቸው፤ ተለማመጧቸው። ታዲያ ሁኔታውን ስለተገነዘቡ ወደ ሥራህ አትኩር ብለዋቸው ያለ ደንብ ልብስ ሥራቸውን መከወን እንደጀመሩ ያስታውሳሉ።
ነፃ አገልግሎት
አርክቴክት ጌትነት በሙያቸው ነፃ አገልግሎት ይሰጣሉ። ምንም እንኳን ወደ ተግባር ባይቀየርም በወቅቱ 600ሺ ብር ወጪ ይጠይቅ የነበረውን ጎንደር የሚገኘውን የአዳሪ ትምህርት ቤት ሙሉ ዲዛይን በነፃ ሰርተው አስረክበዋል።
አረጋውያን መሰብሰቢያ ለማሰራትም ታስቦ ጎንደር ላይ ለታለመ ፕሮጀክት በነፃ የዲዛይን ሥራ ከውነዋል። አሁንም ሀገራዊ ፋይዳ ባላቸው ፕሮጀክቶች ላይ በጎ ፈቃድ ሥራዎችን ለማከናወን ዝግጁ ናቸው። እርሳቸው ለኢትዮጵያ ውለታ በእውቀታቸውና በአቅማቸው ለሚከፈል ወሮታ ሁሌም ዝግጁ ናቸው፤ ኢትዮጵያ ለእርሳቸው ምትክ የላትምና።
ትዳር
አርክቴክት ጌትነት ወደትዳር ዓለም የገቡት በ43 ዓመታቸው ነበር። ‹‹የድሃ ልጅ ስለሆንኩ ዘግይቻለሁ›› የሚል አመለካከት አላቸው። የመጀመሪያ ልጃቸው የውጭ የትምህርት ዕድል አግኝታ የሦስተኛ ዓመት የኮምፒዩተር ሳይንስ ተማሪ ናት። ሁለተኛ ልጃቸው 12 ክፍል ስትሆን ዩኒቨርሲቲ ለመግባት ፈተና እየተጠባበቀች ነው። ሦስተኛ ልጃቸው ደግሞ 10ኛ ክፍል ተማሪ ነው።
‹‹የምታሳድገውን ልጅ መውለድ ጥሩ ነው። መውለድ ያለብህ የምታሳድገውንና ለህብረተሰቡ አንፆ ለማስረከብ ቢቻል በ30ዎቹ የዕድሜ ክልል ትዳር ቢመሰረት እመክራለሁ።
ለህብረተሰቡ ዕዳ የሚሆን ልጅ ወደ ምድር ማምጣት የለብህም›› ባይ ናቸው። ልጆቻቸው በራሳቸው ፍላጎት እንዲማሩ፤ እንዲመራመሩ ፈቅደዋል። እርሳቸውም አቅማቸው በፈቀደውና የሚቻላቸውን ሁሉ እገዛ ያደርጋሉ።
ከሆቴል ዲዛይነርነት ወደ ሆቴል ኢንቨስትመንት
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሦስተኛ ዓመት ትምህርታቸውን እየተማሩ ሳሉ ዶክተር ቬንት የምትባለው አስተማሪያቸው ተማሪዎቿን ሂልተን ሆቴል ወስዳ አስጎብኝታ ነበር። ታዲያ በዚህ ወቅት ነበር አርክቴክት ጌትነት የሆቴል ዲዛይን ሥራ ቀልባቸውን የገዛው።
ፊላንድ የማስተርስ ትምህርታቸውን እየተማሩም በሀገሪቱ አሉ የሚባሉ ቅንጡ ሆቴሎችንም የመጎብኘት ዕድል አግኝተዋል። የማስተርስ ትምህርታቸው የመጨረሻ ፕሮጀክትም ሆቴል ላይ ነበር። እነዚህ ነገሮች ተደማምረው የብዙ ሆቴል ዲዛይን እንዲሰሩ አድርጓቸዋል።
በሂደት ደግሞ እውቀትና ልምዳቸውን ሰብሰብ አድርገው በተወለዱበት ጎንደር ከተማ ‹‹ዞብል ሪዞርት›› ገንብተዋል። በእርግጥ ወደዚህ ሥራ የገቡት ጎንደር ዘመድ ለመጠየቅና ማህበራዊ ሕይወት ለመከወን ሲሄዱ ደረጃውን የጠበቀ የእንግዶች ማረፊያ የሚሆን ሆቴል እጥረት እንዳለ በመገንዘባቸው ነበር። ለሆቴል ግብዓት የሚውሉ ሲሚንቶና ብረትም ከአዲስ አበባ እየገዙ ወደ ጎንደር እየላኩ ሆቴሉን ለመገንባት ለፍተዋል። ጎንደር ከተማ ያሉት ፎርማን እና አርክቴክት ወንድሞቻቸው ሥራውን በባለቤትነት ይመሩትም ነበር።
