▰አሜሪካ በተለይ በቻይና ላይ የጣለችው ታሪፍ 250 ቢሊዮን ዶላር ፤
▰ቻይና በተለይ በአሜሪካ ላይ የጣለችው ታሪፍ 110 ቢሊዮን ዶላር ፤
መግቢያ
እንደ ፖለቲካው ሁሉ የዓለምን ኢኮኖሚ፣ በተለይ ላለፉት 100 ዓመታት በመምራት ረገድ ከፍተኛ የበላይነትን የተቀዳጀችው አሜሪካ ራሷን የዓለም የኢኮኖሚ ማዕከል በማድረግ ከበርካታ አገራት ጋር ጠንካራ የንግድ ትስስር መስርታለች፡፡ በ2007/08 የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ ብትገባም፣ በዓለም የኢኮኖሚ የበላይነቷን አሁንም ከእጇ ፈልቅቆ የወሰደ የለም።
በአሜሪካ የደረሰውን የኢኮኖሚ መዋዠቅ አስመልክቶ የቻይና የኢኮኖሚ ባለሙያዎች በወቅቱ “የአሜሪካ ኢኮኖሚ ከወደቀ የቻይና ኢኮኖሚም አደጋ ላይ ይወድቃል” ማለታቸው ይታወሳል፡፡ አባባሉም “ጤናማ ፉክክር ለጤናማ እድገት” የሚለውን የሚያጠናክር ሆኖ ይገኛል። ባጠቃላይ፤ ዛሬ ሁለቱ አገራት በኢኮኖሚ አቅማቸው ከአለም 1ኛ እና 2ኛ ናቸው። ግን ደግሞ በ“ንግድ ጦርነት” የተወጠሩ፤ ለምን? በዚህ ፅሁፍ ለመዳሰስ የምንሞክረው ጥያቄ ነው።
አሜሪካ
ለረጅም ዓመታት የአለም ኢኮኖሚ የሚዘወረው በእርሷና በርሷ ብቻ ሆኖ እነሆ እስከአሁኗ ሰአትና ደቂቃ ድረስ አለ። ተቀናቃኞቿ መኖራቸው እንዳለ ሆኖ።
እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ በዓለም ሀገራት ላይ እንዳሻት ትሆን ዘንድ የሚያስችላትን “ግሎባላይዜሽን” ይዛ ከተፍ አለች። “ሽብርተኝነት” ስትልም የዓለምን ትኩረት ሳበች፤ በኒውዮርክ መንትያ ህንፃዎች ላይ የደረሰውን ጥቃት (9/11) ተከትላ ዓለም-አቀፉን የፀረ-ሽብር ዘመቻ በከረረ ቁጣ አወጀች። ያልደገፋትንም “የማርያም ጠላት” ስትል ቁርጥ አቋሟን አሳወቀች። የወቅቱ መሪ ትንሹ ቡሽም “World terror” ሲሉ ስም አወጡለት። ከዛን ወዲህ ለአገራት የምታደርገው ድጋፍና ትብብርም በዋናነት መስፈርቱ ከዚሁ ከፀረ-ሽብር ዘመቻ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ሆነና አረፈው። የአሁኑ ትራምፕ ደግሞ የምን ወደውጪ ማየት አሉና ለአገራቸው ያላቸውን አቋም “America First“ ሲሉ ሁሉም ነገር “ከራስ በላይ ንፋስ” መሆኑን ለአለም አሳወቁ።
ቻይና
የምጣኔ ሀብት ባለሙያውና አማካሪው አቶ ጌዲዮን በቅርቡ ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደገለፁት፤ የምእራባውያንን እና የቻይናን ፍጥጫ በተመለከተ ሁኔታውን “ቻይናን ሊቀድሙም ሊቋቋሙም አይችሉም፡፡ በጣም ከባድ ነው፡፡ ቻይናን በምን አግባብ መቋቋም እንደሚችሉ ስለማያውቁ ሥጋት ውስጥ ናቸው፡፡ የቻይና የገንዘብ አቅም ከሚያስቡት በላይ ሆኗል፡፡ ‹‹ቤልት ኤንድ ሮድ›› የተሰኘው የመሠረተ ልማት ውጥኗ ዓለምን ከአንዱ ጫፍ ወደ ሌላው ለማገናኘት ያሰበ ነው፡፡ ድሮ ‹‹መንገዶች ሁሉ ወደ ሮም ያቀናሉ›› ይባል ነበር፡፡ አሁን ግን መንገዶች ሁሉ ወደ ‹‹ቤጂንግ ያቀናሉ›› በሚለው ሳይተካ አይቀርም፡፡ ሲሉ የቻይናን ኢኮኖሚያዊ ጡንቻ መፈርጠም ይገልፁታል።
በ2015 የቻይና መገበያያ ገንዘብ ዩዋን ከዓለም አምስቱ የመጠባበቂያ ክምችት ገንዘብ (Special Drawing Rights (SDR)) አንዱ ተደርጎ እንዲሰራበት አይኤምኤፍ መወሰኑን፤ ይህም የቻይና የፋይናንስ እና የኢኮኖሚ ጥንካሬ እየጨመረ መሄዱን ያረጋገጠ ውሳኔ እንደሆነ በወቅቱ መነገሩ ይታወሳል፡፡
በአሁኑ ሰአት ለእድገቷ መፋጠን ዋናው መሳሪያዋ በጥንታዊ ቻይና ስልጣኔ “የሀር መንገድ” በሚል የሚታወቅን ዓለም-አቀፍ የንግድ መስመር “One Belt, One Road” መልሶ መዘርጋት ነው። ይህ “Silk Road Economic Belt” በሚባል ፕሮጀክት የሚገነባው የየብስ የንግድ መስመር ሲሆን፤ ከቻይናዋ ዚያን ከተማ ተነስቶ በካዛኪስታን፣ ኢራንና ቱርክ አድርጎ ሩሲያ ሞስኮ ከደረሰ በኋላ በጀርመንና በቤልጂዬም በኩል አልፎ የኢጣሊያን ቬኒስ ከተማ የሚደርስ መሆኑ በቻይና መንግስት ይፋ ከተደረገ ሰነባብቷል።
ከኢጣሊያኗ ቬኒስ ከተማ ጀምሮ በግሪክ፣ ግብፅ፣ ጂቡቲና ኬኒያ አድርጎ ወደ ኢሲያ በመሻገር በሲሪላንካ፣ ህንድ፣ ማሌዢያና ቬትናም በኩል የቻይናዋ ግዋንግዡ “Guangzhou” ከተማ ይደርሳል። ይህን የባህር ላይ የንግድ መስመር እውን ለማድረግ ደግሞ “Maritime Silk Road Initiative” የተባለ ፕሮጀክት ተግባራዊ ተደርጓል። የሚለን የስዩም ተሾመ ፅሁፍ ሲሆን፤ ከላይ በተጠቀሱት መስመሮች 68 ሀገራትን ይካትታሉ። ከእነዚህ ሀገራት ውስጥ 14ቱ በምስራቅና ደቡብ ምስራቅ ኢሲያ፣ 13ቱ በመካከለኛውና ደቡብ ኢሲያ፣ 24ቱ በአውሮፓና ዩሮኤዥያ፣ እንዲሁም 17ቱ ደግሞ በመካከለኛው ምስራቅና በአፍሪካ የሚገኙ ሀገራት ናቸው። በመካከለኛው ምስራቅና በአፍሪካ ከሚገኙት 17 ሀገራት የሚከተሉት ናቸው። ባህሬን፣ ጂቡቲ፣ ግብፅ፣ ኢትዮጵያ፣ ኢራን፣ ኢራቅ፣ እስራኤል፣ ጆርዳን፣ ኬኒያ፣ ኩዌት፣ ሌባኖስ፣ ኦማን፣ ኳታር፣ ሳውዲ አረቢያ፣ ሶሪያ፣ የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ እና የመን ናቸው ሲልም ርእሰ-ጉዳዩን ሰፋ አድርጎ ያብራራዋል። የቻይና ኢኮኖሚም በዚሁ ፍጥነትና ርቀት እየሄደ መሆኑንም ልብ ማለት ተገቢ ነው።
የንግድ ጦርነቱ