ሆቴሉን ገንብቶ ለማጠናቀቅ 11 ዓመታት የወሰደ ሲሆን ከኪሳቸው 22 ሚሊዮን ብር በማውጣት እንዲሁም ከባንክ 35 ሚሊዮን ብር ተበድረው ህልማቸውን እውን አድርገውታል። ለሆቴሉ የሚሆኑ ግብዓቶች ከውጭ ሀገር ለማስመጣት የሚሆን የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት እስከ 22 ወራት መጠበቃቸውን ያስታውሳሉ። በዚህ ውስጥ የዶላር ምንዛሪ ከፍና ዝቅ ማለት ስለነበር ለአምስት ሚሊዮን ብር ኪሣራ ተዳርገዋል።
በዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ ውስጥ አልፈው በታሪካዊው አጼ ፋሲል ሥም የተሰየመና 78 መኝታ ክፍሎች ያሉት ‹‹ዞብል›› የተሰኘ ባለ አራት ኮኮብ ሪዞርት ሆቴል በ5000 ሄክታር ላይ ገንብተው ለበርካታ ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል ፈጥረዋል። የሆቴሉ ደህንነት የተጠበቀ እንዲሆን 24 ሰዓት በ28 ከሜራዎች ይጠበቃል። እርሳቸውም አዲስ አበባ ሆነው በሆቴሉ ውስጥ የሚከናወን ማንኛውንም እንቅስቃሴ መመልከትና መከታተል የሚችሉበትን ቴክኖሎጂ ገጥመውለታል።
ሰዎች ምን ይሏቸዋል?
አርክቴክት ጌትነት ከኋላ ታሪካቸው ጀምረው በጎ የሰሩላቸውን ሰዎች ያመሰግናሉ። በግል ማማከር ሥራ ይሰሩ የነበሩ ኢንጅነር ካሣ ኃይሌ እና ኢንጅነር አበራ ካሳዬ የሚባሉት ሁለት ግለሰቦች አርክቴክት ጌትነት የግል ሥራ ጀምረው በተቃና መንገድ እንዲጓዙና ለስኬታቸው ብዙ እንዳገዟቸው በማስታወስ ‹‹ከሙታን መንደር ቢሆኑም አፈር ይቅለላቸው፤ አመሰግናቸዋለሁ›› ሲሉ የእውቀትና የቅንነት ተምሳሌት የሆኑላቸውን ግለሰቦች ያመሰግናሉ። ከእነዚህ ሰዎች ጋር በመሥራቴ በሳይንስ ላይ የተመሰረተ እውቀት እንደተገብር፤ ሌብነትን እንድፀየፍና አቅም በፈቀደ ሁሉ ለሀገሬ በቅንነት እንድሰራ ስህተቴን በጥሩ ላጲስ አርመው፤ ንግግሬን ሞርደው አሳድገውኛል ይላሉ።
አርክቴክት ጌትነትም በተራቸው በሠራተኞቻቸው ይመሰገናሉ። ‹‹ጨዋ፣ ሰው አክባሪ፣ ለድርጅታቸው ሠራተኞች ክብር ያላቸው፣ ንግግራቸው ደርዝ ያለውና በውይይት የሚያምኑ፣ ለእውቀትና ለባለሙያ ቅድሚያ የሚሰጡ›› ስለመሆናቸው ይመሰክሩላቸዋል።
የዞብል ሆቴል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሮቤል ስለ አርክቴክት ጌትነት ሲናገሩ፤ ሙሉ ኃላፊነትን የሚሰጡት ለባለሙያ እንጂ ጣልቃ መግባት አይፈልጉም። በብዙ ነገር ዓርዓያ የሚሆኑ ናቸው። ዝቅ ብለው ሰርተው ቀና ብለው የሚራመዱ እውቀታቸውን በተግባር የሚገልፁ ትሁትና ቁጥብ ሰው ናቸው ይሏቸዋል።
በድርጅታቸው ውስጥ ከሚሰሩት ሌላኛው አቶ ጌታሰው፤ አቶ ጌትነት እንደ ባለሃብት ሳይሆን እንደ ተራ ሰራተኛ ሆነው ደፋ ቀና ብለው የሚሰሩ ታታሪ ሰው ናቸው። ቀረብ ብለው የሰው ልጅ ችግር መረዳት የሚፈልጉ፣ በአባታዊ ቅርርቦሽ የሚጫወቱ ሰዎች ስኬት እንዲጎናጸፉ የሚያግዙ ልበቀና ሰው ስለመሆናቸው ይመሰክሩላቸዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 7/2013