ወቅቱ የትራምፕ አስተዳደር አሜሪካ ከቻይና በምትሸምታቸው 50 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ሸቀጦች ላይ 25 በመቶ፤ ሌሎች 200 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ሸቀጦች ላይ 10 በመቶ፤ በተመሳሳይ ቻይና ከአሜሪካ በ50 ቢሊዮን ዶላር በምትሸምታቸው ሸቀጦች ላይ 25 በመቶ ታሪፍ ጥላለች። ሌሎች 60 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ሸቀጦችም በተመሳሳይ 10 በመቶ ተጨማሪ ታሪፍ የተጣጣሉበት ወቅት ነው።
“በአሁኑ ወቅት በየዓመቱ የ500 ቢሊዮን ዶላር የንግድ ኪሳራ ይደርስብናል። በአዕምሯዊ ንብረት ስርቆት ደግሞ ሌላ 300 ቢሊዮን ዶላር እያጣን ነው” በማለት ቻይናን የሚከሱት ትራምፕ፤ አሜሪካ 200 ቢሊዮን ዶላር በሚያወጡ እቃዎች ላይ አዲስ (3ኛውን) ታሪፍ መጣሏን፤ “ዋነኛ በሚባሉት 800 ያህል የቻይና ምርቶች ላይ የ25 በመቶ ቀረጥ እንዲጣል፤ ከሃምሌ 30/2010 ጀምሮም ተግባራዊ እንዲደረግ ትዕዛዝ” መተላለፉን ይፋ አድርገዋል። ይህ የተደረገውም “ቻይና እያሳየች ላለችው ኢ-ፍትሃዊ የንግድ አሰራር አፀፋ ነው።” ቻይና አፀፋ እመልሳለሁ ብትል ደግሞ አገራቸው 267 ቢሊዮን ዶላር በሚገመት ምርቷ ላይ የሚቀጥለውን ዙር ታሪፍ ተግባራዊ ለማድረግ እንደምትገደድ ማስጠንቀቃቸውም እንደዛው፤
ለንግዱ ጦርነት ከአሜሪካ ይፋዊ ምክንያቶች መካከል፤ በተለይም በኩባንያዎች ላይ ኪሳራ መድረሱና ከገበያ ለማስወጣት እየደረሰ መሆኑ፤ ይህም በበኩሉ የስራ አጥ ዜጎች ቁጥር መጨመሩ፤ ዜጎች ካገር ውስጥ ምርት ይልቅ ወደቻይና ምርት ማተኮራቸው ዋና ዋናዎቹ ናቸው።
እንደ cnbc.com ዘገባ ደግሞ ምስጢሩ ሌላ ነው። በድረ-ገፁ “A major factor behind the US-China trade war is winning at a $12 trillion technology — 5G” በሚል ርእስ የወጣው ዘገባ እንደሚያመለክተው በ2035 የዓለምን 12.3 ትሪሊዮን ዶላር ኢኮኖሚያዊ ወጪ ይሸፍናል፤ የሁሉም ነገር፣ በተለይም የፀጥታና ደህንነት የጀርባ አጥንት ነው የሚባልለትና “የሚቀጥለው ትውልድ የሞባይል ኢንተርኔት/5G”ን ስራ ላይ ከማዋል አንፃር ቀድሞ ለመገኘት፣ በበላይነት ለመቆጣጠርና የሚመራበትን ደረጃ/ስታንዳርድ አውጥቶ ቀዳሚ ተጠቃሚ ለመሆን እየተደረገ ያለ ውጊያ ነው።
ቀደም ሲል እንደጠቀስነው፤ “በሌላ የዓለም ክፍል በተፈጠረው እድገት ምክንያት የኢኮኖሚ የበላይነቷ እየተሸረሸረ መሄዱን እየተረዳች ነው” የሚባልላት አሜሪካና ፈጣን እድገት ላይ መሆኗ የሚነገርላት ቻይና ወደተባባሰ የንግድ ጦርነት ውስጥ እየገቡ መሆናቸውን እየዘገቡ ያሉ መገናኛ ብዙሀን እጅግ በርካታ ሲሆኑ፤ ከነዚህም አንዱ ቢቢሲ ነው።
እንደ ቢቢሲ ዘገባ፤ ባለፈው ሰኔ ወር የትራምፕ አስተዳደር አሜሪካ በቻይና ምርቶች ላይ በተለያዩ ዙሮች ከ10 በመቶ በመጀመር እያደገ የመጣው የታሪፍ ጭማሪ በአሁኑ ወቅት 25 በመቶ፤ የዶላር መጠኑም 500 ቢሊዮን ደርሷል። ቻይና በበኩሏ በዋና ዋና ምርቶች ላይ እስከ 25 በመቶ የመጨመር እቅድ መያዟን ገልፃለች።
በ2017 ብቻ 506 ቢሊዮን ዳላር ግምት ያላቸውን ምርቶች ከቻይና ላስገባችው አሜሪካ የታሪፍ መጨመሯን አስፈላጊነት ጠቅለል አድርጎ “አሜሪካኖች የራሳቸውን ምርት እንዲገዙ ያደርጋቸዋል” በማለት ከንድፈ-ሃሳብ አንፃር የሚተነትነው ቢቢሲ፤ ድርጊቱ ለአጠቃላይ አለማችን የስጋት ምንጭ ብቻ ሳይሆን የከፋ ጉዳትም ሊያመጣ እንደሚችል ይገልጻል።
ሁለቱም ሀገሮች በመቶ ቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር እንዳቸው በሌላኛው _ምርቶች ላይ ከበድ ያለ ታክስ በመጣል _የንግድ _ጦርነት ማካሄዳቸውን ቀጥለዋል_። ባለፈው ዲሴምበር አርጀንቲና ውስጥ በተካሄደው የG20 ጉባኤ_ላይ ሁለቱ ሀገራት ጊዚያዊ ስምምነት ቢያደርጉም፤ የንግድ ጦርነቱ ግን እስካሁን ሊቆም አልቻለም፡፡ እንደ ethiofmradio.com ዘገባ በሁለቱ ጎራዎች ያሉ ልዩነቶች እየጨመሩ ሲሆን፤ በዚህ የንግድ ጦርነትም _ዋሽንግተን እና ቤጂንግ እርስ በእርሳቸው የሚጥሉት_ የታሪፍ ጭማሬ _የዓለምን ኢኮኖሚ እየጎዳው ይገኛል፡፡
እንደዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ጥናት፤ በሁለቱ ሀገራት መካከል_ ባለው ኢኮኖሚያዊ/የገበያ ውዝግብ፤ እንዲሁም የንግድ ጦርነት ምክንያት የ2018/2019 የዓለም ኢኮኖሚ_ እድገት ተቋሙ ከገመተው የ3 ነጥብ 9 በመቶ እድገት ወደ 3 ነጥብ 7 ዝቅ ይላል። ይህም በንግዱ ማህበረሰብ እና በአለም _የኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ_ የሚኖረው ተፅእኖ ቀላል አይደለም። ይህ የሁለቱ አገራት “የንግድ ፖሊሲ የፖለቲካ አካል ነው” የሚለው ድርጅቱ “የአለም ፖለቲካ መረጋጋት የተሳነው በመሆኑ ሌላ ችግር ማስከተሉ አይቀርም” ሲል ስጋቱን ይገልፃል። በሌሎች አካላትም እየተንፀባረቀ የሚገኘው አስተያየት ከዚሁ ጋር ተመሳሳይ ነው።
ማን ያሸንፋል? ለሚለው፤ ጥያቄው የብዙ ትሪሊዮን ዶላር ነው ከማለት ያለፈ ምላሽ እስካሁን ማግኘት አልተቻለም። “So who wins? That’s the multi-trillion dollar question in this case.” cnbc.com
አዲስ ዘመን ጥር29/2011
ግርማ መንግሥቴ